Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትአልጠራ ያለው የእግር ኳሱ ጉሽ

  አልጠራ ያለው የእግር ኳሱ ጉሽ

  ቀን:

  – በአልጄሪያው ጨዋታ ፌዴሬሽኑ ተጨዋቾችን አነጋግሯል

  የኢትዮጵያ እግር ኳስ አገራዊ በሆነ እይታ አጠቃላይ ገጽታው የሚመረመርበትና ሥር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው እየተነገረ ይገኛል፡፡ የዓለም እግር ኳስ በሁለንተናዊ ገጽታው ከደረሰበት ዘመናዊ ዘይቤ ላይ ለመድረስ ዛሬ መሠረቱ የሚጣልበት የእግር ኳስ አብዮት የሚያስፈልግበት አጋጣሚም እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ከሰባት አሠርታት በላይ ሲንከባለል የኖረን ዘልማዳዊ አሠራር ለመፍታት ጊዜ ያስፈልጋል ይላል፡፡

  የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለዓመታት እንደተከታተሉ የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ ወልደዮሐንስ ከሰሞኑ ብሔራዊ ቡድኑ በአልጄሪያ አቻው የደረሰበት 7 ለ 1 ውጤት በብዙዎች ዘንድ ቁጭትን የፈጠረ ቢሆንም በእሳቸው ግን የሚጠበቅ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ መንታ መንገድ ላይ ነው፡፡ አገራዊ በሆነ እይታ አጠቃላይ ገጽታው የሚመረመርበትና ሥር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ የሚያስፈልግበት መንታ መንገድ ላይ ከቆመ ሰነባበቷል፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከሰሞኑ ብሔራዊ ቡድኑ በአልጄሪያ አቻው የደረሰበት ሽንፈት ለአገሪቱ እግር ኳስ የፈጠረለትን ዕድል በተለመደው ሰበባ ሰበብና ጥቅል በሆኑ የተለምዶ ምክንያቶች ማለፍ፣ ‹‹ይህንን የለውጥ መልካም አጋጣሚ ማዳፈን ነው፡፡ የታሪክም ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፤›› በማለትም ይናገራሉ፡፡

  ለዚህ እግር ኳስ ወዳድ ለሆነው ሕዝብ በባለሙያዎች የሚመራ፣ ዘመናዊ አወቃቀርን የተከተለና በረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድና ሥልጡን በሆነ ምህዋር ላይ የሚጓዝ አሠራር መፍጠር ከላይ ከመንግሥት እስከታች ባለድርሻ አካላት ግዴታቸው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ እግር ኳሱን የሚመሩት ሰዎች የዘመናዊ እግር ኳስን ገጽታ የሚረዱና የሚሸከሙ በዕውቀት የታነፁ መሆን እንዳለባቸው የሚያክሉት አቶ ሀብታሙ፣ ሐሳባቸውን እንዲህ ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ በሚያፈስበት ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን እንዲሁም አገራዊ ንቅናቄን የመፍጠር ከፍተኛ ጉልበት ያለው እግር ኳስ በውክልና እና አቅመቢሶች እንዲመራ መፍቀድ የለበትም፡፡ በክልሎችና በዞኖች፣ በክለቦችና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን የመንግሥት የእግር ኳስ ወኪሎች ከፍተኛ አቅምና ራዕይ ባላቸው ባለሙያዎች በማዋቀር ለሚታሰበው መዋቅራዊ ሽግግር የማይተካ ሚና መጫወት አለበት፡፡››

  እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጠቅላላ ጉባኤና አመራር ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በሙያና እውቀት እግር ኳሱን መምራት የሚችሉ፣ ለእግር ኳስ ዕድገት አዳዲስ ራዕይና ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የተለዩ ሐሳቦችን የሚያፈልቁ ባለሙያዎች መሆን እንዳለባቸው የሚያብራሩት አስተያየት ሰጪው፣ ‹‹በውክልናና ተዋፅኦ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደየትም ፈቀቅ ማድረግ ስለማይቻል የግድ ለዓመታት አልጠራ ያለውን የእግር ኳሱን ጉሽ ማጥራት ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡

  የመዋቅራዊ ለውጡ ማጠንጠኛ በልምድና በመተሳሰብ፣ በካምቦሎጆ ዙሪያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እግር ኳሱን ‹‹የሚዘወሩ››፣ እንዲሁም በስመ ስፖርት ሳይንስ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ሳይተዋወቁ እግር ኳሱን ሙጭጭ ብለው የያዙ ግለሰቦች ሙሉ ለሙሉ በአዳዲስ ደሞች (ባለሙያዎች) በመተካት ስፖርቱን በሙያ የመምራትና የማስተዳደርን (ፕሮፌሽናሊዝም) መሠረት መጣል እንደሚያስፈልግ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹በአጠቃላይ የእግር ኳሱ ልማት በባለሙያዎች ሙሉ ተሳትፎ እንዲከናወን በማድረግና ከክለብ ጀምሮ የብሔራዊ ቡድኑን አጠቃላይ አወቃቀር ዘመናዊ መንገድ እንዲከተል በማድረግ የዘመነ የአሠልጣኞች ስብስብ (Coaching Staff) በማዋቀር ሙያዊ ከባቢ መፍጠር ያስፈልጋል፤›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፣ ‹‹አሁን ስለ ጋቦኑ 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማሰባችንን ወደ ጎን ትተን አገራዊ የእግር ኳስ ዕድገት መመሪያ (National Football Development Framework) በማዘጋጀት በሠለጠነ ዕቅድና ራዕይ መመራት መጀመር አለብን፡፡ ዛሬ በሠራነው ሥራ ነው አንገታችንን ቀና ማድረግ የምንችለው፣ አለበለዚያ ያለመዋቅራዊ ለውጥ የለውጥ ሐሳብ የሌላቸው፣ ሙያ የሌላቸው የእግር ኳስ መሪዎችንና ብሔራዊ አሠልጣኞችን ጭምር መቀያየር አሮጌ ወይን በአዲስ አቆማዳ እንደ ማድረግ ነው፤›› በማለት እግር ኳሱ አብዮት እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ፡፡

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያ በደረሰበት አስደንጋጭ ውጤት ምክንያትና ቡድኑ ምንም እንኳ በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ተንቀሳቅሶ 3 ለ 3 በሆነ አቻ ውጤት መለያየቱ ገንፍሎ የወጣውን ቁጣ ቢያቀዘቅዘውም የአገሪቱ እግር ኳስ ከክለቦች አደረጃጀት ጀምሮ የመወቅር ለውጥ እንደሚያስፈልገው የብዙዎች እምነት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

  በተለይም በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ የሚገኙ ክለቦች በየዓመቱ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከማሰብ የተለየ ራዕይ ሰንቀው መንቀሳቀስ ሲገባቸው፣ ምንም እየሠሩ እንዳልሆነና የአገሪቱ ክለቦች ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች አጠቃላይ የእግር ኳሱን ሥራ ከታዳጊዎች ጀምሮ በባለሙያዎች የሚመሩት ምን ያህሉ ናቸው? በክለብ የሚሠሩ እግር ኳሳዊ ሥራዎችስ ለብሔራዊ ቡድኑ አስተዋጽኦ እንዳለው አምነው የሚንቀሳቀሱት ስንቶቹ ናቸው? ሲሉ የሚጠይቁት ሙያተኞች አሁን ብሔራዊ ቡድኑ ባስመዘገበው ውጤት ሊቆጩ እንደማይገባ ይስማማሉ፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ቡድን የክለብ ነፀብራቅ መሆኑ እንዴት ሊሳነን ይገባል ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችና የቡድን አባላትም ከአልጄሪያው የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በጨዋታው ዙሪያ መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡ ከተጨዋቾቹ አንዳንዶቹ፣ አመራሩ ተጨዋቾች በምንም ይሁን ብቻ ውጤት እንዲያመጡ ከመመኘት ባለፈ ለውጤት የሚያበቃ፣ ለቅድመ ዝግጅቶች ትኩረት እንደማይሰጥ፣ ተጨዋቾችን እንደ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችነታቸው ተገቢው ክብርና ቦታ እንደማይሰጣቸው፣ ከቁሳቁስ አቅርቦት ጋር በተያያዘም የይድረስ ይድረስ ካልሆነ በስተቀር ቀደም ተብሎ በዕቅድና በፕሮግራም እንደማይሠራ በተለይ ጉዞና ተዛማጅ አሠራሮችን በተመለከተም የአገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ ለተጨዋቾች ቅድመ ዝግጅት መደረግ እንዳለባቸው ከብዙ በጥቂቱ ያነሷቸው ነጥቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡

  ተጨዋቾቹ ካነሷቸው ነጥቦች በተጨማሪ የቡድኑ ሐኪም ጉዞ በተጨዋቾቹ ወቅታዊ አቋም ላይ ትልቅ ፈተና እንደነበር፣ ሆኖም የፈሰሰ ውኃ እንደማይታፈስ ሁሉ ችግሩ በመማሪያነቱ ተወስዶ እንዲስተካከል ማሳሰባቸውም ተሰምቷል፡፡

  ከሥራ ድርሻ ጋር በተገናኘም ከፌዴሬሽኑ አመራር ጀምሮ ሁሉም ኃላፊነቱንና የሥራ ድርሻውን ለመወጣት ተጠያቂነት እንዳለበት አውቆ እንዲሠራ የማይደረገው ለምንድነው? ሲሉ የጠየቁ ተጨዋቾች እንደነበሩም የዜናው ምንጭ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

  በፌዴሬሽኑና በብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች፣ እንዲሁም የቡድን አባላት መካከል የተደረገውን ውይይት አስመልከቶ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው፣ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል የተደረገው ውይይት በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው የአልጄሪያውን ጨዋታ ተከትሎ ከየአቅጣጫው ሲደመጡ የነበሩ ነገሮችን ለማጥራት ታስቦ የተደረገ መሆኑንና ጎን ለጎንም ለተጨዋቾች ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ለመለገስ የተዘጋጀ መድረክ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

  ተጨዋቾች በፌዴሬሽኑ ላይ ያነሷቸውን አስተዳደራዊ ቅሬታዎችን በተመለከተ አቶ ወንድምኩን፣ ብዙዎቹ ቅሬታዎች ከጉዞ ጋር ተያይዞ መሆኑንና ፌዴሬሽኑም ተጨዋቾቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢና እውነትነት ያላቸው መሆናቸውን ተቀብሎ፣ ነገር ግን ከነበረው የጊዜ እጥረት አኳያ ያንን ከማድረግ ውጪ አማራጭ እንዳልነበረው ከቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አቶ ዮሐንስ ሳሕሌ ጭምር በመነጋገር የተገባበት ውሳኔ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

  ፊፋም ሆነ ካፍ በአገሮች መካከል የሚደረጉ የጨዋታዎች መርሐ ግብር የሚታወቁት ከዓመት በፊት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ፌዴሬሽኑ ጉዞውንም ሆነ ተያያዥ ቅድመ ዝግጅቶችን ቀድሞ ለምን አልተዘጋጀም? ለሚለው ኃላፊው፣ ‹‹ፊፋና ካፍ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ ከውድድር መርሐ ግብሮች ጋር ተያይዞ አዳዲስ አሠራሮችን እንደሚከተሉ፣ ከእነዚህ አሠራሮች የማጣሪያ ውድድሮች በየአራት ቀኑ መደረግ እንዳለባቸው የሚያስገድዱ እንደሆኑና ይኼ ደግሞ በበቂ ሁኔታ የአየር ትራንስፖርት ባልተስፋፋበት አፍሪካ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ፣ ብሔራዊ ቡድናችን ላይ የደረሰው መጉላላትም በዚሁ ምክንያት የተፈጠረ ነው፤›› ብለው፣ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በዚህ ጉዳይ አንድ መፍትሔ ላይ መድረስ ካልቻለ ችግሩ ቀጣይነት እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

  ችግሩ ይኼ ከሆነና ተጨዋቾችም በትራንዚት ምክንያት ረዥም ሰዓታት እንደሚጉላሉ ከታወቀ ቢያንስ ቡድኑ ለትራንዚት በሚያደርግበት አገር ቪዛ አስመትቶ ተጨዋቾቹን በሆቴል ማሳረፍ ለምን አልተቻለም? ለሚለውም፣ የቡድኑ አባላት በተለይም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾችና በልምምድ መሀል የተጎዱ ተጨዋቾች በወቅቱና በጊዜው አለመለየታቸውና አለመታወቃቸው የቪዛ ዝግጅቱን ቀድሞ ለማጠናቀቅ እንዳልቻለ ነው ያስረዱት፡፡

  ሰሞኑን ብሔራዊ ቡድኑ በአልጄሪያ የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ሥር ነቀል የመዋቅር ለውጥ ካላደረገ በቀጣይ የባሰ ውጤት እንደሚመዘገብ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አቶ ወንድምኩን፣ ‹‹ችግሩ አሁን የተፈጠረ ሳይሆን ከሰባት አሠርታት በላይ ሲንከባለል የቆየ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ እንዲህ በቀላሉ በአንድ ቀን ጀምበር ማስተካከል አይቻልም፡፡ እንደዚህም ሆኖ ፌዴሬሽኑ ዘመናዊ አሠራሮችን መከተል ይችል ዘንድ የሦስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ጥናት አጠናቋል፡፡ በቅርቡም ወደ ትግበራ እንደምንገባ እምነት አለኝ፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

  በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው እኩል 20,000 ብር በድምሩ 580,000 ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያንና የአልጄሪያን ጨዋታ ለመከታተል ከገባው ተመልካች ከትኬት ሽያጭ 1,062,000 ብር ሲያገኝ፣ ከማስታወቂያ ደግሞ 60,000 ዶላር (1,200,000 ብር በድምሩ 2,262,000 ብር) ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img