በ2011 በጀት ዓመት ከ44 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል
ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመውጣት እንደገና እንደ አዲስ እንዲደራጅ የተደረገው የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን፣ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳውና የቀን ገቢ ግምት ላይ ተመሥርቶ የሚሰላው ታክስ ላይ ሲነሱ የቆዩ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
በ2003 ዓ.ም. የተካሄደውን ግምታ ተከትሎ ዓምና ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ሲካሄድ በርካታ ቅሬታዎችን ማስከተሉ ይታወሳል፡፡ የዚህ ዓመት የባለሥልጣኑን የገቢ አሰባሰብ ብሎም የ2011 ዓ.ም. ዕቅድን በማስመልከት አፍሪካ ኅብረት አካባቢ በሚገኘው የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሺሕሰማ ገብረ ሥላሴ ስለዚሁ ጉዳይ አብራርተው ነበር፡፡
አቶ ሺሕሰማ እንደገለጹት፣ አብዛኛው የአዲስ አበባ ከተማ ታክስ ከፋይ፣ ኩባንያዎች ሳይሆኑ ግለሰብ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የሚበዛውና ከ90 በመቶ በላይ አነስተኛ ግብር ከፋይ ወይም የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ በመሆኑ የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ አይገደዱም፡፡ ይህ በመሆኑም መንግሥት የቀን ገቢ ግምት ላይ የተመሠረተ የግብር ሥርዓት እየተከተለ ይገኛል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት በሠለጠኑትም አገሮች ውስጥ በተለይም እንደ እስራኤልና ፈረንሣይ ባሉት አገሮች ውስጥም የተለመደ አሠራር ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዓምና በተደረገው የቀን ገቢ ግምት ላይ በርካታ ቅሬታዎች በመነሳታቸው፣ ባለሥልጣኑ ዓመቱን ሙሉ ቅሬታዎችን ሲፈታ እንደከረመ አቶ ሺሕሰማ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በርካታ ማስተካከያዎች እንደተደረጉ፣ በደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋይነት ከተደለደሉት ውስጥ የ40 ሺሕ ግብር ከፋዮች፣ በደረጃ ‹‹ሐ›› ከተደለደሉት ውስጥም ከ193 ሺሕ በላይ ጥያቄዎቻቸው እንደተፈቱ አቶ ሺሕሰማ ገልጸዋል፡፡ መደበኛ የቅሬታ መፍቻ ሥርዓት መዘርጋቱ ቢጠቀሰም፣ ከ2,500 ግብር ከፋዮች በባለሥልጣኑም ሆነ በወረዳና በክፍለ ከተማ የታክስ ጉዳይ ቅሬታ መፍቻዎች ያገኙት ምላሽ ስላላረካቸው ወደ ግብር ይግባኝ ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ መሄዳቸው ታውቋል፡፡
በተፈጠረው ቅሬታ ሳቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን ስለመመለሳቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም ይህንኑ መግለጹን በማስታወስ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አቶ ሺሕሰማ ያብራሩት 30 ሺሕ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን መመለሳቸውን በማስታወስ ነበር፡፡ ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች ከታክስ ዕዳ ነፃ መሆናቸውን የሚገልጽ (ክሊራንስ) ማስረጃ እንዳልወሰዱ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ሆኖ፣ የንግድ ፈቃድ ለመመለሳቸው ምክንያታቸውን እንዲገልጹ ሲጠየቁ አሥር በመቶው ወይም 3,000 ነጋዴዎች ብቻ በግብር ጫና ምክንያት ለመመለስ መገደዳቸውን እንዳስታወቁ ጠቅሰዋል፡፡
በጠቅላላው ከዚህ ዓመት ከተደረጉ ማሻሻያዎች ውስጥ በተለይ የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ የሚገደዱ ግብር ከፋዮች ያቀርቡት የነበረው ዋነኛ ቅሬታ የሒሳብ መዝገባቸው ውድቅ ይደረግባቸው እንደነበር የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ ዓመት ጀምሮ የማንኛውም ነጋዴ የሒሳብ መዝገብ በባለሥልጣኑ ውድቅ እንደማይደረግ አቶ ሺሕሰማ አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ኦዲት መደረግ ያለበት መዝገብና ሒሳብ ግን እንደሚፈተሽ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ነጋዴዎች በሚገጥማቸው ውጣውረድ ሳቢያ የታክስ ክሊራንስ ለማግኘት ሲሉ ንግድ ፈቃድ የሚመልሱበት አግባብ እንዲቀር የሚያደርግ አሠራር መዘርጋቱም ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የሕግ ማስከበር አካላት ከሥነ ምግባርም ከሕግ ውጭም በሆነ መንገድ የነጋዴዎችን ሰነድ መጣልም ሆነ ሌሎች ያተገቡ አካሄዶችን ሲያካሂዱ ይህንን ተከታትሎ መፍትሔ የሚሰጥ አካል መፈጠሩንም አቶ ሺሕሰማ አብራርዋል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት የተደረገው የታክስ አዋጅ ማሻሻያ፣ ቀድሞ የነበረውን ዓመታዊ የግብር ከፋዮች የገቢ መጠን ላይ ለውጥ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ገቢ ከ500 ሺሕ ብር በታች ሲሆን፣ የደረጃ ‹‹ለ›› ከ500 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን እንዲሁም የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ዓመታዊ የገቢ መጠን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በዚህ መጠን የገቢ ደረጃ ያላቸው ግብር ከፋዮች በሚጣልባቸው የታክስ ምጣኔ መሠረት እንዲከፍሉ እየተጠየቁ ይገኛሉ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ግን ተጨማሪ ማሻሻያዎችን እንዳደረገ አቶ ሺሕሰማ ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም እንደ እህል ንግድ ባሉት ሸቀጦች ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የአሥር በመቶ የትርፍ መተመኛ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች በሚከፍሉት የተርን ኦቨር ታክስ ከዚህ ቀደም የነበረውና በዝቅተኛ ግብር ከፋዮች የአሥር በመቶ የግብር ምጣኔ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ መደረጉን፣ ከዚህ ቀደም የሥራ ቀናት ተደርገው ይታሰቡ የነበሩት የዓመቱ 365 ቀናትም በአማካይ ወደ 300 ቀናት ዝቅ መደረጋቸውን አቶ ሺሕሰማ አብራርዋል፡፡ የሥራ ቀናቱ እንደ ንግድ ዓይነቱና የሥራው ፀባይ ከ150 እስከ 300 ቀናት ታሳቢ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ሺሕሰማ 365 ቀናትን እንደ መደበኛ የሥራ ቀናት አስቦ ታክስ ማስከፈል ያስከተላቸውን ቅሬታዎች ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም የሙሽራ ልብስ አከራዮች በዚህ ሥሌት ተጎጂዎች እንደነበሩ ተብራርቷል፡፡ በዚህ ማስተካከያ መሠረት ዓምና በ2003 ዓ.ም. የቀን ገቢ ግምት መሠረት የተርን ኦቨር ታክስ የከፈሉ ግብር ከፋዮች ዘንድሮ ግን በዓምናው ተመን መሠረት እንደሚስተናገዱም ይፋ ተደርጓል፡፡
በጠቅላላው በከተማው አስተዳደር የታክስ ገቢ አሰባሰብ ሒደት ላይ ሦስት መሠረታዊ ጉድለቶች በታክስ ከፋዩና በታክስ ሰብሳቢው አካል መካከል እንደሚስተዋሉ አቶ ሺሕሰማ ይገልጻሉ፡፡ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ችግሮች፣ ደረሰኝ አለመስጠት አለመጠየቅ እንዲሁም የሥነ ምግባር ጉድለቶች ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ በ2011 ዓ.ም. ከከተማው ግብር ከፋይና ከሌሎች የገቢ ምንጮች 44.7 ቢሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ሲገለጽ፣ ከታክስ በቀጥታ የሚሰበሰው ገቢ 22.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ከቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ 11.03 ቢሊዮን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎችና 878 ሚሊዮን ብር፣ ከሌሎች የገቢ ምንጮች 10.2 ቢሊዮን ብር ታሳቢ ተደርጎ በጠቅላላው የ44.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አቶ ሺህሰማ ገልጸዋል፡፡
ይህ ገቢ ከ2009 ዓ.ም. ገቢ አኳያ ሲታይ፣ የ3.9 ቢሊዮን ብር ወይም የ17 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ ዓምና 35.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 31.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ ከሚሰበሰበው ገቢ ውስጥ 60 በመቶው ለካፒታል ወጪዎች፣ 40 በመቶው ለመደበኛ ወጪዎች ማለትም ለትምህርት፣ ለጤናና ለመሳሰሉት ዘርፎች ይውላል፡፡