በርካታ የመንግሥት ተቋማት ከአገልግሎት አሰጣጣቸው ጋር በተያያዘ በብርቱ ሲተቹ ይታያሉ፡፡ የቀበሌ፣ የወረዳ የክፍለ ከተማና የፌዴራል ተቋማት ከነዋሪነት መታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ በየፊናቸው በርካታ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የተቋቋሙ፣ ሕዝቡም ብዙ የሚጠብቅባቸው ናቸው፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናቸው ሲመዘኑ ግን አብዛኞቹ ሕዝብ የሚያስመርሩ፣ ከሥራ ይልቅ ‹‹የለም፣ አይቻልም፣ ዛሬ አገልግሎት አንሰጥም ወዘተ.›› ማለት የሚቀናቸው፣ ሥራ መሥራት ማለት ተገልጋዩን ቁምስቅሉን ማሳየት የሆነባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ እንደ ቴሌ ግድግዳ ስልክ ሳንቲም ካልጎሰረሱ ጉዳይ የማይፈጸምባቸው፣ ዘመድ አዝማድ፣ ዕውቂያና የወንዜ ልጅነት የሌለው ደጅ ባዳ፣ ለአገር እንግዳ ተደርጎ በገዛ ቀበሌው፣ በገዛ መንግሥቱ የሚንገላታባቸው፣ ለሚያጉላሉት የመንግሥት ጀሌዎች ግን ታክስና ግብር እየከፈለ የሚያስተዳድራቸው በርካታ አለሌዎች ዛሬም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ያሉት በርካታ ተቋማት ከእንዲህ ያለው በሽታቸው ገና አልተፈወሱም፡፡
ባለጉዳይ በማያጉላላት፣ በአታካች ቢሮክራሲያቸው ተከልለው አገልግሎት ለመስጠት ያላቸው የሥራ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንደ ክረምቱ አየር የተቀዛቀዙ፣ ቆፈናም ሆነው ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በአገልግሎት አሰጣጣቸው ከሚወደሱ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ እንዲሁም የምዝገባና የሰነዶች ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት በተምሳሌትነት ይጠሳሉ፡፡ አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማቀላጠፍ ለሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ምሳሌ ሆነው የሚታዩ ብቻ ሳይሆን፣ የአሠራራቸው ሒደትና ፍሰቱ በሌሎችም እንዲኮረጅና እንዲተገበር ይደረግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንደውም የምዝገባና የሰነዶች ማረጋገጫ ጽሕፈት በጥራት አሠራር አሠራርና ቅልጥፍናው ተሸላሚ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የኢምግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ለተገልጋዩ ከሚያቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡበት ስሞታዎችና ጥያቄዎች ምን ነካው ያሰኛሉ፡፡ ተገልጋዮች ፓስፖርት ለማውጣት፣ ለማሳደስና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚያጠፉት አላስፈላጊ የእንግልት ጊዜ እያማረራቸው ነው፡፡
ኢምግሬሽን እንደ ተቋም አገልግሎቱን ለማቀላጠፍና ለማዘመን እያካሄደ ባለው ሒደት የሚታዩ ለውጦች በገሃድ ቢታዩም፣ ተቋሙ ከሚያካሂደው ሪፎርም አኳያ ተገልጋዩ ተጠቃሚ አለመሆኑ ወይም እንደታሰበው በቀልጣፋ አገልግሎት አለመስተናገዱ እጀ ሰባራ ሳያሰኘው አይቀርም፡፡
በቅርቡ እንደሰማነው፣ የኢምግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ያላቸውን አዳዲስ አሠራሮችን ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የተቋሙን አገልግሎት ፈላጊዎች በተመረጡ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ማስተናገድ ጀምሯል፡፡ ከጠዋት ጀምሮ በተቋሙ በረንዳ እንደ ጉንዳን ተቀጣጥሎ መሠለፍ ሳይጠበቅበት፣ አስፈላጊውን ክፍያ መፈጸም የሚችልበት አሠራር እንደሆነ የተገለጸው በቅርቡ ነበር፡፡
ይህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሳይጉላሉ፣ በባንኩ በኩል ባስያዙት ወረፋቸውን መሠረት ተራቸውን ጠብቀው በተቀጠሩበት ቀንና ሰዓት በኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ተገኝተው የጠየቁትን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የተዘረጋ አገልግሎት ስለመሆኑም ተገልጾ ብዙ ተወርቶለት ነበር፡፡ የሁለቱ ተቋማት ትስስር ሲፈጠር ታሳቢ የተደረገው ደንበኞችን ከእንግልት ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ በዘመናዊ አሠራር ግልጋሎቱን ለመስጠት ታስቦ እንደነበርም ተደጋግሞ ሲነገረን ሰንብቷል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ደንበኞች በኢምግሬሽን መሥሪያ ተገኝተው አስፈላጊ የተባሉ መስፈርቶችን ካሟሉ በኋላ፣ ፓስፖርታቸውን ለመውሰድ መጉላላት የለባቸውም ተብሎ በፖስታ ቤት በኩል እንዲረከቡ የሚያስችል ትስስርም ተፈጥሯል ሲባል ነበር፡፡ ይህም የተንዛዛ አሠራሩን ለማስቀረት የተደረገ ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬም ድረስ ግን ወደ ኢሚግሬሽን ጎራ እያሉ ያሉ ተገልጋዮች፣ ለቀናት አንዳንዶቹም ለወራት የሚፈልጉትን አገልግሎት ሳያገኙ እንደሚጉላሉ እየታዘብን ነው፡፡ ሥራውን ያቀላል፣ ያቀላጥፋል የተባለው የፖስታ ቤት ቅጥር ግቢም በፖስታ ሳይሆን፣ በፓስፖርት ፈላጊዎች ሲጨናነቅ እየታየ ነው፡፡
ለተሻለ ቅልጥፍና ተብሎ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር በተደረሰ ስምምነት መሠረት እየተደረገ ያለው የፖስፖርት አሰጣጥ ሥርዓት ዜጎችን ሊስደስት አልቻለም፡፡ በተደጋጋሚ አቤቱ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ የታሰበው የለውጥ ዕርምጃም በታሰበው ልክ አለመተግበሩና ውጤት አለማምጣቱ ለምን? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ እየተዘረጋ ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎችም ባሉበት አካባቢ ሆነው ፖስፖርታቸውን እንዲያገኙ ታስቦ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ጭምር ቅርንጫፍ ከፍቶ እየተሠራ በሚገኝበት ወቅት፣ ከቀድሞውም የባሰበት እሮሮ መደመጡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢሚግሬሽን ለዚህ ችግር መፍትሔ መስጠት አለበት፡፡ ምክንያቱን ገልጾም ሊታረሙ የሚገባቸውን አሠራሮች እስካላስተካከለ ድረስ አሁንም በርካታ ተገልጋዮች መጉላላታቸው አካሄድኩ ያለውን ሪፎርም ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡
እርግጥ ነው በቅርቡ የተቋሙ ኃላፊዎች በሚዲያ ከሰጡት ምላሽ ለመረዳት እንደተቻለው የጥሬ ዕቃ በወቅቱ አለመግባት፣ የፓስፖርት ዝግጅቱን እንዳጓተተው፣ ለዓመቱ ታሳቢ የተደረገው የፓስፖርት መጠንና ተገልጋዩ የጠየቀው መጠን ከፍተኛ ልዩነት ታይቶበታል፡፡ የዓረብ አገሮች የሥራ ሥምሪት እየተፈቀደ ከመሆኑ ጋር ሊያያዝ የሚችል ከፍተኛ የፓስፖርት ጥያቄ እየቀረበ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ይህ ግን አጥጋቢ ምክንያት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ከዓረብ አገሮች ጋር ስምምነት ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷልና ነው፡፡
ይህንኑ ሒደትም በሚዲያ ሲያሳውቅ መቆየቱ እየታወቀ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ሲገባ እንደ እንግዳ ደራሽ እንዲሁ ከአቅም በላይ ጥያቄ መጥቶብን ነው የሚል ሰበብ ምላሽ አይሆንም፡፡ ዋናው ጉዳይ አገልግሎት የሚፈልገው ሕዝብ ሜዳ ላይ እንደ እህል ተሰጥቶ እየዋለ በሚታይበት ወቅት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠቱ ለተቋሙም መመስገኛው ነው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ቀድሞ የቀለጠፈ አገልግሎት በመስጠት እንደ ሞዴል የሚታየው ይህ ተቋም አሁን እየዘመንኩ ነው፣ ባለበት ሰዓት እንዲሁም ኦላይን ጭምር ቪዛ እየሰጠ አዳዲስ አገልግሎቶችን ባከለበት ሰዓት ፓስፖርት ለማግኘት አልቻልንም የሚል አቤቱታ መቅረቡ አሠራሩን ድጋሚ እንዲፈተሽ ያስገድደዋልና ለተሻለ አገልግሎት ይንቃ!