Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ቀጣናዊ ግጭት የመፍጠር አዝማሚያ መታየቱ ተጠቆመ

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ቀጣናዊ ግጭት የመፍጠር አዝማሚያ መታየቱ ተጠቆመ

ቀን:

የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከሰሞኑ የተቀሰቀሱት ግጭቶች፣ ሥውር የፖለቲካ ተልዕኮ የያዘና ምሥራቅ አፍሪካን በግጭት የመረበሽ አዝማሚያ የታየበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መከላከያና ፌዴራል ፖሊስ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተሠማርተው፣ የግጭቱን ተሳታፊዎችን በአነስተኛ ኪሳራ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለሕግ እንዲያቀርቡ ሰኞ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

የተቀሰቀሰውን ግጭት በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የካቢኔ አባልና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በመቀስቀሱ ቀጣናዊ ግጭት የመቀስቀስና አካባቢውን የመረበሽ አዝማሚያ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

‹‹አንዳንዴ በሲቪል አንዳንዴ ደግሞ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ወታደራዊ የደንብ ልብስ በመልበስ፣ ከባድ መሣሪያ ታጥቀውና ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመው በአዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎች በመዝለቅ ነዋሪዎችን ተኩሶ የመግደልና ቤቶችን የማቃጠል ጥቃቶች ሰሞኑን ተፈጽመዋል፤›› ብለዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አርብቶ አደሮች በመሆናቸው፣ ከብቶቻቸውን ለመጠበቅ ከረዥም ጊዜ አንስቶ መሣሪያ የመታጠቅ ልምድ እንዳላቸው ያስታወሱት ኃላፊው፣ ጥቃት ሲደርስባቸው አፀፋዊ ዕርምጃ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሶማሌ ወገን አንድ ሰው ሲሞት በጎረቤት አገሮች የሚገኙ ተመሳሳይ ጎሳ አባላት እንዲሳተፉ፣ ‹‹ኦሮሞ ገደለን›› የሚል መረጃ በፍጥነት እንደሚሰራጭና በግጭት የመነገድ አዝማሚያ መኖሩን  አስረድተዋል፡፡

የዚህ እንቅስቃሴ ዓላማ ፖለቲካዊ ግብ የያዘ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል እንደሚገነዘብ የተናገሩት ነገሪ (ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልልን በማተራመስ ማዕከላዊ መንግሥትን ማዳከም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የግጭቱ ፈጻሚዎች መቀመጫቸውን በሶማሌ ክልል በማድረግ ከመሀል አገር እስከ የተለያዩ ጎረቤት አገሮች የተዘረጋ ሰንሰለት እንዳላቸው፣ ከፌዴራል መንግሥት እስከ ክልል የፀጥታ መዋቅሮች የዚህ ኔትወርክ አባሎች እንደሚገኙም መረጃ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በከፍተኛ የዶላር ማስተላለፍና የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተሰማራው ከመሀል አገር አንስቶ እስከ ጎረቤት አገሮች የተደራጀውና የጉምሩክን መዋቅር የሚጠቀመውን ቡድን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና አስተዳደራቸው መበጣጠስ በመጀመራቸው፣ ህልውናቸውን ለማስቀጠል የተቀሩት የቡድኑ አባላት ከጀርባ ሆነው ስፖንሰር የሚያደርጉት ግጭት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥልጣን በያዙ በማግሥቱ ወደ ሶማሌ ክልል በማቅናት በሁለቱ ክልሎች መካከል ባለፈው ዓመት የተከሰተው አሰቃቂ ግጭትና መፈናቀል እንዳይደገም፣ ለዚህም የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በጋራ እንዲሠሩ በማሳሰብና እጅ ለእጅ በማያያዝ ቃል አስገብተው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ሰላም ለመምጣት ያስፈልጋሉ የተባሉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙቶች እስካሁን አልተካሄዱም፡፡

‹‹መታወቅ ያለበት ጉዳይ በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት የለም፡፡ የወሰን ጉዳይ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ምላሽ አግኝቷል፡፡ በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ያለው ግጭት ፈጽሞ ሕዝባችን አይወክልም፤›› ያሉት ነገሪ (ዶ/ር)፣ ከሶማሌ ክልል አመራሮች ጋር በመነጋገር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለመጀመርም ትልቅ ኮንፈረንስ በአዳማ እንዲካሄድ ስምምነት ተደርሶ ቀን ተቆርጦ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ስብሰባው ሊካሄድ ሳምንት ሲቀረው የረመዳን ፆም የሚገባ በመሆኑ ከፆሙ በኋላ እንዲሆን ጥያቄ በመቅረቡ መተላለፉን፣ ከፆሙ በኋላ ግን ግጭት በመቀስቀሱ ማካሄድ አለመቻሉን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የሶማሌ ክልል አመራሮች ለሰላም ዝግጁ ስለመሆናቸው ከሚነግሩን እንረዳለን፡፡ አሁንም ቢሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለመጀመርና ሁለቱ ክልሎች በሚመሩት ፓርቲዎች መካከል ውይይት እንዲካሄድ፣ ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በኩል የተቀሰቀሰውን ግጭት አስመልክቶ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ግጭቶቹ እየተከሰቱ የሚገኙት በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢዎች በጭናክሰን፣ በባቢሌ፣ በሚኤሶ እንዲሁም በቦረና፣ በጉጂና በሞያሌ አካባቢዎች እንደሆነ ነገሪ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አካል የሆነ አንድ የታጠቀ ቡድን የፖሊስ ተቋማትና ፖሊሶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጽም የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት መረጋጋት ታይቶ እንደነበር ነገሪ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተመሳሳይ ጥቃት ሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በቄለም ወለጋ በመንቀሳቀስ ላይ በነበረ አንድ የክልሉ ፖሊስ ተሽከርካሪ ላይ መሰንዘሩን አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል ወደ አገር ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ይታገል ባለበትና ከኦነግ ጋርም ውይይት ለመጀመር ዝግጅት ላይ ሳለ፣ ይህ ድርጊት መፈጸሙ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ማክሰኞ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የፀጥታ ችግር ባጋጠማቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት የማረጋጋት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይል እንዲገባ በወሰኑት መሠረት፣ የመከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በተመረጡ ሥፍራዎች እየገቡ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

ሰሞኑን እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች ከወትሮው ለየት ያሉና ስፋት ያላቸው አካባቢዎችን መሸፈናቸውን ገልጸው፣ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉን ጠቁመዋል፡፡ ከግጭቱ በስተጀርባ ያሉ አካላት በአገሪቱ እየታየ ያለውን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ ኃይሎች መሆናቸውን፣ በቅርቡም ማንነታቸው እንደሚገለጽ አስታውቀዋል፡፡ በመከላከያ ሠራዊቱ አማካይነትም ግጭቶች በአጭር ጊዜ እንደሚቆሙና ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈጠር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...