Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያልተፈታው የውኃ ችግር

ያልተፈታው የውኃ ችግር

ቀን:

ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው 03 ኮንዶሚኒየም መኖር ከጀመረች ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኤልኒኖ ክስተት ባስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዝናብ እጥረት ወደ ግድቦች መግባት የነበረበት ውኃ መጠን በመቀነሱ ከለገዳዲና ድሬ ግድቦች ውኃ ያገኙ የነበሩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ካለፈው ወር ማብቂያ ጀምሮ ውኃ በፈረቃ እንዲያገኙ መደረጉ በአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ተገልጿል፡፡ ፈረቃ ግን  የእነሱን አካባቢ አይመለከትም፡፡ ምክንያቱም ቀድሞም ውኃ የሚያገኙት በፈረቃ ነበርና፡፡ ቢሆንም ግን የውኃ ችግራቸው ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ጠየቅናት ወ/ሪት መስከረም በለጠን በኮንዶሚኒየሙ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ውኃ በአካባቢው ከፍተኛ ችግር መሆኑን ትናገራለች፡፡

እንደ እሷ ገለጻ ሁሌም ለሦስት ወይም ለአራት ቀን ውኃ ይጠፋል፡፡ በተባሉት ቀናት የውኃ መጥፋት የተለመደ ነው፡፡ ውኃ አለ በሚባልበት ቀንም ውኃ የሚኖረው ለሁለት ለሦስት ሰዓታት እንጂ ቀኑን ሙሉ አይደለም፡፡ ‹‹ጠዋት ሰው ከቤት ከወጣ በኋላ ከአራት እስከ ስድስት ወይም ሌሊት ከስምንት እስከ ዘጠኝ ይመጣል፡፡ ይህ በተግባር ሙሉ በሙሉ ውኃ የለም የሚያስብል ነው፤›› ስትል በመደምደም ይህ ውኃ መቅዳት የሰዎች በመደበኛ ሥራ እስኪመስል ድረስ ተፅዕኖ ማሳደሩን በምሬት ትገልጻለች፡፡

እንኳንስ ከፍተኛ የውኃ ችግር በሚኖርባቸው ጊዜአት የውኃ ሁኔታ ደህና በሆነበት ጊዜ እንኳን የኮንዶሚኒየሞች የፍሳሽ ቱቦ የተለያየ ችግር ስላለበት መጥፎ ሽታ ከባድ ፈተና እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ በትክክል ችግሩን ለማወቅ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ሽታው ብዙዎች ላይ የተለያዩ የመተንፈሻ አካል የጤና ችግር ማስከተሉን ማስተዋልዋ ግን በእርግጠኝነት ትናገራለች፡፡ ‹‹የውኃ ታንከር ወይም ትልቅ በርሜል አስቀምጣለሁ እንዳይባል ቤቱ ጠባብ ነው፤›› በማለት በኮንዶሚኒየም ያለው የአኗኗር ዘዬ ከፍተኛ የውኃ መጠን የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ መሬት ላይ ያለው እውነታ ከባድ የውኃ እጥረት ይህን የማይፈቅድ መሆኑ ሁሌም ግራ የሚያጋባ ነው ትላለች፡፡ እሷ ብቻም ሳትሆን ብዙዎች በዚህ ዓይነቱ የአኗኗር ዘዬ የውኃ አለመኖር የተለያዩ የጤና ቀውሶችን እንደሚያስከትል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ወ/ሪት መስከረም አለ የምትለው የውኃ ችግር በሌሎችም ኮንዶሚኒየሞች ያለ ችግር ነው፡፡ እንደ ልብስ ማጠብ ወይም ቤት ፅዳት ያሉ ተግባራት ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ የሆኑ እንደ ምግብ ዝግጅትና ገላ መታጠብ ያሉ ነገሮች እንኳ አስቸጋሪ እስኪሆኑ ድረስ ተፅዕኖው በርትቷል፡፡

ዘነበወርቅ አካባቢ ከሰባት ዓመታት በላይ የኖረችውና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ትዕግሥት ምትኩም ባለፉት ዓመታት ሁሉ ውኃ ለሦስት ለአራት ቀን መጥፋት በአካባቢው እንግዳ ነገር እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡ እነሱ የሚኖሩበት አካባቢ (መሐንዲስ ሠፈር) የማኅበር ቤቶች የፍሳሽ ቱቦዎች የተያያዙ በመሆናቸው የውኃ አለመኖር ከባድ የሽታ ችግር እያስከተለ ነው፡፡

ሁሉም ቤት ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የውኃ ታንከር ቢኖርም ውኃ ሲመጣም ኃይል ስለማይኖረው ታንከሩም መፍትሔ መሆን አልቻለም፡፡ ‹‹እንደ ልብስ ማጠብ ወይም በግ ማረድ የሚሠራው ውኃ የሚመጣበት ቀን ተጠብቆ ነው፡፡ ይመጣል የሚባልበት ቀንም የሚመጣው ለሆነች ሰዓት ነው፤›› በማለት በአካባቢው በፒክ አፕ መኪና ከሌላ ቦታ ውኃ ማስቀዳት እንደ መፍትሔ እንደሚታይ ትናገራለች፡፡

ውኃ እስከ 15 ቀን ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ አለ፡፡ የውኃ ችግራቸው የከፋና ለዓመታት የዘለቀ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ተፈራርመው አቤቱታቸውን ለውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አሰምተዋል፡፡ አንዳንዶቹ አቤቱታዎች እንዲሁ ጆሮ ዳባ ልበስ ሲባሉ ጊዜያዊ መፍትሔ ያስገኙም አሉ፡፡

‹‹ከመመላለሳችን የተነሳ ብዙ ሰው የኃላፊዎቹ ስልክ ሁሉ አለው፤›› የምትለው ወ/ሮ ትዕግሥት ችግራቸውን ለመፍታት ብዙ ቢንቀሳቀሱም ዛሬም እዚያው ውስጥ መሆናቸውን ትገልጻለች፡፡

የውኃ ችግር ውኃ ለመቅዳት ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ሰዎች ሌሊቱን የቀን ያህል እንዲመስል ተፅዕኖ ያሳደረባቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎችም አሉ፡፡ ጣፎ (በተለምዶ ሚሽንና መስጊድ በሚባሉት) እንዲሁም  ካራ ከቀናት በአንዱ ውኃ ሲመጣ ወጣት፣ ሴት፣ ወንድና አዛውንት ሳይባል ሁሉም ቢጫ ጀሪካኑን ይዞ በሌሊት ወዲህ ወዲያ ይላል፡፡ ጣፎ ውኃ ሲመጣ የካራ ሰዎች በሌሊት ወደዚያ ይሄዳሉ፡፡ በተመሳሳይ ጣፎ ጠፍቶ ካራ ሲመጣ የጣፎ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ካራ ይሄዳሉ፡፡

ውኃ ለሳምንታት ብቻም ሳይሆን ለወራት በሚጠፋባቸው በእነዚህ አካባቢዎች የተገለጸው ዓይነት የሌሊት እንቅስቃሴ የተለመደ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ጣፎ አካባቢ የሚገኘው የአዳማ ቁጥር አንድ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችም እነ ወ/ሪት መስከረም በሚኖሩበት ኮንዶሚኒየም ያለው ችግር ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ወደ ኮንዶሚኒየሙ በሚወስደው የኮብል ስቶን መንገድ የፈነዳ አንድ የውኃ መስመርን ብዙዎች እንደ ቧንቧ በመመልከት እየተመላለሱ ውኃ እንደሚቀዱ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በቦታው ተገኝተን አስተውለናል፡፡

በአካባቢው የሚገኘው ወንዝም ሌላው የነዋሪው ዕፎይታ ነው፡፡ ለብዙዎች ሩቅ በመሆኑ የወንዙን ውኃ በአህያ እየጫኑ ከነዋሪው ደጃፍ የሚያደርሱት ጆቢርና ሁሴን የተባሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ አራት አህዮች ሲኖሯቸው በጀሪካን አራት ብር ያስከፍላሉ፡፡ በቀን ከአሥር ጊዜ በላይ ወደ ወንዙ እንደሚመላለሱ ይናገራሉ፡፡

እንደ መገናኛ፣ ፒያሳ ወይም አራት ኪሎ ያሉ አካባቢዎች የውኃ ችግር ያለባቸው ቢሆንም ቢሯቸው በእነዚህ አካባቢዎች የሆነ መኪና ያላቸው ጠዋት ሁለት ሦስት ጀሪካን ይዘው በመውጣት ማታ ውኃ ጭነው የሚገቡም አጋጥመውናል፡፡

ከፍተኛ አቅም ያለው ታንከር ያላቸው ሆስፒታሎችና ሌሎች አገልግሎት ተቋማትም ከችግሩ ነፃ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ 25 ሺሕ ሊትር የሚይዙ ሰባት የውኃ ታንከሮች በአዲሱ ሕንፃ፣ አሥር ሺሕ የሚይዙ ሁለት እንዲሁም አምስት ሺሕ የሚይዙ አራት ታንከሮች ባሉበት የካቲት 12 ሆስፒታልም ውኃ ይጠፋል፡፡ የውኃ አለመኖር በተለያየ መልኩ በአገልግሎቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በሌሎች ሆስፒታሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የውኃ እጥረት ችግር እያስከተለ ነው፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውኃ ላይ በሠሯቸው ጥናቶች ላይ የተሳተፉትና የውኃ ሀብት አጥኚ የሆኑት አቶ ተስፋዬ (ፒኤችዲ በመሥራት ላይ ያሉ ዓለም ሰገድ) የአዲስ አበባ የውኃ ችግር የውኃ አቅም ሳይሆን ውኃውን የማከፋፈል አቅም ውስንነት ችግር ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የዕቅዶች የተለያዩ ሁኔታዎችን (ለምሳሌ የኮንዶሚኒየም የአኗኗር ዘዬ) ያላገናዘቡ መሆን እንዲሁም፣ እንደ ኢንዱስትሪ፣ ማኅበራዊና ሌሎችንም ዘርፎችን ተሳትፎ ያላካተቱ (Cross Sectoral) አለመሆን የችግሩ ምንጭ ነውም ይላሉ፡፡

‹‹እሳት የማጥፋት ሥራ ነው የሚታየው፡፡ የተቀናጀ አካሄድ የለም፤›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ በሌላ በኩል የከተማዋ የውኃ አጠቃቀምን የሚመራ አቅጣጫ ማስቀመጥም እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የዝናብ ውኃም እንዴት አገልግሎት ላይ መዋል አለበት? የሚለው በአቅጣጫ መመራት አለበት እንደ እሳቸው ገለጻ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ቢኖሩ ውኃ ማቆር ወጥነት ባለው መንገድ ይተገበራል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ኃላፊነት የጎደለው የውኃ አጠቃቀም ለምሳሌ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበት የታከመን ውኃ እኩል ለመጠጥና ለመኪና ማጠቢያ የማዋል ነገር መስመር ሊይዝ ይችላል፡፡ ‹‹አሁን ወጥነት የጎደለው ነገር ብዙ ነው፡፡ የቅንጅትና የኮሙዩኒኬሸንም ችግር አለ፡፡ የውኃውን ዘርፍ እያንቀሳቀስነው ያለነው ባለን ልምድና ዕውቀት ላይ እየጨመርን አይደለም፤›› ይላሉ አቶ ተስፋዬ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው የከተማዋን የውኃ አቅርቦትና ስርጭት የማሻሻል ሥራን በተመለከተ በአቃቂ ዌልፊልድ በቀን 70 ሺሕ ሜትር ኩብ በላይ ውኃ ማምረት የሚያስችሉ 19 ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮና ተያያዥ ሥራዎች በመሠራታቸው የተመረተውን 80 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃና እንዲሁም የለገዳዲ ማጣሪያ ጣቢያን በማስፋፋትና የድሬ ግድብን በማሻሻል 30 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ ከአራት ወር በፊት ወደ ሥርጭት እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሁለተኛው የአቃቂ ዌልፊልድ ፕሮጀክት 70 ሺሕ ሜትር ኩብ ማምረት የሚያስችል የ24 ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮና ተያያዥ ሥራዎች ክትትል ተደርጎባቸው ተፈጻሚ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ሥራ ሳይጀመር የቆዩ ባፈው ሳምንት በይፋ ሥራ ጀምረዋል፡፡ 40 ሺሕ ሜትር ኩብ የለገዳዲ ውኃ የተጠናቀቀ ሲሆን እስከ ፕሮጀክቶቹ ማብቂያ ውኃ ለነዋሪው እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ ውኃ ማምረትና ማሰራጨትን በተመለከተ በ2007 ዓ.ም. ከ260 ሺሕ ሜትር ኩብ በላይ ውኃ በአዲስ መልክ ወደ ሥርጭት የገባ ሲሆን፣ የከተማዋ የውኃ አቅርቦትና ስርጭት ላይ መሠረታዊ የሚባል ለውጥ አምጥቷል፡፡ ከውኃ አቅርቦትና ስርጭት ጋር የተያያዙ የውኃ መቆራረጥና የአገልግሎት መስተጓጎል ችግርን ለመፍታትም ተቋሙ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

 እ.ኤ.አ. 2015 ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጋራ ያካሄዱት ግምገማ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን የሚመለከተውን የሚሊኒየሙ የልማት ግብ  MDG 7C አሳክታለች፡፡ ይህ ደግሞ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 57 በመቶ የሚሆነው የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲኖረው አስችሏል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአዲስ አበባ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሽፋን 92 በመቶ ደርሷል፡፡

በመረጃ ደረጃ ያለው ነገር ይህ ቢሆንም እውነታው ግን ዛሬም የውኃ ችግር ዕለት በዕለት እየከፋ መሆኑን ብዙዎች በምሬት ይገልጻሉ፡፡

በተያዘው ዓመት ያለው ፍላጎት ቢጨምርም የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም እንደሚሉት፣ በ2007 ዓ.ም. የውኃ ፍላጎት በቀን 670,000 ሜትር ኩብ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ አቅርቦቱን ከ600,000 ሜትር ኩብ በላይ ያደረሱ ቢሆንም፣ የ70,000 ሜትር ኩብ ክፍተት አለ፡፡ ነገር ግን ከነበረበት ሲታይ ለውጡ ከፍተኛ ነው፡፡

የከተማዋ የመጠጥ ውኃ ሽፋን 92 በመቶ ቢደርስም፣ ሥርጭት ላይ ችግር መኖሩን ያምናሉ አቶ አወቀ፡፡ ለዚህ የሚያስቀምጡት ምክንያት ደግሞ የከተማዋ የውኃ መስመሮች ያረጁ መሆን፣ ከተመረተው ውኃ 37 በመቶ የሚሆነው በብክነት (በሊኬጅ) ተጠቃሚውን መድረስ አይችልም፡፡ የመስመሮችም በተለያየ ምክንያት ተሰብረው በዚህ ምክንያት የተወሰኑ አካባቢዎች ውኃ ሳይደርሳቸው እንደሚቀር፣ ይህ ግን እውነተኛ የውኃ እጥረት አለመሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ተጠቃሚው አቤት ካላለ በስተቀር የሚያውቁበት መንገድም የለም፡፡ ይህ ደግሞ ያለው መረጃ ክፍተት ነው፡፡

በሥርጭት ችግር ምክንያት ምን ያህል ሰዎች ውኃ እየደረሳቸው እንዳልሆነ በትክክል ለማወቅ ጥናት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍ ግን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አቶ አወቀ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የምርቱን ያህል ውኃ ስላልተዳረሰ ትኩረታችንን ሥርጭት ላይ አድርገን እየሠራን ነው›› የሚሉት አቶ አወቀ፣ መስመሮችን ለመቀየር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሔደውን የውኃ መጠን ለማወቅ ትልልቅ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፣ በዚህ ጊዜ ባይባልም በየመስመሩ የሚያልፍ ውኃ መጠንን የሚያሳይ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የትኛው አካባቢ ላይ ውኃ እንደሌለ ወይም መስመር እንደተሰበረ ለማወቅ ያስችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአዲስ አበባ ውኃ ችግር የሚፈታ አይሆንም፡፡

የዕቅዶች ምሉዕ አለመሆንና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያገናዘቡ አለመሆን ለከተማዋ የውኃ ችግር ምክንያት ነው በሚለው ሐሳብ አቶ አወቀ አይስማሙም፡፡ ስትራቴጂዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የተሠሩ ጥናቶችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማትም በተቋሙ ዕቅድና ስትራቴጂ አምነው ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመግለጽ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ከውኃ መስመሮች ችግርና ሥርጭት ጋር በተያያዘ ያለውን ነገር አይቶ ዘርፉ በዕቅድ የማይመራ የሚመስለው ሊኖር ይችላል›› ይላሉ፡፡ ቢሆንም ግን ዕቅዶችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ረገድ ክፍተት መኖሩን ያምናሉ፡፡

ያልተጠበቁ እንደ ቀላል ባቡር መስመር ግንባታ ያሉ ነገሮች የውኃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች የለም የሚሉት የዕቅድ ምሉዕነትና አሳታፊነት ችግር ውጤት ነው፡፡ የሚመለከታቸው ተቋማት ቅንጅት በሚፈለገው ደረጃ እንደሌለ፤ ችግሩ ከባለሥልጣኑ ከሌሎቹም ሊሆን እንደሚችል ግን አቶ አወቀ ይገልጻሉ፡፡

በከተማዋ ለመንገድ ሥራ ቁፋሮ ሲካሄድ የውኃ መስመር መሰበር የትም ቦታ የሚስተዋል ነው፡፡ ለመንገድ ብቻም ሳይሆን ኢትዮ ቴሌኮምም መንገድ ሲቆፍር በተመሳሳይ የውኃ መስመር ይሰበራል፡፡ እነዚህ ተግባራት የሚመለከታቸው ተቋማት በተቀናጀ መንገድ ይሠሩ ዘንድ ለመንገዶች ባለሥልጣን የማስተባበር ኃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም ዛሬም የአንዱ ግንባታ የሌላውን እያፈረሰ ይገኛል፡፡

ባለሥልጣኑ ሁሌም እሳት የማጥፋት ሥራ ስለሚሠራ የከተማዋን የውኃ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ አልቻለም በሚለው አስተያየትም አቶ አወቀ አይስማሙም፡፡ ምርቱን ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ማድረስ የተቻለው በዘላቂ ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አሁንም በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ለመሥራት የታሰቡ ሥራዎች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣትን ያለሙ ናቸው ይላሉ፡፡   

ዘላቂ መፍትሔ ያመጣሉ የሚሏቸው ፕሮጀክቶች የመስመሮች አሮጌነትን፣ የተራራማ ቦታዎች ውኃ በመደበኛ ሁኔታ በፈረቃ ማግኘትን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በቢሊዮን በሚቆጠር ብር የሚገመቱ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ ከውጭ አገር ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንደገለጹት፣ እንጦጦ ተራራ ላይ በሦስት ቢሊዮን ብር ለመገንባት የታሰበው (ከሁለት እስክ ሦስት ዓመት ይፈጃል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል) ግድብ የተራራማ ቦታዎችን የውኃ ችግር ይፈታል፡፡

የኤልኒኖ ክስተት ባስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጠረ የዝናብ እጥረት ወደ ለገዳዲና ድሬ ግድቦች መግባት የነበረበት የውኃ መጠን ባለመግባቱ ከእነዚህ ግድቦች ውኃ ያገኙ የነበሩ ቦታዎች ከየካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በፈረቃ እንዲያገኙ መደረጉም ይታወቃል፡፡

(ዮናስ ዓብይ ለዚህ ጽሑፍ አስተዋጽኦ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...