ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ስፖርቶች የሚዘወተሩባቸውን ሜዳዎች በዘመናዊ መልኩ የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ለዓመታት በኮንክሪት ንጣፍ ከሚታወቁ ማዘውተሪያዎች ውስጥ የቅርጫት ኳስ፣ የመረብ ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የቦክስና ሌሎችም ስፖርቶች ሲዘወተሩበት የቆየው በተለምዶ ‹‹ትንሿ ሜዳ›› እየተባለ የሚጠራው ማዘውተሪያ ተጠቃሽ ነው፡፡ ማዘውተሪያው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ምንም ዓይነት ዕድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ ኮንክሪትም በመሆኑ በርካታ ስፖርተኞችን ከጥቅም ውጪ ሲያደርግ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ችግሩን የተረዳ የሚመስለውና በቅርቡ የተዋቀረው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ማዘውተሪያው ከአገር ውስጥም አልፎ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ በሚያስችለው መልኩ የማሻሻያ ግንባታ እንዲደረግለት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለግንባታው የተያዘለት በጀት አምስት ሚሊዮን ብር መሆኑን ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የሊድ ቢዩልዲንግ ቴክኖሎጂ ባለቤትና መሐንዲስ አቶ መሉዓለም ፈረደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሉዓለም፣ በተለምዶ ‹‹ትንሿ ሜዳ›› እየተባለ የሚጠራው የስፖርት ማዘውተሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሰው ሠራሽ ንጣፍ (ሰንቴቲክ) እየለበሰ ይገኛል፡፡ ሥራው ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች የሚከናወን መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ሙሉዓለም፣ ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም የአሰላውን ጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል መሮጫ ትራክንና ብሔራዊ የወጣቶች ማሠልጠኛ ማዕከል የቤት ውስጥ ስፖርቶች የሚከናወኑበትን ንጣፍ አጠናቀው ያስረከቡ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪም በአዲስ አበባ የራስ ኃይሉና በሐረር ደግሞ ተመሳሳይ ግንባታዎችን አጠናቀው ማስረከባቸውን ጭምር ይገልጻሉ፡፡
በአዲስ አበባ ‹‹ትንሿ ሜዳ›› እየተባለ የሚጠራውን የስፖርት ማዘውተሪያ በበላይነት የሚያስተዳድረው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴንና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አምበሳው እንየው መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ሳይጠበቁ ቦታው ላይ በድንገት በመምጣት ሒደቱን ሲከታተሉ ታይተዋል፡፡