ዓርብ ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ በነበረ የድሬዳዋ ከተማ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኞች ቡድን ላይ ጥቃት ደረሰ፡፡
ጥቃቱ የደረሰው ዓርብ ምሽት ላይ ሲሆን፣ የጋዜጠኞቹ ቡድን ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ የነበረውን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ በነበረበት ወቅት መሆኑን ሪፖርተር ጉዳቱ ከደረሰባቸው የጋዜጠኞች ቡድን አባላት ለመረዳት ችሏል፡፡
ጥቃቱም የደረሰው ሜኤሶ ከተማ ውስጥ በቡድን ተሰባስበው በመጡ ግለሰቦች አማካይነት ሲሆን፣ በወቅቱ አምስት የሚሆኑ የጋዜጠኞችን ቡድን ይዞ የነበረው ኮድ 4 ድሬ-00336 ሚኒባስ መኪና በግለሰቦች እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ጋዜጠኞቹን ማንገላታትና መደብደብ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ግለሰቦቹ የድሬዳዋ ከተማ መገናኛ ብዙኃን የሚል ጽሑፍ ተለጥፎበት ጋዜጠኞቹን ይዞ የሚሄደውን መኪና ካስቆሙ በኋላ፣ ‹‹እናንተ ሰላዮች ናችሁ የመጣችሁትም በተመሳሳይ ቀን ማለትም ዓርብ ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ሜኤሶ ከተማ ላይ ተፈጥሮ ስለነበረው ግጭት መረጃ ለመሰብሰብ ነው፤›› በሚል በጋዜጠኞቹ ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ችለዋል፡፡
በጥቃቱም አቶ ሱሌይማን አህመድ (ሾፌር)፣ አቶ ሙሴ ኡመር (የሶማሊኛ ፕሮግራም ጋዜጠኛ)፣ አቶ አሚን ሸፊፋ (የካሜራ ባለሙያ)፣ አቶ አዕምሮ ተስፋዬ (የፕሮግራም አዘጋጅ) እና አቶ ቢፍቱ የሱፍ (የዜና ክፍል አባል) የተባሉ ጋዜጠኞች ላይ ጉዳት መድረሱን ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የጋዜጠኛው ቡድን አባላት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦች፣ ‹‹እናንተ (በተለይም የኦሮምኛ ቋንቋ የሚችሉትን ጋዜጠኞች) ገንዘብ ተከፍሏችሁ እየሰለላችሁ ነው፤›› በሚል ሁሉም ላይ የጅምላ ጥቃት እንዳደረሱባቸው ተጎጂዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለይም አቶ ሙሴ ኡመር የተባሉት የሶማሊኛ ቋንቋ ጋዜጠኛና አቶ ሱሌይማን አህመድ ላይ ከፍተኛ ድብደባ በግለሰቦቹ የተፈጸመ ሲሆን፣ አቶ ሱሌይማን በድል ጮራ ሆስፒታል የከፍተኛ ክብካቤ ክፍል (ICU) ውስጥ በአሥጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በወቅቱ ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦች የጋዜጠኛ ቡድኑን አባላት እየደበደቡ ለሜኤሶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ማስረከባቸውና በነጋታው ጋዜጠኞቹ መለቀቃቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
‹‹ለዘገባ ወደ አዲስ አበባ ከረፈደ በመላካችን ተቃውመን ነበር፤›› ያሉት ጋዜጠኞቹ፣ በመጨረሻም ለእንደዚህ ዓይነት ጥቃት ተዳርገናል ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የድሬዳዋ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊ አቶ ሐሰን ኢጌ ጥቃቱ መፈጸሙን አምነው፣ አሁን የጋዜጠኞቹን ጤንነት እየተከታተሉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተለይ አቶ ሱሌይማን አህመድን ወደ አዲስ አበባ ለተጨማሪ ሕክምና ክትትል ለመላክ እየተሞከረ መሆኑን አክለዋል፡፡