Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹አብሮነት!›› ውሻ በግና ፍየል በአጎዛ ገበያ (ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኝ በረት)

‹‹አብሮነት!›› ውሻ በግና ፍየል በአጎዛ ገበያ (ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኝ በረት)

ቀን:

ፎቶ በሔኖክ ያሬድ

***********

ጠብቄሽ ነበረ
መንፈሴን አንጽቼ
ገላዬን አጥርቼ
አበባ አሳብቤ
አዱኛ ሰብስቤ
ጠብቄሽ ነበረ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
መንፈሴን አሳደፍኩ
ገላዬን አጎደፍኩ
አበባው ደረቀ
አዱኛው አለቀ፤
ብትቀሪ ጊዜ፣
የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞ ጠፋ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

              – ደበበ ሰይፉ፣ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› (1992)

***********

የጓዳ ውስጥ ባሪያና የመስክ ላይ ባሪያ

 (ይህ ፅሑፍ ከመጠነኛ ጭማሪ እና ቅናሽ በስተቀር ታዋቂው የጥቁር አሜሪካውያን መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስ በአንድ ወቅት ያደረገው ንግግር ትርጉም ነው ሊባል ይችላል)

ማልኮም ኤክስ በሠላሳ ዘጠኝ ዓመቱ በሰው እጅ ተገድሎ ከሞተ ሃምሳ አንድ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ንግግሩ ውስጥ ያለው ምሳሌ ግን ዛሬም ድረስ አለ፡፡

…እንግዲህ በአስከፊው የባሪያ ንግድ ዘመን ከአፍሪካ እንደ ከብት እየተነዱ ወደ አሜሪካ ተወስደው በጥጥ እርሻ ላይ የተሰማሩ ባሪያዎች ነበሩ፡፡ ባሪያዎች ሁሉ ግን አንድ ዓይነት አልነበሩም፡፡

በዘመኑ ሁለት ዓይነት ባሪያዎች ነበሩ- የጓዳ ውስጥ ባሪያና የመስክ ላይ ባሪያ፡፡

የጓዳ ውስጥ ባሪያ የሚኖረው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ጌታዬ›› እያለ ከሚያደገድግለት አሳዳሪው ጋር፡፡ ደህና ይለብሳል፡፡ ደህናም ይመገባል፡፡ ጌታው እግሩ ወጣ ሲል ለእርሱ የተዘጋጀውን ምግብ ስለሚቀላውጥ ደህና ምግብ ይመገባል፡፡

ከኩሽና ጥግ፣ መሬት ላይ ኩርምት ብሎ ቢተኛም የሚኖረው ግን ባሳዳሪው ጣሪያ ስር፣ ከጌታው ቤት፣ ከጌታው ጋር ነው፡፡

የጓዳ ውስጥ ባሪያ ጌታውን ጌታው ራሱ ራሱን ከሚወደው በላይ አጥብቆ ይወዳል፡፡ የጌታውን ቤት ከመፍረስ ለመታደግ ከእሱ ቀድሞ አንገቱን ይሰጣል፡፡

ጌታው ‹‹እዩትማ ይሄን ቤታችንን…ግሩም ነው አይደል?!›› ብሎ የጠየቀ እንደሆን ፈጠን ብሎ ‹‹እንዴታ! ይሄ ቤታችንማ እጅግ ግሩም ነው!›› ብሎ ያሽቋልጣል፡፡

የጓዳ ውስጥ ባሪያ ሁነኛ መለያም ይሄው ነው፡፡ ጌታው ‹‹እኛ›› ሲል ‹‹እኛ››፣ ‹‹የእኛ›› ሲል ‹‹የእኛ›› ይላል፡፡

ጌታው ታምሞ ባየ ጊዜ ‹‹ምነው ጌታዬ!? አመመን እንዴ?›› ብሎ በጭንቀት ይጠይቃል፡፡ አመመን እንዴ!

የጓዳ ውስጥ ባሪያ ሕልውናውን ከጌታው ጋር ያቆራኘ ነው፡፡ ካለጌታው መኖርን ሊያስብ አይችልም፡፡ ያለጌታው አንድ ቀን የሚያድር አይመስለውም፡፡ ያለጌታው ፈቃድ ፀሐይ እሺ ብላ የምትወጣ፣ በጄ ብላ የምትጠልቅ አይመስለውም፡፡

እናም አንዱ የመረረው ወደ እሱ መጥቶ ‹‹…ይሄ ኑሮ አይደለም…! እባክህ ከዚህ እንጥፋ…እናምልጥ!›› ቢለው በመገረም አይቶት ‹‹አንተ ያምሃል እንዴ…?! ምንድነው እናምልጥ ማለት…? ከዚህ የተሻለ ቤት የት አገኛለሁ…? ከዚህ የተሻለ ልብስ ከየት አመጣለሁ…? ከዚህ የተሻለ ምግብስ የት አባቴ አገኛለሁ…? ሆ…ሆ…! እናምልጥ ይለኛል አንዴ?!›› ብሎ ይመልሳል፡፡

በተመሳሳይ የጥጥ እርሻ፣ የመስክ ላይ ባርያዎች ይኖራሉ፡፡ በቁጥር ሲሰላ የመስክ ላይ ባሮች ከጓዳ ውስጥ ባሪያዎች እጅግ ይልቃሉ፡፡

የመስክ ላይ ባሪያ ውራጅ ይለብሳል፡፡ የመስክ ላይ ባሪያ የጌታውና የጓዳ ውስጥ ባሪያዎች ትርፍራፊን ይበላል፡፡ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ይኖራል፡፡ በዚህ ላይ፣ ከንጋት እስከ ውድቅት መባተሉ ሳያንስ ይደበደባል፡፡ ይቀጠቀጣል፡፡

ጌታውን ግን አጥብቆ ይጠላል፡፡ የጓዳ ውስጥ ባሪያ ጌታውን ሲያፈቅር፣ የመስክ ላይ ባሪያ ግን አምሮሮ ይጠላዋል፡፡

ብሩህ አእምሮ አለው፤ ምክንያቱም እንደእሱ ያሉ ባሪያዎች ከማንም በቁጥር እንደሚበልጡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

የመስክ ላይ ባሪያ፣ የጌታው ቤት በእሳት ሲያያዝ እግዜር የነፋሱን ጉልበት አንዲያበረታ ይፀልያል እንጂ በጭራሽ እሳቱን ለማጥፋት አይሞክርም፡፡

ጌታው ሲታመምም ‹‹አምላኬ ሆይ! ይሄንን ሰውዬ ዛሬ ገንድስልኝ!›› እያለ እግዜርን ይማፀናል እንጂ አይጨነቅም፡፡

የመስክ ላይ ባሪያን ማንም ሰው መጥቶ ‹‹ከዚህ ቦታ እንጥፋ… ከዚህ ኑሮ እናምልጥ›› ቢለው፣ ፈጠን ብሎ ‹‹እሺ! እንሂድ… እናምልጥ! ከዚህ የማይሻል ቦታ የለም!›› ይላል እንጂ ፈፅሞ አያንገራግርም፡፡

… ይህ የማልኮም ኤክስ ምሳሌ ዛሬም፣ በእኛም ዓለም አለ፡፡

ዓለም ዛሬም የጓዳና የመስክ ላይ ባርያዎችን ይዛ ትኖራለች፡፡

  • ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር

************

ግብፅን ያስቆጣው የሜሲ የጫማ ዕርዳታ

የዓመቱ የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቹ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ ጫማውን ግብፅን ለመርዳት ገቢ ማሰባሰቢያ እንዲሆን መስጠቱ ግብፃውያንን አስቆጥቷል፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ የግብፅ ፓርላማ አባልና የቴሌቪዥን ዝግጅት አቅራቢው ሰኢድ ሁሴን በቶክ ሾው ላይ ጫማውን አውልቆ ለተቸገሩ አርጀንቲናውያን እንደሚረዳ በምፀት ተናግሯል፡፡ ‹‹እኛ ግብፃውያን የምንሸጠው የሜሲን ጫማ ነው? የአንድ ግብፃዊ ሕፃን ጥፍር ቢሸጥ ከጫማው በላይ እንደሚያወጣ አያውቅም? ሜሲ ከፈለግክ ጫማህን ለእስራኤል መስጠት ትችላለህ›› ሲል ነበር ንዴቱን የገለጸው፡፡ ሜሲ የባርሴሎና ማሊያውን ለግብፆች ቢሰጥ የተሻለ ተቀባይነት ያገኝ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ምግባሩ የግብፃውያንን የሰባት ሺሕ ዓመታት ሥልጣኔ የሚያዋርድ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ‹‹እኛ ግብፃውያን ምግብ አጥተን ሊሆን ይችላል፤ ክብራችን ግን አሁንም አለ፤›› ብሏል፡፡ ሜሲ ስለጉዳዩ የሰጠው አስተያየት ባይኖርም፣ የተለያዩ የግብፅ ባለሥልጣኖች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ሜሲ ያለው ክቡር ነገር ጫማው በመሆኑ ለዕርዳታ ማቅረቡ መነቀፍ እንደሌለበት የተናገሩም አሉ፡፡

********

ሚሊዮን ዶላሮች ያላስቆሙት ወርቅ ቆፋሪ

ብዙዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሎተሪ አልያም ዕጣ ሲደርሳቸው፣ ገንዘብ ለማግኘት መኳተናቸውን እርግፍ አድርገው ትተው፣ ያገኙትን ገንዘብ ላሰኛቸው ነገር ማዋልን ይመርጣሉ፡፡ የትውልደ ሜክሲኳዊው ኤፍረን አግዊሬ ውሳኔ ግን ከብዙዎች የተለየ ነው፡፡ ኤፍረን የወርቅ ቁፋሮ ሠራተኛ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ከሥራ በኋላ ጎራ ያለበት መዝናኛ ውስጥ በሳንቲም በሚሠራ ማሽን ተጫውቶ 12.5 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሄደው ይህ ሜክሲኳዊ 64 ዓመቱ ሲሆን፣ አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው፣ ሥራውን በጣም ስለሚወድ ለ16 ዓመታት የዘለቀበትን ወርቅ ቁፋሮ እንደሚገፋበት ተናግሯል፡፡ ካገኘው ገንዘብ በጥቂቱ ቀንሶ ከባለቤቱ ጋር ቤት የገዙ ሲሆን፣ የተቀረውን ለክፉ ቀን ይሆናል በሚል ባንክ አስቀምጠው ወደ ሥራው ተመልሷል፡፡

***********

በማሽተት ፍቅረኛ ማግኘት

ሰዎች የፍቅር አጋር ለማግኘት የሚጠቀሙባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው ፍቅረኛን በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ማፈላለግ በአንድ ወቅት እንግዳ ነገር ነበር፡፡ ብዙ ድርጅቶች የተለያየ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ጥንዶችን በማግኘት ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ ኒውዮርክ ያለ አንድ ጥንዶች አገናኝ ድርጅት ጥንዶችን በሰውነት ጠረናቸው ማገናኘት መጀመሩን አሳውቋል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ድርጅቱ ለደንበኞቹ ቲሸርት ያድልና ለሦስት ቀን ለብሰውት ሳያጥቡት ለድርጅቱ ይመልሳሉ፡፡ ድርጅቱም የቲሸርቶቹን ቅዳጅ ለሌሎች ደንበኞቹ ይልካል፡፡ ደንበኞቹም በሽታ የመረጡትን ሰው ያሳውቃሉ፡፡ ከዛም ይገናኛሉ፡፡

በሽታ ፍቅረኞችን የሚያገናኘውን ድርጅት የመሠረቱት በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጽሑፍ መምህር ቲጋ ብራየንና በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ የሆነው ሳም ላቪኝ ናቸው፡፡ ደንበኞቻቸው 25 ዶላር ይከፍሉና ስለ ሰዎች ምንም መረጃ ሳይሰጣቸው በሽታው ብቻ የወደዱትን እንዲመርጡ እንደሚደረግ ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያሉ የፍቅረኞች መገናኛ መንገዶች ፎቶግራፍና ሌሎችም የሚታዩ ነገሮችን የተመረኮዙ እንደሆኑና ጠረን ከእይታ የበለጠ ሰዎችን የማስተሳስር አቅም እንዳለው ያምናሉ፡፡ በድርጅታቸው ብዙዎች የፍቅር አጋር እንደሚያገኙም ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...