የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጅማ ከተማ አውቶብስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ተለይቶ ራሱን እንዲችል በ2003 ዓ.ም. ከወሰነ በኋላ ርክክብ ባለመፈጸሙ፣ በአቅም መዳከም ምክንያት ሥራ ለማቆም እየተንደረደረ መሆኑ ተሰማ፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቀደምት ከተሞች ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት የሚያገኘው ጅማ ከተማ ብቻ ነው፡፡ ላለፉት 43 ዓመታት የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎትን ሲያገኝ የቆየው ጅማ ከተማ፣ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ በቂ ድጋፍ እያገኘ ባለመሆኑ መስመሮቹን ከመቀነስ ባሻገር አገልግሎቱን እያቆመ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት የጅማ ከተማ ቅርንጫፍ ቀደም ሲል በከተማው ነዋሪዎች፣ እንዲሁም አጎራባች ለሆኑ ከተሞች በተለይም ለየቡ፣ ለሰቃ፣ ለዴደና ለሰርቦ ከተሞች አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት መስመር ላይ የሚገኙት ሦስት አውቶብሶች ብቻ በመሆናቸውና በብልሽት ምክንያት ከመስመር የሚወጡበት አጋጣሚ በመብዛቱ፣ የጅማ ቅርንጫፍ ህልውና አደጋ ላይ ነው ተብሏል፡፡
የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መክዩ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጅማ አውቶብስ አገልግሎት ለከተማው ከትራንስፖርት በላይ ትርጉም አለው፡፡ ‹‹የአውቶብስ አገልግሎቱ ጅማ ጥንታዊና ከመጀመርያ ጀምሮ ዘመናዊ ከተማ መሆኗን ከሚያመለክቱ ምልክቶች አንዱ ነው፤›› የሚሉት አቶ መክዩ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ አንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ርክክብ ባለመካሄዱ በተሟላ ደረጃ አደራጅቶ ሥራውን ለማስቀጠል ችግር ሆኗል፤›› ሲሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም. የአዲስ አበባና የጅማ ከተማ አውቶብስ ድርጅቶች ተነጣጥለው ራሳቸው ችለውን እንዲደራጁ ወስኗል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ርክክብ ባለመደረጉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በማቋረጡ ለጅማ ቅርንጫፍ መዳከም ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተለይ የጅማ አንበሳ አውቶብስ አገልግሎት ከአዲስ አበባም ሆነ ከኦሮሚያ ክልል በቂ ድጋፍ እየተደረገለት ባለመሆኑ ዕጣ ፈንታው ሥጋት ተጋርጦበታል፡፡