Thursday, February 22, 2024

የዘንድሮው ፓርላማ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አምስተኛው የምርጫ ዘመን ሦስተኛ ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመቱን ሥራ የጀመረው በመደናገር ውስጥ ሆኖ ነበር፡፡ የመደናገሩ ምክንያትም የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የአገሪቱ ከፍተኛ የሆነውን ሥልጣን አልፈልግም በማለት መልቀቂያ በማቅረባቸው ነው፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ምክር ቤቱ ሥራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡበት ምክንያት፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት ከሁለቱም ወገን በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመፈናቀላቸው ነበር፡፡

‹‹የምወክለው ሕዝብና የድርጅቴ ክብር ተረግጦ በሥልጣን ላይ መቆየቱን አልመረጥኩም፤›› በማለት ምክንያታቸውን በይፋ የተናገሩት የቀድሞው አፈ ጉባዔ አባዱላ፣ ‹‹የሕዝብና የድርጅቴን ክብር ለማስመለስ እታገላለሁ፡፡ ከአፈ ጉባዔነት ብለቅም በምክር ቤት አባልነት እቀጥላለሁ፤›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡ አቶ አባዱላ ይኼንን በይፋ በመናገራቸው ምክንያት ምክር ቤቱ የ2010 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን ለመጀመር በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ቀን ማለትም መስከረም 29 ቀን የሚካሄደውን ስብሰባ በአፈ ጉባዔነት ላይመሩት እንደሚችሉ በርካቶች ገምተው ነበር፡፡ ምክር ቤቱም በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ በመገመት በጉጉት የተጠበቀ ዕለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የዓመቱን የሥራ ዘመናቸውን ለመጀመር በጋራ የሚያካሄዱትን ስብሰባ በመክፈትና በዓመቱ ትኩረቱ እንዲደረግባቸው የተለያዩ ጉዳዮችን ለምክር ቤቶቹ ለማሳሰብ፣ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የተገኙበትን የጋራ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በአፈ ጉባዔነት መርተውታል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የሥራ መክፈቻ ንግግር፣ ከ2009 ዓ.ም. መጀመርያ አንስቶ ጥገኛ አስተሳሰቦች የወለዷቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች የተጠቀሙበት አለመረጋጋት በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበሩ በመሆኑ፣ ለአሥር ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁን በማስታወስ፣ ‹‹ከሕዝባችን ጋር ባደረግናቸው መጠነ ሰፊ ውይይቶች በተደረሰው መግባባት በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባናል፤›› ብለው ነበር፡፡ ለዘመናት አብረው በአንድነት በኖሩት የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት በጭራሽ ሊከሰት የማይገባው መሆኑን በመጠቆም፣ በ2010 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ወደ ነበረበት የሰላም ሁኔታ እንዲመለስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችንም መልሶ በፍጥነት ማቋቋም ላይ ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የሰጡት የሥራ አቅጣጫ በአመዛኙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ዓበይት የትኩረት ርዕሶችንም አስመልክተው አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2010 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑ ፈጣንና ፍትሐዊ ልማትን የሚደግፉ፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ የሕዝብ ተሳትፎን ይበልጥ የሚያጎለብቱ፣ የአገሪቱን ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችሉ አዋጆችንና ፖሊሲዎችን ማፅደቅ እንደሚጠበቅበት አስታውቀው ነበር፡፡

ከእነዚህም መካከል በ2008 ዓ.ም. የተጀመረውንና የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓትን ለማሻሻል በፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት የተደረገበትን የማሻሻያ ሕግ በማፅደቅ፣ በ2012 ዓ.ም. ለሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በ2010 ዓ.ም. የሚካሄደውን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች ምርጫንና በመላ አገሪቱ የሚካሄደው የአካባቢ ምርጫን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲካሄድም አሳስበው ነበር፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውና እንቅስቃሴያቸው እንዲጎለብት ሲሉም ለሁለቱም ምክር ቤቶች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ካደረጉት የሥራ ዘመን መክፈቻ ንግግርና የዓበይት ጉዳዮች አቅጣጫ ከተከናወነ በኋላ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጣይ በሚያደርጋቸው መደበኛ ስብሰባዎቹ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት የሚጨመረውንና የሚቀነሰውን በማከል የፕሬዚዳንቱን ንግግር ማፅደቅ ይጠበቅበታል፡፡

ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ይኼንን ኃላፊነቱን የተወጣው እጅግ ዘግይቶ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ የሕዝባቸውንና የድርጅታቸውን ክብር ለማስመለስ  መታገል እንዳለባቸው ወስነው ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት የአቶ አባዱላ ጉዳይ ምላሽ ባያገኝም፣ እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገኙበትን የፓርላማ ስብሰባ በአፈጉ ባዔነት ለመምራትም ሆነ እንደ ፓርላማ አባል ለመታደም አልተገኙም፡፡ ይህ ስብሰባም በምክትል አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ነበር የተመራው፡፡ የፕሬዚዳንቱን ንግግርና ዓበይት የሥራ ዝርዝሮች ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት የሚቀበለው መሆኑን በማረጋገጥ ለማፅደቅ በተሰየመው ምክር ቤት የተገኙት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በርካቶቹ፣ የወቅቱን የአገሪቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት የተመለከቱ ነበሩበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ ለነበረው ግጭት በአገሪቱ ፕሬዚዳንትም ሆነ በሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሲቀርብ የነበረውን ያልተካለለ ወሰን ምክንያት ለመጀመርያ ጊዜ በመቃረን  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ይኼ ግጭት የወሰን ግጭት አይደለም›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹በዚህ አካባቢ ያለውን የጫት ንግድ ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በዚህ መስመር ላይ ከፍተኛ ሕገወጥ የዶላር ዝውውርና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የብሔር ግጭት አዋጭ እንደሆነ ያመኑ የሥርዓታችን ጥገኞት የቀሰቀሱት ነው፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ምንም ዓይነት ግጭት የለም፡፡ የዚህ ግጭት መፍትሔም ፖለቲካዊ ነው፡፡ እነዚህን ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች በመድፈቅ መፍትሔ ካልተሰጠ በስተቀር መቼም ቢሆን ግጭቱን ለማቆም አይቻልም፤›› በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ባቀረቡት መልቀቂያ መሪ የፖለቲካ ድርጅቱ ተወያይቶ ውሳኔ እንዳልሰጠ፣ አቶ አባዱላ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ጥያቄያቸውን አንስተው ቢቀበሉ ደስተኛ መሆናቸውን አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

ፓርላማው የፕሬዚዳንቱን ንግግርና የሥራ አቅጣጫ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ካፀደቀ በኋላ የነበሩትን የመደበኛ ሰብሰባ ቀናት እምብዛም አልተጠቀመባቸውም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሥራ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የበጀት ዓመት የሥራ ዕቅድና የሦስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በመከታተል ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ፡፡

የምክር ቤቱ የኅዳር ወር 2010 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባዎች የተለያዩ አጋጣሚዎችን አስተናግደዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለምክር ቤቶቹ የሥራ መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ትኩረት እንዲደረጉባቸው ካሏቸው ውስጥ ፓርላማው ፈጣንና ፍትሐዊ ልማትን የሚደግፉ፣ የአገሪቱን ፌዴራላዊ ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችሉ አዋጆችና ፖሊሲዎች ፓርላማው ማፅደቅ እንደሚጠበቅበት አሳስበው ነበር፡፡

በኅዳር ወር ውስጥ ለፓርላማው ከቀረቡ አዋጆች መካከል ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ረቂቅ አዋጆች፣ የተስተናገዱበት መንገድ እንደ ልዩ ስህተት ታይቶ ነበር፡፡

የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅን በዝርዝር የተመለከተው የመሠረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ለማቅረብ፣ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. መደበኛው ስብሰባ ተጠርቶ ለመጀመር የሚያስፈልገው ምልዓተ ጉባዔ አሟልቶ እንዲጀምር የሚያስችል መሆኑ ታዛቢዎችን አጠራጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በቆጠራ በተረጋገጠው መሠረት ምልዓተ ጉባዔውን ለማሟላት የሚያስፈልገው የ275 አባላት መገኘት ሲሆን፣ በዕለቱ የተገኙትም 275 መሆናቸውን ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ  ሽታዬ ምናለ ገልጸው ወደ ውይይት ተገብቷል፡፡

በወቅቱ የቀረበው የከተማ ፕላን አዋጅ የአገሪቱ ከተሞች የከተማ ፕላን ወጥ በሆነ ተመሳሳይ ደረጃ እንዲቀርፁ፣ የፌዴራል መንግሥት አካል በሆነው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር እያፀደቁ የሚተገብሩበት፣ እንዲሁም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አተገባበሩን እንዲቆጣጠር ሥልጣን የሚሰጥ ነበር፡፡ ይህ የሕግ ሰነድ በኦሮሚያ ክልል ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለተቃውሞ ምክንያት የነበረውን የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በፌዴራል መንግሥት በኩል እንዲፅድቅ የሚያደርግ እንደሆነ፣ ይኼም ግጭትን ይቀሰቅሳል የሚል ሥጋት በተለይ ከኦሮሚያ ክልል በተመረጡ የምክር ቤቱ አባላት ላይ እንዳጫረ ይነገራል፡፡

በዚህ ዕለት የምክር ቤቱ ምልዓተ ጉባዔ መሟላት የቻለው 275 አባላት ተገኝተው ሲሆን፣ አንድ አባል ቢጎድል ኖሮ ሊበተን ይችል ነበር፡፡ በዚህ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ሳይገኙ የቀሩት በርካቶች ከኦሮሚያ ክልል የተወከሉ መሆናቸው በረቂቅ አዋጁ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ እንደሆነ ጥርጣሬ ቢያጭርም፣ ስብሰባውን የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ግን አባላቱ የቀሩት ለመሰክ ሥራ ከአዲስ አበባ ውጪ በመሰማራታቸው መሆኑን በወቅቱ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡

 በዚሁ በኅዳር ወር የቀረበው ሌላ አዋጅ በተመሳሳይ የፌዴራል መንግሥትንና የክልሎችን የሥልጣን ክፍፍል የሚያጣርስ እንደሆነ ትችት የቀረበበበት የደን ልማትና ጥበቃ አዋጅ ነበር፡፡ ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች የሚገኙ ደኖችን የፌዴራል መንግሥት እንዲያስተዳድር፣ እንዲሁም ሁለት ክልሎች የሚጋሩዋቸው የደን ይዞታዎችን የፌዴራል መንግሥት እንዳያስተዳድር የሚያደርግ ድንጋጌዎችን በመያዙ ክርክር ገጥሞት የነበረ ቢሆንም ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በ13 ድምፅ ተዓቅቦ ፀድቋል፡፡

በታኅሳስ ወር በፓርላማው ልዩ ሁነት ሆኖ የተመዘገበው ደግሞ የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚኖራትን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር ከባለድርሻዎች ጋር ለመነጋገር የጠራው ውይይት፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተወከሉ አመራሮችና በምክር ቤቱ መቀመጫ ባላቸው በክልሉ ሕዝብ በተመረጡ ተወካዮች ተቃውሞ መስተጓጎልና በኋላም ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉ ነው፡፡

የጉዳቱ ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ግጭት ውስጥ ወድቆ ከ600 ሺሕ በላይ ተፈናቅለው በመጠለያዎች የችግር ሕይወት እየገፉና የክልሉ መንግሥትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጠምዶ ሳለ፣ ይህ አዋጅ የኦሮሞ ሕዝብ በስፋት ሳይመክርበት ሊፀድቅ ስለማይገባ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የክልሉ አመራሮች አጠንክረው በመጠየቃቸው፣ ሰፊ ሰዓታት ከወሰደ ንትርክ በኋላ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተወስኗል፡፡

ይኼ አዋጅ ፓርላማው የ2010 ዓ.ም. የሥራ ዘመን አጠናቆ ለዕረፍት እስኪመለስ ድረስ በድጋሚ አልቀረበም፡፡

በዚሁ በታኅሳስ ወር በፓርላማው ትልቅ የመወያያ ጉዳይ የነበረው ሌላው አጀንዳ፣ ራሱ ምክር ቤቱ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ሥፍራዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ወገኖችን ሁኔታ እንዲገመግም ያሰማራው ግብረ ኃይል ያጠናቀረውን ሪፖርት ያደመጠበትና የምክር ቤቱ አባለት በቁጭት የተንገበገቡበት ነበር፡፡ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው ስብሰባ የቀረበው ሪፖርት ‹‹የደረሰብንን በደልና ግፍ ስታሰሙ በሕዝብ ወንበር ላይ መቀመጣችሁ ለምን ያስፈልጋል?›› የሚል የተፈናቃዮችን ወቀሳ የያዘ ነበር፡፡

በፓርላማው ልዩ ሁኔታ የተስተናገደው ጥር 15 ቀን በተካሄደው ስብሰባ ወቅት ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ሥልጣኑን እንደሚሽርበት አቤቱታውን ያሰማበት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ረቂቅ አዋጅ ለማፅደቅ ፓርላማው በዕለቱ ተሰይሟል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በረቂቁ ላይ ያነሳቸውን ተቃውሞዎች በመቀበል በአዋጁ ላይ ማስተካከያ ቢደረግም፣ ፓርላማው ይኼንን ረቂቅ የማፅደቅ ሥልጣን እንደሌለው የምክር ቤቱ አባላት አንስተው ተከራክረውበታል፡፡ በመጨረሻም በኢሕአዴግ የፓርላማ ታሪክ ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ተቃውሞ ተመዝግቧል፡፡ የቀረበው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ በ67 ተቃውሞና በ30 ድምፀ ተዓቅቦ ፀድቋል፡፡

በኢሕአዴግ የፓርላማ ታሪክ ትልቅ ታቃውሞ የቀረበው ፓርላማው በየካቲት ወር ለእረፍት ተበትኖ ከነበረበት በአስቸኳይ ተጠርቶ፣ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፀደቀበት ነበር፡፡

የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ88 የኦሕዴድ አባላት ተቃውሞና በሌሎች ሰባት የኦሕዴድ አባላት ድምፀ ተዓቅቦ የፀደቀ ቢሆንም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፅደቅ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሁለት ሦስተኛ ድምፅ አላገኘም፣ እንዲሁም አግኝቷል የሚሉ ክርክሮች በማስረጃ ተደግፈው እውነቱ ሳይለይ የፀደቀበት ነበር፡፡

የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመስከረም ወር ጀምሮ ፖለቲካዊ ወጀቦችን እሱም አብሮ በማስተናገድ መጋቢት ወር ላይ ይደርሳል፡፡

በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ የሥልጣን ትግል በማሸነፍ ሊቀመንበር የሆኑትን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመሰየም፣ የተሰበሰበው መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ በአገሪቱ ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ ለማበጀት ይደረግ የነበረው ፈርጀ ብዙ ጥረትና ትግል ውስጥ ‹‹የመፍትሔ አካል ለመሆን›› ከጠቅላይ ሚኒስትርነት በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቂያ ባቀረቡት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምትክ፣ እልህ አስጨራሽ እንደነበር የሚነገርለትን የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የተመረጡት ዓብይ አህመድ፣ መጋቢት 24 ቀን የፓርላማ በዓለ ሲመታቸው ወቅት ሥልጣን ከሚያስረክቡት አቶ ኃይለ ማርያም ጋር በጥልቅ ስሜት በመተቃቀፍ የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማና ሕገ መንግሥት ከተረከቡ በኋላ ለምክር ቤቱ ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነትን፣ ፍቅርንና ይቅር መባባልን በይፋ የሰበኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለፍትሕ የቆመ የሕግ ሥርዓት እንደሚገነቡ፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በደም የተሳሰሩት የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መልስው እንዲገናኙ ከልብ እንደሚሠሩ በይፋ አውጀዋል፡፡ ‹‹ነፃነት ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብስበና የመደራጀት መብቶች እንዲከበሩ የሚሠሩ መሆኑን በወቅቱ ይፋ አድርገዋል፡፡

ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የነበረው የምክር ቤቱ ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚያቀርቡትን የካቢኔ ሹመት ማፅደቅ ነበር፡፡ ሹመቱ ከመፅደቁ አስቀድሞ እንደ አዲስ ለቀረቡትም ሆነ ባሉበት ለሚቀጥሉ የካቢኔ አባላት፣ የእሳቸው የማይታለፉ ቀይ መስመሮች ያሏቸውን ሁለት ጉዳዮች በይፋ አስታውቀዋል፡፡

እነዚህ ነጥቦችም ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብበት የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲስተካከልና ሌብነትን የማይታገሱ መሆናቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡

ይኼንን የምክር ቤቱን ስብሰባ የመሩት ፓርላማው የዓመቱን የሥራ ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ከአፈ ጉባዔነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ነበሩ፡፡

‹‹የሕዝቤንና የምወክለውን ድርጅት ክብር ለማስመለስ እታገላለሁ፤›› ብለው የነበሩት አፈ ጉባዔ አባዱላ የፓርቲያቸው ሊቀመንበርና ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያቀረቡትን የካቢኔ ሹመት ፓርላማውን በመምራት እንዲፀድቅ ካደረጉ በኋላ በራሳቸው ፈቃድ ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ በድጋሚ አቅርበውት የነበረው መልቀቂያ በኢሕአዴግ ተቀባይነት አግኝቶ በዚሁ ዕለት ተሰናብተዋል፡፡

በምትካቸውም የደኢሕዴን ከፍተኛ አመራር የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በአፈ ጉባዔነት በዚሁ ቀን ተሰይመዋል፡፡

በዚሁ በሚያዝያ ወር ፓርላማው ያሳለፋቸው ሌሎች ውሳኔዎች ደግሞ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ፣ እንዲሁም የአካባቢ ምርጫን ዘንድሮ ማካሄድ ባለመቻሉ፣ ለ2011 ዓ.ም. እንዲሸጋገርለት ምርጫ ቦርድ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ይገኝበታል፡፡ በሌላ በኩል ዘንድሮ መካሄድ የነበረበት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በተመሳሳይ በ2011 ዓ.ም. እንዲከናወን የቀረበው የሕግ ማሻሻያ ይገኝበታል፡፡ ሁለቱንም ውሳኔዎች ፓርላማው ያሳለፈው ሕግን መሠረት አድርጎ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይተቻሉ፡፡

በግንቦት ወር በፓርላማው ውሳኔ ከተሰጠባቸው ዓበይት ጉዳዮች አንዱ በየካቲት ወር የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት ነበር፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል ምክንያት የነበሩ አለመረጋጋቶች በአንፃራዊ ሁኔታ በመሻሻላቸው፣ አዋጁ ከሚያበቃበት ነሐሴ ወር አስቀድሞ እንዲነሳ በመንግሥት የቀረበውን ውሳኔ ምክር ቤቱ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡

በሌላ በኩል በየዓመቱ በግንቦት ወር ለፓርላማው የሚቀርበው የፌዴራል ዋና ኦዲተር የፌዴራል መንግሥት የበጀትና ሀብት አጠቃቀም ኦዲት ግኝት ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የኦዲት ችግር ያለበት ሪፖርት ለፓርላማው ያሰሙት ዋና ኦዲተር ገመቹ ዲቢሶ፣ ‹‹ይህ ዘጠነኛ ሪፖርቴ ነው፣ ተመሳሳይ ሪፖርት በየዓመቱ እያቀረብኩ ነው፤›› ሲሉ ምክር ቤቱ ዕርምጃ መውሰድ እንዲጀምር ጠይቀዋል፡፡

በምክር ቤቱ የሰኔ ወር ዓበይት ክስተቶች ደግሞ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ መቀበሉን፣ ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር መወሰኑን ተከትሎ በራሱ በኢሕአዴግና በኅብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን ግራ መጋባት ምንጭ ለመገንዘብ ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጠራበት ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማው ተገኝተው ከምክር ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚን ለማስቀጠልና ከውጭ ምንዛሪ ችግር አዙሪት ለመውጣት የግድ የመንግሥት ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ሙሉ በሙሉና በከፊል ማዘዋወር እንደሚገባ፣ ይህም በጥንቃቄ መንግሥታቸው የሚያከናውነው መሆኑን ግልጽ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ሁኔታ ለመቀየር ሲወሰን፣ የድንበር ጉዳይ ሕዝብ የሚወያይበት መሆኑ በግልጽ ተወስኖና ሕዝብ እንዲወያይበትም አመራር ተሰጥቶ ሳለ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል የሚነዛው ስህተት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት በምሕረትና በይቅርታ ስም ሕግ ጥሶ አሸባሪውንና ሙሰኛውን መቅጣቱ ተገቢ እንዳልሆነ ወቀሳ አዘል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ይቅርታ እየተሰጠ ያለው በሕግ መሠረት ብቻ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገሪቱ ያለችበትን የቀውስ ምዕራፍ በይቅርታ መዘጋት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

ይቅርታ እየተደረገላቸው የነበሩት በሕግ የተያዙት ግለሰቦች በእስር ቤቶች ሰብዓዊ መብታቸው ተረግጦ አካል እስከ ማጉደል የደረሰ በደል እንደተፈጸመባቸው፣ አንዳንዶቹ የታሰሩት መብታቸውን በመጠየቃቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹አሸባሪው ማነው?  አሸባሪው መንግሥት አይደለም ወይ?›› ሲሉ ጥያቄውን በትችት ጭምር መልሰዋል፡፡

በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ ደግሞ በምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተው፣ ለ2011 ዓ.ም. የቀረበውን ከ346 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ማብራሪያ በመስጠት እንዲፀድቅ አስደርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት ከሰጧቸው ማብራሪዎች ውስጥ አንዱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግና ኤክስፖርት ማሸጋገር ተወጥኖ፣ ለአሥር ዓመታት ተደረገው ልፋት ውጤት አለማምጣቱንና እሳቸው በልዩ ሁኔታ ትኩረት የሚያደርጉት በግብርና ዘርፍ፣ በኤክስፖርት፣ በማዕድንና በቱሪዝም ልማት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው ፓርላማ ለእረፍት ከተበተነ በኋላ ሰሞኑን አፈ ጉባዔ ሙፈሪያት ካሚል የሚቀጥለውን ዓመት ቅድመ ዝግጅቶች አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ፓርላማው የሚኒስትሮችንና የከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎችን እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችለውን አሠራር እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የታሰበ አሠራር መሆኑን አክለዋል፡፡ ይህም የፓርላማ አባላት ዘንድሮ ያሳዩትን መነቃቃት የበለጠ ይጨምረዋል የሚል አንድምታ ለመፍጠር እንደሚረዳ ይታሰባል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -