Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ችግር የመፍቻ ሐሳቦች

የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ችግር የመፍቻ ሐሳቦች

ቀን:

በያሬድ ኃይለ መስቀል

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደ ሠለጠነው ዓለም ለውይይት፣ ለክርክርና ለሐሳብ ልውውጥ በሩን ክፍት ያደረገ አይደለም፡፡ ውሳኔዎችም ሆኑ ፖሊሲዎች በሚስጥር ድንገት ዱብ የሚሉ እንጂ፣ በኢኮኖሚስቶችና በሌሎች ሙያተኞች ለክርክር የሚቀርቡ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ፖለቲከኞች የሚሏቸው ነገሮች ሁሉ እንደ ምጣኔ ሀብት ሀተታዎች ተወስደው ሲደጋገሙ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ብጠቅስ የቀድሞው የኢኮኖሚ ልማትና ገንዘብ ሚኒስትር አቶ ሱፍያን አህመድ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር በእኛ ሕይወት አይፈታም፤›› ብለው ለፓርላማው ተናግረዋል፡፡ ይህ አባባል እንደ ምጣኔ ሀብት ሀተታዎች ተወዶ ሲደጋገም ይሰማል፡፡ በእርግጥ ይህ አባባል መሠረት ያለው ነው? የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የማይፈታ ነውን? እኔ ከእዚህ አባባል ጋር አልስማማም፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር በጥቂት ወራት ውስጥ ሊፈታ ይችላል፡፡ ይኼንን ስል እንደ ትልቅ ድፍረት ሊቆጠር ይችላል፡፡

      ይኼ ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበት በመረጃ አስደግፌ ስለማቀርብ ነው፡፡ እንዴት እንደሚቻል ከመዘርዘሬ በፊት የችግሩን መንስዔዎች ልዘርዝር፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር መንስዔ ርዕዮተ ዓለምና ርዕዮተ ዓለሙ የፈጠረው የድህነት አስተሳሰብ ነው፡፡ እኔ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ልጅ ብሆንም፣ የውጭ ምንዛሪ ችግር አልነበረም ሲባል እሰማለሁ፡፡ አንድ የአሜሪካ ዶላር በሁለት የኢትዮጵያ ዶላር ከሰባት ሳንቲም ይቀየር ነበር፡፡ ዶላር ሄዶ መቀየርም ሆነ ይዞ መገኘትም ወንጀል አልነበረም፡፡ እንደ ማንኛውም የመገልገያ ነገር በአቅርቦትና በፍላጎት የሚገዛ ነበር፡፡ የእኛ ችግር ሶሻሊዝም የችግራችን ሁሉ መፍትሔ ነው ብለን ስንቀበል ይጀምራል፡፡ ካርል ማርክስ በዘመኑ ጥሩ ኢኮኖሚስት ተብሎ ቢከበርም ብዙዎቹ ሐሳቦቹ የተሳሳቱ እንደነበሩና የሶሻሊዝም ሥርዓትም የረሃብ፣ የችግርና የራሽን ሕይወት ሆኖ በመገኘቱ ከመሠረቱ ተንዷል፡፡ የማርክስ ትልቁ ስህተት የዓለም ሀብት ውስን ነው ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ ማርክስ ሀብት በቡርዧው እጅ የተከማቸ ሲሆን፣ ደሃው ሠራተኛ ደግሞ ምንም ስለሌለው ተነስቶ የመደብ ጠላቱን ቡርዧዋና ፊውዳል በመደምሰስ፣ የምርት ማምረቻና መገልገያውን መቆጣጠር አለበት፡፡ ከዚያም ሀብቱን እኩል ተካፍሎ በደስታና በተድላ ይኖራል የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡

      ይኼንን ርዕዮት ስንቀበል የድህነትን አስተሳሰብ አብረን ተቀበልን፡፡ ስለዚህ ለሁሉም እኩል እንዲደርስ በራሽን መከፋፈል ነበረበት፡፡ ስለዚህ በሶሻሊዝም ዘመን የዳቦ፣ የፓስታ፣ የዘይት፣ የሳሙና፣ የነዳጅ፣ የውጭ ምንዛሪና ሌሎችም ራሽኖች ታወጁ፡፡ የዳቦ ካርድና ራሽን ሲመጣ ከጀርባው የማርክሲስት ርዕዮት አለ፡፡ ዳቦ ነፃ በሆነ ገበያ ከተሸጠ አንዱ ሀብት ኖሮት ከበላ ሌላው ፆሙን ያድራል ከሚል እምነት ነበር፡፡ ይሁንና ከመንግሥት መቀየር በኋላ የዳቦ ራሽን ሲጠፋ ዳቦም አልጠፋም፡፡ ዛሬ በየዳቦ ቤቱ የስንዴ፣ የገብስ፣ የአጃ፣ የጤፍ፣ ወዘተ. እየተባለ ይገኛል፡፡ ዛሬ ነጭ ዳቦ፣ ጥቁር ዳቦ፣ ለስላሳ ዳቦና ቃ ያለ ዳቦ ተብሎ ተመርጦ ይገዛል፡፡ ማርክሲስቶች እንደፈሩት የዳቦ ቁጥጥር ሲነሳ አንዳንዱ ሁለት በልቶ ሌላው ዳቦ አጥቶ አላደረም፡፡ የዳቦ ራሽን ሲነሳ የዳቦ ምርት ጨመረ፡፡ በየመንደሩ የዳቦ ቤት ተቋቁሞ መፎካከር ስላለበትም የገብስ፣ የአጃና የጤፍ ጣፋጭ ለስላሳ እያለ ዳቦ ገበያውን ሞላው፡፡ ገንዘብ ተይዞ ዳቦ አልጠፋም፡፡   የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር ከዚሁ ከማርክሲስትና ከእጥረት አስተሳሰብ የተነሳ ነው፡፡ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በ1969 ዓ.ም. የወጣውን የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ይኼው ለ42 ዓመታት ሳናነሳው ዳር ዳሩን ብቻ እየተነካካ ከውጭ ምንዛሪ ችግር አልወጣንም፡፡  እኛም ከምሥራቅ አውሮፓ የተቀዳውን ሕግ ነው የያዝነው፡፡ አንደኛው ሁሉም የሶሻሊስት አገሮች ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ችግር ነበራቸው፡፡ ሩሲያ፣ ፖላንድ፣ ሐንጋሪ፣ ዩጎዝላቪያና ሮማንያ ብለን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ሶሻሊስት ያልነበሩም እንደ ህንድ ያሉ አገሮችም ተመሳሳይ የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ሕጎች ነበሯቸው፡፡ የበርሊን ግንብ ሲፈርስና የሶሻሊስት አገሮች ነፃ ሲወጡ ይኼንን የኮሙዩኒስት ሕግ አንስተው ጣሉ፡፡ አሁን በፖላንድ፣ በሮማንያና በሩሲያ የውጭ ምንዛሪ ችግር የለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር ወሬ ያለው አንደኛ ከዚህ ሕግ ጋር ሙጥኝ ብለው ካሉ አገሮች ጋር ነው፡፡ ምናልባትም ኮሪያና ኩባ ይሆናሉ፡፡

      የትናንትናዋ ኮሙዩኒስት ቻይና ዶላርን ይዛ በዓለም ላይ እየዘራችው ነው፡፡ ቻይና የዶላር መግባትና መውጣትን እቆጣጠራለሁ ብትል ኖሮ ዶላሩን ይዞ ገብቶ ቻይና ውስጥ ማንም ሀብት አያፈስም ነበር፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው የችግሩ መፍቻ መንስዔ የኮሎኔል መንግሥቱን የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ማንሳት ነው፡፡ ይኼንን ለማንሳት ትልቅ ፍርኃት ያለ ይመስለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ይህ ሕግ መኖሩን ያወቅኩት የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ኮንፈረንስ በኢሲኤ አዳራሽ ይካሄድ ነበር፡፡ በውጭ ምንዛሪ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ፀደቀ ይሁኔ የኢትዮጵያ የ1969 ዓ.ም. ሕግ ለምን እስካሁን አልተቀየረም? ብለው ሲጠይቁ በጣም ግር ብሎኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እኔም በዚሁ ጉዳይ ላይ ማሰብና መመራመር የጀመርኩት፡፡ ጊዜ ሰጥቼ ሳጠናው በእርግጥም የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር መነሻው ይህ ሕግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና የብሔራዊ ባንክ መሪዎች ይህ ሕግ ቢነሳ ሰማይ የሚወድቅ መስሎ ነው የሚታያቸው፡፡ በዚሁ በኮሙዩኒስት አስተሳሰብ ያደጉ ስለሆኑ ከቁጥጥር ውጪ ዓለም የሚፈርስ ነው የሚመስላቸው፡፡ እዚህ ላይ ይኼንን ሕግ ብናነሳ የመጨረሻው መጥፎ ነገር ምንድነው? ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው፡፡ ግፋ ቢል ያለንን የወር የውጭ ምንዛሪ እናጣለን፡፡ ይህ እኮ እየሆነ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪያችን ክምችት ወደ ዜሮ እየሄደ መሆኑንና ዜሮ እንደሚሆንም ለመገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ ሕልም ተፈርቶ አለመተኛት መምረጥ ነው፡፡

      ይኼንን የድህነት አስተሳሰብ ውጤት የሆነ ቁጥጥር ስናነሳ ችግሩ ሁሉ ይፈታል፡፡ ዶላር ወደ አገራችን በስፋት ይመጣል፣ ይከማቻል፡፡ ሁለተኛው ችግር የኢኮኖሚ ቃላትን የመቀላቀል ነው፡፡ አንደኛው የንግድ ሚዛን (Trade Balance) እና ሁለተኛው የውጭ ምንዛሪ እጥረት (Foreign Currency Shortage) የሚባለው ነው፡፡ ሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች የተገናኙ ይሁን እንጂ አንድ አይደሉም፡፡ ከዜሮ በታች የንግድ ሚዛን የሚመጣው ወደ ውጭ የምንልከው ከምንገዛው ሲያንስ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማለት ግን ተቀባይነት ያለው የመገበያያ ገንዘብ ማጣት ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች ለይተን ካላየን የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎችና የአቶ ሱፍያን አህመድ የተሳሳተ ሐሳብና ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡

      አቶ ሱፍያን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ በእኔ ዕድሜ አይፈታም ያሉት ምናልባት የወጪ ንግዳችን ከገበያችን የሚበልጥበትን ጊዜ እያሰቡ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ያለው ግንኙነት ውስን ነው፡፡ ትርፍ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያላቸው አገሮች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑት አገሮች የሚያስገቡት ከሚሸጡት በጣም ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ጉድለት (ኔጌቲቭ) አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ እንደኛ መገበያየት አላቃታቸውም፡፡ ጉድለት ያለባቸውን አገሮች ብንጠቅሰ ህንድ፣ ቱርክ፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ብሪቴን፣ አሜሪካ፣ ሶማሊያና ኬንያን ለምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ አገሮች ግን የውጭ ምንዛሪ ተቆጣጣሪ ሞግዚት አልሰየሙም፡፡ ሞግዚት የነበራቸውም ከሶሻሊዝም መክሰም ጋር ትተውት አልፈዋል፡፡ እኛ ሌላው ቢቀር ከሶማሊያ ብዙ መማር ነበረብን፡፡ በሶማሊያ መንግሥት በመፍረሱ ተቆጣጣሪውም አብሮ ጠፍቷል፣ የዶላር ችግር አልተፈጠረባቸውም፡፡ እንዲያውም ከቻይና ቀጥላ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ሁለተኛ መዳረሻ ሆናለች፡፡ ሞግዚት የሌላትና የወጪ ንግዷም ከሰል፣ ፍየልና ሙዝ የሆነ አገር እንዴት ከቻይና ቀጥላ የእኛን ዕቃ ገዥ ሆነች? የውጭ ምንዛሪውንስ ከየት አመጣች? የሚለውን ብንጠይቅ መልሱ የንግድ ሚዛንና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ግንኙነት ውስጥ ያለ መሆኑን ነው የሚታየው፡፡

      ይኼንን ከተስማማን የዶላር እጥረት አለ እንዴ ብለን እስቲ እንጠይቅ፡፡ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ጠበብቶችን ጽሑፍ የምናነብ ከሆነ ዓለምን የሚያስፈራው ዶላር ታትሞ መበተኑ እንጂ እጥረቱ አይደለም፡፡ ሲቢኤን የሚባለው ሚዲያ በዓለም ላይ የተበተነው ዶላር 12.5 ትሪሊዮን ይደርሳል ይላል ሲል፣ ሲኤንኤን ደግሞ ከፍ አድርጎ ወደ 15 ትሪሊዮን ያደርሰዋል፡፡ እነዚህ የተጋነኑ ይመስለኛል፡፡ ይሁንና እስቲ እኛው እንደምረው፡፡ በአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ግሪክንና አንዳንድ ባንኮችን ለመታደግ በወር ከ60 እስከ 80 ቢሊዮን ዩሮ የታተመበት ጊዜ ነበር፡፡ በአጠቃላይ 700 ቢሊየን ዩሮ ወይም ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር አካባቢ አትሞ የባንኮችን ዕዳ ገዝቷል፡፡ የእንግሊዝ ማዕከላዊ ባንክ ድረ ገጽን ብንመለከት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት 445 ቢሊዮን ፓውንድ ማተሙን ይገልጻል፡፡ በእዚህም የባንኮችን ዕዳ ገዝቷል፡፡ የአሜሪካኖቹ አጠያያቂ ነው፡፡ ፋይናንሻል ታይምስ የታተመውን የአሜሪካ ዶላር ወደ ሦስት ትሪሊዮን ያደርሰዋል፡፡ ሌሎችም አገሮች እንደ ጃፓን ያሉ ተመሳሳይ ዕርምጃ ወስደው እ.ኤ.አ. በ2008 ካጋጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ ለመዳን ችለዋል፡፡ ይኼንን በቅርብ የማይከታተል ሰው እንዲያው ዶላር ከዛፍ ይሸመጠጣል ወይ? ቢል አይገርመኝም፡፡ መልሱ አዎ ነው፡፡ ይህን የወረቀትና የኤሌክትሮኒክስ ብር ኢኮኖሚስቶቹ ‹‹ኳሊቴቲቭ ኢዚንግ›› (Qualitative Easing) ወይም በአጭሩ (QE) ይሉታል፡፡

      እ.ኤ.አ የ2008 የኢኮኖሚ ቀውስ መንስዔው ‹‹ክሬዲት ክራንች›› ይባላል (የብር መጥፋት ወይም እጥረት)፡፡ ይኼንን ለማቅለል ብር ማተም መፍትሔ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህ እንግዲህ ለጊዜው ችግሩን ወደ ሩቅ ይለጋው እንጂ በዓለም ላይ ትልቁን የኢኮኖሚ ውድቀትና የዋጋ ግሽበት ያመጣል ብለው ይሟገታሉ፡፡ ይኼንን የአሜሪካ ፌዴራል ባንክ ከአየር ዶላር የመፍጠርን አካሄድ ስለፈሩ፣ ሁሉንም ሰው እንደፈለገ የሚያላውስ መገበያያ የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ያስፈልጋል ብለው ፈጠሩ፡፡ ይኼንን ቢትኮይን (Bitcoin) ብለውታል፡፡ ይህ ቢትኮይን የተሻለ ሀብት ማስቀመጫ ነው ብለው ብዙዎችን አሳምነዋል፡፡ በመጨረሻ ዶላር ወረቀት ይሆናል ብለው ያመኑ ሁሉ፣ ዶላራቸውን ወደ ኮምፒዩተር ቢትኮይን ቀየሩ፡፡ ይህም ተቀባይነት አገኘ፡፡

      እንግዲህ ዓለም የታተመውን ዶላርና ዩሮ የሚያደርግበት ባጣበት ዘመን ነው እኛ ዶላር ቸገረን የምንለው፡፡ የዶላር ችግር የለም፣ ዋናው ችግሩ መብዛቱ ነው፡፡ ታዲያ ለምንድነው እኛ አገር እንዲህ ችግር የሆነው ካላችሁ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚከተለው የኮሙዩኒስት የቁጥጥርና የሞግዚትነት ተግባር ነው፡፡ የ1969 ዓ.ም. ሕግ ካልተነሳ መቼም ቢሆን የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር አይፈታም፡፡ እዚህ ላይ የምንሸጠው ነገር ከምንገዛው ካልበለጠ እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ በእርግጥ ይነሳል፡፡ ምላሹ እንደሚከተለው ነው፡፡ ከላይ የወጪ ንግድና የመገበያያ ዶላር እጥረት ያላቸው ግንኙነት ትንሽ ነው ያልኩት በምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱም ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት የዓለም አገሮች ወደ አገሪቱ የሚያስገቡት ከሚሸጡት ይበልጣልና፡፡ የንግድ ሚዛን እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ነው፡፡ ሁለት ቡድኖች በአንድ ጨዋታ አሸናፊ አይሆኑም፡፡ አንዱ ያሸንፋል፣ አለበለዚያ እኩል ይወጣሉ፡፡ በእንግሊዝኛው የዜሮ ድምር (Zero Sum Game) ይሉታል፡፡ ዶላርን  እንደ ኳስ እንውሰደውና ኳስ መረቡ ውስጥ ሲገባ የገባበት ቡድን ኳሱን አያስቀርም፡፡ ግቡ ተመዝግቦ ኳሱ ግን ይመለሳል፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ኳሱን በሙሉ አጠራቅሞ ጨዋታው በቆመ ነበር፡፡ ስለዚህ ኳስ እንዴት ይመለሳል ብለን ስናስብ የአሜሪካ ዶላር ከቻይና ዕቃ ለመግዣ ይሰጣል፡፡ አሜሪካ ለረዥም ዓመታት የንግድ ጉድለት አለባት፡፡ መጀመርያ ከጃፓን ጋር አሁን ደግሞ ከቻይና ጋር እየሄደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የጃፓን ትልልቅ ኩባንያዎች እንደ ሶኒ ያሉ ቴፕና ቴሌቪዥን ሸጠው የሰበሰቡትን ገንዘብ ይዘው አልተቀመጡም፡፡ ገንዘቡን ይዘው ወደ አሜሪካ በመሄድ ትልልቆቹን የአሜሪካ ኩባንያዎች ነው የገዙት፡፡ ለምሳሌ ሶኒ በሆሊውድ ትልቁ ባለቦታ ነው፡፡

ስለዚህ ፖዘቲቭ የንግድ ሚዛን ያላቸው አገሮች ዶላሩን ይዘውት አይቀመጡም፡፡ ወዲያው ዶላሩን ይዘው እጥረት ወዳለበት አገር ነው የሚያፈሱት፡፡ ይህ ባይሆንማ ቻይና የአሜሪካን ዶላር ሰብስባ ማስቀመጫም በጠበባት ነበር፡፡ ወዲያውኑ ወደ አፍሪካ፣ ወደ አውሮፓ፣ ወደ አሜሪካ ተመልሶ ይወጣና ሀብት ይገዛበታል፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች ባለማወቅ ቻይናን እንደ ቅዱስ አገር ወስደው ሲያሞጋግሱ ይሰማሉ፡፡ ቻይና አፍሪካን ስለወደደች አይደለም በአፍሪካ መዋዕለ ንዋይ የምታፈሰው፡፡ ብሩ ተመልሶ ካልወጣ የቻይና ኩባንያዎች በሚቀጥለው ዓመት የሚያመርቱትን ዕቃ የሚገዛ ሰው አይኖርም፡፡ ስለዚህ ቻይና የአፍሪካን ማዕድናት ትገዛለች፣ ፋብሪካ ታቋቁማለች፣ ገንዘቡን እዚያ ታውለዋለች፡፡ አሁንማ የቻይና ዜጋ ሁሉ ይኼንን ዶላር በቅናሽ ተበድሮ ከአገር ይዞ ወጥቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ ታበረታታለች፡፡ ስለዚህ ዶላር እንደ ውኃ ካለበት ወደ ሌለበት የሚሰርግ ነገር ነው፡፡ እኛ አገር የዶላር እጥረት ካለ የእኛ አገር ጥሪት (Asset) ዋጋም ተፎካካሪ ሆኖ ዝቅ ይላል፡፡ ስለዚህ ዶላር ወደ እኛ ይፈሳል፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ብንከብር የእኛ ጥሪት ይወደዳል፣ ወደዚህ የሚመጣው ይቀንሳል፡፡

      ስለዚህ አቶ ሱፍያን አህመድ ያሉት የኢኮኖሚ ትንታኔ የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ፣ ሌሎች ፖለቲከኞች ሲደጋግሙት ደግሞ እንደ እውነት የሚቆጠር ይመስላል፡፡ ይኼንን ጉዳይ ከመዝጋታችን በፊት እስኪ እኛ የምናገኘው ዶላር ከምናወጣው በጣም ያንሳል የሚለውን እንመልከት፡፡ እኛ ዕቃ የምናስመጣው በእርግጥ በ17 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ አይካድም፡፡ የምናገኘው ዶላር ግን ከ17 ቢሊዮን ዶላር በጣም ከፍ ይላል፡፡ ይህ ሰው ጤና አልያዘውም እንዴ ብትሉ አይገርመኝም፡፡ መረጃው ግን እንደሚከተለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትሸጠውና ከምትገዛው ተቀናንሶ በቅርብ ጊዜ 13 ቢሊዮን ዶላር እንደ ደረሰ መረጃው በርካታ ቦታ ይገኛል፡፡ ይህ እንግዲህ ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚላከውን ዶላር ሳይጨምር ነው፡፡ ይህ በግድ በመንግሥት ባንክ ካልገባ አይቆጠርም፣ አይገባም፡፡ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን ሬሚተንስ (ሐዋላ) በእዚህ ገደማ ይመድቡታል፡፡ ይኼንን አምስት ቢሊዮን ከ13 ቢሊዮን ስንቀንሰው ስምንት ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ትልቁን የዕርዳታ ገንዘብ የምታገኝ አገር ናት፡፡ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች፡፡ ከስምንት ቢሊየን ሦስት ቢሊዮን ስንቀንስ አምስት ቢሊዮን ጉድለት ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት መዋዕለ ንዋይ አግኝታለች የሚል መረጃ አለ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ ያለብን ጉድለት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

      እኛም ትንሽ ይሁን እንጂ ዶላር የሚያመጡ ኩባንያዎችም አሉን፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተደምረው ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያመጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ምን ያህሉ በብር ምን ያህሉ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እንደሆነ ለማጣራት ጊዜ አላገኘሁም፡፡ ይሁን እንጂ ካለብን 1.2 ቢሊየን ዶላር በላይ ያመጣሉ፡፡ ስለዚህ በቂ ሊኖረን ይገባ ነበር፡፡ እዚህ ጋ አላበቃም፡፡ ያለን ገቢና ወጪ ከተመጣጠነ ትርፍ የለንም? አለን፣ ይህም የቱሪስት ገቢ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ወደ ሚሊዮን ሰዎች መጥተው ነበር ይባላል፡፡ አንድ ሚሊዮን ሰዎች አንድ ሺሕ ዶላር ኢትዮጵያ ውስጥ አውጥተዋል ብለን ካሰብን አንድ ቢሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህ ትርፋችን መሆን ነበረበት፡፡

እኔንም ጨምሮ ስለአዲስ አበባ የምንኩራራው ከዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማቶች  ካፒታል ነች እያልን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ ቀጥላ ትልቋ የዲፕሎማቲክና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ነች፡፡ እነዚህ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት፣ ሠራተኞች፣ የአውሮፓ ኅብረት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያፈሳሉ፡፡ እዚህ ላይ አንቆምም፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት ብዙ ቢሊዮን ዶላሮች ከዓለም ባንክ፣ ከአይኤምኤፍ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከጃፓን፣ ከህንድ፣ ከቱርክና ከአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ባንክ ብድር ታገኛለች፡፡ ከላይ እንዳየነው የኢትዮጵያ ገቢ ቢያንስ ቢያንስ ከ20 እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ ወጪው የሚታወቅ 17 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ታዲያ ይኼንን ከሦስት እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ምን በላው? በአጭሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ ይህ ዶላር እዚህ አገር እንዳይቀመጥ የሚያደርጉ ሕጎች ፈጥሮ ዶላርን ሲያባርር ኖሯል፡፡ ይህ ጽሑፍ ከጋዜጣ ዕትመት በላይ ስለረዘመ በሚቀጥለው ዶላሩ የት እንደገባና ይኼንን ቀዳዳ እንዴት መድፈን እንዳለብን አቀርባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ድርሰት ትረካ አንጠልጥዬ እንዳልተወው በአጭሩ መፍትሔ ልጠቁም፡፡

  1. እዚህ አገር የውጭ ምንዛሪ እንዳያድር የሚያደርገው የብሔራዊ ባንክ በ28 ቀናት ውስጥ ዶላርህን ካልተጠቀምክበት ትቀማለህ የሚለው ነው። ይህ ሕግ የውጭ ምንዛሪ ያመጣ ሰው ወዲያው ዶላሩን እንዲለጋው ያስገድደዋል፡፡ ዛሬ ሰሊጥ ልኮ የውጭ ምንዛሪ ያገኘ ይኼንን ዶላር አጠራቅሜ ፋብሪካ አቋቁማለሁ ብሎ ከሚያስብ፣ በ28 ቀናት ውስጥ 70 በመቶውን ከመቀማቴ በፊት የልጆች ምግብ ወይም ፓስታ አስመጥቼ ላትርፍበት ብሎ እንዲያስብ ያስገድደዋል።
  2. የብሔራዊ ባንክ ማነቆ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የዶላር አካውንት መክፈት መከልከሉ ነው። የኢትዮጵያ ሦስተኛዋ የዲፕሎማቶች መቀመጫ ብትሆንም፣ እነዚህ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ በውጭ ምንዛሪ ያገኙትን ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ በአገር ቤት ባንኮች ማስቀመጥ አይችሉም። ስለእዚህ ኬንያ፣ ጂቡቲና ዱባይ ወይም ሌላ አገር ነው ደመወዝ የሚከፈላቸው። ስለዚህ ይህ ክልከላ ይነሳ፡፡
  3. የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር እንዳይገባ የሚወስነው የዳያስፖራ የባንክ ሒሳብ ክልከላ ነው። ባለው ሕግ 50,000 ዶላር ብቻ ነው አንድ ሰው ማስቀመጥ የሚፈቀድለት። ያለውን ጥሪት ሁሉ በኢትዮጵያ ባንክ ቢያስቀምጥ ለኢትዮጵያ ጉዳቱ ምን ላይ ነው? ስለዚህ ይኼም ክልከላ ይነሳ፡፡
  4.  የዶላር ማምጫው መንገድ ከተፈለገ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን እዳይገዙ የሚከለክለውን ሕግ ማንሳት ነው። ይህ ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር በቀላሉ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ክልከላ ይነሳ፡፡
  5. የዶላር ምንጭ የአክሲዮን ገበያ ማቋቋም ነው። ለኢትዮጵያ ሁለት ዓይነት የአገር ውስጥና የዳያስፖራ ኢንቨስተሮች አሉ። የመጀመሪያዎቹ ሥራቸውን ትተው የራሳቸውን ኩባንያ አቋቁመው የሚሠሩ ሲሆኑ፣ ሁለተኞቹ ግን በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የራሳቸውን ሥራ ሳይለቁ ያላቸውን ትርፍ ገንዘብ አክሲዮን የሚገዙ ናቸው፡፡ የአክሲዮን ገበያ ቢቋቋም ግን ብዙ ሰዎች አክሲዮን አትራፊና ሥራ ፈጣሪ ይሆናሉ። በተለይ እንደ ባቡር፣ ኤሌክትሪክ፣ ማዕድን፣ አየር መንገድ፣ ወዘተ. ስለዚህ ይህ ክልከላ ይነሳ፡፡
  6. የቱሪስት ቪዛ ችግር ነው። የኢትዮጵያ መግቢያ ቪዛ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር ነው። ሌላው አገር በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር ነው። የአገር ደኅንነት በአሜሪካ ሲአይኤና ኤፍቢአይ የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች ሁሉን ነገር ተጠራጣሪ ሰዎችን ነው የሚቀጥሩት። የአሜሪካ ቪዛ በሲአይኤ ቢሆን የሚሰጠው ማንም ሰው ወደ አሜሪካ አይገባም ነበር። ስለዚህ ኢምግሬሽን ወደ ውጭ ጉዳይ ይዘዋወር፡፡
  7. የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል መሬትን ለቀቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር  ቤት ተመልሰው አይመጡም፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ አገራቸው የሚያርፉበትና የሚጦሩበት ቤት ይፈልጋሉ፡፡ መንግሥት ደግሞ በድህነት አስተሳሰብ ውስጥ በሚኖሩ አመራሮች ተይዞ ትንሽ ትንሽ መሬት እየቆነጠረ በሊዝ በካሬ ሜትር 100 ሺሕ ብር መሸጥ ነው የሚፈልገው። ይልቁንም ገበሬውም እንዲጠቀም የገበሬውን የካሳ ክፍያ የአስተዳደር ወጪን ብቻ ቀንሶ ገበሬው እንዲያገኝ ቢያደርግና መሬት ለቤት ግንባታ ቢያቀርብ፣ ነገ 250 ካሬ ትሜር በ10 ሺሕ ወይም በ20 ሺሕ ዶላር ለ100 ሺሕ ሰዎች በስድስት ወራት ውስጥ መሸጥ ይችላል። ለኮንዶሚኒየም ምዝገባ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንደተመዘገበው ሁሉ፣ 100 ሺሕ ዳያስፖራ ቢገዛ በቀላሉ አገሪቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች። ስለዚህ በዶላር ቢሸጥ ብዙ ዶላር ያመጣል፡፡
  8. ለውጭ ምንዛሪ እጥረት መቀነስ ብር ከአገር እንዳይወጣ ሲደረግ፣ በሌላ አገር መገበያያ መሆኑ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ጥንካሬ እንደሚያሳይ መገንዘብ ይገባል። ስለእዚህ ተቀባይ ካገኘ ብር ይዞ መውጣት ወንጀልነቱ ይቅር።
  9. መፍትሔው ደግሞ የየትኛውም አገር ሰው በኢትዮጵያ ባንክ የዶላር አካውንት መክፈት ይቻል፣ የወንጀል ዶላር እስካልሆነ ድረስ። የእኛ አገር ሰዎች በኬንያ፣ በጂቡቲ፣ በዱባይና በኡጋንዳ መክፈት ይችላሉ። ይህ እዚህ ቢፈቀድ ምን ይጎዳል? ስለዚህ ይህም ክልከላ ይነሳ፡፡

      እነዚህ ዘጠኝ ክልከላዎች ቢነሱ የዶላር ከምችቱ ያድጋል፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ አሥረኛውን መፍትሔ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይኼም የ1969 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥርን ማንሳት ነው፡፡ እኔ ይኼንን ጽሑፍ እያረምኩ የነበርኩት ኬንያ ሆኜ ነው፡፡ በኪሴ ያለን ዶላር ይዘህ አትውጣ የሚለኝ የለም፡፡ ያለኝን ሁሉ በዶላር ቀይሬ መውጣት መብቴ ነው፡፡ ስለዚህ ዶላር ይዤ ወደ ኬንያ ለመግባት አልፈራም፡፡ ፍተሻም ብርበራም የለም፡፡

      ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም ኮንሰልቲንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፣ ዓለም አቀፋዊ የፕራይቬት ኢኩቲ ኢንቨስተር በማምጣት የኢትዮጵያን ኩባንያዎች ለኢንቨስትመንት በማብቃት የማማከር ሥራ በመሥራት ላይ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...