Tuesday, April 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ብሔራዊ የጠለፋ መድን ኩባንያ ምሥረታ ሰሞነኛ ትኩሳት

በኢዮቤድ ጥበቡ ልሳነወርቅ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ግንቦት 1 ቀን 2014 በቁጥር SIB/1/2014 ባወጣው መመርያ (Directive) መሠረት የብሔራዊ የጠለፋ መድን ኩባንያ ለማቋቋም የመድን ኢንዱስትሪው ማኅበረሰብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አገር በቀል የጠለፋ መድን መቋቋም ዛሬ በአገራችን አዲስ ጅምር ይሁን እንጂ አያሌ ታዳጊ አገሮች ለምሳሌ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ አንጎላ፣ ህንድ፣ ወዘተ ከረጅም ዓመታት ጊዜ ጀምሮ በዘርፉ ከተሰማሩ ዓመታት ተቆጥረዋል ፡፡

በአብዛኛው ብሔራዊ የጠለፋ መድን ኩባንያ የሚሠራው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግሥት ባለቤትነት ይዞታ ነው፡፡ የአገር በቀል የጠለፋ መድን ጥቅም በዋናነት ለድንበር ዘለል የጠለፋ መድን ሰጪዎች በዓረቦን መልክ የሚወጣውን ውድ የውጭ ምንዛሪ በከፊል በአገር ውስጥ ለማስቀረት ነው፡፡ ስለዚህ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪዎች (Direct/primary Insurers) በአስገዳጅ (Mandatory/Compulsory) የጠለፋ መድን ሕግ  “አስገዳጅ ሴሽን” (Compulsory Cession) በቅድሚያ ለአገር በቀሉ የጠለፋ መድን ሰጪ እንዲያቀብሉ ይገደዳሉ፡፡ አያሌ አገሮች በአስገዳጅ ሴሽን ድርሻ መጠን ላይ አምብዛም ስምምነት የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ህንድ፣ ናይጄሪያና ሌሎች አገሮች ደርሻው እንዲቀነስና ገበያው ዘና እንዲል ሲጥሩ፣ በኬንያ ድግሞ 18 በመቶ የነበረውን ደርሻ ወደ 20 በመቶ ከፍ እንዲያድግ ይፈልጋሉ፡፡ በአገራችን የጠለፋ መድን “አስገዳጅ ሴሽን” መጠን ስንት እንደሆነ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለጊዜው መረጃ የለውም፡፡

ይሁን እንጂ አገር በቀል የጠለፋ መድን ኩባንያ መቋቋም የአንድን አገር የመድን አገልግሎት ስፋትና ዕድገት አያመለክትም፡፡ የአንድ አገር የመድን አገልግሎት ዕድገት ከሚለካባቸው መሥፈርቶች መካከል “የመድን ጥልቀት ምጣኔ” (Insurance Penetration) እና “የመድን እፍግታ ምጣኔ” (Insurance Density) ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይኸውም በዓመት ውስጥ የተጻፈውን የመድን አገልግሎት ዓረቦን (Written Premium) ከዓመቱ ጠቅላላ ምርት (GDP) ጋር በመቶኛ በማነፃፀር የምናገኘው አኃዝ የመድን ጥልቀት ምጣኔውን ያሳየናል፡፡ እሱም የመድን አገልግሎት ጠቅላላ ዓረቦን  ለአገሪቱ ጠቅላላ ምርት (GDP) ያበረከተውን አስተዋጽኦ ይለካል፡፡ በዓመት ውስጥ የተመረተውን የመድን ጠቅላላ ዓረቦን በሕይወትና ሕይወት ነክ ባልሆነ የመድን ዘርፍ ተለይቶ ለሕዝብ ብዛት ሲካፈል ደግሞ ለእያንዳንዱ የመድን ዘርፍ ዓይነት “የመድን እፍግታ ምጣኔውን” ያመለክተታል፡፡ ይህ ደግሞ የነፍስ ወከፍ የመድን ዋስትና ዓረቦን ምጣኔን የሚገልጽ ነው፡፡

የመድን አገልግሎት ውል አጻጻፍ በእንግሊዝ አገር በሎይድስ ቡና ቤት ከተጀመረ  348 ዓመት ሆኖታል፡፡  በኢትዮጵያ ለጉዳት ሥጋት የመድን ዋስትናን በአለኝታነት መቀበልና መስጠት ለረጅም ዘመናት የቆየ ባህላዊ ዘዴ  መሆኑ  እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዘመናዊው  የመድን አገልግሎት ሥራ በዳግማዊ አፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ከተጀመረ 111 ዓመት  ተቆጥሯል፡፡ ይህም  ዘመናዊ የመድን አገልግሎት በዓለም ደረጃ ከተጀመረ ሲሶውን ጊዜ ያህል የመድን ሥራ በኢትዮጵያ እንደቆየ መረዳት አያዳግትም፡፡

ከዚህ የጊዜ ርዝመት አኳያ የኢትዮጵያ ዘጠና አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ስለ መድን አገልግሎት መሠረታዊ ግናዛቤው ምን ያህል ዳብሯል? በአገልግሎቱስ ኅብረተሰቡ  እንዲጠቀም ባለድርሻ አካላት ምን ያህል ጥረት አድርገዋል? ተብሎ ቢጠየቅ አመርቂ የሆነ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡ የመድንን በረከትና ትሩፋት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ስለመቀዳጀቱ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው ጎረቤት አገሮች አንፃር እንኳን ሲመዘን በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እሙን ነው፡፡ “ሀ” ሳይሉ “ለ”ን እንዳማይቆጥሩ ሁሉ ስለ መሠረታዊ የመድን ጽንሰ ሐሳብና የአሠራር ዘይቤ ግንዛቤው አናሳ ለሆነ ኅብረተሰብ “ስለጠለፋ መድን” ሲነገረው (ሰሞኑን መገናኛ ብዙኃን ዜናውን ሲዘግቡ ከርመዋል) የሚፈጠርበትን ግርታ በመጠኑም ቢሆን ለማጥራት  ይኼ ጽሑፍ ሙከራ ያደርጋል፡፡

የግሪኩ ፈላስፋ “አርስጣጣሊስ” (Aristotel) የሰው ልጅ ራሱንና ንብረቱን ከጉዳት መጠበቅና መከላከል የተፈጥሮ ግዴታው ነው ብለዋል፡፡ እንዳሉትም የሰው ልጅ ከልዩ ልዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ራሱንና  ንብረቱን ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋል፡፡ የጉዳት ሥጋትን ለመቀነስ፣ ለመከላከል፣ ብሎም ለመቋቋም በተግባር ከዋሉት ዘዴዎች መካከል “የመድን ዋስትና” ዋነኛው ነው፡፡  በሞት፣ በሕመምና በአካል መጉደል፣ እንዲሁም በተለያዩ አደጋዎች ክስተት በንብረት  ላይ ጉዳት ሲደርስ ወይም በሕጋዊ ግዴታ የኃላፊነት ጥያቄ  ሲከተል  የሚደርሰውን “ኢኮኖሚያዊ ወይም ፋይናንሲያዊ የጉዳት ክስረት” (Financial or Economic Loss) ለመቋቋም ወይም ጉዳቱን በገንዘብ ለማካካስ እንዲቻል በቅድሚያ የሚታወቅ አነስተኛ ወጪ (ዓረቦን) በመክፈል፣ ሰዎች ከመድን ሰጪ ኩባንያ የሚገዙት የመድን ዋስትና ውል “ዘመናዊ የጉዳት ሥጋት ማሸጋገሪያ ዘዴ” (Modern Risk Transfer Mechanism) በመባል ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የመድን ዋስትና ለኅብረተሰብ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል ዓበይት የሆኑትን እንደሚከተለው መጥቀስ ይቻላል፡፡

(ሀ)   የመድን ዋስትና በድንገተኛ ደራሽ አደጋ የወደመን (የጠፋን) ንብረት መልሶ ይተካል፡፡ በድንገተኛ አደጋ ንብረት ሲወድም ለተጎጂው ወገን በቁሳዊ ንብረት ውድመት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የሥነ ልቡና ችግርም የሚያስከትል ነው፡፡ ጉዳት የሚደርሰው በንብረት ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ላይ “ያለ ጊዜ መሞት” (Premature Death) ሕመም ወይም የአካል ጉዳት የሚፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ ወይም ፋይናንሲያዊ ክስረት መድን በአለኝታነት የሚታደግ ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡

(ለ) የመድን ዋስትና መኖር ጭንቀትን ያቃልላል፡፡ የመድን ዋስትና የሌለው አልሚ ባለሀብት ወይም ቤተሰብ ያለው አባወራ ወይም እማወራ ጥሩ እንቅልፍ አይተኙም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሥራ ላይ ያዋለውን ገንዘብና በሥሩ የሚተዳደሩትን ቤተሰቦች በአጋጣሚ ከሚደርስ አደጋ ለመታደግ ተገቢውን የመድን ዋስትና በአለኝታነት የጨበጠ ሰው ግን፣ ሥጋትና ጭንቀት ስለሌለበት ሥራውን ብሎም ሕይወቱን በሰከነና በተረጋጋ አኳኋን ሊመራ ይችላል፡፡

(ሐ) ድንገተኛ ደራሽ አደጋ የጊዜ ቀጠሮ የለውም፡፡  በእጅ ያለ ገንዘብ ወይም የተበደሩት ገንዘብ  በሥራ ላይ ውሎ ከፍ ያለ ጥቅም ሊያስገኝ ሲችል ለክፉ ቀን ተብሎም በመጠባበቂያነት የሚታሰር ከሆነ፣ የገንዘቡ ጥቅም ያንሳል ወይም ገንዘቡ በብድር የተገኘ ከሆነ የዕዳው መጠን በየጊዜው እየናረ ይሄዳል፡፡ ገንዘብ በልማት ሥራ ላይ ሲውል ጥቅሙ ለአልሚ ባለሀብቶች ብቻ ሳይወሰን አጠቃላይ ጥቅሙ ለአገር ኢኮኖሚና ለኅብረተሰብ ኑሮ ዕድገት ጭምር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

(መ)   “ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ዋስትና ሰጪዎች” (Direct/Primary Insurers) እና  “የጠለፋ መድን ሰጪዎች” (Reinsurers) የተለያዩ አደጋዎች ሊያደርሱ  የሚችሉትን የጉዳት ሥጋቶች መንስዔ በማጥናትና በማስጠናት አደጋዎች እንዲወገዱ ወይም እንዲቀነሱ በማድረግ ረገድ፣ ብሎም የአደጋዎችን መከላከያ ዘዴዎችንና ዕርምጃዎችን በማፍለቅና በሥራ ላይም የሚውሉበትን መንገድ በማመቻቸት ምክሮችንም በመለገስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡

(ሠ)   ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪዎችም ሆኑ የጠለፋ መድን ሰጪዎች የሥራ ዕድል ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ የሥራ አጥነትን ችግር በመቀነስ ረገድ የማይናቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡

(ረ) ከድንበር ዘለል (Cross Boarder) የባንክና የጠለፋ መድን “ከማይታየውና ከማይዳሰሰው የወጪ ንግድ” (The Invisible Export) ከሚባለው የንግድ ዘርፍ አያሌ አገሮች ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝ ከጠቅላላ “የቁሳቁስ ወጪ ንግዷ” (Comodity Export) የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይልቅ ከባንክ፣ ከጠለፋ መድንና ከመሳሰሉት ንግዷ የምታፈራው የውጭ ምንዛሪ ይበልጣል፡፡

በጥቅሉ ለማስቀመጥ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ሕጋዊ ሰውነት (Legal Personality) ያለው ድርጅት ወይም ተቋም በጫንቃው ላይ ተሸክሞት ያለው የጉዳት ሥጋት (Risk)፣ ሊያስከትልበት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ወይም ፋይናንሲያዊ የጉዳት ክስረት ለጉዳቱ ተመጣጣኝ ካሳ አግኝቶ ክስረቱን ለማስተካከል እንዲችል የጉዳት ሥጋቱን ወደ “ጉዳት ሥጋት ተሸካሚ” (Risk Carrier) (የመድን ዋስትና ሰጪዎች የጉዳት ሥጋት ተሸካሚዎች ይባላሉ) ያሸጋግራል ወይም ያስተላልፋል፡፡

አንድ ሰው  የጉዳት ሥጋቱን ለማሸጋገር የመድን ዋስትና ሲገዛ በተለምዶ “መድን ገቢ” (Insured) ይባላል፡፡  የንግድ ሕጉ  “ኢንሹራንስ የገባ ሰው” ይለዋል (አንቀጽ 654)፡፡ የጉዳት ሥጋቱ የሚሸጋገርለትን የመድን ተቋም “ኢንሹራንስ ሰጪ” (Insurer) ብሎ ሕጉ ጠቅሶታል፡፡ እነዚህን የመድን ቃላት በተሻሻለ አማርኛ ቃል  ለመሰየም  የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ “የጉዳት ሥጋትና መድን” (Risk and Insurance) በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ ባዘጋጀው አዲስ ረቂቅ መጽሐፍ ውስጥ እንደገለጸው፣ መድን (Insurance) ከሚለው ነገረ ቃል መድን ገቢን “ተመዳኝ” (Insured) እንዲሁም መድን ሰጪን “መዳኝ” (Insurer) በሚሉ አቻ አዳዲስ ቃላት ተክቷቸዋል፡፡ በረቂቅ መጽሐፉ ውስጥ አያሌ የመድን ቴክኒካዊ ወይም ሙያዊ የእንግሊዝኛ ቃላት በተስማሚ አማርኛ ተርጉሟቸዋል፡፡ ለምሳሌ በመድን ዓውድ (context)፣ የጉዳት ሥጋት (Risk)፣ ጉዳት አድራሽ (Peril)፣ ጉዳት አሥልጥ (Hazard)፣ ሰብዓዊ ጉዳት አሥልጥ (Moral Hazard)፣ ርቱዕ ጉዳት ሥጋት (Pure Risk)፣ ገመታ ጉዳት ሥጋት (Speculative Risk)፣ “ተመጣጣኝ ካሳ” (Indemnity)፣ ቅርብ መንስዔ (Proximate cause)፣ “የጉዳት ሥጋት ተጎጂዎች” (Risk Victims)፣ እርግጠኝነት (Certainty)፣ ኢ እርግጠኝነት (Uncertainty) የተባሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ እንደመሆኑ መጠን ኅብረተሰቡ ለምሳሌ መድን (Insurance) እና ዓረቦን (Premium) የተሰኙትን ቃላት በጥቅም ላይ አውሎ እየተግባባቸው ይገኛል፡፡ ከባዕድ ቋንቋዎች ይልቅ በራስ መግባቢያ ቋንቋ መጠቀም እንደሚበጅ ከእነዚህ ሁለት ቃላት በላይ ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡

ድንገተኛ ደራሽ አደጋን ለመቋቋም መዳኝና ተመዳኝ በተዋዋሉት የመድን ውል ሰነድ (Insurance Policy) ውስጥ የመድን ሽፋን ወይም ከለላ (Cover) በተሰጣቸው “ጉዳት አድራሾች” ወይም በእነሱ ቅርብ መንስዔ ምክንያት በደራሽ  አደጋዎች ጉዳት ሲያደርስ  የመድን ዋስትናው አለኝታ ሆኖ  ለጉዳት ክስረት ተመጣጣኝ ካሳ ለማግኘት የመድን ዋስትና ጠቃሚ ነው፡፡ “ተመጣጣኝ ካሳ” ከመድን ሕጋዊ መርሆች አንዱ ሲሆን፣ መሠረተ ሐሳቡንና አተገባበሩን ኅብረተሰቡ በሚገባ እንዲረዳው ከላይ በተጠቀሰው ረቂቅ መጽሐፍ ውስጥ በሰፊው ተተንትኖ ቀርቧል፡፡ ስለዚህ መድን “የጉዳት ሥጋት ተጎጂዎች” ከጉዳት በፊት ወደ ነበሩበት የንብረት ወይም የንዋይ አቋም እንዲመለሱ ወይም ለጉዳታቸው ፋይናንሲያዊ ጥቅም እንዲያገኙ የሚረዳ ዋና መሠረታዊ የአገር ኢኮኖሚ አጋር ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የመድን ዋስትናን ጥቅም አውቆና ተረድቶ በስፋት እንዲጠቀምበት በማድረግ ረገድ መንግሥትና የባለድርሻ አካላት እንዲሁም የመድን ባለሙያዎች ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

እንደ መድን ባለሙያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የበኩሉን አስተዋተዋፅኦ ለማድረግ  በረጅም ጊዜ ጥረትና ምርምር 700 ገጾች ያሉት ስለጉዳት ሥጋትና መድን በስፋት የሚተነትን መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉ በረቂቅ መልክ መጠናቀቁን  በዋናነት ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣንና ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ማኅበር በደብዳቤ አብስሯል፡፡ የኢንዱስትሪው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሚገኙበት ዓውደ ጥናት (Workshop) ተዘጋጅቶ የመጽሐፉን አጠቃላይ ይዘት ጸሐፊው እንዲያስተዋውቅና ቀጥሎም የመጽሐፉን ቴክኒካዊና ሕጋዊ ብቃት የሚገመግሙ ባለሙያዎች ተመርጠው እንዲያዩትና ታትሞ ለሕዝብ እንዲደርስ ለኢንዱስትሪው ባለሥልጣናት ከጥቂት ወራት በፊት በጽሑፍና በቃል ጸሐፊው አሳስቧል፡፡ እስካሁን ድረስ ከማንኛቸውም ወገን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ  አልተገኘም፡፡  ይኼ ጠቃሚ መጽሐፍ ታትሞ ለሕዝብ እስኪደርስ ድረስ ጸሐፊው ተስፋ ሳይቆርጥ ጥረቱን በየአቅጣጫው  ይቀጥላል፡፡   

  1. “የጠለፋ መድን” ምንድነው?

የታሪክ ማህደር እንደሚዘግበው የመጀመርያው የጠለፋ መድን ውል በላቲን የተጻፋው በሐምሌ ወር 1370 ጄኖዋ (Genoa) ላይ ነው፡፡ ይኸውም ከካዲዝ (Cadiz, Spain)፣ ወደ ስሉዝ ፍላንደርስ (Sluis, Flanders) በባሕር ለተጓጓዘ ጭነት የተሰጠ የጠለፋ መድን ዋስትና ነው፡፡ ዛሬም በመድን የሥራ ሒደትና አፈጻጸም የጠለፋ መድን  ክፍተኛ  ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡  “ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪም” ሆነ  “የጠለፋ መድን ሰጪ” ከተመዳኞች የሚሸጋገሩላቸውን የጉዳት ሥጋቶች በሙሉ ብቻቸውን ተሸክመው አይቀሩም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ እንደተብራራው የመድን  ዋነኛና መሠረታዊ የአሠራር ዘይቤና ሥልት “የጉዳት ሥጋት ክፍፍል” (Risk Distribution/sharing)  ነው፡፡  “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” (Fifty Lemmons are Burden for One Person but Adornments for Fifty) እንዲሉ፡፡ ይኼ የጥንት ኢትዮጵያዊ ብሂል መሠረታዊውን የመድን አሠራር ዘይቤ ይገልጻል፡፡ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ ከተመዳኞች የተቀበለውን የጉዳት ሥጋት እንዳቅሙ በራሱ ሒሳብ የሚሸከመውን ያህል፣ የጉዳት ሥጋት አስቀርቶ ተራፊውን ለጠለፋ መድን ሰጪ ያከፋፍላል፡፡  ቀጥተኛ ወይም ቀዳሚ  መድን ሰጪ “ከተመዳኙ ሕዝብ” (Insuring Public)  ጋር ያለው የግንኙነት መስመር ቀጥተኛ ሲሆን፣ መድን ገቢ  ከጠለፋ መድን ሰጪው ጋር ያለው ግንኙነት  ኢቀጥተኛ ነው፡፡ ስለዚህ በጠለፋ መድን ውል ተዋዋይ ወገኖቹ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪውና የጠለፋ መድን ሰጪው ናቸው፡፡ 

ስለጠለፋ መድን በምናወሳበት ጊዜ ከመድን ገቢው ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን መድን ሰጪ “ቀጥታ ወይም ቀዳሚ” የሚል ገላጭ ቅጽል ማከላችን በሁለቱ የሥራ ሒደቶች መካከል ያለውን ልዩነት ግልጽ ለማድረግ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው፣ ከተመዳኝ ደንበኛው የተሸጋገረለትን የጉዳት ሥጋት ቀጥተኛ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ፣ ከጠለፋ መድን ሰጪ ዘንድ በከፊል ወይም በሙሉ የጠለፋ መድን ዋስትና ይገዛለታል፡፡ በግልጽ አነጋገር የጠለፋ መድን  “የመድን መድን” (Insurance of Insurance) ሲሆን፣ በእርግጥም ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪው በበኩሉ የራሱን ጉዳት ክስረት ለመጠበቅ ሲል የሚገዛው የጠለፋ መድን ዋስትና ነው፡፡ በጠለፋ መድንም አያሌ ቴክኒካዊ ወይም ሙያዊ ሥነ ቃላቶች አሉ፡፡ ለእነዚህ ቴክኒካዊና ወይም ሙያዊ ሥነ ቃላት የአማርኛ አቻ ትርጉም ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡   በሥነ ቃላቱም የሚጠቀሙት የመድን ባለሙያዎች እርስ በርሳቸው ስለሆነ  የእንግሊዝኛ ሥነ ቃላቱን እንዳሉ ተውሰን በአማርኛ ፊደል ጽፈን ብንጠቀምባቸው እንደሚበጅ ከላይ በተጠቀሰው የጉዳት ሥጋትና መድን ረቂቅ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ተብራርቷል፡፡ ይኸውም ኮምፒዩተር፣ ሬዲዮ፣ ቴሌፎን፣ ኮት፣ ሸሚዝ፣ ሞባይል ብለን እንደምንጠቀመው ዓይነት  ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በጠለፋ መድን የሥራ ሒደት ለተመዳኞች የመድን ዋስትና የሰጠው ቀጥተኛ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ “ሲዲንግ ኩባንያ ወይም ሲዳንት” (Ceeding Company/Cedante) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ለቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ ኩባንያ የጠለፋ መድን ዋስትና የሚሰጠው “የጠለፋ መድን ሰጪ” (Reinsurer) ነው፡፡ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ ኩባንያ በጠለፋ መድን ፕሮግራሙ መሠረት ለራሱ ሒሳብ የሚያስቀረው የጉዳት ክስረት መጠን “የሪቴንሽን ወሰን” (Retention Limit)፣ ወይም “ኔት ሪቴንሽን” (Net Retension) ይባላል፡፡ ወደ ጠለፋ መድን ኩባንያው የሚያሸጋግረው ሒሳብ ደግሞ “ሴሽን” (Cession) ሲሆን፣ ሲዳንቱ (ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪው) ለጠለፋ መድን ዋስትና “የጠለፋ መድን ዓረቦን”  ይከፍላል፡፡ አደጋ በደረሰ ጊዜ የጠለፋ መድን ሰጪው በድርሻው መሠረት የጉዳት ካሳ ለቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪው ስለሚከፍል፣ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪውም በተመዳኝ ደንበኛው ላይ የጉዳት ክስረት ሲደርስ የራሱን ድርሻና ከጠለፋ መድን ሰጪዎች የተከፈለውን ካሳ ሰብስቦ፣ ለተጎጅ ደንበኛው የጉዳቱን ተመጣጣኝ ካሳ ይከፍላል፡፡ ለጠለፋ መድን ዋስትና ሰጪ በውጭ ምንዛሪ ዓረቦን የሚከፈለው ሲሆን፣ የጠለፋ መድን ዋስትና በተሰጠው ሕይወት ወይም ንብረት ጉዳት ሲደርስ ካሳውን የሚከፈለው በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡

የጠለፋ መድን ሰጪዎችም “ለራሳቸው ሒሳብ”  ድርሻ ድርሻቸውን አስቀርተው ከሌሎች ጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር ይከፋፈላሉ፡፡ በዚሁ መሠረት የጠለፋ መድን ሰጪው በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የጠለፋ መድን ሰጪዎች መልሶ የሚያከፋፍለው ሒሳብ “ሬትሮሴሽን” (Retrocession) ይባላል፡፡ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና በሌሎችም አካባቢዎች በርካታ አስተማማኝ የጠለፋ መድን ሰጪዎች በጠለፋ መድን ገበያ ውስጥ የመሳተፋቸውን ያህል፣ አስተማማኝ ያልሆኑ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ነን ባዮችም ደግሞ የጠለፋ መድን  ገበያውን እንደሚያወናብዱ መዘንጋት የለበትም፡፡

2. የጠለፋ መድን ጥቅሞች

የጠለፋ መድን ለቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ የሚሰጣቸው ጥቅሞች  አያሌ ሲሆኑ፣ ዋና ዋናዎቹን ቀጥለን እንገልጻለን፡፡

2.1. የውል አፈጻጸም አቅምን (Underwriting Capacity) ያጠናክራል፡፡ የቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ “የውል አጻጻፍ አቅም”  በጠለፋ መድን ይጠናከራል ሲባል  መድን ሰጪ የተለያዩና ብዙ ቁጥር ያላቸውን የዋስትና ዓይነቶች ለመድን ፈላጊዎች ለመሸጥ የሚያስችል አቅም ያገኛል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ እያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር የመድን ዋስትና ገንዘብ  (Sum Insured) ያላቸውን አንድ ሺሕ የመድን ውሎች ቢሸጥና በውል ዘመኑ ውስጥ እንዳጋጣሚ በሁሉም መድን ገቢዎች ላይ አደጋ ቢደርስ፣ የመድን ሰጪው በተመዳኝ ደንበኞቹ ላይ የደረሰውን የጉዳት ክስረት ለመካስ ለእያንዳንዱ የመድን ውል ብር አንድ ሚሊዮን  በድምሩ አንድ ቢሊየን ብር ሊደርስ የሚችል የጉዳት ካሳ ሊከፍል ይችላል፡፡ ስለዚህ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ ለእዚህ ከፍተኛ የጉዳት ክስረት እንዳይጋለጥ አስተማማኝ የጠለፋ መድን ዋስትና ሽፋን ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ አኳኋን የመድን ሰጪው ከጠለፋ መድን ብርቱ አቅም አገኘ ማለት ነው፡፡  አዳዲስ መድን ሰጪዎችም ብዙ አቅም ከገነቡ ከነባር መድን ሰጪዎች ጋር በገበያው ውስጥ ሊወዳዳሩ የሚችሉት ጠለፋ መድን በሚፈጥርላቸው አቅም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

2.2. የፋይናንስ አቋምን ያረጋጋል፡፡ በተፈጥሯዊና በሰው ሠራሽ የተለያዩ ጉዳት አድራሽ አደጋዎች የአንድ መድን ሰጪ “የጉዳት ክስረት ልምዱ” ተለዋዋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያም ሳቢያ ዓመታዊ የፋይናንስ ውጤቱም ሆነ የጉዳት ክስረት ልምዱ በየጊዜው ተለዋዋጭ ከሆነ፣ የመድን ሰጪው ትርፍ አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ሊል ወይም በተከታታይ ዓመትም ክስረት ሊደርስበት ይችላል፡፡ ይኼን መሰሉን “ወጣ ገባ ወይም ተለዋዋጭ የፋይናንስ ውጤት” (Fluctuating Financial Result)  ለማደላደል  መድን ሰጪውን የሚረዳው የጠለፋ መድን ፕሮግራሙ ነው፡፡ ለምሳሌ በንብረት ላይ እንዳጋጣሚ ከፍተኛ ውድመት ቢደርስ መድን ሰጪው ለራሱ ሒሳብ ካስቀረው ድርሻ ወይም ከሪቴንሽኑ በላይ የደረሰበትን የጉዳት ክስረት የሚሸፍነው፣ የጠለፋ መድን ሰጪዎች በሚከፍሉት የካሳ ድርሻ  ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቀጥታ ወይም ቀዳሚው መድን ሰጪ የጠለፋ መድን ዋስትናው አለኝታ ካልሆነው  ከጨዋታ ውጪ ሊሆን ይችላል፡፡

2.3. “ያልተበላ ዓረቦን መጠባበቂያ ጫናን” ያቃልላል፡፡ ከመድን ባለሙያዎች ውጪ “Unearned Premium” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቴክኒካዊ ወይም ሙያዊ ሐረግ በአማርኛ ተስማሚ ቃል ለመተርጎም ከላይ በተጠቀሰው “የጉዳት ሥጋትና መድን” ረቂቅ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው፣ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ብዙ ተመራምሯል፡፡ ለቃሉ አተረጓጎም ቁልፍ ምንጭ ሐሳብ ያገኘውኅ ኅብረተሰባችን በዕቁብ ሥራ ላይ   የሚግባባቸውን “የተበላ ዕቁብ” እና “ያልተበላ ዕቁብ” ከተሰኙት የመግባቢያ ሐረጎች ነው፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳ የነገረ ቃላቱን አጠቃቀም በምሳሌያዊ ትንታኔ በቅድሚያ እናንሳ፡፡ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ 12 ጓደኛሞች አንድ መቶ ብር በየወሩ  እየጣሉ ዕቁብ መሠረቱ እንበል፡፡ በመጀመርያው ወር የተሰበሰበውን ገንዘብ ማን እንደሚወስድ ዕጣ ሲያወጡ ከዕቁብተኞቹ መካከል ለአንዱ አባል ዕጣው ወጣለት፡፡  የዕቁቡ ሰብሳቢ ዳኛ ሆኖ የተመረጠው ከእያንዳንዱ ዕቁብተኛ የሰበሰበውን አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ብር ለባለዕድሉ አስፈርሞ  ይሰጠዋል፡፡  ዕቁብተኞች ለባለዕድሉ ያዋጡት አንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር ሲሆን፣ አንድ መቶው ብር ግን የባለዕድሉ የራሱ መዋጮ ነው፡፡ የመጀመርያው ባለዕድል ዕቁብተኛ ለሚቀጥሉት አሥራ አንድ ወራት የሚጥለው “የተበላ ዕቁብ”  ነው፡፡  ስለዚህ በመጀመርያ ከዕቁብተኞች የተጣለውን አንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር የበላው ዕቁብተኛ ወደፊት የሚከፍለው ዕዳው ነው፡፡ በዕቁቡ መጨረሻ 12ኛው ዕቁብተኛ የሚያገኘው አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ብር  “ያልተበላ ዕቁብ” ነው ፡፡ በዚህ ምሳሌ  “የተበላና ያልተባለ ዕቁብ” የሚሰኙትን ነገረ ቃላት  ከዕቁብ ጋር በተመሳስሎ (Analogy) ዘዴ ተጠቅመን “Earned Premium” እና “Unearned Premium” ለተሰኙት የመድን ቴክኒካዊ ወይም ሙያዊ ቃላት “የተበላ ዓረቦን” እና “ያልተበላ ዓረቦን”  በሚሰኙ ተስማሚ አቻ የአማርኛ ቃላት ትርጉም ለመስጠት  ነው፡ 

በዚህ እሳቤ በመድን የአሠራር ዘይቤ “የተጻፈ ዓረቦን” (Written Premium) የሚለው ሐረግ በተወሰነ የውል ዘመን (እንበል አንድ ዓመት) ውስጥ መድን ገቢዎች ለተለያዩ የመድን ዋስትናዎች በቅድሚያ ለመድን ሰጪው የከፈሉት ጠቅላላ ዓረቦን ነው፡፡ “የተበላ ዓረቦን” የውል ዘመናቸው በከፊል ወይም በሙሉ ለተጠናቀቀው የመድን ውሎች መድን ሰጪው ለሰጠው የመድን  ዋስትና አገልግሎት የበላው ዓረቦን መሆኑን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ በተጻፈ ዓረቦንና በተበላ ዓረቦን መካከል ያለው ልዩነት የመድን ውሉ ሽፋን ዘመን በመጠናቀቁና ባለመጠናቀቁ የሚለይ ይሆናል ማለት ነው፡፡  እንደሚታወቀው የመድን ደርጅቶች ሒሳብ የሚዘጋው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወር ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ አገር በቀል መድን ሰጪዎች የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከሐምሌ 1 ቀን  እስከ  ሰኔ 30 ቀን ድረስ ነው፡፡  የመድን ዋስትና ውሎች በሙሉ በአንድ ቀን ውስጥ የሚሸጡ ሳይሆኑ በበጀት ዓመቱ ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን   በቅደም ተከተል የሚሸጡ ናቸው፡፡ የአንዳንዶቹ ውሎች የውል ዘመን ከተሸጡበት በጀት ዓመት ሒሳብ መዝጊያ አልፈው ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት ሊዘልቁ ይችላሉ፡፡ የአንድ በጀት ዓመት ሒሳብ ሲዘጋ “በሀብትና ዕዳ ሚዛን” (Solvency Margin) መሠረት መድን ሰጪው በከፊል ያልበላው ዓረቦን (የውል ዘመናቸው ያልተጠናቀቀው ማለት ነው) ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት ሒሳብ ዕዳ ሆኖ ይሻገራል፡፡  በዚህም ምክንያት በመድን ሥራ አዋጁ መሠረት መድን ሰጪው ገና ላልበላው ዓረቦን መጠባበቂያ መያዝ አለበት፡፡

ጽንሰ ሐሳቡን ግልጽ ለማድረግ አንድ ሰው “ከፈጥኖ ደራሽ መድን ኩባንያ” (ለምሳሌ ያህል ስሙ የተጠቀሰ በእውን የሌለ መድን ኩባንያ ነው) ግንቦት 1 ቀን ለተሽከርካሪው የመድን ዋስትና ገዛ እንበል፡፡ የበጀት ዓመቱ ሰኔ 30 ሲዘጋ በበጀት ዓመቱ ውስጥ ኩባንያው የበላው ዓረቦን የሁለት ወር ማለትም 2/12ኛ እጁን ብቻ ነው፡፡ ሒሳቡ ሲዘጋ ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት የሚሸጋገረውና ኩባንያውም ገና ያልበላው    የአሥር ወር ያልተበላ  ዓረቦን  አለ፡፡  ይኸውም ደንበኛው ከከፈለው ዓረቦን ውስጥ 10/12ኛ እጁ ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት ሒሳብ የሚያልፍ ዕዳ ስለሆነ መጠባበቂያ ይያዝለታል፡፡ “Unearned Premium” የሚለውን የእንግሊዝኛ ሐረግ የመድን ሥራን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁ. 746/2004 አንቀጽ ሁለት ትርጓሜ ተራ ቁ. 36 (ሐ) “የውለታ ጊዜያቸው ላላለቀ የጠቅላላ መድን ሽፋኖች የተከፈለ ዓረቦን መጠባበቂያ…….” የሚለውን ረጅም ዓረፍተ ነገር የመድን ባለሙያ ያልሆነ ሰው በቀላሉ ሊረዳው አይችልም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ረቂቅ መጽሐፍ ለነገረ ቃሉ የተሰጠው ስያሜ “ያልተበላ ዓረቦን” ሲሆን፣ የውለታ ጊዜው ገና ላልተጠናቀቀውና ወደ ቀጣዩ ዓመት የተሸጋገረውን ዓረቦን ያመለክታል፡፡ 

ላልተበላ ዓረቦን መጠባበቂያ ለምን ያስፈልጋል? ከላይ በምሳሌ የተጠቀሰውን የተሸከርካሪ መድን ዋስትና የገዛው ሰው በጥቅምት ወራት (ከስድስት ወራት በኋላ ማለት ነው) ውሉን ቢሰርዝስ? የተሽከርካሪው የመድን ዋስትና ሽፋን ጸንቶ ለቆየባቸው ስድስት ወራት መድን ሰጪው የበላውን ዓረቦን (የዋስትና ሽፋና መዳኙ ለሰጠበት ጊዜ ያፈራው ዓረቦን ማለት ነው) ቀንሶ ያልበላውን የስድስት ወር ዓረቦን በውሉ ውስጥ በተጠቀሰው የአጭር ጊዜ ዓረቦን ስሌት ቀመር መሠረት ለተመዳኝ ደንበኛው የመመለስ የውል ግዴታ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ኩባንያው ራሱ በመድን ውሉ ውስጥ በተመለከተው የውል ሁኔታ መሠረት የዋስትና ውሉን ሊሰርዝም ይችላል፡፡ በእነዚህ አግባባዊ ምክንያቶች የመድን ኩባንያው ላልበላው ዓረቦን መጠባበቂይ ባይዝለት ኖሮ ተመላሹ ገንዘብ ከየት መጥቶ ይከፈል ነበር?  የልተባላ ዓረቦን መጠባበቂያ ሥነ አመክንዮን በዚህ መልኩ ልንገነዘበው እንችላለን፡፡

በሌላ በኩል ያልተበላ ዓረቦን መጠባበቂያ የሚያረጋግጠው ነገር መድን ሰጪው በቅድሚያ ዓረቦን የተቀበለና የዋስትና ሽፋን ከሰጣቸው ውሎች ውስጥ የከፊሎቹ ውሎች የዋስትና ዘመን ገና ያልተጠናቀቀ መሆኑን ነው፡፡ የውሎች ዋስትና ዘመን በተገባደደ ቁጥር መድን ሰጪው የሚበላው ዓረቦን እያደገ ያልተበላውም ዓረቦን እየቀነሰ ሄዶ የውሉ ዘመን ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ቀሪው ዜሮ ይሆናል፡፡ በውሉ ዘመን ውስጥ  ዋስትና ለተገባለት የጉዳት ሥጋት አደጋ ሲደርስ ካሳ ሊከፈል የሚችለውም ዓረቦኑ ሲበላ ነው፡፡ ከላይ እንደተብራራው አዲስ የመድን ሰጪ ኩባንያ ገና ሥራ ሲጀምር ያልተበላ ዓረቦን መጠባበቂያ አያያዝ ጫና ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራ ሲጀምር ለጻፋቸው የዋስትና ውሎች  የተቀበለውን ዓረቦን በሙሉ በመጠባበቂያ መልክ መያዝ አለበት፡፡ አዲሱ መድን ሰጪ በተቋቋመበት የመጀመርያው ዓመት ለውል አፈጻጸም ወጪዎች ለሰነዶች ኅትመት፣ ለልዩ ልዩ የቢሮ ዕቃዎችና ቆሳቁሶች ግዢ፣ ወዘተ በጥቅሉ የመቋቋሚያ ከፍተኛ ወጪ ጫና አለበት፡፡ ስለዚህ በመጀመርያው ዓመት ያልተበላ ዓረቦን መጠባበቂያ ሒሳብ  አያያዝ  አዲስ ለተቋቋመ መድን ሰጪ ፈተና ነው፡፡

የአዲስ መድን ኩባንያ የመቋቋሚያ ወጪ ከጠቅላላ ዓረቦን ገቢው ለምሳሌ 30 በመቶ እንደሚሆን ቢገመት፣ ገንዘቡ ሊገኝ የሚችለው በቀጥታ ከመድን ሰጪው ሰርፕለስ ነው፡፡ ሰርፕለስ (አንዳንድ ጊዜ “የመድን ገቢዎች ሰርፕለስ” በመባል ይታወቃል) ምንድነው? የመድን ሰጪ ካፒታል በሁለት ይከፈላል፡፡ ይኸውም በባለአክሲዮኖች “የተከፈለው  አክሲዮን”  አንዱ ሲሆን፣ የተከፈለው  አክሲዮንና የካበተው ትርፍ ድምር ሰርፕለስ በመባል ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በመጀመርያው ዓመት አንድ መድን ሰጪ በለስ ቀንቶት ብዛት ያላቸው የዋስትና ውሎችን መጻፍ ቢችል፣ ላልበላው ዓረቦን መጠባበቂያ እንዲይዝ የሚገደደው ከሰርፕለሱ ነው፡፡ በርካታ ውሎችንም መጻፍ ከቀጠለ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሰርፕለሱን “ማንጠፍጠፍ” (Exhaust)  ሊኖርበት ነው፡፡ ይህም እንዲሆን ስለማይፈለግ ብዙ ውሎችን መጻፍ የሚችል መድን ሰጪ የገበያ ዕድገቱን ጋብ ለማድረግ ይገደዳል፡፡ ስለዚህ የጠለፋ መድን ዋስትና መኖር ሕግ የሚጠይቀውን ያልተበላ ዓረቦን መጠባበቂያ “መደላድል” (Level) መጠን እንዲቀንስና የሰርፕለስ ሒሳብ መጠን ከፍ እንዲል ስለሚያደርግ የባለአክሲዮኖች ሰርፕለስ ከተጣራ “የተጻፈ ዓረቦን”  ጋር በንፅፅር ተሻሽሎ ለመድን ሰጪው ያለ አንዳች ችግር ዕድገቱን እንዲገፋበት ያስችለዋል፡፡

2.4.   ከመጠነ ሰፊ ውድመት (Catastrophic Loss) ይታደጋል፡፡ ከጠለፋ መድን ጥቅሞች አንዱ መድን ሰጪውን ከመጠነ ሰፊ ውድመት መታደግ ነው፡፡ በፋብሪካዎች ፍንዳታና የእሳት ቃጠሎ፣ በአውሮፕላኖች መከስከስ፣ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የጉዳት ክስተቶች፣ እንዲሁም ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሌሎች አደጋዎች ምክንያት በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመቶች ይደርሳሉ፡፡ የእነዚህ ዓይነቶቹ ከፍተኛ ውድመቶች ሲያጋጥሙ ለጉዳት ክስረቶቹ የሚከፈለው ካሳ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡  የጠለፋ መድን  (እስከ ጠለፋ መድን ዋስትናው መጠን ድረስ) ከፍተኛና መጠነ ሰፊ ውድመት ሲደርስ የመድን ሰጪዎችን፣ እንዲሁም ለሕይወትና ለንብረት የመድን ዋስትና ለገዛው ጠቅላላ ኅብረተሰብ አለኝታ የሚሆኑት በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

2.5.   ለበላይ አስተዳደርና ለቴክኒክ ባለሙያዎች ሥልጠና ወይም ምክር ይገኝበታል፡፡ የጠለፋ መድን ሰጪዎች በጉዳት ሥጋትና መድን፣ እንዲሁም ተዛማች ዕውቀቶች፣ ከህሎቶችና የአሠራር ዘይቤዎች የላቀ ሙያ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪዎች የበላይ አስተዳደሮችና የመድን ቴክኒክ ባለሙያዎች በጠለፋ መድን ሰጪዎች የምክር አገልግሎት ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ በቂ ልምድ በሌለውና ከፍተኛ መጠን ባላቸው የጉዳት ሥጋቶች መስክ ዋስትና መስጠት እንዲችል የሚያስፈልገውን የምክር አገልግሎትና ዕርዳታ የሚያገኘው ከጠለፋ መድን ሰጪው ነው፡፡ ከጠለፋ መድን ሰጪዎች የሚገኙት ምክሮችና የሥልጠና አገልግሎቶች ብዙውን ጊዜ የሚያተኩሩት በውል አጻጻፍ (Underwriting)፣ በአደጋ ጉዳት ቅንቀና (Loss Surveying)፣ በግብይት፣ በዓረቦን አተማመን (Rate Making)፣ አደጋን በመከላከል፣ በካሳ አስተዳደር (Claims Management)፣ በመጠባበቂያ ሒሳብ ስሌትና አያያዝ፣ በአስሊ ሙያተኞች አገልግሎት (Actuarial Service)፤ በመዋዕለ ንዋይ አጠቃቀም፣ አንዲሁም  በመሳሰሉት የአቅም ግንባታ መስኮች ላይ ነው፡፡

የጠለፋ መድን ገዥዎችና ሻጮች እነማን እንደሆኑ ግልጽ የሆነ ልየታ ለማድረግ ይቸግራል፡፡ ምክንያቱም ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ “የወጪ ጠለፋ መድን” (Out Ward Reinsurance) ገዥ ሲሆን፣ “የገቢ ጠለፋ መድን” (In Ward Reinsurance) ሻጭም ሊሆን ይችላል፡፡ የገቢ ጠለፋ መድን ለመቀበል የፋይናንስንና የሙያ ብቃት አቅም ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ይኼንን ሥራ ለመፍቀድ ጥንቃቄ የሚያደርጉት፡፡ ቅድመ ደርግ ከነበሩት አሥራ ሦስት የመድን ኩባንያዎች መካከል አፍሮ ኮንትኔንታል ይባል የነበረ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ቡልጋሪያ ከሚገኝ አንድ ጠለፋ መድን ሰጪ ጋር በተጓዳኝ “ሂው ፖል” (Hugh Paul) ለሚባል አውስታራሊያዊ ደርጅት የንፋስና ዝናብ የቀላቀለ አደጋ (Hurricane) የገቢ ጠለፋ መድን ተቀብሎ ነበር፡፡ በመሀሉ አፍሮ ኮንትኔንታል በቀድሞ ደርግ ተወርሶ የመንግሥት ንብረት ይሆናል፡፡ “ሂው ፖል” በማዕበሉ ይመታና ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት አፍሮ ኮንትኔንታል ኢንሹራንስ ኩባንያ በጠለፋ መድን ሰጪነቱ 700,000 ዶላር እንዲከፍል ይጠየቃል፡፡ በዚያን ጊዜ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩትን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያስተዳድር የነበረው ጊዜያዊ የኢንሹራንስ ቦርድ ስለነበረ ጉዳዩ ከባድ ፈተና ሆኖ  እንደነበር በወቅቱ የቦርዱ ጸሐፊ የነበረው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያስታውሳል፡፡  የአፍሮ ኮንትኔንታል ኢንሹራንስ ኩባንያ ያንን ያህል የገቢ ጠለፋ መድን ያውም በአውስትራሊያ ግዛት ለማዕበል የጉዳት ሥጋት ለመቀበል በቂ አቅም እንዳልነበረው ግልጽ ነበር፡፡

ከላይ እንደተገለጸው፣ በጠለፋ መድን ውል መድን ገቢው ቀጥተኛ ተሳትፎ የለውም፡፡ የጠለፋ መድን ሰጪው በሆነ ምክንያት ግዴታውን ማክበር ቢሳነው እንኳን፣ ኃላፊነቱ የሚወድቀው በቀጥታ ወይም በቀዳሚ መድን ሰጪው ላይ እንጂ መድን ገቢው በጠለፋ መድን ሰጪው ላይ ቀጥተኛ የመብት ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም፡፡ የጠለፋ መድን ውል ይኑር አይኑር አብዛኛው መድን ገቢም አያውቅም፡፡ አንድ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ ከአስተማማኝና ግዴታቸውን በሚገባ ሊያከብሩ ከሚችሉ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር እንዲዋዋል ማድረግ የመድን ተቆጣጣሪ አካላት ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡  የብዙ ታዳጊ አገሮች ተቆጣጣሪ አካላት ባሳዩት ቸልተኝነት አስተማማኝነት ከሌላቸው የጠለፋ መድን ሰጪዎች  ዋስትናዎች ተገዝተው ጠለፋ መድን ሰጪዎቹ  ግዴታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው፣ በመድን ኢንዱስትሪዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡

3. የጠለፋ መድን ዓይነቶች በጥቅሉ የጠለፋ መድን በሁለት ዓበይት ክፍሎች ይመደባል፡፡ አንደኛው “ፋኩልቴቲቭ ጠለፋ መድን” (Faculitative Reinsurance) ሲሆን፣ ሁለተኛው “ትሪቲ ጠለፋ መድን”  ነው፡፡ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪ በፋኩልቴቲቭ ጠለፋ መድን የሚጠቀመው አቅሙን በተለየ ሁኔታ ለማጎልበት ሲፈልግ ነው፡፡ ከሪቴንሽን ወሰን በላይ የሆነ ዋስትና ጥያቄን ለማስተናገድ ወይም በባሕሪያቸው ለየት ለሚሉና መጠነ ሰፊ ውድመት ሊያደርሱ ለሚችሉት እንዲሁም የዋስትና ገንዘብ መጠናቸውም ከፍተኛ ለሆኑ የጉዳት ሥጋቶች ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪዎች ፋክሉቴቲቭ የጠለፋ መድን ውል በመግዛት ይጠቀማሉ፡፡ 

“ትሪቲ የጠለፋ መድን ” (Treaty Reinsurance) ወደ አማርኛ ሲመለስ “የጠለፋ መድን ስምምነት ወይም ውል” ማለት ነው፡፡ ቃሉ እንደሚገልጸው፣ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ መድን ሰጪና የጠለፋ መድን ሰጪ ተደራድረው በስምምነት ለአንድ ዓመት ጊዜ  የሚያቋቁሙት ሁለተኛው ዓይነት የጠለፋ መድን ዓይነት ነው፡፡ በትሪቲ ጠለፋ መድን ውል መሠረት ቀዳሚ መድን ሰጪ ለደንበኞቹ ከሚሰጣቸው የመድን ዋስትና ውሎች በስምምነቱ መሠረት የራሱን ድርሻ እያስቀረ፣ የጠለፋ መድን ሰጪውን ድርሻ  ማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡ በአንፃሩም የጠለፋ መድን ሰጪውም በበኩሉ ከቀጥታ ወይም ቀዳሚው መድን ሰጪ በስምምነቱ መሠረት የሚተላለፍለትን የጠለፋ መድን ድርሻ መቀበል ግዴታው ነው፡፡ ስለዚህ ቀዳሚ መድን ሰጪ የትሪቲው ጠለፋ መድን  ማዕቀፍ በሚፈቅድለት መብትና ግዴታ መሠረት ለመድን ፈላጊዎች የሚሸጣቸውን  ውሎች  በፍጥነትና በቀጥታ የስምምነቱ ወገን ከሆነው የጠለፋ መድን ሰጪ ማግኘት ይቻለዋል ማለት ነው፡፡ የፋኩሊቴቲቭ ጠለፋ መድን ውል ግን እንደ ትሪቲ ጠለፋ መድን በፍጥነትና በቀጥታ የሚገኝ ስላልሆነ፣ እያንዳንዱ የፋክሉቴቲቭ ጠለፋ መድን ውል በተናጠል ድርድር ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ቀጥታ ወይም ቀዳሚ  መድን ሰጪ ብዙ  ውጣ ውረድ እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው [BA,  LLB (GD), Graduate Dipl. in Development Administration (India), ACII, Chartered Insurer (UK), ACS (USA)] ለረጅም ዓመታት በመድን ሥራ፣ በሥልጠና፣ በመድን ምርምርና ሥነ ጽሑፍ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles