የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ ወደ 11 ሺሕ የሚጠጉ አፓርትመንት ቤቶች ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ቦሌ አራብሳ ያስገነባቸውን 1,192 ቤቶችን ለሠራተኞቹ በቅርቡ አስረክቧል፡፡ የመጀመርያዎቹ 30 አባወራዎች ወደ ቤታቸው መግባታቸውን አስመልክቶ ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የጉብኝት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያምና ሌሎች ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት በዝግጅቱ ላይ የታደሙ ሲሆን፣ ወደ ቤታቸው የገቡትን የድርጅቱን ሠራተኞች ተዟዙረው በመጎብኘት፣ ‹‹ቤት ለምቦሳ›› ብለዋቸዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ተወልደ በአዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቤት እጥረት እንዳለ ገልጸው፣ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ድርጀቱ የሚችለውን ያህል ዕገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ቤት መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያን ቪሌጅ›› በመባል የተሰየመው የመኖሪያ መንደር የተሟላ አገልግሎት ያለው የተዋበ መንደር እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
‹‹እንደ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር፣ እንደ ኤርባስ 350 አውሮፕላኖች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማራኪ የመኖሪያ መንደር መሆን ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ቪሌጅ›› የራሱ የገበያ ማዕከል፣ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት እንዲኖረው የቤት ሥራ ማኅበሩና ኩባንያው በጋራ ተባብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
‹በጋራ እንሠራለን፣ አንድ ላይ እንኖራለን፣ ልጆቻችንንም አንድ ላይ እናስተምራለን፡፡ ሲጀመር የማይቻል ይመስላል፡፡ ዛሬ ይኼው እዚህ ደርሰናል፡፡ በቀጣይ የገበያ ማዕከል፣ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል መገንባት ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች መኖሪያ መንደር የተገነባው ድርጅቱ ቀደም ሲል በሊዝ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተረከበው 310,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ በመጀመርያ ዙር ለተገነቡት 1,192 ቤቶች 1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገ ታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 650 ሚሊዮን ብር ያህሉን አየር መንገዱ በብድር የሸፈነ ሲሆን፣ የተቀረውን ሠራተኞች በቅድሚያ ክፍያ እንደሸፈኑት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሠራተኞቹ ለቤት መሥሪያ ከአየር መንገዱ የተሰጣቸውን ብድር በ15 ዓመት ከደመወዛቸው እየተቆረጠ እንደሚከፍሉ ታውቋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ ጠንክሮ ሌት ከቀን የሚሠራ በመሆኑ የተመቻቸ የመኖሪያ ሥፍራ ያስፈልገዋል፤›› ብለዋል አቶ ተወልደ፡፡
በሁለተኛ ዙር የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም 11,000 አፓርትመንት ቤቶች ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ ቤቶቹ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚገነቡ ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪያቸው 20 ቢሊዮን ብር ይገመታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንባታውን የሚያከናውን ተቋራጭ ለመቅጠር ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቷል፡፡ ዘጠኝ ያህል የቻይናና የሲንጋፖር ኩባንያዎች በጨረታው እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን፣ የጨረታው ውጤት በመስከረም 2011 ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ የፕሮጀክት ፋይናንስ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና አየር መንገዱ ለሠራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ እንዳደረገ ታወቀ፡፡ የኩባንያው ማኔጅመንትና ሠራተኞች ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄዱት ዓመታዊ የድርጅት ስብሰባ አቶ ተወልደ ለሁሉም ሠራተኞቹ ከጁላይ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የ20 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የትራንስፖርት፣ የቤት አበልና የኃላፊነት አበል ማስተካከያ እንደተደረገ ለሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ላለፉት 20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የአስመራ በረራ ይጀምራል፡፡ የመጀመርያውን በረራ በቦይንግ 787-9 ድሪምላይነር አውሮፕላን የሚከናወን ሲሆን በዚህ በረራ 315 ተሳፋሪዎች ተመዝግበዋል፡፡
በመጀመርያው በረራ የቲኬት ፈላጊዎች ቁጥር ከተገመተው በላይ በመሆኑ አየር መንገዱ ሁለተኛ አውሮፕላን ለመመደብ ተገዷል፡፡ ሁለተኛው አውሮፕላን ቦይንግ 737-800 ኔክስት ጄኔሬሽን አውሮፕላን 154 መንገደኞች አሳፍሮ ወደ አስመራ እንደሚበር ታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ አስመራ በረራው 1፡10 ሰዓት የሚወስድ ሲሆን፣ የደርሶ መልስ ቲኬት 8,900 ብር ተመን ወጥቶለታል፡፡ በመጀመርያው ቀን ሁለት አውሮፕላኖች የሚበሩ ቢሆንም፣ በቀጣይ ዕለታዊ አንድ በረራ እንደሚኖር ታውቋል፡፡