Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሮሚያ የቀድሞ ሹም አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ይመራሉ

የኦሮሚያ የቀድሞ ሹም አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ይመራሉ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ በምክትል ከንቲባነት አዲስ አበባን እንዲያስተዳድሩ ተሾሙ፡፡

በቅርቡ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ያልሆነ ምክትል ከንቲባ መሆን ችለዋል፡፡ በምክትል ከንቲባነት የተሾሙት አቶ ታከለ የከተማውን ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን በመተካት ኃላፊነቱን ማክሰኞ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ተረክበዋል፡፡

አቶ ታከለ ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ደግሞ የሱሉልታ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅና የሆለታ ከተማ ከንቲባም ነበሩ፡፡ የሰበታ ከተማ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ በመሆን መሥራታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሻሻለው የከተማው ቻርተር መሠረት ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት አባላት ውጪ እንዲሾም በመወሰኑ፣ አቶ ታከለ የከተማው ምክር ቤት አባል ስላልሆኑ በቀጥታ ከንቲባ ሆነው መምራት አይችሉም፡፡ ነገር ግን ምክትል ከንቲባ ሆነው የከንቲባውን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ተረክበው አዲስ አበባን በበላይነት ይመራሉ፡፡

አቶ ታከለ በዚህ ታሪካዊ ወቅት የአገሪቱን ዋና ከተማ ለማገልገል በመሾማቸው ክብርና መታደል እንደሚሰማቸው አስታውቀዋል፡፡ አዲስ አበባ ክልል፣ ሃይማኖት ወይም ማኅበራዊ የመደብ ልዩነት የማይገድባቸው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኗን ጠቁመው፣ የአፍሪካ የዲፕሎማቲክ ከተማ ስለሆነች ወደፊት ተስፋ ያላት ከተማ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ከተማዋ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉባት እንደሚረዱ ተናግረው ዕድገቷን ማስቀጠል፣ የነዋሪዎቹን ሕይወት ማሻሻል፣ እያደገ የመጣውን የኑሮ ልዩነትና ቤት አልባነት ጉዳይ ትኩረት መስጠት፣ የውኃ እጥረትና የንፅህና ችግርን መቅረፍ፣ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ ለድሆች የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦትን ተመጣጣኝና ተደራሽ ማድረግ፣ የወጣቶች ሥራ አጥነትን መቅረፍና አዲስ አበባን ዘመናዊ ከተማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፈተናዎችን ለመቋቋም ዝግጁ ስለሆኑ በጋራ በመሆን ፈተናዎችን መጋፈጥና ማሸነፍ ስለሚቻል፣ ለዚች ታላቅ ከተማ በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

ላለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን በከንቲባነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ድሪባ ኩማ በሥልጣናቸው እንደማይቆዩ በቅርቡ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተደርገው መሾማቸው አይዘነጋም፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከምክትል ከንቲባው በተጨማሪ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ እንዲሁም የከተማው መንገዶችና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ተሹመዋል፡፡ ሁለቱ ተሿሚዎች የትኞቹን ዘርፎች እንደሚመሩ አልታወቀም፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዋነኛ መነሻ ምክንያት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በተቃውሞው ምክንያት የጋራ ማስተር ፕላኑ መሰረዙ አይዘነጋም፡፡ በዚህም ሳቢያ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለብቻው ተሠርቶ መፅደቁም ይታወሳል፡፡

አዲስ አበባ ባለፉት 27 ዓመታት ሰባት ከንቲባዎች የተፈራረቁባት ሲሆን፣ አሁን በምክትል ከንቲባነት ሙሉ ኃላፊነት የተረከቡት አቶ ታከለ ኡማ ስምንተኛው ይሆናሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነዋሪዎች ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ የሚቀርብበት ሲሆን፣ በተለይ የመልካም አስተዳደርና የመሬት ጉዳይ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በአስተዳደሩ ውስጥ ፅኑ የሆነ ሙስና መንሰራፋቱ በስፋት ይነገራል፡፡

ለመልካም አስተዳደር መንስዔ ናቸው ከሚባሉት ችግሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ከተማውን የሚያስተዳድሩት ባለሥልጣናት፣ ከአራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የተውጣጡ በመሆናቸው የከተማውን ሕዝብ ችግርና ሥነ ልቦና የማይጋሩ እንደሆኑ ብዙዎች በምሬት ይገልጻሉ፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አዲስ አበባ መመራት ያለባት አዲስ ከተማ ውስጥ ተወልደው ባደጉ ባለሙያዎችና አመራሮች መሆን አለበት ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

ከተማን ለመምራት የከተማውን ነዋሪዎች ሥነ ልቦና ከመረዳት በተጨማሪ የማስተዳደር ብቃትና ክህሎት መሆን ይገባቸዋል እንጂ፣ የፖለቲካ ሹመኞች ሊመሯት አይገባም የሚሉ ክርክሮች በስፋት ይሰማሉ፡፡ እንደ ምሳሌ የሚያነሱት የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ፣ በከተማው ሁለገብ እንቅስቃሴዎች ፈጣን ውሳኔ የመስጠት፣ ለመሠረታዊ ለውጥ ዝግጁ የመሆን ብቃትን የተላበሰ አመራር አስፈላጊነትንም ያወሳሉ፡፡

አንድ በከተማ ፕላነርነት ለረዥም ጊዜ በውጭ አገር ያገለገሉ ስማቸው እንዲጠቀሱ ያልፈለጉ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምንም እንኳን አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆን ከጄኔቭና ከኒውዮርክ ቀጥሎ ሦስተኛ የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ ብትሆንም፣ ከስሟ ጋር የሚመጥን የከተማ አስተዳደር አልነበራትም፡፡ ‹‹ለዚህ አባባሌ እንደ ማሳያ የሚሆነው ለከተማዋ ነዋሪዎች በቂ መናፈሻዎችና የሕዝብ መዝናኛዎች ካለመኖራቸውም በላይ፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የቆሻሻ ክምሮች ስሟን እያጎደፉ ነው፡፡ መንገዶች በአግባቡ ስለማይገነቡ ዝናብ ጠብ ሲል ኩሬ ይሆናሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በክረምት ወራት የእግረኛ መንገዶች ግንባታ መካሄዱ ምን ያህል የአመራር ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች ሥራ አጥ መሆናቸው፣ የነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መክፋቱ፣ የቤት አልባ ዜጎች ምሬትና የመሳሰሉትን በርካታ ሕፀፆችንም ማሳየት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

እኚህ ባለሙያ እንደሚሉት፣ የፖለቲካ ተሿሚዎች ቢኖሩም እንኳ በከተማው አስተዳደር ከላይ እስከ ታች ያሉ መዋቅሮች በባለሙያዎች መመራት አለባቸው፡፡ ሁሉም ቦታ የፖለቲካ ተሿሚ እጁን ማስገባት ሲጀምር ባለሙያዎችን የሚሰማቸው እየጠፋ ሥራዎች ከመበላሸታችውም በላይ፣ አቅዶ መፈጸም ቀርቶ በአግባቡ ማቀድ እንኳን አይቻልም በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከተማን ለመምራት ያደጉና የበለፀጉ አገሮችን ልምዶች ከራስ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...