ቢራቢሮ ቆንጆና በኅብረ ቀለማት የተዋቡ በራሪ ነፍሳት ሲሆኑ፣ እንደአብዛኞቹ ነፍሳት ስድስት እግር አላቸው፡፡ አራት ክንፍ ያለው የቢራቢሮ አካል በጥቃቅን ፀጉሮች የተሸፈነ ነው፡፡
ጥንድ አንቴና ያላቸው ቢራቢሮዎች በምርጥ በራሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡ የሚበሩት ግን የሰውነት ሙቀታቸው ከ86 ዲግሪ በላይ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በተለያዩ ቀለማት የተዋበው ጥንዱ ክንፋቸው፣ ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ እየለቀቀ ይመጣል፡፡
በሚበሩበት ጊዜ የፍጥነት መጠናቸው እንደየዝርያቸው ዓይነት ይለያያል፡፡ መርዛማ ቢራቢሮዎች መርዛማ ካልሆኑት ጋር ሲነፃፀሩም የመብረር አቅማቸው ያነሰ ነው፡፡ አንድ መርዛማ ያልሆነ ቢራቢሮ በሰዓት 30 ማይል የሚበር ሲሆን፣ ዝቅተኛ የመብረር አቅም ያላቸው ዝርያዎች በሰዓት አምስት ማይል ድረስ መብረር ይችላሉ፡፡
በ‹‹ኪድስ በተርፍላይ›› ድረ ገጽ እንደሰፈረው፣ አብዛኞቹ ቢራቢሮዎች ቅጠል ተመጋቢ ናቸው፡፡ ፈሳሽ ምግቦችን በተለይም ከበሰበሱ ቅጠሎችና አበቦች ላይ የሚጠራቀሙ ፈሳሾችን ይመጣሉ፡፡
በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩትና 150,000 የሚጠጉ ዝርያዎች ያላቸው ቢራቢሮዎች ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ ደረቅና እርጥበት፣ ተራራና ረባዳ ቦታዎች አይወስኗቸውም፡፡
የቢራቢሮ አመጣጥ አበባ ከሚሰጡ ተክሎች ጋር ተያይዞ እንደሆነ ሳይንሳዊ ጥናት ያመለክታል፡፡ 130 ሚሊዮን ዓመታት እንደቆየ የሚነገርለት የቢራቢሮ ቅሪተ አካልም መገኘቱም ይወሳል፡፡