Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ለረዥም ጊዜ የታየ ድንቅ ቴአትር ነበር፡፡ በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ተተርጉሞ የተዘጋጀው ‹‹ኦቴሎ›› ቴአትር በተዋንያኑ ድንቅ ብቃት በወረፋ ነበር የሚታየው፡፡ በተለይ ‹‹ኢያጎ›› የተባለውን ገጸ ባህርይ ወክሎ የተጫወተው ነፍሱን ይማረውና ሱራፌል ጋሻው ነበር፡፡ በዓለም ላይ ይኼንን ቴአትር ያስወደደው የኢያጎን ባህሪ የሚጫወቱ ሰዎች የነበራቸው የአተዋወን ብቃት ነው፡፡ በእንግሊዝ አገር ይኼንን ገጸ ባህርይ የተጫወተ ሰው በአንድ ተመልካች በሽጉጥ መገደሉ ይነገራል፡፡ በገጸ ባህሪው የትወና ችሎታ ምክንያት መድረኩ ከገሐዱ ዓለም የተመሳሰለበት ተመልካች ተዋናዩን ከገደለው በኋላ፣ በፈጸመው ድርጊት ተፀፅቶ ራሱን ይገድላል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ጎን ለጎን እንዲቀበሩ ይደረግና ሐውልት ይቀረፅላቸዋል፡፡ ለተገደለው ተዋናይ ‹‹ግዳጁን በብቃት የተወጣ ተዋናይ›› ተብሎ ሲጻፍ፣ ለገዳዩ ደግሞ ‹‹የዋሁ ተመልካች›› ይባልለታል፡፡ የእኛው ኢያጎም በማዘጋጃ ቤት መድረክ ላይ ለበርካታ ጊዜያት በጫማ ተደብድቧል፡፡ የኢያጎን አናዳጅ ድርጊት በሚገባ በመተወኑ በርካቶችን አስለቅሷል፡፡ ትወና ማለት እንዲህ ነው፡፡ እነ ወጋየሁ ንጋቱን ጭምር እያስታወስን ማለት ነው፡፡

‹‹ዓለም የቴአትር መድረክ ናት፣ ተዋንያኑም በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፤›› ብሎ ነበር አሉ ዝነኛው እንግሊዛዊ ፀሐፌ ተውኔት ዊልያም ሼክስፒር፡፡ በዚህ ባለንበት ዘመን በርካታ ተዋንያንን እያየን ያለነው በቴአትር ቤት መድረኮች ወይም በየቀኑ በሚፈበረኩ ፊልሞች ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላው የሕይወት ውጣ ውረዳችን ውስጥ መሆኑን እየተገነዘብኩ ከመጣሁ ከራረምኩ፡፡ ዊልያም ሼክስፒር እንዳለው የሰው ልጅ በሙሉ ትወና ላይ ነው፡፡ አንዳንዱ ቁም ነገሩን በቀልድ እያዋዛ አንጀታችንን ሲያርሰው፣ ምድረ ቀሽም ደግሞ እያቃጠለን ነው፡፡ በቀሽም ደራሲ የተደረሰ ቴአትር በቀሽም ዳይሬክተር እየተዘጋጀና በቀሽም ተዋንያን እየተተወነ ለተመልካቾች ቢቀርብ ትርፉ ኪሳራ ብቻ ይሆናል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ውስጥ ቀሽሞች እየገቡ ሲፈተፍቱ ኧረ በሕግ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ሰሞኑን አንድ ቀሽም ነገር ቢያጋጥመኝ ነው ከላይ እንደ መንደርደሪያ የቴአትሩን ዓለም ያነሳሁት፡፡ አንድ ገበያ ላይ የሚሸጥ መጽሐፍ በ150 ብር እገዛና እየተጣደፍኩ ቤቴ ሄጄ ማንበብ እጀምራለሁ፡፡ ከገጽ ገጽ ባነበው፣ ባነበው የመጽሐፉ ይዘትና ለመጽሐፉ ምክንያት የሆኑት ሰው ማንነት አልገናኝ አለኝ፡፡ ስማቸው የገዘፈው ግለሰብ በፖለቲከኝነት ለረጅም ዓመታት የሚታወቁ ናቸው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ደግሞ ላለፉት 20 ዓመታት አውቃቸዋለሁ፡፡ መጽሐፉን እያነበብኩ ያለፉትን 20 ዓመታት ባወጣና ባወርድ ግራ ግብት አለኝ፡፡ ፖለቲካ ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛስ ምን ዓይነት ነው? የሚል ጥያቄ አጫረብኝ፡፡ የማነበው በእኚህ ሰው የተነገረን ታሪክና ያለፉበትን ውጣ ውረድ ነው? ወይስ ምንድነው? አልኩ ለራሴ፡፡ መጽሐፉን ባነበው፣ ባነበው አልገባኝም፡፡ እኔ ከመጽሐፉ የምጠብቀው ሰውዬው ይታወቁበታል በሚባለው ደረጃ ነው፡፡ የማነበው ግን የፖለቲከኛ ውሎ አልመስል አለኝ፡፡ ጎበዝ ግራ ገባኝ፡፡ ግራ ሲገባኝ መፍትሔው ከጓደኛዬ ጋር መወያየት ነው አልኩ፡፡

ጓደኛዬን መጽሐፉን እንዲያነበው ነገርኩት፡፡ ተውሶኝ በሁለት ቀን ፉት አደረገው፡፡ ዕረፍት ላይ ስለነበር አልተቸገረም፡፡ ‹‹ታዲያስ?›› አልኩት፡፡ እየሳቀ ‹‹አለና!›› አለኝ፡፡ ‹‹ምኑን አለን ትላለህ?›› በማለት ቆጣ አልኩት፡፡ አሁንም እየሳቀብኝ፣ ‹‹ምን ልበልህ ታዲያ?›› ብሎ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰው፡፡ እየተናደድኩ፣ ‹‹መጽሐፉን እንዴት አገኘኸው?›› ማለት፡፡ የበለጠ እየሳቀ፣ ‹‹የቱን መጽሐፍ?›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹ከእኔ ተውሰህ ያነበብከውን የሰሞኑን መጽሐፍ እኮ ነው የምጠይቅህ?›› ስለው፣ ‹‹መጽሐፍ አነበብኩ ከምል ተባራሪ ወሬ ሰማሁ ብል ይቀለኛል፤›› ብሎኝ በዚህ ጉዳይ መነጋገር እንደማይፈልግ ነግሮኝ ተለየኝ፡፡

‹‹ጨነቀኝ ጠበበኝ እኔን…›› ያለችው ዝነኛዋ ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ ወዳ አልነበረም ለካ? ነፍሷን ይማረውና፡፡ ሲመሽ ለጓደኛዬ ስልክ ደውዬለት፣ ‹‹በቃ ስለሰውዬውና ስለመጽሐፉ ያለህን አስተያየት ባጭሩ ንገረኝ እኔም ተንፈስ ልበል፤›› አልኩት፡፡ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እንዳልጠይቀው አስጠንቅቆኝ፣ ‹‹መጽሐፍ ከማለት ይልቅ በአጭሩ ተራ ወሬ ማለት ይቀላል፤›› ብሎኝ ስልኩን ሊዘጋው ሲል፣ ‹‹ሰውዬውስ?›› ስለው፣ ‹‹ሰውዬውንማ የዋህ ወይም ጅል ከማለት ሌላ ምን ይባላል?›› ሲለኝ ዓይኔ ፈጦ ቀረ፡፡

የነገሬ መነሻ ቴአትርና መጽሐፍ ቢሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መንበረ ሥልጣኑን ከጨበጡ ወዲህ የማስተውላቸው ነገሮች ግርም እያደረጉኝ ነው፡፡ ባለሥልጣኖቻችን የሚታወቁበትን መጀነን አሽቀንጥረው ጥለው ሕዝብን መምሰላቸው፣ ከባድና የማይደፈሩ የሚመስሉ ጉዳዮችን ቀለል አድርገው በፍጥነት እንዲፈጸሙ ማድረጋቸው፣ ለሰማይ ለምድር የከበዱ የሚመስሉትን ከሥልጣን ላይ ማንሳት መቻላቸው፣ ለሃያ ዓመታት በደም የተለወሰውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ጠላትነት ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በይቅርታና በፍቅር ወደ ቤተሰብነት መመለሳቸው፣ የገዛ መንግሥታቸውን ኃጢያት በአደባባይ አምነው መናገራቸውና የመሳሰሉትን ሳሰላስል የባከነው ዘመናችን አሳዘነኝ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ዕውቀት ወይም ምግባር ሳይኖራቸው በአገር ላይ ሲቀልዱ ለኖሩት ደግሞ አፈርኩላቸው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ካሁን በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እኩል መደመጥ የማይችል ባለሥልጣን ወይም የአደባባይ ሰው ሕዝብ ፊት ለመቅረብ ወይም ሥራውን ለማቅረብ ይቸገራል፡፡ እያንዳንዱ ጉዳይ እየተለካ ያለው እሳቸው ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ጋር ነውና፡፡ ወገኖቼ እየተዝረከረክን መሳቂያ እንዳንሆን ብንጠነቀቅስ? መጽሐፍ ስንጽፍ፣ ቴአትር ወይም ፊልም ስናዘጋጅ፣ አሊያም በተለያዩ ጉዳዮች አስተያየት ስንሰጥ ለወቅቱ ሁኔታ ቢመጥን ይሻላል እላለሁ፡፡ አይመስላችሁም?

(እስክንድር ሙሉጌታ፣ ከካዛንቺስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...