ከአዲስ አበባ በሰበታ ከተማ በኩል 35 ኪሜ ርቀት በምትገኘው አዋሽ ከተማ በጎዳና ሩጫ ልምምድ ላይ ሳሉ በሚኒባስ ተሸከርካሪ ጉዳት ከደረሰባቸው 11 አትሌቶች መካከል ሕይወቱ ያለፈው አትሌት አሻግሬ ግርማ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ፡፡
መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ የተነሱትና ሰበታ ከተማን አልፈው ልምምድ ሲያደርጉ ከነበሩት አትሌቶች አምስቱ ከፍተኛ አደጋ ሲደርስባቸው አራቱ መጠነኛ አደጋ እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡
በሆስፒታል ሕክምና ሲደረግለት የቆየው አትሌት አሻግሬ ያረፈው መጋቢት 19 ቀን ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብሩም መጋቢት 21 ቀን በትውልድ ቦታው አርሲ ሮቤ መፈጸሙን የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ ገዛኸኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው አትሌቶችም ሕክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ታውቋል፡፡