ከሃያ ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ጥላቻ በመወገዱ፣ ረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚደረገው የመጀመርያ በረራ በኤርትራ ፕሬዚዳንት ልዩ ግብዣ የተደረገላቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በክብር እንግድነት የኢትዮጵያ ልዑካን በመምራት ወደ አስመራ ይጓዛሉ፡፡
ከሐምሌ 7 እስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የክብር እንግዳ አድርገው አቶ ኃይለ ማርያምን የጋበዟቸው፣ ኢትዮጵያ ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደገቡ በቤተ መንግሥት በተደረገላቸው የምሳ ግብዣ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በምሳ ግብዣው ላይ ታድመው የነበሩትን አቶ ኃይለ ማርያምን የተቀመጡበት ቦታ ድረስ ሄደው ሞቅ ያለ ሰላምታ የሰጧቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ ከተማ በሚደረገው የመጀመርያ በረራ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ይዘህ እንድትመጣ ጋብዤሃለሁ፤›› በማለት እንደ ጋበዟቸው አጠገባቸው ከነበሩ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም የፕሬዚዳንቱን ግብዣ በደስታ መቀበላቸውን በወቅቱ ምላሽ ከመስጠታቸውም በላይ፣ የክብር እንግዳ ሆነው የኢትዮጵያ ልዑካንን በመምራት ወደ አስመራ እንደሚጓዙ ተረጋግጧል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም ከእሳቸው በፊት የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ተክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች ሰላም ስንል አስመራ ድረስ ሄደን እንነጋገራለን፣ እንደራደራለንም፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ሌላው ለዛሬው በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለት አውሮፕላኖችን መድቦ በድምሩ 469 ኢትዮጵያውያንን ይዞ ወደ አስመራ ይበራል፡፡ በድሪምላይነር 787 አውሮፕላን 315 መንገደኞች፣ በቦይንግ 737-800 ኔክስት ጄኔሬሽን አውሮፕላን ደግሞ 154 መንገደኞች ይጓጓዛሉ፡፡ ዛሬ በሚደረገው በረራ ባለሀብቶች፣ በጦርነቱ ምክንያት ከዘመዶቻቸው ጋር የተለያዩ፣ የጉዞ ወኪሎች፣ ጋዜጠኞች፣ ወዘተ የሚጓዙ ሲሆን፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶችን ይዞ የሚጓዘው ዋፋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡