Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉስሜታችንን ቆንጠጥ አድርገን በማስተዋል እንራመድ

ስሜታችንን ቆንጠጥ አድርገን በማስተዋል እንራመድ

ቀን:

በሰለሞን መለሰ ታምራት

‹የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር› በማለት ወደ ሥልጣን የተጠጋው ደርግ ለ17 ዓመታት ያለ ዕረፍት ከወዲህና ከወዲያ ሲላጋ ቆይቶ እጁ የዛለበት፣ ‹ለነፃነት› የሚታገሉ ኃይሎች ደግሞ ‹ጉሮ ወሸባዬን . . . ›› እየዘፈኑ ወር ተራቸውን ወደ ሥልጣን የመጡበት 1983 ዓ.ም. የትናንትን ያህል ቅርብ መስሎ ይሰማኛል፡፡

      በእዚያን ጊዜ ‹‹ነፍስ ያወቀ›› ሁሉ እንደሚያስታውሰው፣ በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙት የሁሉም የኢትዮጵያውያን ስሜት በተለያየ መንገድ ጫፍ የነካበት ወቅት መሆኑን ማስተዋል ይችል ነበር፡፡ አሸናፊዎቹ ጠላታቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አፈር ከመሬት የደባለቁት በመሆናቸው ጠዋትና ማታ በጭፈራና በሆታ ምድሪቱን ቀውጢ ሲያደርጓት፣ በሽንፈት እልህ ውስጥ የሚገኘው ሌላው ወገን ደግሞ በበኩሉ ይኼንን የተንኮል ሴራ ሥር ከመስደዱ በፊት በወቅቱ ፋሽን በነበረውና ትርጉሙንም በቅጡ ባልተረዳው በዴሞክራሲያዊው መንገድም ይሁን በአመፅ፣ አሊያም በተገኘው መንገድ ለማስወገድ እንደ አዲስ ደፋ ቀና ማለት ጀመረ፡፡

       ከላይ የተገለጹትን ሁለቱንም ጎራዎች የሚያመሳስላቸው ዋነኛው ጉዳይ በከፍተኛ ስሜት ሲመሩ የነበሩ መሆናቸው ነበር፡፡ የስሜት ህዋሳቶቻችን ከሰውነታችን ውጪ የሚገኘውን ዓለም እንድንረዳባቸው የተሰጡን ፀጋዎቻችን በመሆናቸው፣ እጅግ አስፈላጊ የህልውናችን መሠረቶች ናቸው፡፡ የአንዱ ወይም የሌላው ስሜታችን መጉደል፣ ለጎደለው ቦታ የሌሎችን በጎ ፈቃድ ለመጠየቅ የምንገደድበትን ሁኔታ ስለሚፈጥር በመጠኑም ቢሆን ያጎድለናል፡፡ ከእዚህኛው ጉድለት የበለጠ የሚያጎድለን ደግሞ እነዚህን የስሜት ህዋሳቶቻችን ያላግባብ ስንጠቀምባቸው ነው፡፡ ያላግባብ ማለት በብዛት ወይም ከመጠን በላይ፣ እጅግ በተጋነነ መልኩ ከራሳችን አልፎ ሌሎችን ልንመዝንበትና የሌሎችን ድንበር አልፈን ለመሻገር በምንሞክርበት ጊዜ ማለት ነው፡፡

      በምሳሌ ላብራራውና ጆሯችን ከስሜት ህዋሳቶቻችን መካከል አንዱ ነው፡፡ እናም በመንገድ ላይ ስንሄድ የመኪና ጎማ ሲፈነዳ ሰማንና በድንጋጤ (እባብን ያየ በልጥ ይደነግጣል እንደተባለው) ቦምብ የፈነዳ መስሎን አካባቢውን ማሸበር እንጀምራለን፡፡ በአካባቢያችን ያለው ሰው በሙሉ እኛ የሰማነውን በትክክል የሰማ ቢሆንም፣ ሁሉም የሰማው በራሱ . . . በግሉ ጆሮ ነውና እያንዳንዱ የሚወስደው ዕርምጃ የተለያየ ነው የሚሆነው፡፡ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት አደጋ እዚህ ላይ ነው የሚከሰተው፡፡ አንደኛው ነገር የሰማነውን ድምፅ ከማጣራታችን በፊት አላስፈላጊ ዕርምጃ ወስደናል (በድንጋጤ ራሳችንን ከአደጋ አጋልጠናል)፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ሌሎች በአካባቢያችን ያሉ ሰዎችን በግል ስሜቶቻችን ላይ ተመሥርተን የግላቸው የሆነውን መብታቸውን ተጋፍተናል፣ ዕርምጃ እንዲወስዱም ግፊት አድርገንባቸዋል (ቢያንስ ጊዜያዊ ሰላማቸውን ነስተናቸዋል)፡፡ እንደ ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ስጦታዎች ሁሉ ስሜትንም ያላግባብ (ያለ ቦታውና ያለ ጊዜው) ስንጠቀምበት ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ አንዳንዴም ምነው ስሜት ባልኖረን ያሰኛል፡፡

      ይኼንን ሁሉ ሐተታ ያቀረብኩት ዛሬን በትናንት መነጽር ሳስተውለው፣ ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ስለሠጋሁ ነው፡፡ ዓለም በሙሉ እየተረዳው እንደመጣው በአገራችን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ለውጥ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ማኅበራዊውንና ኢኮኖሚያዊውን ዓለም የሚዘውረው ደግሞ ፖለቲካው ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡

      ቀደም ሲል የሃይማኖት ተቋማት የማኅበራዊና የኢኮኖሚውን ደንብ በማውጣት ትልቁን ድርሻ ይወጡ የነበረበት ዘመን እያከተመ፣ ዛሬ ዛሬ ፖለቲከኞች ሆነዋል፡፡ እነዚህን የሃይማኖት ተቋማት አደብ የሚያስይዙት በዓለም ላይ እንደተከናወኑት በርካታ ለውጦች ሁሉ፣ ይኼው በአገራችን የነፈሰው የለውጥ ንፋስ መሽቶ በነጋ ቁጥር አዳዲስ ነገሮችን እያሳየን ይገኛል፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙበት ያለፉት ሦስት ወራት ከሦስት ዓመታትም በላይ የፈጠኑ መሆናቸው ሲሆን፣ ለአንዳንዶቻችንም ሕልም እንጂ ዕውን አልመስል እንዳሉን እንገኛለን፡፡ ታዲያ እንደ ማንኛውም ለውጥ ሁሉ በእዚህም ለውጥ መካከል የሚያተርፍም ሆነ የሚከስር አካል መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ትልቁ መገለጫው ደግሞ በአብዛኛው እነዚህን ሁለት አካላት ቦታ የሚያቀያይር መሆኑ ነው፡፡ ለእዚህም ሳይሆን አይቀርም ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ጭምር ለውጥ (ምርጫ) ሲመጣ ከጦርነት ያልተናነሰ ውዝግብ የምናየው፡፡ በእዚህ ከፍተኛ ውዝግብ መካከል ሕግ የበላይ ሆኖ ካልተገኘና የሕግ አስከባሪ አካላትም ስሜታዊ ሆነው ለአንዱ ወይም ለሌላኛው ወገን ካደሉ ‹አዲዮስ›! ያቺ አገር አበቃላት ማለት ነው፡፡

      ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 27 እና ከእዚያም በላይ ዓመታት ልጆችና የእንጀራ ልጆች በሚመስል ሁኔታ የዜጎች የኑሮ ልዩነትም ሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ ክፍተት በከፍተኛ ደረጃ እየሰፋ በመምጣቱ፣ በሌላ አነጋገር አብዛኛው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ የሚኖርና በፖለቲካው ውስጥም ድምፁ የታፈነ በመሆኑ፣ ዛሬ ዕድሉን ያገኘ ሲመስለው ነባራዊውን ሁኔታ አፈራርሶ በእጁ ለማስገባት መጣጣሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ በአንፃሩም ላለፉት ዓመታት በተከፈቱላቸው የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድሎች ምክንያት ብዙ ርቀቶችን የተጓዙ ‹የጊዜው› ሰዎች፣ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ ያላቸውን አቅም በሙሉ አሟጠው ለመጠቀም መፈለጋቸውም ተፈጥሯዊ ነው፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያን የግል የውስጥ ስሜቶቻችንን በመቆጣጠር በኩል ከሌሎች የአፍሪካም ሆነ የዓለም አገሮች የተለየን ብንሆንም (ተርበን እንዳልተራብን፣ ተገፍተን እንደተመቸን፣ ከፍቶን እየሳቅን መኖር የምንችልና ስሜቶቻችንን ለማንም ሳንገልጽ ዕድሜ ዘመናችንን መቆየት፣ በአጭሩ ድብቅነታችን ወሰን ያለፈ መሆኑ)፣ ይኼው የተደበቀው ማንነታችን ጊዜውን ጠብቆ ሲፈነዳም ሰማይና ምድር የተጋጠሙ እስከሚመስል ድረስ ትንፋሽ የሚያሳጣ ሲሆን ይታያል፡፡ ለያዥም ለገላጋይም አስቸጋሪ ነው የምንሆነው፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ለዘመናት ታፍኖ የቆየው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል ሲፈነዳ ምን ያህል ስሜታዊ ሆኖ እንደነበር፣ ከኢሕአፓ ጎን ተሠልፈው የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ወታደራዊ መንግሥት ለመገዳደር የደፈሩትን እነዚያን የአንድ ትውልድ ወጣቶች በማስታወስ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ዛሬም ታሪክ ራሱን ሲደግም በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ሆነ ሌሎች ወታደራዊ ዕርምጃዎችን ሳይፈሩ ባደረጉት ተከታታይ ተጋድሎ፣ ድምፃቸውን የሚሰማና የሚመልስ አካል ቀድሞውንም ድምፃቸውን አፍኖ ከነበረው፣ ሲገድልና በየዘብጥያው ሲወረውራቸው ከነበረው አካል መካከል ብቅ በማለቱ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከዳር እስከ ዳር ነቅለው በመውጣት ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

      በአንፃሩም ባለፉት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ አካሄድ ተመችቷቸው የነበሩና ዛሬ እየነፈሰ ያለው የለውጥ ንፋስ በአንድ ወይም በሌላ ሁኔታ ጥቅማችንን ያስቀርብናል ብለው ያሰቡ ኃይሎችም (በኢሕአዴግም ሆነ በተቃውሞው ጎራ ተሠልፈው የነበሩትን ሁሉንም ያጠቃልላል)፣ የሚታየውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሲያጣጥሉና ከተራ የሕገወጦች ግርግር (Mob Rule) ጋር ሲያመሳስሉት እያስተዋልን ነው፡፡ ከላይ በተመለከትናቸው በሁለቱም ጎራዎች ውስጥ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች በይበልጥ ስሜቶቻችንን ያላግባብ ወደ አንደኛው ፅንፍ እንደ ጎተትናቸው ከዳር ቆሞ ለሚያስተውል ተመልካች በግላጭ የሚታዩ ናቸው፡፡ በተለይም በማኅበራዊው ሚዲያ የሚሰማው ሥርዓት ያጣ አምባጓሮ (የማኅበራዊ ሚዲያውን መዘዝ አሳንሶ መመልከት ጊዜው የደረሰበትን የሥልጣኔ ደረጃ ካለማስተዋል የሚመነጭና ‹ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ› ተብሎ የተተረተውን ምሳሌ አለማስተዋል ይመስለኛል)፣ የምናያቸውን መልካም አጋጣሚዎች የሚያጨልም፣ አደብ ካልተበጀለትና በጥንቃቄ ካልተያዘም ባልተጠበቀ አቅጣጫ አገሪቱን ወደ ጥፋት ሊወስዳት የሚችል መሆኑን መገመት እንደ ጨለምተኛነት ሊያስቆጥር አይገባም፡፡

      በምሥራቅ አውሮፓም ሆነ በሰሜን አፍሪካ ተጀምረው ፍፃሜያቸው ካላማረውና ጊዜው ረዝሞብን ካልዘነጋነውም ራሳችን የ1966 ዓ.ም. የለውጥ እንቅስቃሴዎች ትምህርት በመውሰድ፣ የተጀመረው አጋጣሚ እንደታሰበው ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጣናው ሰላምና ብልፅግና የሚያመጣ እንዲሆን ልናስችለው ግድ ይለናል፡፡ ይኼንንም መልካም ጅምር ከግብ ለማድረስ የሚቻለው ስሜቶቻቸውን መቆጣጠር የሚችሉና በዕድሜ የበሰሉ ‹ትልልቅ› ሰዎች በጉዳዩ ጣልቃ ሲገቡበት አንተም ተው፣ አንተም ተው በማለት የተቆረጠውን አርጩሜ ማስጣል ሲችሉ ነው፡፡

      በበኩሌ ለእዚህ ትልቅ ኃላፊነት ራሴን ለማጨት የማልደፍር ተራ ዜጋ ብሆንም፣ የሁኔታው አካሄድ ስላላማረኝ በእዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ድርሻ ያላቸው ወገኖቼን፣ በአጠቃላይ እየገነፈለ የመጣውን ስሜታቸውን እንዴትአርግበው ሊጓዙበት የሚገባውን መንገድ በትህትና ለመጠቆም ነው የዛሬው ጽሑፌ አቅጣጫ፡፡ እነዚህ ድርሻ ያላቸው አካላትም የለውጡ እንቅስቃሴ ደጋፊዎችና የለውጡ ተቃዋሚዎች (ተቺዎች) ሲሆኑ፣ ሦስተኛው የለውጡ እንቅስቃሴ አካልም አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት የክልል መንግሥታትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ናቸው፡፡ በእነዚህ አስጨናቂ ወቅት የሦስቱም ሚና ምን መሆን እንዳለበት የበኩሌን ምልከታ ከዚህ ቀጥዬ አቀርባለሁ፡፡

ለለውጡ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች

   በከፍተኛ ደረጃ ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል የተካተተበት ይኼ ምድብ ስሜቱ ጫፍ የነካበትን እንቅስቃሴ ማንም ተመልካች ማስተዋል ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ወጣቶች የቀድሞውን ሥርዓት ያልደረሱበትና የጭካኔውንም ልክ ያላዩት በመሆናቸው፣ እንዴት ደርግንና ‹አብዮታዊውን መሪ› ሊናፍቁ እንደቻሉ ይገርመኛል፡፡ በእዚህ ደረጃ ስሜታዊ የሆኑበትና ባለፉት 27 ዓመታት የተገኙትን መልካም ነገሮች በሙሉ (ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጨምሮ) ለማየት እንዳልወደዱ ላስተዋለው፣ የስሜታችሁን ጫፍ መድረስ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የለውጡ ደጋፊዎች ሆይ! ድጋፋችሁን ‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው› በሚለው መንገድ አታድርጉት፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱን አካል በሠራው መልካምም ሆነ በጎ ሥራው ልትደግፉት ወይም ልትቃወሙት ይገባል፡፡ ድጋፍና ተቃውሟችሁንም ቢቻል ዛሬ ያሉትን የአገሪቱን ሕጎች በማክበር ይሁን፡፡ ቢቻል ያልኩበት ምክንያት አንዳንዶቹ ሕጎች ራሳቸው ሕገወጥ መሆናቸውን ስለምረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የኮከብ ምልክት የሌለበትን ልሙጡን ባንዲራ መያዝ ሕገወጥ የሚሆንበት ምክንያት ጨርሶ ባይገባኝም፣ ከመሀሉ የሚገኘውን የኮከብ ምልክት ግን ቀዶ በማውጣት ባንዲራውን መያዝና መርገጥ ግን ፅንፍ የወጣ ስሜታዊነት በመሆኑ ሊታሰብ አይገባውም ነበር፡፡ የለውጡን እንቅስቃሴ የማይደግፉትን በሙሉ እንደ ጠላት መመልከትም አይገባም፡፡ ይልቁንም አብዛኛዎቹ የለውጡ ነቃፊዎች ለዘመናት ሲሰበክላቸው የነበረው ‹እኛ ከሌለን ትጠፋላችሁ› ፕሮፓጋንዳን አምነው የተቀበሉና የነብርን ጭራ እንደያዙ የሚሰማቸው በመሆኑ፣ ሊታዘንላቸው የሚገቡ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

      ከመካከላችሁም በርካታ የበግ ለምድ ለብሰው የገቡ ተኩላዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አውቃችሁ አካባቢያችሁን በንቃት መመልከት አለባችሁ፡፡ ከተሸነፈው የቀደመው አስተሳሰብ ጋር ጎንበስ ቀና ሲሉ የነበሩና ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ የተባሉት አንዳንዶቹ ዛሬ ጃኬታቸውን ገልብጠው በመልበስ (የሰሜን ኮሪያው የወቅቱ መሪ የአገራችን ወጣት ወንዶች በሙሉ ፀጉራቸውን ራሳቸው በተቆረጡት ዓይነት እንዲቆረጡ የሚል ትዕዛዝ አውጥተው ነበር አሉ)፣ ሲቀላቅሏችሁ ተስተውሏልና የቁጥራችሁን መብዛት ብቻ ዓይታችሁ ሥራችሁን እንደ ጨረሳችሁ አይሰማችሁ፡፡ ይልቁንም ዛሬ እየተሰበከ ያለው የፍቅርና የመደመር ጥሪን በአግባቡ ተረድታችሁና ስሜታችሁን በመቆጣጠር፣ በአካባቢያችሁ የሚገኙትን ሌሎችንም በፍቅር የለውጡ ደጋፊ ለማድረግ ትችላላችሁ፡፡

ለለውጡ እንቅስቃሴ ተቃዋሚዎች

ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ እንደ ነበረው የትኛውንም ጉዳይ መቃወም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ለመላዕክትም የተሰጠ ተፈጥሯዊ መብት ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሁሉም ሰው አንድን እንቅስቃሴ የሚቃወምበት በቂ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ጥያቄው ያለው ምክንያቱ ትክክለኛና ተጨባጭ ነው? ወይስ የተሳሳተና በምናባዊ ስሜት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ? የሚለው ብቻ ይሆናል፡፡ እናንተም የለውጡ ተቃዋሚዎች (ተፎካካሪዎች ባለማለቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ) የለውጡን አካሄድ መቃወማችሁ ምንም ዓይነት ስህተት እንደሌለበት በትህትና ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡ የመጣውንም የእንደመር ጥሪ አለመቀበል የተከበረ ሙሉ መብታችሁ መሆኑን ማንም ሊነግራቸሁ አይገባም፡፡ ተቃውሟችሁ ግን ፈጽሞ በመሸነፍ ስሜት ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም፡፡ በመሠረቱ ዛሬ የተሸነፈ ሐሳብ ከጥቂት ማስተካከያ ጋር ከመጣ ነገ ደግሞ አሸናፊ ሊሆን እንደሚችል በተለያዩ አገሮች ያየናቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች አስተምረውናል፡፡

      ከመሸነፍ ስሜትም በላይ የሚጎዳው ሌላው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ደግሞ፣ ተቃውሞውን ኃይል ወደ ቀላቀለ ዕርምጃ መገፋፋት ነው፡፡ በእዚህ የኃይል ዕርምጃ ማንም አትራፊ ሊሆን ካለመቻሉም በላይ፣ ጨዋታውን በሙሉ በዜሮ አባዝቶ የሚከፍል አስቀያሚ ውጤት የሚያመጣ ነው የሚሆነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ነገ መታረቅ ሊመጣ ይችላልና ፀብንም ቢሆን በልክ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለማስፈራራት እንኳን ተብሎ የሚጀመር እንቅስቃሴ ድብልቅልቅ ያለ ጦርነትን ሊቆሰቁስ እንደሚችል የኢትዮ ኤርትራን የ1990 ዓ.ም. ግጭት ያስተዋሉት ሰዎች ነግረውናል፡፡ በተለይም አሁን የሚታየው የለውጥ እንቅስቃሴን ለማምጣት ከላይ እንደ ገለጽኳቸው ዓይነት ወጣቶች ብዙ ዋጋ የከፈሉበትና በጣም ስሜታዊ የሆኑበት በመሆኑ፣ ሌሎች የለውጥ ተቃዋሚ ወጣቶችን ወደ ኃይል ዕርምጃ መገፋፋት እጅግ አክሳሪ ጨዋታ መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላችኋል፡፡

      ከሁሉም በላይ ግን ለውጡ ይዞት የመጣው መልካም አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል፣ በጎ ገጽታውን መመልከት መቻል ብልህነት ይመስለኛል፡፡ በተለይ ይኼንን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚቃወሙ የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የወጣውን የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ቁጥር 1888 (ታሪካዊ ቁጥር ነው አይደል?) ገጽ 39 ላይ የተጻፈውን መልዕክት ቢያነቡት ልብ እንዲገዙ የሚያስችላቸው ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም ቢሆን ፍላጎታችን አገራችን የብጥብጥ አውድማ እንዳትሆን ከሆነ፣ ዛሬ ‹‹ግንፍል ግንፍል›› የሚል ስሜታችንን አደብ በማስያዝ ለተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር ብንሠራ ይበጃል፡፡

ለክልልም ሆነ ለማዕከላዊ መንግሥታት

ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገሮች በምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን የወጡ መሪዎች የሚያደርጉት የመጀመርያ ንግግር ላይ አፅንኦት የሚሰጡት፣ አገልጋይነታቸው መንግሥታቸውን ለመረጡት ብቻ ሳይሆን ለምርጫ ተቀናቃኛቸው ድምፃቸውን ለሰጡትም ጭምር መሆኑን ነው፡፡ ይኼ ንግግር የተሸናፊነት (የበታችነት) ስሜትን እጅግ የሚያስቀር ብቻ ሳይሆን፣ ተቃዋሚዎች በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ዕርምጃ እንዳይወስዱ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተዳድር መንግሥት ለየትኛውም የፀብ ምክንያት በር የሚከፍት ሆኖ መገኘት የለበትም፡፡ መንግሥት በአሸናፊነት መንፈስ በመኩራራት ደጋፊዎቹንና ነቃፊዎቹን ለመከፋፈል የሚሞክር ከሆነ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ጨዋታ መጀመሩን ሊገነዘበው ይገባል፡፡

      ዛሬ ጥቂቶች የሆኑት ተሸናፊዎች ነገ በብዙ እጥፍ ተባዝተው የሚመጡ መሆናቸውን ማስተዋልም ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ለጠላትህ ጉድጓድ ስትቆፍር አታርቀው ነገ ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና›› የሚለው አባባል፣ ይኼንን ጊዜ በትክክል የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ወቅቱ የሁሉም ስሜት ጫፍ የነካበት በመሆኑ፣ ማን እስከ መጨረሻው ድረስ አብሮን እንደሚጓዝ አናውቀውምና ሁሉንም በእኩል ዓይን መመልከት፣ ከመንግሥታት የሚጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ለደጋፊዎቻቸው የሰጡትን ገደብ የሌለው መብት ለተቃዋሚዎቻቸውም መንፈግ የለባቸውም፡፡ ማንም ቢሆን ለምን በእዚህ መንገድ ሐሳብህን ገለጽክ ተብሎ ጣት ሊቀሰርበት አይገባም፡፡

      በተለይ መንግሥት የየትኛውንም የመገናኛ ብዙኃን መብት ለመዳፈር ፈጽሞ መሞከር የለበትም፡፡ በቅርቡ እንደተደረገው ይህንና ይኼንን ዘገባ ለምን አልሠራችሁም የሚልበት አንዳችም ምክንያት ሊኖረው አይገባም፡፡ እንደኔ እንደኔ መንግሥት ለቀጠራቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም እንኳን (አይደለም በደመወዝ ለማያስተዳድራቸው) በእዚህና በእዚያ መንገድ ልትጓዙ ይገባል ብሎ አቅጣጫ ባይመራ እመርጣለሁ፡፡ ኪነ ጥበብ ከውጭ በሚመጣ ግፊት መንቀሳቀስን አጥብቆ እንደሚፀየፍ ይገባኛልና፡፡ መንግሥት ለእያንዳንዳቸው ነፃነታቸውን ከሰጣቸው ጥበብ እንደመራቻቸው ቢሠሩ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ዘመናችን ቅን አሳቢዎችን ብቻ ሳይሆን ለሆዳቸው የሚሞቱ በርካታ አርቲስት ተብዬዎችንም አፍርቷልና፡፡ ይኼንን የመንግሥትን ስሜታዊነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የለመዱትን የብልጣ ብልጥነት ቀረርቷቸውን እንዲሞክሩ ማበረታታት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

      በአጠቃላይ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ከስንት አንድ ጊዜ ብቅ የሚለው የለውጥ ንፋስ በአገሪቷ ላይ መታየቱ በሚሰጠን ተስፋ በመነቃቃትና ፅንፍ ከወጣ ስሜታዊነት በመታቀብ፣ የተጀመረው የፍቅርና የመተሳሰብ ስሜት ከአገራችን አልፎ ለመላው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የሰላምና የብልፅግና ጅማሮ እንዲሆን በማስተዋል ልንራመድ ይገባናል፡፡ ‹‹ከታሪክ የማይማር ታሪክን ለመድገም ይገደዳል›› እንደሚባለው፣ ስሜታችንን መቆጣጠር አቅቶን ያገኘነውን መልካም ዕድል እንዳናበላሸው አደራ እላለሁ፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡                             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...