Saturday, December 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትሸጋገረው በሥርዓት መምራትና መመራት ሲቻል ነው!

ኢትዮጵያ አገራችን ከአንድ የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላው እየተሸጋገረች ነው፡፡ ይህ ሽግግር ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተቋማዊ እንዲሆን ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በአገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ለውጡን የሚመጥን ዕውቀት፣ አስተዋይነትና ታታሪነት ያስፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተንሰራፋባት ድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅና ወደ ዘመናዊ አገርነት ለመቀየር፣ የተቋማት ጥንካሬና የሕግ የበላይነት መቼም ጊዜ ቢሆን ሊታለፉ የማይገባቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ከቆመችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በርካታ መንግሥታት ቢለዋወጡም፣ እንደ ትልቅ ጉድለት የሚታየው ተቋማት በሚፈለገው መንገድ አለመደራጀታቸው ነው፡፡ ከፀጥታ ኃይሎች (መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት…) ጀምሮ እስከ ሲቪል ሰርቪሱ ድረስ የገዥዎች ጥገኛ በመደረጋቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይገነባ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ሥርዓት በተለወጠ ቁጥር በገለልተኝነት ማገልገል የሚገባቸው ተቋማት ባለመደራጀታቸው ምክንያት በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ አሁንም እያጋጠሙ ነው፡፡ አገር በሥርዓት ስትመራ ውጤት የሚገኘውን ያህል፣ ሥርዓት ከሌለ ግን ነባሮቹ ችግሮች ይቀጥላሉ፡፡ ሕዝብ በሥርዓት የሚመራው መሪ ሲያገኝም በሥርዓት ለመመራት የሚችለው ተቋማት በአግባቡ ሲደራጁ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከፊቷ ብሩህ ተስፋ እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ አመላካቾች ታይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ስሜት የሰጠው ድጋፍ፣ መንግሥት ሕዝብን ለማገልገል ከልቡ ሲጣጣር ሕዝብ አብሮት እንደሆነ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ሕዝብን ከጎኑ ማሠለፍ የቻለ መንግሥት ደግሞ ሰላምና ልማትን ከማምጣት አልፎ፣ አገር ዘለቄታና አስተማማኝነት ያለው ሥርዓት እንድትገነባ ጥርጊያውን ማመቻቸት ይችላል፡፡ መንግሥት ለተቋማት ግንባታና ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሥራውን ሲያከናውን፣ ተመሪው ሕዝብ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ምርታማነቱ ይጨምራል፡፡ ድህነትን ያስወግዳል፡፡ ግጭቶችን ጠራርጎ ያጠፋል፡፡ ሌብነትና ኢሞራላዊ ድርጊቶችን ይፋለማል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መደላድሉን ያመቻቻል፡፡ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን በመልካም መንገድ ይኮተኩታል፡፡ የአገር ፍቅር የጋለ ስሜትን ያሰርፃል፡፡ አንድ ኅብረተሰብ የላቀ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችለው ለእናት አገሩ በሚከፍለው መስዋዕትነት መጠን ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትተላለፈው መስዋዕትነት ሲከፈልላት ነው፡፡ ይህ መስዋዕትነት በሥርዓት መምራትና መመራትን ይፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን እጅግ በጣም የሚያፈቅር በመሆኑ ከምንም ነገር በላይ ህልውናዋ ያሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ አምባ ሆና በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ገናና እንድትሆን ፅኑ ፍላጎቱ ነው፡፡ ይህ የጋለ ፍላጎት ዕውን መሆን የሚችለው ግን በሕዝቡ መካከል ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና የጋራ ዕጣ ፈንታ ሲኖር ነው፡፡ የገዛ ወገኑን እየናቀና እያመናጨቀ ከባዕድ ጋር የሚዘፍን፣ አገሩን እየዘረፈ ባዕድ አገር የሚያከማች፣ የበታቹን እያዋረደና እያሳቀቀ ለበላዩ የሚያሸረግድ፣ በሥሩ የሚያስተዳድራቸውን ሠራተኞች እየጨቆነ በየሚዲያው የአዞ እንባውን የሚያዘራ፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን እያስለቀሰ ስለሰብዓዊ መብት የሚደሰኩር፣ ለታዳጊዎችና ለወጣቶች አርዓያ መሆን የሚያስችል ሞራል የሌለው የሥነ ምግባር ሊቅ ሆኖ የሚፈላሰፍ፣ ወዘተ ለአገር ፋይዳ የላቸውም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመደመር ጽንሰ ሐሳብ በአግባቡ ሳይረዱ የገዛ ወገናቸውን ምሕረት የለሽ በሆነ ምላስ የሚሳደቡና የዘረኝነት መርዝ የሚረጩ የድል አጥቢያ አርበኞች እየበዙ ነው፡፡ የፍቅርና የይቅርታ እጅ እየተዘረጋና በአደባባይ ይህ በኩረ ሐሳብ እየተሰበከ፣ በተቃራኒው ቂምና በቀል ይዘው እየጮኹ ‹ተደምረናል› ማለት ኃጢያት ነው፡፡ ጥሩ መሪ ሲገኝ በአግባቡ መመራት ካልተቻለ ትርፉ ገለባ መውቃት ነው፡፡ ገለባ ደግሞ ፍሬ የለውም፡፡ በሥርዓት መመራት የሚረዳው አመርቂ ውጤት ለማግኘት ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ፀጋዎች ምድር ናት፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ከሚገመተው ሕዝቧ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 30 ሚሊዮን የሚጠጉት በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአገር ከዚህ በላይ በረከት ከየት ይመጣል? የኢትዮጵያ ማህፀን በተለያዩ ማዕድናት የተሞላ ነው፡፡ ፍለጋው በስፋት ቢቀጥል የተትረፈረፈ የነዳጅ ሀብት እንዳለ የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እጅግ በጣም ሰፊ ለም መሬትና ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሀብት አሉን፡፡ ለእርሻና ለእንስሳት ልማት ተስማሚ የሆኑ የአየር ንብረቶች አሉን፡፡ ከማንኛውም የአፍሪካ አገር የበለጡ የቱሪዝም መስህቦች ሞልተውናል፡፡ ሌሎች ተፈጥሮ የቸረችን ገፀ በረከቶች በስፋት ይገኛሉ፡፡ በአግባቡ የተደራጁ ብርቱ ተቋማትና የሥራ መሪዎች ቢኖሩን እኮ የድህነት መጫወቻ አንሆንም ነበር፡፡ አሁን ግን ከጥልቅ እንቅልፋችን እየነቃን ስለሆነ ልናስብበት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አገራቸውን በሚወዱ ልጆቿ እየተመራች በሥርዓት መተዳደር ከቻለች ሀብት ብርቅ አይሆንብንም፡፡ ዴሞክራሲም ቅንጦት ሆኖ አይሸሸንም፡፡ እንደ ቀልድ የባከኑ ጊዜያት እየቆጩን በአንድ ልብ መክረን አገራችንን ወደ ከፍታው ማማ እናድርሳት፡፡ እርስ በርስ ከመተናነቅ ወጥተን ሥርዓት ያላት አገር እንፍጠር፡፡ ‹ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት› እንደሚባለው፣ ራሳችንን ሳናታልል በሥርዓት ለመምራትና ለመመራት እንዘጋጅ፡፡ የሚበጀው ይኼ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ለውጥ በሥርዓት መመራት አለበት ሲባል፣ የሕግ የበላይነት የሁሉም ነገር ማሰሪያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሕዝብ መሪውን በአግባቡ መከተል የሚችለው በሕግና በሥርዓት የሚመራባቸው ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ ለውጥ በምክንያታዊነት ሲመራ ስሜት ይሰክናል፡፡ ለውጥ በዕውቀት ሲመራ አላዋቂዎች በደመነፍስ የሚጨፍሩበት ዓውድ ይዘጋል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ማውጣት የሚቻለው የሰከነ አመራር በሕግና በሥርዓት ሲደራጅ ነው፡፡ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንደ ህብስተ መና አይገኙም፡፡ በአስተዋይነትና በዕውቀት መመራት የማትችል አገር መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች እንደሚያመልጧት፣ ከአገራችን ኢትዮጵያ የበለጠ ምሳሌ ማግኘት አይቻልም፡፡ መልካም ዕድሎችን መጠቀም እያቃተ ብዙ ነገሮች መበላሸታቸውን ታሪካችን ከሚገባው በላይ አስተምሮናል፡፡ መልካም ዕድሎችን የመጠቀም ወይም የማበላሸት ምርጫው በእጃችን ላይ ስለሆነ፣ ለአስተዋይነትና ለዕውቀት ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ‹በማስተዋል የማይራመድ እግር ዘንዶ ጉድጓድ ያደርሳል› እንደሚባለው፣ ለውጡ በማይረቡ ምክንያቶች ተደነቃቅፎ እንዳይወድቅ ስክነት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት መራመድ እንድትችል ሰከን ብሎ በማስተዋልና በዕውቀት መምራትና መመራት የግድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ሰላም፣ ፍትሕ፣ ነፃነትና ብልፅግና ያስፈልጉታል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች በተሟላ ሁኔታ ሊረጋገጡ የሚችሉት ከደመነፍሳዊ አመራር ወደ ተቋማዊ አመራር በመሸጋገር ነው፡፡ ለውጡ መቀላጠፍ የሚችለውም ከግለሰቦች ይልቅ ተቋማት ላይ ማተኮር ሲቻል ነው፡፡ ተቋማት ሥራቸውን በነፃነትና ሕጉ በሚፈቅድላቸው መንገድ ሲያከናውኑ ፍትሕ የጥቂቶች መጫወቻ አይሆንም፡፡ በዴሞክራሲ ስም አይነገድም፡፡ በሕግ ስም ወንጀል አይሠራም፡፡ የሕግ የበላይነት በተግባር ይረጋገጣል፡፡ ሥርዓትም ሆነ ግለሰቦች ሲቀያየሩ ተቋማት አገርና ሕዝብን በነፃነት ማገልገል ይቀጥላሉ፡፡ አቶ እከሌ ወይም ወ/ሮ እከሌ ሲደሰቱም ሆነ ሲከፉ የተቋማት ባህሪ አይቀያየርም፡፡ ዘመናዊነትና ሥልጣኔ ዕውን መሆን የሚችሉት ደግሞ በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ተቋማት እንደሌሉ ሲቆጠሩ ግን ግለሰቦች ሕግ ይሆናሉ፡፡ በሚሊዮኖች ህልውና ላይ እንዳሻቸው ይወስናሉ፡፡ የተከበረች አገርን የከብት በረት ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው አገራቸውን ወደ ሥልጣኔ ለማሸጋገር መነሳት አለባቸው፡፡ ለውጡ መሠረት ጨብጦ የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ መጓዝ የሚችለው፣ ኢትዮጵያ በሥርዓት ስትመራ ብቻ ነው! ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትሸጋገረውም በሥርዓት መምራትና መመራት ሲቻል ነው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...