Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሙያ ማኅበራቱ ሥጋትና ቃና ቲቪ

የሙያ ማኅበራቱ ሥጋትና ቃና ቲቪ

ቀን:

በቅርቡ መደበኛ ስርጭታቸውን ከሚጀምሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱ ቃና ቲቪ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ የመጀመርያ ዝግጅቱ ይተላለፋል፡፡ ስለስርጭቱ መጀመር በሚገልጹ ማስታወቂያዎች ጣቢያው 70 በመቶ ሽፋን የሚሰጠው ወደ አማርኛ የተተረጐሙ የውጪ አገር ፊልሞችን ጨምሮ ለውጪ ዝግጅቶች እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ስርጭቱ ሊጀመር ቀናት ሲቀሩት ግን የኪነ ጥበቡ ዘርፍ ማኅበራት፣ ጣቢያው 70 በመቶ ሽፋኑን ለውጪ ዝግጅቶች መስጠቱን እንደሚቃወሙ አሳውቀዋል፡፡

መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲውሰሮች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፣ አላቲኖስ ፊልም ሠሪዎች ማኅበርና የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር የጣቢያው አካሄድ በባለሙያዎች ሙያዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡

ማኅበራቱ ከተወያዩ በኋላ የደረሱበትን አቋም ያሳወቀው የቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ቢያንም ወርቁ፣ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አገር ውስጥ የተሠሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በጣቢያው በሚተላለፉ የውጪ ፊልሞች እንዳይዋጡ ማኅበራቱ እንደሚሠጉ ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በጣቢያው የሚተላለፉ የውጪ ፊልሞችና ዝግጅቶች ኢትዮጵያውያን ፊልም ሠሪዎችን፣ ሙዚቀኞች፣ ደራስያንና የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችን ከገበያ ውጪ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

በጣቢያው የሚተላለፉ ፊልሞች በአማርኛ ተተርጉመው ስለሚቀርቡና በምስልና ድምፅ ጥራታቸው የአብዛኛውን ኅብረተሰብ ቀልብ በቀላሉ ሊገዙ ስለሚችሉ ለአገርኛ የጥበብ ሥራዎች የሚሰጠው ቦታ እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገልጻል፡፡ ‹‹የጣቢያው ዝግጅቶች ፕሮዲውሰሮች፣ አዘጋጆች፣ ደራስያን፣ ተዋንያን፣ የፊልም ሙዚቃ ፈጣሪዎች፣ አቀናባሪዎች፣ የቀረፃ ቦታ ነዳፊ ሠዓሊያን፣ የገፀ ቅብ ባለሙያዎችና የሌሎችም የሥራ ዕድል ላይ ጫና ያሳድራሉ፤›› ሲል ያብራራል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ተመልካቾች ወደ ትርጉም ሥራዎቹ ፊታቸውን ሲያዞሩ ባለሙያዎች ከሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ባሻገር፣ በማኅበረሰቡ ባህል ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡

አገር ውስጥ የሚዘጋጁ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችም ይሁን ፊልሞች የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ሲሆኑ፣ የውጪዎቹ በተቃራኒው የሌላ አገር ማኅበረሰብን ባህል ያሳያሉ፡፡ ይህም በማኅበረሰቡ በተለይም በታዳጊዎች ማንነት ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ቢንያም ይናገራል፡፡ አገርኛ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የማኅበረሰቡን አንገብጋቢ ጉዳዮች ከመዳሰሳቸው ባሻገር ባለሙያዎች ለአንዳንድ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሔ ለማምጣት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚያነሳሱም ይገልጻል፡፡ ‹‹ዘርፉ ወደፊት በርካታ አመርቂ ውጤት የሚጠበቅበትና ለዜጎች ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ ይህ የበርካታ ባህሎችና ታሪኮች መገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ የሚችለው የሲኒማ ጥበብ ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ የቃና ቲቪ የይዘት ምጣኔ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እንዲሁም የፊልም ጥበብን፣ ባህልና ኢኮኖሚን ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያላማከለ ነው፤›› ሲል ያስረዳል፡፡

ቢንያም እንደሚለው፣ የጣቢያው አሠራር ፍትሐዊ ያልሆነ የገበያ ውድድርና ጥቂቶች ብቻ የሚጠቀሙበት የንግድ አሠራር ሊፈጥር ይችላል፡፡ አካሄዱ በነባርና አዳዲስ ጣቢያዎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም ማኅበራቱ ይገምታሉ፡፡ የጣቢያው ኃላፊዎች ሥጋታቸውን ከግምት በማስገባት አካሄዱን አስተካክለው ለኢትዮጵያዊ ኪነ ጥበብ ሥራዎች ሰፊ ሽፋን እንዲሰጡ ከማኅበራቱም ጋር እንዲወያዩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ለማኅበራቱ ኃላፊዎች ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር፡፡ ከነዚህም አንዱ ‹‹አሁን በአገሪቱ የሚሠሩ ፊልሞችም ይሁን ድራማዎች ምን ያህል ደረጃቸውን የጠበቁና የኅብረተሰቡን ፍላጎት ያማከሉ ናቸው?›› የሚለው ነው፡፡ የውጪ ፊልሞች የኢትዮጵያውያንን ባህል ይበርዛሉ ቢባልም አገር ውስጥ የሚሠሩ ፊልሞች ምን ያህል የማኅበረሰቡን እሴት የሚያንፀባርቁና የኅብረተሰቡ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ናቸው የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሮዲውሰሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ቢንያም ዓለማየሁ እንደሚለው፣ በፊልሙ ዘርፍ ችግሮች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ስለሆነ ለአገራዊ የጥበብ ሥራዎች ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ‹‹የትምህርት ቤቶች አለመኖር፣ የመሣሪያ እጥረትና ሌሎችም ያሉብንን ችግሮች ለመቅረፍ እየተጣጣርን ባለንበት ወቅት ሌላ ችግር ሊጨመርብን አይገባም፡፡ የጣቢያው አሠራር እኛን ስለማያካትት የዘርፉ ባለሙያዎችን ይጎዳል፤›› ይላል፡፡   

ፊልሞችን በትርጉም ማቅረብ (ደቢንግ) ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አለመሆኑና ጣቢያው ስርጭት ጀምሮ ዝግጅቶቹ ሳይታዩና የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቢኖር እንኳን ጥናት ሳይሠራ አስቀድሞ ቅሬታ ማቅረብ ተገቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ቀድሞ ገበያ ላይ ይቀርቡ የነበሩ የትርጉም ፊልሞች ስርጭት ውስን እንደሆነና የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ሰፊ ስለሆነ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የማኅበራቱ ተወካዮች ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም የቃና ቲቪ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ቢንያም ተናግሯል፡፡

የማኅበራቱ ተወካዮች የአገር ውስጥ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለሕዝብ ማድረስ አገራዊ ኃላፊነት እንደሆነ በማስረገጥ 70 በመቶ የውጪ አገር ዝግጅቶች የሆነው ምጣኔ እንዲስተካከል አሳስበዋል፡፡ ሆኖም ስርጭቱ ሊጀመር ቀናት ሲቀረው ቅሬታ ማቅረባቸው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ሚና እንደሚኖረው ተጠይቀዋል፡፡ ተወካዮቹም ሥጋታቸውን ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ ላይ እንዳተኮሩና እርስ በርስ ተወያይተው በጨረሱበት ጊዜ እንዳሳወቁ ተናግረዋል፡፡

ጣቢያው በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች የጣቢያው ኃላፊዎች ሪፖርተርን ጨምሮ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሳውቀዋል፡፡ ቀስ በቀስ በኢትዮጵያ ፊልም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት እንደሚጣጣሩም ተናግረዋል፡፡ የአላቲኖስ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር አባል ሰለሞን ሃፍቱ በበኩሉ፣ በጣቢያው የሚተላለፉት ፊልሞችና ዝግጅቶች የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን እንዳያስረሱ እንደሚሠጋ ገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ፣ የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ አካሎች ሊያደረጉላቸው የሚገባውን ድጋፍ ባላገኙበት ሁኔታ ተጨማሪ ችግር ሊደቀንባቸው አይገባም ይላሉ፡፡ በሙዚቃው ኮፒ ራይትን ለመታገል ያለፉትን እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠቅሳሉ፡፡ አሁንም ግን በፍላሽና ሚሞሪ የሚቸበቸበው ሙዚቃ የባለሙያዎች ራስ ምታት ነው፡፡ የአገሪቱ የባህል ፖሊሲ ለአገርኛ የጥበብ ሥራዎች መደረግ ስላለበት ድጋፍ ቢያትትም፣ ተገቢውን ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በፊልሙ ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ አካሎች አለመበረታታቸውና መሣሪያዎችን ከውጪ ለማስገባት ያለው ውጣ ውረድ እንዳለ ሆኖ  ጣቢያው የበለጠ ዘርፉ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይናገራሉ፡፡

የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ የተለየ ሐሳብ አለው፡፡ የማኅበራቱ ጥያቄ ተገቢ እንዳልሆነና ጣቢያው የሚያሳልፋቸው ፊልሞች ለአገሪቱ ባለሙያዎች ተምሳሌት መሆን እንደሚችሉ ያምናል፡፡ ጣቢያው የመዝናኛ አማራጭ ከመስጠቱ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ፊልም በታሪክ፣ በትወናና በአሠራር ረገድ የሚወሰዱ ትምህርቶች አንደሚኖሩ ይገልጻል፡፡ ‹‹ጥያቄው መሆን ያለበት ፊልሙ ተወዳዳሪ እየመጣበት ስለሆነ የተሻለ ለማድረግ በምን መንገድ መሄድ አለብን? የሚለው ነው፤ በጣቢያው መደናገጣችን የሚያሳየው ፊልሙ ያለምንም አቅጣጫ እየተጓዘ እንደነበር ነው፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

ፊልሞቹ የጥራት ልኬትን እንደሚያሳዩም ያምናል፡፡ አገሪቱ ላይ ላሉት ባለሙያዎችና ፊልም የማምረት አቅም አሁን ያሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቂ እንደሆኑም ያስረዳል፡፡ ሌላው የማኅበረሰቡን ባህል የመሸርሸር  ጉዳይ ሲሆን፣ ባለሙያው እንደሚለው፣ አብዛኛው ተመልካች ቃና ከመምጣቱ በፊትም የውጪ ፊልሞች ተመልካች ነበር፡፡ ፊልሞቹን በአማርኛ ተርጉሞ ማቅረብ በተወሰነ መጠን ችግሩን የሚቀንስ እንጂ የሚያባብስ እንዳልሆነም ይናገራል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርነው የቃና ቲቪ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ተክለሃይማኖት፣ በጣቢያው የሚተላለፉትን ፊልሞች የሚመርጡት በይዘታቸውና በጥራት ደረጃቸው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቢሚዲያ ፕሮዳክሽን የተባለው ድርጅት ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ይመጥናሉ ያላቸውን ፊልሞች ወደ አማርኛ ከመለሱ በኋላ ለቃና ቲቪ ይሸጣል፡፡ እነዚህ ፊልሞች የአገሪቱን ባህል ባማከለ መልኩ ወደ አማርኛ እንደተመለሱና በፊልሞቹ ላይ በድምፃቸው፣ በዝግጅት፣ በአርትኦትና ሌሎችም ሥራዎች የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ በሌሎች አገሮችም ፊልሞችን ተርጉሞ ማቅረብ የተለመደ እንደሆነና የአንድ አገር ፊልም ዘርፍ ባለሙያዎች ከተተረጐሙት ፊልሞች ትምህርት የሚቀስሙበት አሠራር እንዳለ ያክላል፡፡

አቶ ኃይሉ እንደሚለው፣ ቃና ቲቪ በሠራው ጥናት መሠረት ሳተላይት ቴሌቪዥን ከሚከታተሉ ሰዎች 50 በመቶው የውጪ አገር ተከታታይ ፊልሞችን ይመለከታሉ፡፡ ለነዚህ ሰዎች በአገሪቱ ቋንቋ የሚቀርቡት ፊልሞች ይዘታቸው የማኅበረሰቡን አኗኗር ያማከለና ዓለም አቀፋዊ ስምምነት የሚፈጥሩ ጉዳዮች (ዩኒቨርሳል ቲም) የሚዳሰሱ መሆኑንም ይገልጻል፡፡ ‹‹የምናቀርባቸው ፊልሞች ባህልና እሴትን እንደማይጋፉ አይተን የመረጥናቸው ናቸው፡፡ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በሰጠናቸው ሥልጠና ለዘርፉ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤›› ይላል፡፡ ቢሚዲያ የአገር ውስጥ ፕሮዳክሽኖችንም እንደሚያካትትም አቶ ኃይሉ ገልጾ፣ ስለጉዳዩ ከማኅበራቱ የደረሳቸው ጥያቄ አለመኖሩን  ተናግሯል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...