Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሰንደቅ ዓላማው ነገርና ሕጋዊ አንድምታዎቹ

የሰንደቅ ዓላማው ነገርና ሕጋዊ አንድምታዎቹ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ላመጧቸው ለውጦችና እንዲፈነጥቅ ላደረጉት ተስፋ ለማመሥገንም ለመደገፍም በተለያዩ ከተማዎች ሠልፎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ሠልፎች በሚደረጉበት ወቅት ሠልፈኞቹ የተለያዩ መፈክሮችና ምልክቶች ይዘው ነበር፡፡ ከምልክቶቹ መካከል በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና እሱን ተከትሎ በወጡ አዋጆች መሠረት ያልተፈቀዱ ሰንደቅ ዓላማዎች ይገኙበታል፡፡ ይህ ጽሑፍ ዓርማ የሌለውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩንና ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎችን በእንዲህ ዓይነት ሠልፎች መያዝ የሚኖራቸውን ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ አንድምታዎች መፈተሽ ነው፡፡

ምንነቱ

ሰንደቅ ዓላማ የሚለው አኃዝ (Term)  ‹‹ሰንደቅ›› እና ‹‹ዓላማ›› ከሚሉ ቃላት የተዋቀረ ሲሆን፣ ‹‹ሰንደቅ›› የግዕዝ ቃል፣ ነባር ዘር (ራሱን ችሎ የቆመ ስምና ከግስ በእርባታ ያልተገኘ) ሲሆን ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር፣ መስቀያ፣ መያዣ፣ መስቀያና ማንጠልጠያ የሚል ትርጉም ሲኖረው ‹‹ዓላማ›› ደግሞ ምልክት፣ አቋም፣ ስብስብ፣ እንዲሁም የነፃነት፣ የሉዓላዊነት ምልክት፣ ባንዲራ ማለት እንደሆነ በርካታ ምሁራን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ቃላት በአንድ ላይ ሲጣመሩ የአገር መታወቂያ፣ የሕዝብ አንድነት መጠበቂያ እንዲሁም የክብርና የነፃነት መለያ ምልክት የሚሉትን ሐሳቦች ያሳያል፡፡ በአገርነት መታወቂያነቱ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሕዝብንና የአገርን ሉዓላዊነት፣ ሥልጣንና ነፃነት ምልክት ወይም ተምሳሌት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የሚለው ሐረግ ባንዲራ በሚል የጣሊያንኛና እስፓኒሽኛ ቃልም ይጠራል፡፡ ባንዲራ ወይም ሰንደቅ ዓላማ የሚሉትን ተመሳሳይ ሐሳብን የሚገልጹ ናቸው፡፡ የአገሩ ጉዳይ የሚገደው፣ እንደሚገደው የሚያሰላስል ሰው ሰንደቅ ዓላማውን ሲመለከት የሚመለከተው አገሩን ራሷን ነው፡፡ የሰንደቅ ዓላማው ውክልና ምንም ይምሰል ምን፣ በሰንደቁ ላይ የሚገኘው ዓርማ እንደፈለገው ይቀያየር፣ ምንም ይሁን ምን፣ ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚነበበው የአገሩ አስተዳደር ነው፡፡ አገሪቱ የምትመራባቸው መርሆች ናቸው፡፡ የአገሪቱ ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ ብቻ ሳይሆን መጻኢ ተስፋም ጭምር ነው፡፡ ሰንደቁ የነፃነት ዓርማ፣ የአገሪቱ ሉዓላዊነት ማሳያ ነው፡፡ ከባንዲራው ጀርባ የሚነበቡት እንዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡  ዜጎች በአገራቸው ባንዲራ እንዲህ ዓይነቶቹን ዕሴቶች ከማንበብ ይልቅ ተቃራኒው የሚሰማቸው ከሆነ ባንዲራው ላይ ሳይሆን አገሪቱ አስተዳደርና መርህ ላይ ጥያቄ አላቸው ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አጠቃላይ አገሪቱ የዜጎች የጋራ ተቋምነቷ ላይ ጥያቄ መኖሩን ያመለክታል፡፡

ሰንደቅ ዓላማው በኢትዮጵያ ሕግጋት

የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ረዘም ያለ ታሪክ ቢኖረውም ከዚህ ቀደም የነበሩት የኢትዮጵያ ሕግጋተ መንግሥታት መካተት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን በምንመለከትበት ጊዜ፣ የመጀመርያው ሕገ መንግሥት ስለሰንደቅ ዓላማ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ በ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 124 ላይ ከላይ ከመጀመርያው አረንጓዴ፣ መካከለኛው ቢጫ፣ ከታች መጨረሻው ቀይ ሆኖ በአግድም የሚደረግ የሦስት ቀለማት ጨርቅ ነው በሚል ድንጋጌ እናገኛለን፡፡ ሌላ ዓርማ እንዲኖረውም አያመለክትም፡፡

1980 ዓ.ም. የደርግ ዘመኑ ሕገ መንግሥት ደግሞ አንቀጽ 113 ላይ የሰንደቅ ዓላማውን ቀለም ሲገልጽ የሪፐብሊኩ ዓርማ ግን በሕግ እንደሚወሰን አንቅጽ 114 ላይ ተቀምጧል፡፡ ዓርማን በሚመለከት የደርግ ዘመኑና የአሁኑ ሕግጋተ መንግሥታት ተመሳሳይ ድንጋጌ አላቸው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ግን የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዓርማ እንዲኖረው ያደረገ ሕገ መንግሥት የለም፡፡ የአሁኑ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 3 ሥር ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሚል ርዕስ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ሥር የአገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀሉ ብሔራዊ ዓርማ እንደሚኖረው ደንግጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ስለሰንደቅ ዓላማ የተቀመጠውን ጠቅላላ መርህ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል  ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ዝርዝር አዋጅና ሁለት ማሻሻያ አዋጅን አውጥቷል፡፡ እነዚህም የሰንደቅ ዓላማና ዓርማ አዋጅ ቁጥር 16/1988፣ የሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 48/1989፣ የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 እና የሰንደቅ ዓላማ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 863/ 2006 ናቸው፡፡ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 654/2001/አንቀጽ 5 ላይ ከተደተደነገገው መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ሰንደቅ ዓላማው የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መግለጫ ነው፡፡ አገሪቷ ራሷን ችላ በራሷ የምትተዳደርና ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሕዝቦቿ ፍላጎት የምትመራ ነፃ አገር መሆኗንና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍላጎትና በመፈቃቀድ ላይ በተመሠረተ መልኩ በአንድነት የሚኖርበት የአንድነታቸው መገለጫ ምልክት ነው፡፡ ይህ ትርጓሜ ከላይ ከቀረበው ጠቅለል ያለ መግለጫ ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ለእያንዳንዱ ቀለማት ውክልና መግለጫ አለው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በሕግ እንደሚወሰን የተመለከተውን ብሔራዊ ዓርማም በሚመለከት ብያኔ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም መሠረት ክብ የሆነው ሰማያዊ መደብ ሰላምን፣ ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች ደግሞ የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እንዲሁም የሃይማኖቶችን እኩልነት ያመለክታሉ፡፡ የኮከቡ አወቃቀር ደግሞ የኢትዮጵያን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሠረቱትን አንድነት የሚያመላክት ነው፡፡ ጨረሩ በቢጫ መሆኑም በመፈቃቀድ አንድነት ለመሠረቱት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ እንዲያሳይ የታለመ ነው፡፡ የሰንደቅ ዓላማውን መጠን፣ እንዴት እንደሚሰቀልና እንደሚወርድ፣ የት ቦታ እንደሚሰቀል፣ ሊሰጠው ስለሚገባው ክብር ሁሉ ይህ አዋጅ ይዘረዝራል፡፡ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማውን በሚመለከት የተከለከሉ ተግባራትም እንዲሁ በሰፊው ተገልጸዋል፡፡

ከተከለከሉት አድራጎቶች ውስጥም ሰንደቅ ዓላማውን ያለ ብሔራዊ ዓርማው መጠቀም፣ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ቃላቶችን መጻፍ፣ ሌሎች ምልክቶች ወይም ዓርማዎችን ወይም ሥዕሎችን መሳል ወይም በመለጠፍ መገልገልን ይከለክላል፡፡ እንዲሁም ያረጁ፣ የተበላሹ፣ ቀለማቸው የደበዘዘና የተቀዳደዱ ሰንደቅ ዓላማዎችን መጠቀም፣ ሰንደቅ ዓላማው በወጣበት ሰንደቅ (ምሶሳ) ላይ ማስታወቂያ መለጠፍ፣ ያለአግባብ ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎችን ወይም ዓርማዎችን ጨምሮ ማውለብለብ ወይም መጠቀም፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ሰንደቅ ዓላማን በጽሑፍ ወይም በቃል ወይም በድርጊት ወይም በሌላ በማንኛውም አኳኋን መድፈር ወይም ማዋረድ ወይም ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግ፣ የሰንደቅ ዓላማው ቀለማት ቅደም ተከተል እንዲሁም የብሔራዊ ዓርማውን መጠን ሳይጠብቁ ማዘጋጀትና መገልገል፣ ሰንደቅ ዓላማውን ከምሽት 12፡00 ሰዓት በላይ ሳያወርዱ ማቆየት፣ በስብሰባ ወይም በማናቸውም መሰል ክንውኖች ሰንደቅ ዓላማውን የጠረጴዛና የሕንፃ ወይም የሌሎች ቁሳቁሶች መሸፈኛ ማድረግ ከተከለከሉት ተግባራት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ክልከላዎች የተላለፈም በወንጀል እንደሚቀጣ ይኼው አዋጅ ይገልጻል፡፡ እንግዲህ ከላይ የተከለከሉትን ተግባራት በምንመለከትበት ጊዜ አንዳንዶቹን ሕዝቡ ሲጠቀምባቸው የኖሩ ናቸው፡፡ በአዋጁ ግን ተከልክለዋል፡፡ ለሰንደቅ ዓላማው ክብር መገለጫም እነዚህን ድርጊቶች የተላለፈ በወንጀል ይቀጣል፡፡ ይህንን ተከትሎም በርካታ ሰዎች በወንጀል ተከስው ተቀጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱና አዋጆቹ ምንም ይበሉ ምን ሰሞኑን በተካሄዱት ሰላማዊ ሠልፎች ላይ የተስተዋለው በተወሰነ መልኩ ከዚህ የሚስማማ አይደለም፡፡ እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ስምምነት የሌለ መሆኑን ወይም የያዘው ሐሳብ አለመሳካቱን፣ አገዛዙ ላይ ተቃውሞ መኖሩን ያመለክታል ማለት ይቻላል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ እንደ ብሔራዊ ምልክት

ሰንደቅ ዓላማውን ስንሰቅል ከግል ሃይማኖታችን፣ ከአካባቢያዊ ማንነታችን ከብሔረሰባችንና ከፖለቲካዊ ቁርኝታችን በላይ መሆኑን ለጋራ አገራችን ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ትምህርት ወይም ምልክት ነው፡፡ የባንዲራው ቀለም በዓይናችን ሲያልፍ ውልል ሊልብን የሚገባው በአገራችን ላይ የሚኖረን ኩራታችን፣ ፍቅራችንና እምነታችን መሆን አለበት፡፡

ባንዲራ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በመባል ይጠራል፡፡ ያለምንም ገላጭ ሰንደቅ ዓላማ የሚለው በበርካታ አገሮች ዘንድ የሚያሳው በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አስተዳደሮች፣ ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶችን ባንዲራን ነው፡፡ የአገሪቱ ሲሆን ግን ‹ብሔራዊ› የሚለው ገላጭ/ቅጽል መጨመር የተለመደ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የአማርኛው ስያሜ ‹ሰንደቅ ዓላማ› ብቻ በሚል ሐረግ ይገልጸዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚኖረውን ዓርማ ግን ብሔራዊ አድርጎታል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ሳይሆን ዓርማውን ብሔራዊ አድርጎታል፡፡ ከባንዲራው ይልቅ ዓርማውን አገራዊ አድርጎታል ሕገ መንግሥቱ፡፡ ሳይታሰብ የተደረገ ነው እንዳይባልም በዚሁ አንቀጽ ላይ ስለዓርማው ሲገልጽ ብሔራዊ/አገራዊ ግቡን አብሮ በማሳየት ነው፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነት በአንድነት ለመኖር የሚኖራቸውን ተስፋ የሚገልጸው በዓርማው እንጂ በባንዲራው አይደለም፡፡ ይህንን የበለጠ ለመረዳት በአንቀጽ አራት ላይ ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርም እንዲሁ ብሔራዊ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ብሔራዊ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የጋራ አገርን መኖርን ነው፡፡ የተለያዩ ማንነቶች ቢኖሩም በእነዚህ ልዩነት ውስጥ አንድ የሚያደርግን ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ባንዲራውን በሕገ መንግሥቱ ብሔራዊ አለማድረጉ በራሱ የተሰጠውን ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህንን የበለጠ የሚያጠናክረው ደግሞ ሕገ መንግሥቱን እንዲያፀድቁ ተመርጠው የነበሩት ጉባዔያተኞች ያደረጉት ክርክር አስረጂ ስለሆነ እሱን በአጭሩ እንመልከት፡፡ የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያ ላይ ደግሞ የሰንደቅ ዓላማው ዋና ዕሴት የነፃነት ምልክት መሆኑ ብቻ እንደሆነ ነው የተቀመጠው፡፡ ይኼው ማብራሪያ ሰንደቅ ዓላማውን ከሰው ሕይወትና መብት በላይ ተደርጎ ይቆጠር እንደነበር ይገልጻል፡፡ በዚህ ባለፈ ትኩረት ያደረገው ግን ይህ ሰንደቅ ዓላማ የዜጎች ነፃነትንና መብትን መጨቆኛና መርገጫ ሆኖ አገልግሏል የሚል ነው፡፡

የነፃነት ዓርማ ቢሆንም የዜጎች መብትና ነፃነት በላይ የተውለበለበ ቢሆንም የዜጎች መጨቆኝያ በመሆኑ የጋራ ኢትዮጵያዊነት ምልክት ሊሆን ስለማይችል ዓርማውን ብሔራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያትታል፡፡ እንደውም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ቢቀየር በሌሎች አገሮችም ዘንድ የሚታወቅ በመሆኑ ሌላ አዲስ ቀለማት ባለው ባንድራ መተካቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስለታመነበት ባንዲራውን እንዳለ እንዲቀጥል ነገር ግን የብሔራዊነታችን (ኢትዮጵያዊነታችን) ምልክት የሚሆን ዓርማው መዘጋጀት እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በዋናነት ባንዲራው የነፃነት ምልክት፣ ዓርማው ደግሞ የዜጎችና የሕዝቦች እኩልነትና መብት መከበር መለያ እንደሆነ ያትታል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሕገ መንግሥቱ በሚፀድቅበትም ወቅት ከባንዲራው ጀርባ የነበረው መልዕክት የነፃነት እንጂ የአንድነት እንዳልሆነ ከእንደገና በዓርማው አማካይነት የአንድነትና የእኩልነት መለያ እንዲሆን ታሳቢ መደረጉን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃና ዕውቅና የተሰጠው ባለአዲስ ዓርማው የቀድሞ ባንዲራ የዜጎችና የሕዝቦች መብትና እኩልነት ሲጣሰ መብቴና እኩልነቴ ተጥሷል የሚለው ወገን ይህንን ዓርማ መለያውና ምልክቱ ባያደርገው የሚገርም አይሆንም፡፡ የተቀየረው ዓርማው ከሆነና ያዘለውም መልዕክት የመብት መከበር የእኩልነት ሆኖ ሳለ ይህ ካልተከበረ ቃል ኪዳንነቱ ቀርቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ሰነድ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ለሕዝብ ውይይት ሲቀርብ ለአወያዮች የተሰጠ የተዘጋጀ ነው፡፡

ከዚህ ሰነድ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱን የሚያፀድቅ ጉባዔያተኞች በተሰበሰቡት ወቅትም የተነሱትን ሐሳቦችም በምናይበት ጊዜ ከይዘት አንፃር ብዙም ልዩነት የለውም፡፡ ሰንደቅ ዓላማው የነፃነት ምልክት ወይም ዓርማ መሆኑ ላይ ብዙም ልዩነት የለም፡፡ ልዩነት ያለው ሁለት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አንደኛው ሰንደቅ ዓላማው በነፃነትና በአንድነት ስም ሕዝቦችን የጨቆነና የዜጎችን መብት ለመጣስ ያገለገለ ነው የሚል በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው ሳይሆን የሕዝቦችን መብትና ነፃነት የጣሱት ገዥዎች እንጂ ሰንደቅ ዓላማው ጋር የሚያያዝ አይደለም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩነት ደግሞ ዓርማውን የሚመለከት ነው፡፡ በአንድ በኩል ሰንደቅ ዓላማው የሕዝቦችና የዜጎችን መብትና ነፃነት መጨቆኛ ሆኖ ስለነበር ዓርማውን ብሔራዊ ይሁን የሚል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ዓርማው ብሔራዊ መሆን የለበትም የሚል አስተያየት ነበር፡፡

በአጠቃላይ ጭብጡን የጉባዔው ዋና ጸሐፊ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡ ‹‹በአንድ በኩል ባንዲራው ባለፈው ታሪክ ሕዝቦችን ነፃ ያወጣ፣ ከኋላ ቀርነትና ከጭቆና ያላቀቀ፣ የአገር አንድነትን ያሰጠበቀ፣ ሕዝቦችን በውስጣቸው ያለውን ኋላቀር አስተሳሰብ እንዲፍቁ ያደረገና በአጠቃላይ ያለፉት አባቶች ሕዝቡን በማሠልጠንም ሆነ በአገር ነፃነትን በማስጠበቅ የተገለገሉበት መሆኑ ሳይጎድፍና ምንም ሳይነካካ እንዳለ መቀመጥ አለበት የሚል ሐሳብ መቅረቡን፣ በሌላ በኩል ግን ባንዲራው መለያ እንደሆነና እስከዛሬ ድረስ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ለሕዝቦች ነፃነት የቆመ ሳይሆን ሕዝቦች የታረዱበት የተጨፈጨፉበት እንጂ ሕዝቦችን ነፃ ሲያወጣ አልታየም፡፡ ከዚህ አኳያ ባንዲራው የሕዝቦችን ሉዓላዊነት፣ የብሔር/ብሔረሰቦችን መብት መግፈፊያ ሆኖ እንደቆየ ይሁን እንጂ ይህንን ያደረገውና ሕዝቦችን የጨፈጨፉት የነበሩት ሥርዓቶች በመሆናቸው በባንዲራው ላይ የብሔር/ብሔረሰቦችንና ሃይማኖቶችን እኩልነት የሚያንፀባርቅ ብሔራዊ ዓርማ እንዲታከልበት የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡››

በጉባዔያተኞቹ ረዘም ያለ ውይይት ከተደረገባቸው አንቀጾች መካከል ባንዲራውን የሚመለከተው ነው፡፡ የልዩነት ሐሳብ ከተስተናገደባቸው አንዱ ነው፡፡ ልዩነት የተስተዋለው የአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ አንድና ሦስት ላይ ሳይሆን ዓርማውን የሚመለከተው ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ ከቀረበው መረዳት የምንችለው ሕገ መንግሥቱ በጸደቀበት ወቅትም ዓርማውን በሚመለከት ልዩነት መኖሩን ነው፡፡ ሰሞኑን በተካሄዱት ሠልፎች ላይ ሕዝብ ወደ አደባባይ ይዟቸው ከወጣው ሰንደቅ ዓላማዎች መካከል አንዱ ዓርማ የሌለው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ነው፡፡ ዓርማው የሚወክለው ደግሞ የሕዝቦችና የዜጎች መብት መከበርና እኩልነት ነው ከተባለ በሠልፎቹም ላይ ዓርማ ያለውን ሰንደቅ ዓላማ አለመያዝ የሚያመለክተው የሕዝቦችና የዜጎች መብትና እኩልነት ያልነበረ መሆኑን ነው ማለት ይቻላል፡፡ የታሰበለትን ግብ አለማሳካቱን አመላካች ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማን ሐሳብን በነፃነት እንደ መግለጫ ምልክት

ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (2) ላይ እንደተገለጸው ማንም ሰው ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት አለው፡፡ ሐሳቡን በሚገልጽበት ጊዜ ማድረግ የሌለበት (ገደቦቹ)  በሌላ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ወይም የሌለውን ክብር ሳይነኩ፣ የወጣቶችን መልካም አስተዳደግ ላይ ጉዳት የሌለው፣ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ እንዳይሆን በመጠንቀቅ የራሳቸውን ሐሳብ ወይም አመለካከት በፈለጉት መንገድ መግለጽ ይችላሉ፡፡ ከሚገልጹባቸው መንገዶች መካከል  በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በሥዕልና በምልክት የመሳሰሉት ሊሆን ይችላል፡፡

ሰሞኑን በተካሄዱት ሠልፎች ላይ በርካታ ዜጎች በሠልፉ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ሐሳብ ወይም አመለካከት በተሻለ ሁኔታ ይገልጽልናል ያሉት ምልክት ውስጥ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ባንዲራ፣ የኦነግ ባንዲራ፣ ወይም ሌላ ዓይነት ባንዲራ መሆኑ ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጻቸውን ወይም ለመግለጽ መሞከራቸውን ያሳያል፡፡ ይህ እንግዲህ በሕገ መንግሥቱም ዋስትና የተሰጠው መብት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በሕጋዊ መንገድ በሥራ ላይ ያለውን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ አደባባይ አለመውጣት ሕገ መንግሥትን እንደተጣሰ ከመውሰድ ይልቅ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው የሚለው ሚዛን የሚደፋ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የግለሰቦችን መብትና ክብር ስለማይነካ፣ የወጣቶችን መልካም አስተዳደግ ስለማያውክ እንዲሁም የጦርነት ፕሮፓጋንዳም ስለማይሆን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ገደብም ሊሆን ስለማይችል ነው፡፡

ሕገወጥነትን ከኢሕገ መንግሥታዊነት መለየት

ሕገ መንግሥቱ ሰንደቅ ዓላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም መቀመጥ እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 3(1) በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በአንፃሩ ዓርማውን በተመለከተ ደግሞ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 3(2) ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚንፀባርቅ ይሆናል፤›› የሚሉ አመላካች ሐሳቦችን ከማስቀመጥ የዘለለ ዓርማው ምን እንደሚመስል ሳይደነግግ አልፎታል፡፡ በሌላ ሕግ ዓርማው ምን እንደሚመስል እንደሚደነገግ በመግለጽ አልፎታል፡፡

ከዚህ የምንረዳው አንደኛው ነጥብ ሰንደቅ ዓላማውን ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል መለወጥ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ ዓርማውን በሚመለከት ግን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት ሐሳቦች የሚያንፀባርቅ እስከሆነ ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊቀይረው ይችላል ማለት ነው፡፡ ውሳኔ ማንኛውንም ዓይነት ምልክት/ቅርፅ/ምስል የብሔራዊ ዓርማ እንዲሆን ሊደነግግ እንዲሁም በሌላ ሊቀይር የሚችል መሆኑን ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የወጡት አዋጆችም ምንም እንኳን ዓርማውን ባይቀይሩትም መሻሻላቸው ከዚሁ አመክንዮ ውጭ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱን ጥሷል ከማለት ይልቅ እሱን ተከትሎ የወጡ አዋጆችን የሚቃረን ነበር የሚለው ሚዛን ይደፋል፡፡

ለማጠቃለል ያህል በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሰንደቅ ዓላማና የብሔራዊ ዓርማ አዋጁ መሠረት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡበት ሲሆን፣ ብሔራዊ ዓርማው በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ የሚፈነጥቁ ጨረሮች ያሉት በቢጫ መስመር የተዋቀረ ኮከብ ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ አለመውጣት በአንድ በኩል ብሔራዊ አለመግባባት አለመኖሩን የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ዓርማው ምልክት የሆነለት ሐሳብ አለመሳካቱን ያሳያል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከወጡት አዋጆችም የሚያመለክቱት ባንድራው ጋር የሚያያዙ ድርጊቶችን በሕግ ኃይል አማካይነት ወጥ እንዲሆኑ የማድረግ አካሄዱ በዜጎች ዘንድ ያለው ቅቡልነት ተመሳሳይ አለመሆኑን ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ዜጎች አንድ የሚያደርጓቸውን፣ የሚጋሯቸውን፣ የጋራ ዕድል ፋንታና መፃኢ ዕድል የሚያመለክት የስሜታዊ ትስስር መገለጫም ስለሆነ በተለያዩ ሠልፎች ላይ የተንፀባረቀው ይህ ሁኔታ ላይ እንከን መኖሩን ነው፡፡ ይህ እንከን የሚያያዘው ደግሞ ከአገዛዙ ጋር መሆኑን ያሳዩበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ  ሐሳብን በነፃት የመግለጽ መብት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...