Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየምንታገለው ምኞታዊነትና ሕልመኛነት የጋረጠብንን ተላላ ፖለቲካ ነው

የምንታገለው ምኞታዊነትና ሕልመኛነት የጋረጠብንን ተላላ ፖለቲካ ነው

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

ሁለት ዓለማት አሉ፡፡ በአካል የምንኖርበት ተጨባጭ ዓለምና የተምኔት (ፋንታሲ) ዓለም፡፡ ጥንት ከተምኔት ጋር የምንገናኘው በሌሊት ቅዠት፣ በቀን ቅዠትና በእነ ዓሊ ባባ ዓይነት ተረቶች (መናፍስት ጂኒዎች ብዙ ተዓምራት በሚሠሩባቸው) አማካይነት ነበር፡፡ የፊልምና የቪዲዮ ጥበብ ከመጣ ወዲህ ግን ተምኔት ከውስጣዊ ቅዠትነትና በቋንቋ ከመተረክ አልፎ፣ በድርጊት ሲፈጸሙ የሚታዩ ትዕይንቶች ለመሆን በቅቷል፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመናችን የተምኔቱ ዓለም እጅግ እየተንተረከከ ነው፡፡ ተጨባጩና ተምኔታዊው ዓለም የተቀላቀሉባቸውን የእነ ‹ሃሪ ፖተር› እና ‹የካሪቢያን የባህር ዘራፊዎች› ታሪኮችን ጨምሮ የማይፈጠሩ ታሪኮች፣ የማይፈለሰፉ ጉግማንጉጎች፣ የማይፈለሰፉ የፀሐያዊ ሥርዓቶች ውጊያዎች የሉም፡፡ የጊዜያችን ዘመናይ ወጣቶችና ሕፃናት በፊልምና በቪዲዮ ጨዋታዎች፣ በአሻንጉሊቶች ሁሉ ከእነሱ ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ እነሱንም ሆነው እየኖሩ ነው፡፡ በአሻንጉሊት መልክ አካላዊነት ባገኙ ጉግማንጉጎች ተከበው ወይም የጉግማንጎቹን አልባሳት ለብሰውና አሻንጉሊታዊ መሣሪያቸውን ታጥቀው ተምኔታዊ ተዓምራት ያካሂዳሉ፡፡ ተዓምራታቸው ከሥጋ ለባሽ አፍ ጨረርና እሳት ከመትፋት፣ ወይም ከሥጋ ለባሽነት ወደ ነበልባልነት ከመቀየርና ከመሳሰሉት እጅግ ርቆ የሚሄድ ነው፡፡ ይህን መሰሉ ተምኔታዊ ሕይወት እጅግ ቅርብና ዕለታዊ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ እነ ‹‹ስፓይደር ማን››፣ ‹‹ፓወር ሬንጀርስ››፣ ወዘተ የንግግር ምሳሌዎች እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡

በዚህ መሰሉ ኑሮ ውስጥ የእኛም ዘመናይ ሕፃናትና ወጣቶች ከትልልቅ ከተማ እስከ ገጠር ድረስ አሉበት፡፡ ፈረንጅ የሚያመርታቸው ፊልሞች፣ ቪዲዮዎችና ኮምፒዩተር ነክ ጨዋታዎች በቀላል መሣሪያዎች አማካይነት የትም መግባት የሚችሉ (ገጠርነት የማያግዳቸው) መሆናቸው ፈረንጆች የቀጩትን ዓለም ‹‹ለመቅጨት›› አብቅቶናል፡፡ የእኛዎቹ ፊልምና ቪዲዮ ሠሪዎች ግን ተምኔታዊ ሸቀጦችን የማምረት ደረጃ ላይ ገና አልደረሱም፡፡ ምኞትን በማሟላት ጥንታዊ ደረጃ ውስጥ ገና እየዳከሩ ነው፡፡ ድብልቅልቅ ያለ ሠርግ፣ እንከን የለሽ ፍቅርና ትዳር እናልማለን፡፡ በዕውን ኑሮ የሌለንበት ደግነት ባህርያችን ሆኖ በየመንገዱ ያለውን ሰው ሁሉ ብንረዳ እንመኛለን፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ምኞቶቻችን ገፀ ባህርይና ታሪክ ሆነው በፊልሞቻችን ብቅ ይላሉ፡፡ እናም እነዚህን ፊልሞች (በምናያቸው ሰዓት) በዕውናዊ ኑሮ ያጣነውን ነገር ይሞሉልናል/ይክሱናል፡፡

ምኞታዊነትን በሌላ መልክም እንኖረዋለን፡፡ በፊልምና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ወዘተ ውስጥ የምናየውን ምዕራባዊ አኗኗርን (አለባበስ፣ አበጣጠር፣ አካሄድ፣ ሰላምታ አሰጣጥ፣ አነጋገር) በመቅዳት፣ አገራዊ ስሞችን ፈረንጅኛ እንዲመስሉ በማድረግ፣ ወዘተ ምኞታችንን እናሟላለን፡፡ ይህ ኑሮ ወጣቶቻችን ላይ ከመፅናቱ በቀር ጎልማሶቹንም ሁሉ ለመሰልቀጥ የቻለ ነው፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ የረር በር የሚባል ሠፈር የሄደ ሰው ‹‹ጃክሮስ›› የሚባል ቅብጥ ያለ መንደርን በአንድ ጎን ማየቱ አይቀርም፡፡ በመንደሩ ውስጥ የማለፍ ዕድል ካጋጠመውም ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለሁት? ብሎ ሊገረም ይችላል፡፡ በ1980ዎቹ ውስጥ ያ ሥፍራ ለጥ ያለ ሜዳና የእርሻ ሥፍራ ነበር፡፡ ወደዚያው ጃክሮስ የሚባል አንድ ግሪካዊ ቤት አልሚ ነኝ ብሎ በአገር ውስጥና በውጭ ከነበሩ ውስን አትዮጵያውያን ገንዘብ (በዓረብ አገሮች ግርድና የተጠራቀመችን ፍራንክ ጭምር) ለቃቅሞ ሽው ይላል፡፡ ቀሊጦች ለመንግሥት ኡኡ፣ አቤት ይላሉ፡፡ አቤቱታቸው ተጓትቶም ቢሆን መልስ ያገኝና በአዳዲስ አባላት አቅማቸውን አጠናክረው እዚያው ሥፍራ ላይ ቤት እንዲገነቡ ይፈቀዳል፡፡ የጃክሮስን ስም ግን አልፋቁትም፡፡ ፈረንጅኛን የሚያሟላው ስም የቄንጠኛው መንደር መታወቂያ ከመሆን አልፎ፣ በዚያ አካባቢ የተከፈቱ አንዳንድ ንግድ ቤቶችም ለቀም ያደረጉት መጠሪያ ሆነ፡፡ ወላጆች ዛሬ ‹‹ሠልጥነን›› ለልጆቻችን የምናወጣውን ስምና ድሮ ‹‹ሳንሠለጥን›› እናወጣ የነበረውን ስም ብናነፃፅር፣ ለእነፓስታና ለእነፉርኖ ያዳበርነውን አክብሮት ከዕውቀት የመጣ ወይስ ከፈረንጅ አምልኮ? ብለን በመመርመር ከምንደርስበት ውጤት የሚራራቅ አይደለም፡፡ ሐበሻ ከሆነ ሐኪም ይልቅ ፈረንጅ ለሆነ ሐኪም ያላንዳች መረጃ ዓይናችንን ጨፍነን የላቀ ግምት ለፈረንጁ መስጠት፣ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያለ ችግራችን ነው፡፡ ፈረንጅን በድፍኑ አዋቂ፣ ሥልጡን፣ የማያታልል፣ ፈረንጅ የሠራውን ነገር ኮሾ ያልሆነ አድርጎ ማየት ገመናችን ነው፡፡ ይህ የተዛባ አመለካከታችን የፈረንጅ አኗኗርን እየቀዱ የጥቁር ፈረንጅ የመሆንን ምኞት ከማሟላት አልፎ፣ ፈረንጅ ቤት ያለ ዕውቀትንና ጥበብን እየበዘበዘ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ጥረትና ውጤትን ያመጣ ግን አይደለም፡፡ ጃፓኖችንና እኛን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ አንስቶ ያለያየንም ይህ ልዩነት ነበር፡፡

የፈረንጅ ጥበብን ቀድቶም ሆነ የአገር ልጅ ጥበብን መሠረት አድርጎ የአገር ውስጥ አመራረት እየዳበረ እንዳይሄድም፣ ይኼው ፈረንጅን ከማምለክ የመጣ ከአገር ውስጥ ምርት ይልቅ ከውጭ የሚመጣን ዕቃ የማምለክና የማንኳተት ጭፍን ዝንባሌ እስከ ዛሬ ድረስ እያወከ ነው፡፡ የእሱ አዋኪነት ሳያንስን፣ በአገር ውስጥ ሐሰተኛ ሥራዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው ጭራሽ የውጭ ዕቃ አምላኪነትና ልማደኝነት እንዲጠናከርና በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪያዊ የሥራ ክፍፍሎሽና ሰፊ አመራረት እንዳያድግ እያደረገም ነው፡፡ ከፋብሪካዊ አዘገጃጀትና አቅርቦት ጀምረው የነበሩት የታሸገ የጤፍ ዱቄት፣ በርበሬና ቅመማ ቅመሞች በሐሰት ሥራ ምክንያት ክውታ ደርሶባቸዋል፡፡ የአገር ልጆች ላለመታለል፣ እንደ ድሯቸው ጥሬ ምርት ገዝቶ፣ አበጥሮ በየቤት የማዘጋጀትና የማስፈጨት አድካሚ ሥራ ውስጥ እየተመለሱ ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት የሽሮ፣ የገንፎ እህል፣ የአጃ ዱቄት፣ የቡላና ብዙ ብዙ ነገሮች ወደ ሰፋፊ አመራረት እያደጉ ሥራ መፍጠሪያ የመሆናቸው ዕድል ከወዲሁ እየተሰናከለ ይገኛል፡፡ ዛሬ የግዥ እንጀራንና ሆቴል ተመጋቢነትን ወዶ ከሚያደርገው ይልቅ ምርጫ አጥቶ የሚያደርገው ይበልጣል፡፡ ‹‹የፈረንጅ ሥራ›› እየተባለ የእኛን አገር ጣዕም ያሟላ የሽሮ፣ የአጃም ሆነ የጤፍ እሽግ ዱቄት ከውጭ ቢገባ፣ አቅም ካልገደበው በቀር እዚያ ላይ የሚጠመጠም ብዙ ሰው ይኖራል፡፡

ፈረንጅን እየጠቀመ ያለ የሐበሻ ሌላ የተላላነት ገጽታን እናንሳ፡፡ እንደ ዛሬው ቢራ ፋብሪካዎች ባልበረከቱበት ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ የነበሯቸው የጠርሙስ ቢራና የድራፍት ምርቶች በ1970 እና 1980ዎች ውስጥ ምን ያህል ዝነኛ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ዛሬ ድረስ በተለይ የሜታ ቢራ ፋብሪካ ድራፍት የነበረውን ጣዕም በናፍቆት የሚያስታውሱ ጥቂት አይደሉም፡፡ አንድ ወቅት ላይ ያ ጣዕም ከተሰለበ ወዲህ እስከ ዛሬ ድረስ ያንን ጣዕም መልሶ ማምጣት ፋብሪካው አልተሳካለትም ወይም አልጣረም፡፡ ዛሬ ያሉት በርካታ ቢራ ፋብሪካዎች በአክሲዮንም ሆነ ሙሉ በሙሉ በአያሌው በፈረንጅ የተያዙ ናቸው፡፡ የአገር ልጆች እየተሰባሰቡ ያቋቋሟቸው የቢራ ፋብሪካዎችም ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው ብሔረሰብ አጋዳይ የሆነ አመሠራረት ያላቸው ተደርገው የሚታዩና በዚያው ምክንያት ገበያቸው የብሔርተኛ መወለካከፍ የደረሰበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በደረሰ የገበያ ውስንነትና በካፒታል አቅም ማነስ ፈረንጅ እጅ ውስጥ ከመግባት አንዳቸውም አላመለጡም፡፡ የአገር ልጆች በብሔርተኛነትና በጎጠኛነት ሳይጣበቡ አገር ያካለለ ኅብረ ብሔራዊ የአክሲዮን ግዙፍ አቅም ፈጥረው ቀድሞ ዝነኛ የነበሩ የቢራ ጣዕሞችን መልሰው ማምጣት ቢቻላቸውስ ኖሮ? ዛሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንዳንድ የውጭ ኩባንያ ቢራዎች ያገኙትን የሞቀ ገበያ ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎች ቢራዎችን ሁሉ ገበያ ነጥቀው የፈረንጅ ሲሳይ የሆነውን የአገር ልጆች ብር መልሰው ወደ ኪሳቸው ባስገቡ፣ ገበያ የደራላቸውም የአገር ልጅ የቢራ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ ያሉ የፈረንጅ ቢራ ፋብሪካዎችን በክሲዮን ግዥ/በውህደት እየሰለቀጡ በተንሰራፉ ነበር፡፡ የእኛ ተላላነት እስከዚህ ድረስ ነው፡፡

ጠቆም እንደተደረገው ከዚህ የንግድ ተላላነት ጀርባ ተላላ ፖለቲካም አለ፡፡ ተላላው ፖለቲካ ደግሞ የፈረንጅን አኗኗር ሳናበጥር እንደምንለቃቅም ሁሉ፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦችንም ለአገራችን መበጀት አለመበጀታቸውን በቅጡ ሳንመረምር ከመቅዳትና ከመደንጎር ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በ1960 ዓ.ም. ውስጥ የታዩት በተማሪዎች ትግል በኩል የመጡ የፖለቲካ ዝንባሌዎች በአንድ ወይም በሌላ መልክ ከውጭ የተቀዱ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በምኞታዊነት ኢትዮጵያ ላይ ለመትከል የሞከሩ ነበሩ፡፡ በካፒታሊዝም ዕድገት ከተሰረሰረ የኢምፓየሮች እርጅና ጋ የመጣው የአውሮፓ የብሔር መንግሥታት ምሥረታ፣ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ እውነታ ጋር ምንም እንደማይመሳሰል፣ ካለመመሳሰልም በላይ አውሮፓንም እንኳ በሞላው በየብሔር መዘርዘር ያልቻለ መሆኑን ከማየት ፈንታ፣ ‹‹የብሔሮች እስር ቤት የሆነችው››ን ኢትዮጵያን አፍርሶ የየብሔር አገሮችን ለመመሥረት ያለሙም ወገኖች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያን አቅኚ ኢምፓየር፣ በውስጧ ያሉ ብሔረሰቦችን ቅኝ የተያዙ አድርጎ ያየ ምኞታዊ ሥዕል የፈጠሩና በየብሔረሰቡ ብሔርተኛ የሐርነት ትግል ለመክፈት የሞካከሩ እንቅስቃሴዎችም የዚሁ የምኞታዊ ፖለቲካ ግብ ሌላ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚበጃቸው የብሔረሰቦች እኩልነትና መብት የተረጋገጠበት አንድ አገር ማደራጀት ነው የሚል አመለካከት የነበረው የእነ ኢሕአፓና የእነ መኢሶን ተራማጅነትም ቢሆን የገባር ጭሰኛ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት፣ ገና በ1967 ዓ.ም. በአዋጅ በተሰረዘበት አሮጌ የባላባታዊ ሥርዓት ባህልና የተፈጥሯዊ ኢኮኖሚ አፈር ላይ ሶሻሊዝምን በአቋራጭ ሊገነቡ ያለሙ (ህልሙን ከእነ አቋራጭ መንገዱ በጭፍኑ የቀዱ) ነበሩ፡፡ ደርግን ወታደራዊ አገዛዝ አልነውም አላልነው፣ በእሱ በኩል ተራማጆቹ የሞከሩትና የተገኘው ሥርዓት የምኞታዊ ፖለቲካቸው የክሽፈት ፍሬ መሆኑ ሊካድ የማይችል ነው፡፡ የዘመነ ‹‹ተራማጅነት›› ፖለቲከኞቻችን የነበራቸው የሶሺሊስት ንቃት ራሱ ለተቀጂው ርዕዮተ ዓለም በመታመን የተቆጠበ ሳይሆን፣ ኩረጃና ምኞታዊነት የተላፉበትም ነበር፡፡

ሶሻሊስት ነን ባዮቹ ሁሉ ምርኩዝ ባደረጉት የስታሊን የብሔር ብሔረሰቦች መመዘኛዎች መሠረት ‹‹ብሔሮች›› የሚሰኙት ካፒታሊስት ወይም ኢንዱስትሪያዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የዘለቁ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ የመነጠል መብትም የተያያዘው ራስን ችሎ ለመላወስ ያስችላል ተብሎ ከታሰበው ከዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ጋር ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ በጊዜው በታሪካዊ ማኅበረሰቦች የተናጠል ዕድገት ደረጃ ቀርቶ፣ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር በሞላ ከካፒታሊስታዊ የጅምርማሪ ቅንጣቶች በቀር በተፈጥሯዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የምትዳክር መሆኑ የገጠጠ እውነታ ነበር፡፡ ተራማጆቹ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔሮች አሉ ወይስ የሉም ከሚል ክርክር አላመለጡም፡፡ ክርክሩን አድበስብሰው በምኞታዊነት ለብሔረሰቦች ሁሉ የመነጠል መብትን የሰጡ፣ ወይም ማኅበረሰባቸውን ብሔር ነው የሚል ሹመት የሰጡ ነበሩ፡፡ ከበረሃ የትጥቅ ትግል ተነስቶ፣ ከዚያ ኢሕአዴግ ሆኖ በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይዞት የቆየው ብሔር ብሔረሰብ ባይነት የዚሁ ውጤት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እነማን እነማን፣ እንደሆኑ ተለይቶ አይነገርም፡፡ ‹‹የትግራይ ብሔር››፣ ‹‹የአማራ ብሔር››፣ ‹‹የኦሮሞ ብሔር››፣ ወዘተ ሲባል ግን መስማት እንግዳ አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬም ብሔር ተደርገው የሚታሰቡት ማኅበረሰቦችም ሆኑ አገሪቱ ገና ቅድመ ኢንዱስትሪያዊ መሆናቸው አንድና ሁለት የለውም፡፡ ከእውነታ ይልቅ ምኞታዊነት ስለበለጠ ግን ዛሬም ብሔር ብሔረሰብ እያሉ ልዩነት ለማድረግና እኛ ብሔረሰብ ሳንሆን ብሔር ነን እያሉ ለማለት ይሞከራል፡፡ እኛ ብሔር ነን የሚባለው ብሔርነት የመነጠል መብትን ያስገኝልናል ተብሎ እንደሆን አይባል ነገር፣ ዛሬ ቁልጭ ብሎ በሚታየው የቀንዱና የምሥራቅ አፍሪካ ሁኔታ ውስጥ እነጠላለሁ የማለት ነገር የማይጠፋ እሳት ውስጥ ለመግባት የመፈለግ ነገር ሆኗል፡፡ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች” የሚባለው፣ ነገ እያንዳንዱ ብሔረሰብ በየበኩሉ ብሔር ለመባል (አገር አከል ለመሆን) የሚያበቃ ኢንዱስትሪያዊ ልማት ይጎናፀፋል ተብሎ እንደሆነም፣ የዓለም ጉዞ ለዚህ ዓይነት የየብቻ ጉዞ ዕድል የሚሰጥ አልሆነም፡፡ ከመሬት እየገፉ በመስፋፋት ጦርነት ምክንያት በብዙ መቶ ሺዎች ለመጨፍጨፍና በሚሊዮኖች ለመፈናቀል የበቁት የዳርፉር ሕዝቦች፣ መፍትሔ የሚሆናቸው በየብሔረሰብ የመነጠል መብትን መታደል ወይም የተወሰነ የተቃጠለ መሬት ድርሻ ይዘው ዓረብ ነን ከሚሉት የጃንጀዊድ ሚሊሻዎችና ገዥነቱን ከተቆጣጠሩት ወገኖች መለየት አይደለም፡፡ መፍትሔያቸው ከአድልኦና ከተስፋፊነት የታረመ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ማደራጀት፣ ፍትሐዊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ የሱዳን መሬት የምትሰጣቸውን የነዳጅ ፀጋ እየተቋደሱ በመሬት ከሚያባላ ጥንታዊ የአስተራረስና ተንቀሳቃሽ አርቢነት የሚያላቅቅና በረሃማነትን ለማከም የሚያስችል ልማት ውስጥ መግባት ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ባሉ ድህነትና ጦርነት በፈደፈዳቸው ኅብረተሰቦች አካባቢ ተስማምቶና ተባብሮ ግፍንና ድህነትን ማሸነፍ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ እውነት አኳያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የሚሉ መለያዎች ማበጀትም ሆነ፣ የመነጠልን መብትን ነው ከብሔር ብሔረሰብነት ጋር ማዛመድ አሮጌ ነገር ሆኗል፡፡ እናም ታሪካዊ ማኅበረሰቦችን ለመግለጽ አንዱን ስም መርጦ ጥቅም ላይ ማዋል ስህተት አይሆንም፡፡ የመነጠል ጉዳይም መብትህ እያሉ ስብከት ሊደርግበት የማይገባ፣ ጥያቄው ሲመጣ ግን (ከአንድ ብሔረሰብም መጣ፣ ብዙ ብሔረሰቦችን በአንድ ላይ ካቀፈ አካባቢም መጣ) ግድ በሰላማዊና በዴሞክራሲ መንገድ መፈታት ያለበት ነገር መሆኑ ሊካድ አይገባውም፡፡

በዚህ ደረጃ አመለካከትን ማስተካከል ዛሬም ድረስ ግን እንደ አውሊያ የሚያዳፋ እንደሆነ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን መነጠል ሰላምን፣ ነፃነትንንና ልማትን የመቀዳጀት ዋስትና አልሆነም፡፡ በውስጧ ያሉትን ብሔረሰቦች/ጎሳዎች ራሳቸውን የቻሉ አገሮች እንዲሆኑ ማድረግም የባሰ ከነፃነት፣ ከሰላምና ከልማት የሚያርቅ ጥፋት ነው፡፡ የዲንቃ፣ የሙርሲ፣ የኑኤር፣ ወዘተ ‹‹ክልሎች›› የተፈጠሩበትና የእያንዳንዳቸው የመነጠል መብት የተረጋገጠበት ፌዴራላዊነት ቢፈጠር፣ ወይም የሶማሌ ጎሳዎች ፌዴራሊዝም የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል ከሚል ‹‹መብት›› ጋር ቢያያዝ በጣም አስቂኝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ቅድሚያ ነገር መነጠል መብት ተብሎ መገተሩ ከማደናገርና ከማሳሳት በቀር ላለመበታተንና ላለመባላት ዋስትና አይሆንም፡፡ ዋስትና የሚሆነው በእኩልነትና በፍትሐዊ ግንኙነት፣ በልማትና በዴሞክራሲ ውስጥ መኖር ነው፡፡ ሁለተኛ ነገር እንኳን በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ደረጃና አያያዝ፣ በኢትዮጵያም ደረጃና አያያዝ፣ ፌዴራል መንግሥት እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ኢንዱስትሪዎችን እያደለም ሆነ የየአካባቢ አስተዳደሮችና ብሔረተኞች እያቋቋሙ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ወይም ‹‹ክልል›› ለየራሱ የበቃ ኢንዱትሪያዊ ማኅበረሰብ ወደ መሆን የሚቀየርበት ዕድል አይኖርም፡፡ ኢንዱትሪያዊ ልማት ከሰመረ በውድድር የሚጥለውን እየጣለ፣ አካባቢዎችን እርስ በርስ ማቆላለፉ፣ ማኅበረሰቦችን ከአንዱ ወደ አንዱ ማፋሰሱና በኢንዱስትሪ መናኸሪያ አካባቢዎች ውስጥም ብዙ ቅይጥይጥ ሕዝብ መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የሰላም፣ የነፃነትና የኢንዱስትሪያዊ ልማት ስኬት በአገር ደረጃ ተቀናብሮ መሥራትን ከመጠየቅም አልፎ፣ ቢያንስ በክፍለ አኅጉር ደረጃ ተባብሮና ተሳስሮ መሥራትን ግድ የሚል ፈተና ሆኗል፡፡ ከዚህ ብሔር ብሔረሰብነትንም አገርነትንም ከዘለለ፣ በሰላምና በዕድገት ውስጥ ከመኖርና ካለመኖር እውነታ አኳያ ሲታይ ነው በየብሔረሰብ ወሰን ለማበጀት ትንንቅ ውስጥ መግባትም ሆነ፣ ከብሔር ብሔረሰብ የመነጠል መብት ጋር መሟጨጭና በእዚያ ላይ መነታረክ አስቂኝ መደናበር የሚሆነው፡፡

‹‹የብሔር ብሔረሰብ መብት እስከመነጠል ድረስ›› ከሚባል ነገር ጋር ፍቅራቸውን ያጠበቁ የአገራችን ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራቶች›› ወይም ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኞች›› ነን ባዮች ግን የዚህን አስተሳሰብ ስብከት የሚያግዝ ነገር አፍሪካ ውስጥ ሲጠፋባቸው፣ አውሮፓ ድረስ ተሻግረው ይህ መብት ዛሬም እየተጠየቀ ስለመሆኑ ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ ትልቁ የሳቱት ነገር ግን በአፍሪካ ዓይነቱ አኅጉር ውስጥ ባለው የኋላ ቀርነትና የድህነት እውነታ ውስጥ ብሔረሰባዊ በደልን በመገንጠል መንገድ ለመገላገል (ብጥስጣሽ አገር ለመፍጠር) መሞከር ግፍንም፣ ድህነትንም የማሸነፍ አቅምን የማዳከምና በሰላም ዕጦት ለመማቀቅ መጋለጥ መሆኑን ነው፡፡ አንድ አገርነት እንደተጠበቀ በየብሔረሰብ የመሬት ድርሻን ለመካፈል ቢሞከር እንኳ ጦርነት በጦርነት ከመሆን አያመልጥም፡፡

በአውሮፓ/ምዕራብ ዓለም ውስጥ ኩቤክ ከካናዳ ብትወጣ፣ ስኮትላንድ ከብሪታኒያ ብትለይ ድህነትና መባላት አይወርሳቸውም፡፡ ሰሜን አየርላንድ ከብሪታኒያ ብትወጣ ከልማት ዕድል ጋር አትለያይም፡፡ ከአየርላንድ ጋር ተዋህዳና በአውሮፓ ኢንዱስትሪያዊ ደመና ተጀቡና ታገኘዋለች፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በዘመናዊ ግብርናና በፋይናንስ ኢንዱስትሪ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላቸው ስዊዘርላንዶች ከአካባቢያዊ ራስ ገዝነት ወደ መነጣጠል መሄድ ቢከጅሉ ጉድ አይወለድም፡፡ በአራቱም ማዕዘን የከበቧቸው የጀርመን፣ የፈረንሣይ፣ የኦስትሪያና የጣሊያን ሕዝቦች ትርፍራፊዎች እንደ መሆናቸው፣ ቢበዛ ወዲህና ወዲያ ከመቀላቀልና (ድሮውንም ለብቻ አገር መሆን እንዳልነበረባቸው ከማስመስከር) በቀር የሚያመጡት ጣጣ የለም፡፡ የባርሴሎና እግር ኳስ ቡድን ቲፎዞነትን ከፖለቲካ መለየት የተማታባቸው አውቅን ባዮች፣ አንድ ሰሞን በ‹ኤፍኤም› ሬዲዮ ጣቢያ ሁሉ ተንታኝ እንሁን ያሉበትን የካታሎኒያን ጥያቄ ገባ ብለው ቢያዩት፣ ከጭቆና ጋር ያልተገናኘ መሆኑን በመነጠል ጥያቄው ውስጥ ከካታሎኒያ ውጪ ያለውን ቀሪ የስፔይን ክፍል በኋላቀርነት አንኳሶ የሚያይና በእኛ አካባቢ ዕድገትና ብልፅግና ላይ ሌላው እየኖረ ነው የሚል የስስት አመለካከትም እንዳለበት ይደርሱበታል፡፡

አውሮፓ ውስጥ ሆና ድህነት የዋጣት ኮሶቮ የማደግ ዕድሏ ደካማ የሆነበትን ሚስጥር ለመረዳት የፈለገም፣ ኮሶቮ ውስጥ ያለው እውነታ የእነ ስዊስና ሞናኮ ዓይነት እንዳልሆነ፣ በሰርቦችና በኮሶቮ አልባኒያውያን መበቃቀል የማቀቀችው ኮሶቮ ተግባብቶና ተሳስቦ ልማት ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ደጅ በመሰደድ ኦዙሪት ውስጥ የመገኘቷ እውነታ፣ ለእኛ ዓይነቱ እውነታ የቀረበ መሆኑን ይደርስበታል፡፡ የመካከኛው ምሥራቅ ኩርዶችም ቀዳዳ ፈልጎ ለመነጠል ከመሞከር ቅዠት ወጥተው ያሉበትን አካባቢ እሳታማ እውነታ እስካላጤኑና በያሉበት አገር ውስጥ ካሉ ሕዝቦች ጋር አድሏዊ ገዥነትን አስወገዶ በእኩልነትና፣ ከፍ ካለም በራስ ገዝነት መኖርን ዓላማ እስካላደረጉ መከራቸው መብዛቱ ይቀጥላል፡፡ የእኛም ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራቶች›› የእንግሊዝኛ ጥቅሳ ጥቅስና  ከእኛ ጋር የማይገጥም እውነታ እያመጡ ከሚያምታቱ፣ ወደ እኛ እውነታ ቢወርዱ ለሁላችንም ይበጃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...