Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹የነዳጅ ፍለጋው ወደፊትም ስለሚቀጥል የሚፈለገው የክምችት መጠን እንደምንደርስ ተስፋ አደርጋለሁ››

  አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ

  (ኖክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

  አቶ ታደሰ ጥላሁን ላለፉት 40 ዓመታት በነዳጅ ኢንዱስትሪው ውስጥ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ በተለያዩ የኃላፊነት መስኮች ለረዥም ዓመታት በዘርፉ ሙያዊና አስተዳደራዊ ክህሎት ያዳበሩት አቶ ታደሰ፣ ከሼል ኩባንያ ጋር ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያና በናይጄሪያም አገልግለዋል፡፡ በተለይ በኬንያ 11 አገሮችን በሚያካልለው የምሥራቅ አፍሪካ የቀጣናው የአቅርቦትና የኦፕሬሽንስ ሥራዎች ኃላፊ በመሆን ማገልገላቸውን ግለ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ እስከ 1994/5 ዓ.ም. የሼል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅና የኩባንያው የኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ያገለገሉት አቶ ታደሰ፣ ከ1994/95 ዓ.ም. ጀምሮ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) ኩባንያን ከሌሎች የአክሲዮን ባለድርሻዎች ጋር በመሆን መሥርተዋል፡፡ የኖክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆንም እስካሁን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ከነዳጅ ኢንዱስትሪው ተሳትፏቸው በተጓዳኝ በአገር ውስጥና በውጭ ተቋማት ውስጥ በልዩ ልዩ መንገዶች እየተሳፉ የሚገኙት አቶ ታደሰ፣ የአፍሪካን ሪፋይነርስ አሶሴሽን የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ናቸው፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተገኘውን ድፍድፍ ነዳጅ በማስመልከት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለነዳጅ ፍለጋ ሥራዎች፣ ድፍድፍ ነዳጁ ስለሚያስገኛቸው ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጠቀሜታዎች፣ ስለነዳጅ ማጣሪያ አስፈላጊነት፣ ስለነዳጅ ማከፋፈል ሥራና ተግዳሮቶቹ አሥራት ሥዩም አቶ ታደሰን በማነጋገር የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ነዳጅ አምራች የሚባሉት የአፍሪካ አገሮች በምዕራብና በሰሜኑ ክፍል የሚገኙት ነበሩ፡፡ ሆኖም እርስዎ በጻፉት ጽሑፍ ውስጥ እንደተገለጸው፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም የነዳጅና የጋዝ አምራችነቱን እየተቀላቀሉ ነው፡፡ ጽሑፉ ከወጣ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የዚህ ጎራ አባል ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

  አቶ ታደሰ፡- በአፍሪካ ካለው የነዳጅ ፍለጋ፣ የማጣራትና የሥርጭት ሥራዎች ብንጀምር ጥሩ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድፍድፍ ነዳጅ ሲመረት የቆየው ሰሜን አሜሪካ፣ ምዕራብ አፍሪካና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በደቡባዊ አፍሪካ ነው፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በድፍድፍ ነዳጅ አምራችትና ላኪነት የታወቁ ነበሩ፡፡ ከአሜሪካ የድፍድፍ ነዳጅ መውጣት በኋላ አብዛኛው ከምዕራብ አፍሪካ ወደ አሜሪካ ይላክ የነበረው ድፍድፍ ነዳጅ፣ ወደ ሌላው ዓለም በተለይም ወደ ሩቅ ምሥራቅ መላክ ተጀምሮ ነበር፡፡ ድፍድፍ ነዳጅን ወደ አሜሪካ ለመላክ የነበሩት አጋጣሚዎች ትልቅ ነበሩ፡፡ አሜሪካ 30 በመቶውን የነዳጅ ምርቶች ትጠቀም ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ገበያ ለአፍሪካ ዝግ ሆኗል፡፡ በተለይም ናይጄሪያና አንጎላ ለምዕራቡ ዓለም በነዳጅ ላኪነት የታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ግን የተጣራ ምርት መልሰው ወደ አገራቸው ያስገባሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ነው ትልቁ ፈተና፡፡ ድፍድፍ ነዳጅህን ወደ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ለመላክ ትወዳደራለህ፡፡ ይህ አካባቢ ለአፍሪካ ገበያ እጅግ የራቀ ነው፡፡ የአፍሪካ ድፍድፍ ነዳጅ ላኪዎች በሚገባ ከዳበሩት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ነው የሚወዳደሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ነዳጅ ማጣራትም እየተገባ በመሆኑ የአፍሪካ አገሮች በዚህ መስክ እየተሰማሩ ነው፡፡ በናይጄሪያ አሊኮ ዳንጎቴ ትልቁን የነዳጅ ማጣሪያ እየገነቡ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ግንባታው አልቆ የምርት ሙከራ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ 600 ሺሕ በርሜል በቀን የሚያጣራ በመሆኑ በአፍሪካ ትልቁ ይሆናል፡፡ ይህ ከተሳካ ናይጄሪያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ትተርፋለች፡፡ ይህ ሲሆንም የምሥራቅ አፍሪካ የድፍድፍ ነዳጅ ገበያ ሁኔታ እንደሚቀየር ግልጽ ነው፡፡ እስካሁን በአፍሪካ የነበሩት ማጣሪያዎች በጣም አነስተኛና የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ የማያሟሉ ነበሩ፡፡ በሰሜን ይሁን በምዕራብ የሚገኙት ማጣሪያዎች ተሻሽለው ዘመናዊ የመደረጋቸው ነገር አይቀሬ እየሆነ ነው፡፡

  እንዳልከው ሰሜን፣ ደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ብቻ ነዳጅ አምራቾች መሆናቸው የቀረ ይመስላል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የድፍድፍ ነዳጅ አምራችነት ጎራውን ተቀላቅለዋል፡፡ እንደ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ እንዲሁም እንደ ሱዳን ያሉት አገሮች የራሳቸውን ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት ማቅረብ እየጀመሩ ነው፡፡ በመሆኑው የኢንዱስትሪው የወደፊት ሁኔታ ቀላል አይሆንም፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ትልልቅ ማጣሪዎች ለምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ጋር ለመወዳደር ተመሳሳይ አቅም በምሥራቅ አፍሪካ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ህንዶችም ትልልቅ የነዳጅ ማጣሪያዎች አሏቸው፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን ድፍድፍ ነዳጅ መጠቀም ከፈለጉ አቅማቸውን በማጣመር የጋራ ማጣራ መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ድፍድፍ ነዳጁን ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ መሸጥ ቀላል አይሆንም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ድፍድፍ ነዳጁ የሚገኘው መሬት ውስጥ ስለሆነ ወደ ወደብ መውሰድ የሚቻልበት ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሥራ የቧንቧ ዝርጋታ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ኡጋንዳና ኬንያ ያሉት አገሮች ድፍድፍ ነዳጅ ቢያገኙም ማምረት አልጀመሩም፡፡ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በታንዛንያ፣ በሞዛምቢክ፣ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ በኬንያ የተፈጥሮ ጋዝም ተገኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ወደብ ቧንቧ መውሰዱ ቀላል ሆኗል፡፡ የኃይል ማመንጫዎች፣ ግብርናና ሌሎችም ከተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡  

  ሪፖርተር፡- ስለተፈጥሮ ጋዙ ወደ ኋላ እናነሳለን፡፡ ለአሁኑ ግን ከሰሞኑ መውጣት ስለጀመረው ድፍድፍ ነዳጅ እንነጋገር፡፡ ድፍድፍ ነዳጁ በተገኘበት አካባቢ ላለፉት 80 ዓመታት ያህል ፍለጋ ሲካሄድ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲካሄዱ የቆዩ ፍለጋዎች ለምን ነበር ያልተሳኩት? የአሜሪካ ኩባንያዎችና ሌሎችም ሲፈልጉ ቆይተው ያልቻሉትን ቻይናውያኑ አሳክተዋል፡፡ ለምን ነበር የቀደሙት ፍለጋዎች ውጤታማ መሆን ያልቻሉት?

  አቶ ታደሰ፡- በድፍድፍ ነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ኩባንያዎች በኦጋዴን፣ በደቡባዊ ክፍል፣ እንዲሁም በጋምቤላ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ እስካሁን ግን ለንግድ ሊውል የሚችል መጠን ያለው ነዳጅ ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡ በቅርቡ በኦጋዴን የተገኘው የሚበረታታ ነው፡፡ ባለኝ መረጃ መሠረት የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እያካሄዱ የነበሩት ቻይናውያን በድንገት ነው ድፍድፍ ነዳጅ ያገኙት፡፡ ነዳጁ ቢገኝም ለንግድ ማዋል የሚያስችል የክችምት መጠን ስለመኖሩ ገና እርግጠኛ አልሆኑም፡፡ ድፍድፍ ነዳጁን የማውጣት ሒደቱ ወደፊትም በደንብ ሲቀጥል፣ ለንግድ ለማዋል የሚያስችል መጠን ስለመኖሩ ይረጋገጣል፡፡ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ሲታወቅ የማጣሪያ ወይም የቧንቧ መስመር ዝርጋታ ማካሄድ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በቀን እየወጣ ያለው መጠን 400 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ነው፡፡ ይህ መጠን ግን ለማጣሪያ ግንባታ ወይም የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ያሟላ ድፍድፍ ነዳጅ ለማምረት አያስችልም፡፡ ቻይናውያኑ ድፍድፍ ነዳጁን መሸጥ እንደሚፍልጉ ሲነግሩን ናሙናውን እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ በላቦራቶሪ በተደረገው ፍተሻ መሠረት የተገኘው ምርት እንደ ድፍድፍ ነዳጅ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያገልግል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ደረጃ እንጂ ለወጪ ንግድ በሚውል መጠን የሚውል ድፍድፍ ነዳጅ ገና አልወጣም፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ለአንባቢያን በደንብ እንዲያብራሩልን የምንፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ይኼውም በዓለም ላይ በርካታ የድፍድፍ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ስላላቸው አገሮች በስፋት ሲነገር ቆይቷል፡፡ ለአብነት ሩሲያ በዓለም ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክችምት ያላት አገር ነች፡፡ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የትኛውም የተፈጥሮ ሀብት ክችምት በሚካሄድበት የፍለጋ ሥራ መጠን ይወሰናል፡፡ በርካታ ፍለጋዎች በርካታ ክምችት ስለመኖሩ ይጠቁማሉና ክምችቱን ፈልጎ የማግኘቱ አቅም ነው የሚጎላው? ወይስ ክምችቱ በራሱ መኖሩ ነው ዋናው ጉዳይ?

  አቶ ታደሰ፡- በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ ክምችት ይታያል፡፡ እንደ ሩሲያና ቬንዙዌላ ያሉት፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝም ሆነ የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች በቂ ፍለጋ ባለመካሄዱ እንጂ በርካታ ክምችት ሊኖር ይችላል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ከዚህ ቀደም ያልነበረውን አሁን በብዛት እያየን ነው፡፡ ታንዛኒያና ሞዛምቢክ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አግኝተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት በኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳለን ተረጋግጦ ነበር፡፡ በሌሎችም አካባቢዎች የተፈጥሮ ጋዝ እንዳለ ይታወቃል፡፡ የፍለጋ ሥራው በተስፋፋ ቁጥር ያለው የተፈጥሮ ሀብትም እየታወቀና ለውጭው ዓለም የሚቀርብበት ዕድል ይኖራል፡፡

  ሪፖርተር፡- በርካታ የፍለጋ ሥራዎች ኦጋዴንን ጨምሮ በጋምቤላ፣ በኦሞ ሸለቆና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ የተገኘው ነዳጅ የሌሎች ፍለጋዎችን ጥረት ለማነሳሳት የሚኖረው ፋይዳ ምንድነው?

  አቶ ታደሰ፡- ውጤቱ ሌሎች የፍለጋ ሥራዎች እንዲቀሰቀሱና ፍላጎት እንዲነሳሳ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሌሎችም ከውጭ መጥተው በዘርፉ እንዲሠማሩ ፍላጎት ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ከኦጋዴን በተጨማሪም ደቡባዊ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም ጋምቤላ አካባቢ ስላለው ክምችት በቂ ግኝቶች ወጥተዋል፡፡ ብዙ ፍላጎት እንደሚፈጠርና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኢንቨስተሮች እንደሚኖሩ ተስፋ አለኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- በጽሑፍዎ የነዳጅ ማጣሪያ መገንባት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ ነዳጁ ከመውጣቱ በፊት በአፍሪካ በተለይም በምሥራቁ ክፍል የጋራ የነዳጅ ማጣሪያም ሊገነባ እንደሚገባ ጠንካራ ሐሳብ አለዎት፡፡ ይህ ዕውን ሊሆን ስለሚችልበት ጉዳይ ቢያብራሩልን?

  አቶ ታደሰ፡- ኬንያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ አቅራቢ በሚገኙ አካባቢዎች ትልልቅ የነዳጅ ማጣሪያዎች ይገኛሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ማጣሪያዎች ለምሥራቅ አፍሪካ በቅርበት የሚገኙ ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት እየተገኘ ካለው ድፍድፍ ነዳጅ አኳያ ማጣሪያ ለመገንባት ቅድመ ሁኔታው ድፍድፍ ነዳጅ በተገቢው መጠን መኖሩ ነው፡፡ ማጣሪዎች ትልልቅ መጠን ያላቸውና ውስብስብ እየሆኑ ነው፡፡ በናይጄሪያ በቀን 600 ሺሕ በርሜል ማጣራት ይችላሉ ብለናል፡፡ ይህንን ያህል አቅም ያለው ማጣሪያ በቀጣናው እንዲኖር ካስፈለገ ከጎረቤት አገሮች ጋር መተባበር ያስፈልገናል፡፡ ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳ ጋር በጋራ መጠቀም የሚያስችል የጋራ ማጣሪያ መገንባት ይቻላል፡፡ ማጣሪያው በየትኛው አገር ይተከል የሚለው ብዙም የሚያሳስብ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ግን ለመወዳደር የሚያስችል አቅም መፍጠሩ ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚላክ ድፍድፍ ነዳጅ ለማቅረብ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር መወዳደርን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ አገሮች የዳበረ አቅምና የጥራት ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ድፍድፉ ከተገኘ የራስን ምርት መጠቀሙና ማጣራቱ ወጪን ይቀንሳል፡፡ ትልቅና ሰፊ ማጣሪያ መገንባት ከወጪው ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን ማጣሪያ መገንባት አለባት የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ማጣሪያ እንድትገነባ ተፈላጊው የድፍድፍ ነዳጅ መጠን መኖር አለበት፡፡ ማጣሪያ በኢትዮጵያ ለመገንባት በቅድሚያ ማጠራቀሚያ በጂቡቲ ወደብ መገንባትና የማስተላለፊያ ቧንቧ መስመሮችን መዘርጋት ይጠይቃል፡፡ ይህ ግን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ድፍድፍ ነዳጁ እዚሁ ካለ በሚገኝበት አካባቢ ማጣሪያውን መገንባቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ድፍድፍ ነዳጁ በሚገኝበት አካባቢ ነዳጅ ማጣሪያውም ቢኖር ለኬሚካል ኢንዱስትሪው፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራውና ለሌላውም መስክ በርካታ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን መጀመርያ ድፍድፍ ነዳጁ መኖር አለበት፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የጋራ ግልጋሎት የሚሰጥ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት፣ በአገሮቹ መካከል ካለው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳይ አኳያ በአሁኑ ወቅት መተግበሩ አዋጭ ነው ይላሉ?

  አቶ ታደሰ፡- በፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ላይ ምክንያታዊ ዕይታ ሊኖር ይገባል፡፡ ኡጋንዳ ያገኘችውን ድፍድፍ ነዳጅ ለውጭ ገበያ እንደምታውለው ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ ነገር ግን ይህንን እስካሁን ማሳካት አልቻሉም፡፡ ይህንን ለማድረግ ፋይናንሱን የሚሰጣቸውም አላገኙም፡፡ ነገር ግን በኡጋንዳ የነዳጅ ማጣሪያ ተገንብቶ በቅርባቸው ለሚገኙ አገሮች መሸጥ ቢችሉ ጥቅሙ ለሁሉም ነው፡፡ ይሁንና በኡጋንዳ የተገኘውን ድፍድፍ ነዳጅ አጣርቶና በመስተላለፊያ መስመሮች አማካይነት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የማይታሰብ ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ በኬንያ፣ በኢትዮጵያ አሊያም በደቡብ ሱዳን ማጣሪያ ቢተከል ግን ሊያስኬድ ይችላል፡፡ በኬንያ ከሚገኙ አጋሮቻችን ጋር ስለዚሁ ጉዳይ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ በተለይም በኬንያና በኢትዮጵያ የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያው ቢተከል ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ኬንያዎች ድፍድፍ ነዳጅ እያገኙ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቅርብ በሆነ አካባቢ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በሞያሌ ወይም ሌላ ቅርበት ባለው የድንበር አካባቢ ማጣሪያው ቢገነባ በቀላሉ በማስተላለፊያ መስመር ወደ አዲስ አበባ እንዲደርስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ ሌሎችም አገሮች እንዲቀላቀሉበት ቢደረግ ወደ ውጭ ለመላክ ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶቹ የትኛው አካሄድ ጠቃሚ እንደሚሆን የሚወስኑት ይመስለኛል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ድፍድፍ ነዳጅ ወደ ውጭ ልከው በምትኩ የተጣራውን ነዳጅ ማስገባታቸው አዋጭ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና የዓለም የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ የነዳጅ ማጣሪያ ሥራ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እንዳደረገው እየታየ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የቀጣናውን የጋራ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ማስኬዱ ምን ያህል ያዋጣል?

  አቶ ታደሰ፡- በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የሆነ ዓይነት ትስስር ሊፈጠር ይገባል፡፡ አሊያም ይህንን ሥራ ሊተገብር የሚችል የቢዝነስ አካል መኖር አለበት፡፡ በቀጣናው መንግሥታት መካከል ምክክር መጀመር አለበት፡፡ ለአፍሪካ ትስስር አንዱ ጠቃሚ ጉዳይ ኢነርጂ ነው፡፡ የአፍሪካ ትስስር ከተነሳ በኢነርጂ መስክ አብሮ ለመሥራት የሚደረጉ ምክክሮች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በመንግሥታት ደረጃ የሚደረገው ውይይት ለግል ኩባንያዎች ተሳትፎም ወሳኝ ነው፡፡ አዋጭነቱ እስከተረጋገጠ ድረስ በርካታ ፋይናንስ አቅራቢዎች ፕሮጀክቱን እንደሚደግፉት ጥርጥር የለውም፡፡ ፕሮጀክቱ ሊሳካ እንደሚችል ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ አልቆርጥም፡፡

  ሪፖርተር፡- ነዳጁን ያገኘው የቻይና ኩባንያ ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማጣሪያዎችን የመትከል ሐሳብ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የነዳጅ ማጣራት ሥራ ለማከናወን ፍላጎት አለው፡፡ የተንቀሳቃሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ አዋጭነት እንዴት ይታያል?

  አቶ ታደሰ፡- ከዚህ ቀደምም በአሁኑ ወቅትም የሚቀርቡ በርካታ አማራጮች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የካሉብ ጋዝ ፕሮጀክት የሚባል ነበር፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተፈጥሮ ጋዝን በሳይንሳዊ ዘዴ ወደ ፈሳሽነት በመቀየር ለቡታ ጋዝና ለሌሎችም ምርቶች ምንጭ እንዲሆን ታስቦ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ በበርካታ ምክንያቶች ውጤታማ አልሆነም፡፡ ሆኖም ፕሮጀክቱ አሁንም ድረስ ሊተገበር የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ እየተመረተ ነው፡፡ የማስተላለፊያ መስመሩ ተገንብቶ ሲያልቅ ወደ ጂቡቲ እንዲተላለፍ ተደርጎ፣ ጋዙ ወደ ፈሳሽነት ተቀይሮ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ተንቀሳቀሽ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ ማተኮር ያለብን አይመስለኝም፡፡ ማጣሪያ ሊገነባ የሚገባው ከሚመረተው ድፍድፍ ነዳጅ መጠን አኳያ ተነፃፅሮ፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ ተፈትሾና ከሌሎች አቅራቢዎች ጋር ተወዳድሮ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ታይቶ ነው የሚፈለገውን መሥፈርት በማያሟላ ምርቱን ልታጣራ አትችልም፡፡ በአፍሪካ የሚመረተው ነዳጅ የአውሮፓ ደረጃ የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 በመላው አፍሪካ ጥቅም ላይ የሚውል የነዳጅ ምርት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አማካይነት እየተዘጋጀ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ምርት ለማቅረብ የጥራት ደረጃውና አቅሙ ያለው ማጣሪያ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ነዳጅ ከተገኘ ተንቀሳቃሽ ማጣሪያም ሆነ ሌላውን መገንባት አብሮ የሚታይ ይሆናል፡፡

  ሪፖርተር፡- የተፈጥሮ ጋዝን በሚመለከት ፍለጋ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ኩባንያ በካሉብና በሒላላ ተጨማሪ ክምችት ማግኘቱ ታውቋል፡፡ የተገኘው ሦስት ትሪሊዮን ኩብ ጫማ (TCF)፣ አጠቃላይ ክምችቱን ወደ ስምንት ኩብ ጫማ TCF ያደርሰዋል፡፡ እንዲህ ያለው ግኝት ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አኳያ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አቅም ምን ያህል እንደሆነ ሊያሳይ ይችላል?

  አቶ ታደሰ፡- የእያንዳንዱን አገር ክምችት ከኢንተርኔትም ማግኘት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በታንዛንያ ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከፍተኛ ነው፡፡ በሞዛምቢክም እንዲሁ ነው፡፡ በእኛ የተገኘው መጠን እንደ እነዚህ አገሮች ከፍተኛ መጠን ያለው አይመስለኝም፡፡ የነዳጅ ፍለጋው ወደፊትም ስለሚቀጥል የሚፈለገው የክምችት መጠን እንደምንደርስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የማስተላለፊያ መስመሩ ግንባታ ማለቅ በርካታ ነገሮችን ያቃልላል፡፡ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም ለሚፈለገው ሥራ ኢንቨስት ለማድረግ አቅም ይሰጣል፡፡ በኦጋዴን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጥሮ ጋዝ አለ፡፡

  ሪፖርተር፡- የተፈጥሮ ጋዙን ያወጣው የቻይና ኩባንያ ምርቱን ወደ ጂቡቲ የሚያስተላልፍ መስመር ለመግባት አቅዷል፡፡ የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ቻይና ለመውሰድ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል፡፡ የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ቡታ ጋዝና መሰል ምርቶች በመቀየር ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ሐሳብም አለ፡፡ ለውጭ ገበያ ወይም ለአገር ውስጥ ይቅረብ በሚለው ሐሳብ ላይ ሚዛኑ የቱ ነው ሊሆን የሚገባው? ቅድሚያ በውጭ ገበያው ላይ ማተኮር ይገባል? ወይስ ለአገር ውስጥም ማቅረቡ ተገቢ ነው?

  አቶ ታደሰ፡- ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ መሠረተ ልማቱ መፈጠር አለበት፡፡ የተፈጥሮ ጋዙን ወደሚፈለገው አካባቢ ለማድረስ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ በወጪ ንግዱ ላይ በማተኮር በአንድ መስመር ማስተላለፊያ ቧንቧ ተዘርግቷል፡፡ ይሁንና ለቡታ ጋዝ ምርት ያን ያህል ወጪ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ከተፈጥሮ ጋዝ ሌሎችም ምርቶችን ማውጣት የወደፊቱ ዕቅዳቸው ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም እርስዎ በቡታ ጋዝ ሥርጭት ላይ ኖክ በሰፊው የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ሲገልጹ ነበርና ስለዚህ ጉዳይ የተፈጥሮ ጋዙን ከሚያወጣው ኩባንያው ጋር የተነጋገራችበት አግባብ ይኖር ይሆን?

  አቶ ታደሰ፡- በአሁኑ ወቅት ቡታ ጋዝን በሚመለከት ከሱዳኖች ጋር ነው እየሠራን ነው፡፡ ፖርት ሱዳን ላይ በሚገኘው ማጣሪያ የተጣራውን ጋዝ በራሳችን አጓጉዘን ወደ መጠራቀሚያችን በማምጣት እያሠራጨን ነው፡፡ የምንፈልገውን ያህል በቂ ባይሆንም መላ አገሪቱን ማዳረስ የሚያስችል የቡታ ጋዝ አቅርቦት ሥራ ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተፈጥሮ ጋዙን በማምጣት በሱዳን ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት ሥራ ነው፡፡ የራሳችን የቡታ ጋዝ ፋብሪካ እንዲኖረን ድፍድፍ ነዳጅ ወይም የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ማጣሪያውን በሚገባ ለመጠቀም ድፍድፉ ለሥራው የሚፈለውገውን ያህል መጠን ሊሆን ይገባዋል፡፡ እኛ ማጣሪያውን ለመትከል እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን የድፍድፉ መጠን ወሳኝነት አለው፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ለውጡን የምናየው ይሆናል፡፡ ቡታ ጋዝ በጂቡቲ በኩል ለማስገባት ያልቻልነው ያላቸው ማከማቻ በጣም አነስተኛ ስለሆነብን ነው፡፡ ትልልቅ መርከቦች ይዘው የሚመጡትን የቡታ ጋዝ መጠን ማራገፍ የሚችሉበት ማከማቻ የለም፡፡

  ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ያለው የቡታጋዝ አቅርቦት በከፍተኛ መጠን እጥረት ይታይበታል፡፡ ምርቶቹ በከተሞች አካባቢ ብዙም አይታዩም፡፡ ለምንድን ነው እጥረቱ ሊፈጠር የቻለው?

  አቶ ታደሰ፡- ኬንያን ብንወስድ በዓመት 300 ሺሕ ቶን የቡታ ጋዝ ፍጆታ አላቸው፡፡ በኡጋንዳም ሆነ በታንዛንያ ተመሳሳይ የፍጆታ መጠን አለ፡፡ እነዚህ አገሮች ግን ከኢትዮጵያ ያነሰ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው የኢኮኖሚ ደረጃ የቡታ ጋዝ ፍጆታን ያን ያህል የሚፈልግ አልነበረም፡፡ አሁን ያለው ዕድገት ግን የቡታ ጋዝ አቅርቦት በየኢንዱስትሪው፣ በየሆቴሉና በየመኖሪያ ቤቱ እንዲኖር የሚጠይቅ ነው፡፡ የቤቶች ግንባታ ሁኔታ ነጭ ጋዝ ወይም ከሰል መጠቀምን አያበረታታም፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ርካሽ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የቡታ ጋዝ ተፈላጊነት ያን ያህል ነበር፡፡ አንዱ ችግር ለሕዝቡ ርካሽ በሆነ ዋጋ ከማቅረብ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ከፍተኛ የአቅርቦት አቅም መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ዋጋው ሲቀንስ ተፈላጊነቱም ይጨምራል፡፡ በፖርት ሱዳን በኩል በትልልቅ መርኮች እየጫንን ለማስገባት የተነሳነውም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚጠይቀውን የማጓጓዣ ወጪ በመቀነስ አቅርቦቱን ከፍተኛ ለማድረግ ነው፡፡ የሱዳን መንግሥት ለዚህ አገልግሎት በቂ የመርከብ አገልግሎት እንዲሰጠን ጠይቀናል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የኬንያን ያህል ባይሆንም ወደዚያ የሚቀርብ አቅርቦት መፍጠር እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለቡታ ጋዝ ምርት አቅርቦት አለመኖር አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ?

  አቶ ታደሰ፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ወደ አገር ውስጥ በሚገባው ማንኛውም ምርት ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ይኖራል፡፡ ቡታ ጋዝም አንዱ ቅድሚያ የሚሰጠው ምርት በመሆኑ አግባብነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንደምናገኝ ተስፋ አለኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- በነዳጅ ችርቻሮ ሥራ ላይ ለበርካታ ዓመታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ስትነጋገሩ ቆይታችኋል፡፡ የዘርፉ አዋጭነት እየቀነሰ በመምጣቱ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ብዙም ሲገቡ አይታይም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲነሳ የነበረ ጉዳይ እንደ መሆኑ መጠን፣ ለመፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ለመንግሥት ለማቅረብ ሞክራችኋል? ያቀረባችሁት ነገር ካለስ ችግሩ መቼ ሊስተካከል ይችላል?

  አቶ ታደሰ፡- ድፍድፍ ነዳጁ ከተገኘ በኋላ ስለማጣሪያና ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ነው የምታስበው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ስለሥርጭቱና ችርቻሮው ማሰብም የግድ ነው፡፡ እንደ ኬንያ ያሉ ጎረቤት አገሮችን ያየን እንደሆነ ከ2400 በላይ የነዳጅ ማደያዎች አሏቸው፡፡ ይህ ማለት በመላ አገሪቱ በቂ ምርት ታገኛለህ ማለት ነው፡፡ በቂ የነዳጅ ሥርጭት ሲኖርም ኢኮኖሚው በሚገባ ይንቀሳቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ካየነው ግን ካለው የሕዝብ ብዛትና ከኢኮኖሚው ዕድገት የሚመጣጠን የነዳጅ ማደያዎች ኔትወርክ አልተዘረጋም፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት በየማደያው ሠልፎች ይታያሉ፡፡ ይህ ብክነት ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ተገቢውን ያህል የነዳጅ ማደያዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ እስካሁን መንግሥት በቂ ትኩረት አልሰጠውም፡፡ አሁን ግን መንግሥት ጆሮውን የሰጠ ይመስለኛል፡፡ ካለው የተሻሻለ ነገር በመነሳት በነዳጅ ማደል ሥራ የሚሠማሩ ኩባንያዎችም መግባት ይጀምራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በርካታ ኩባንያዎች በዚህ ዘርፍ ውስጥ ተሰማርተዋል ብለው የሚያስቡና ሥራውም አዋጭ ነው ብለው የሚገምቱ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማከፋፈል ሥራ ውስጥ የሚታዩ በርካታ ያልተገቡ ተግባራት አሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መንግሥት የሚያስበው ነጭ ጋዝ በአብዛኛው ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምበት በመሆኑ ድጎማ ያስፈልገዋል ብሎ ያስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ነጭ ጋዝ ከናፍጣ ጋር እየተቀየጠ ለመኪናዎች ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ እኛም ይህንን ጉዳይ ለማስተካከል ብዙ ስንጥር ቆይተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በናፍጣና በነጭ ጋዝ መካከል የነበረው የዋጋ ልዩነት በመስተካከሉ ለመቀላቀል የነበረው ፍላጎት ቀንሷል፡፡ ይህም ሆኖ ከቤንዚን ጋር የመቀላቀል ሙከራዎችም ነበሩ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች እስከ ወዲያኛው እንዲቀረፉ ለነዳጅ ማደያዎች የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ አንዳንዶች እኮ መዝጋት ጀምረዋል፡፡ የነዳጅ ችርቻሮ ንግድ ሥራውን መሥራት ያልቻሉ ሰዎች ከዘርፉ እየወጡ ነው፡፡ ለንግድ ሚኒስቴር ይህን ጉዳይ አቅርበናል፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንደሚኖር እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን ተስፋ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ነገር እስካሁን አላየንም፡፡ 

  ሪፖርተር፡- የነዳጅ ማደያዎች ከነዳጅ ትርፍ ይልቅ የሞተር ቅባትና ሌሎች ምርቶችን በመሸጥ ሥራውን እንደሚደጉሙ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ምርቶች አሁን አትራፊነታቸው ቀርቷል ማለት ነው? ያለው ለውጥ ምንድነው?

  አቶ ታደሰ፡- እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ውስጥ በርካታ የጎንዮሽ ንግድ ሥራዎችን ማስኬድ ይቻላል፡፡ ሱፐርማርኬት፣ ካፊቴሪያ፣ የመኪና እጥበትና ሌሎችም ደጋፊ ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከከተማ ውጪ ያሉ ነዳጅ ማደያዎች እንዲህ ያለውን ንግድ ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ገበያ አያገኙም፡፡ ብቸኛው ሥራ ከነዳጅ ማደል የሚገኘው የትርፍ ህዳግ ነው አማራጫቸው፡፡ የትርፍ ህዳጉ ዝቅተኛ በመሆኑ ሳቢያም በርካታ ማደያዎች እየተዘጉ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ለማጠቃለል ያህል የነዳጅ መገኘትን ተከትሎ አንዳንዶች ተስፋ የሚያለመልም አዝማሚያ እንደሚታይ ያምናሉ፡፡ አንዳንዶች ግን አገሪቱ ካሉባት ችግሮችና ካለውም የፖለቲካ ሁኔታ አኳያ ተጨማሪ አበሳ እንዳይሆን ሥጋት አላቸው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ዕይታ ምንድነው?

  አቶ ታደሰ፡- እኔ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ ለብዙ ዓመታት ተከፋፍለን ቆይተናል፡፡ ወደፊት ግን በዚህ አኳኋን እንደማንቀጥል አስባለሁ፡፡ እንደ አገር እንደ ሥርዓት ለመቆየት ከራሳችን ጋር ዕርቅ ማውረድ አለብን፡፡ ከሌሎች ጥያቄ ካላቸው ቡድኖችም ጋር መታረቅ ይኖርብናል፡፡ የተፈጥሮ ጋዝም ሆነ ሌላም ነገር ማግኘታችን፣ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ፣ የስኳር ፋብሪካዎቻችን ሲጠናቀቁና እንደ ኤታኖል ያለውን ምርት ጭምር ማምረት ስንጀምርና ሌሎችም ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ አገሪቱ ያሉባት ችግሮች ተቀርፈው የተሻለ ጊዜ እንደምናይ ተስፋ አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተመጣጣኝ እየሆነ በመሆኑ ለወደፊት ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አሉ፡፡  

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ሕጉ በተጨባጭ የማይተረጎምና ችግሮችን የማይፈታ ከሆነ ለሕገ መንግሥት ታማኝነት አይኖርም›› መድኅን ማርጮ (ዶ/ር)፣ የሥነ ማኅበረሰብ ልማት ፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ

  ‹‹የወላይታ ሕዝብ የራሱ ክልል ይገባዋል፤›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ክላስተር የክልል አደረጃጀትን ሕገ መንግሥቱ አያውቀውም በማለትም በአንቀጽ 46 ላይ ሕዝቦች ወይም ብሔረሰቦች ማንነትን፣ ቋንቋንና የሕዝብ አሠፋፈርን...

  ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ካገኘሁት ገቢ ላይ ግብር መክፈል አለብኝ የሚለው አስተሳሰብ ብዙ ይቀረዋል›› አቶ ሙሉጌታ አያሌው፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት

  የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለና በመንግሥትና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ከታክስ ጋር በተያያዙ የሚነሱ አመግባባቶችን የሚመለከት ተቋም ነው፡፡ ግለሰቦችና ነጋዴዎች...

  ‹‹የእኛ ብሔርተኝነት የበሰለና ዴሞክራሲያዊ ነው›› አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር

  ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ እንዲሁም ከኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ በሄልዝ ኦፊሰርነት ተመርቀዋል፡፡ ገና ባህር ዳር...