ግንኙነታቸውን ዳግም እያደሱ የሚገኙት የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ከሃያ ዓመታት በኋላ የአሰብ ወደብ ሥራ እንዲጀምር ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ሁለቱ መሪዎች በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት በኢትዮጵያ በኩል የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በጋራ ግብረ ኃይል አቋቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንተርፕራይዙ ረቂቅ የድርጊት መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሰብ ወደብ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ፣ በተለይ ቀደም ሲል ወደቡን የሚያውቁ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አቶ ሮባ አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ እስከ አሰብ ወደብ የተዘረጋው መንገድ 200 ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው ከባድ ተሽከርካሪዎች ይጓጓዙበት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት እስከ 600 ኩንታል ድረስ የመጫን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎች በጂቡቲ ኮሪደር ይንቀሳቀሳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በደርግ ዘመነ መንግሥት ለወደቡ የተገዙት 18 ክሬኖችን የማንሳት አቅም ከስምንት እስከ 12 ቶን ድረስ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 40 ቶን በአንድ ጊዜ ማንሳት የሚችሉ ክሬኖች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአሰብ ወደብ ጥልቀት ትልልቅ መርከቦችን ያስተናግዳል? ወይስ አነስተኛ መርከቦችን ያስተናግዳል? የሚለው ጉዳይ እየተጠና መሆኑ ተገልጿል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ የምትጠቀመው በጋራ ልማት መርህ ነው? ወይስ በኪራይ ነው? የሚለውን ጉዳይ እስካሁን ከበላይ አካል ውሳኔ ያላገኘ መሆኑን አቶ ሮባ ገልጸው፣ አሁን የተሰጠው መመርያ በፍጥነት ወደቡን ሥራ ማስጀመር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት መዋቅሮች ከኤርትራ አቻዎቻቸው ጋር እየሠሩ መረጃ እየተለዋወጡ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ ሥራ ካቆመችበት ጊዜ አንስቶ ያለሥራ የተቀመጠ ሲሆን፣ በአንፃሩ የምፅዋ ወደብ ሥራ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በ1990 ዓ.ም. ጦርነት በተጀመረበት ጊዜ በወደቡ ይገለገሉ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ወደብ የደረሱ ዕቃዎቻቸው እንደተወረሱባቸው ይታወሳል፡፡