በአሁኑ ወቅት ሮቦቶች የቴክኖሎጂ ርቀትን፣ የሰው ልጆች የፈጠራ አቅምን የሚያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጆች የህልውና ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉበት ፈጠራዎች ስለመሆናቸው የሆሊውድ የሲኒማ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት በሠሯቸው ፊልሞች ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የመጀመርያው ሥጋትም የቴክኖሎጂ ርቀት ጫፍ በሚነካበት ዘመን ሥራዎች በሙሉ በሮቦቶች የሚሠሩበትና ሠርቶ ማደር ለሰዎች እየከበደ የሚሄድ መሆኑ ነው፡፡ ይህ በጥናት የተረጋገጠ ትንበያ ነው፡፡
እንደ ሰው በቋንቋ መግባባት የሚችሉ፣ ያለ ጠባቂ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ሌሎችም ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጡ ተፈጥሯዊ ባህሪያትን ከሰዎች የሚጋሩ ሮቦቶች ብቅ ብቅ ማለትም ጀምረዋል፡፡
ነጭ የቆዳ ቀለም ያላት፣ እንግሊዝኛ፣ ዓረብኛ ሲላት ደግሞ አማርኛ የምታወራው ‹‹ሶፊያ›› የተሰኘችው ሮቦትም አንድም ወቅታዊውን የቴክኖሎጂ አካሄድ፣ አንድም ደግሞ ሮቦቶች በሰዎች አምሳል ተቀርፀው ሰዋዊ ሕይወት እንደሚኖራቸው ጅምር ማሳያም ነች፡፡ የሳዑዲ ዜግነት ካላት ከዚህች ሮቦት በስተጀርባ የኢትዮጵያ ልጆች አሻራ አለ፡፡ የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ ሆና የቆየችው ሮቦቷ ከሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ብቅ በማለት ከአድናቂዎቿ ተገናኝታ ነበር፡፡
በሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ ዝግጅት ላይ ቀርባም ነበር፡፡ የሶፊያን መምጣት የሰሙ ሕፃናት ከነቤተሰቦቻቸው አብረዋት ፎቶ ተነስተዋል፡፡ የአይሲቲ ባለሙያዎች ከፊሉ ልምድ ለመቅሰም፣ የተሻለ ለመሥራት መነሳሳት እንዲፈጥርላቸው ለአምስት ቀናት በቆየው ዓውደ ርዕይ ሲገኙ ልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡ ባለሙያዎችም ፈጠራቸውን ሲያስተዋውቁበት ሰንብተዋል፡፡
ከሶፊያ ባልተናነሰ መልኩ የታዳሚውን ትኩረት ስበው የነበሩ መግቢያ ላይ የነበሩት ኳስ የሚጫወቱ ሮቦቶች ነበሩ፡፡ በተዘጋጀላቸው መጫወቻ ሜዳ ላይ ኳሷን እያደኑ በሚጠልዙት ሮቦቶች ዙሪያ እርስ በርስ ተደጋግፈው የቆሙት ተመልካቾች የሚያዩት ተዓምር ሆኖባቸው በግርምት እርስ በርስ ሲተያዩ ሮቦቶቹን የሠሩት ፈጣሪዎች ደግሞ ከአንደኛው ግርግም ሆነው በኮምፒውተር ላይ አፍጠዋል፡፡
ኳስ የሚጫወቱ ሦስቱን ሮቦቶች የሠሩት ፎርኬ ሮቦቶች ናቸው፡፡ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) ላይ አተኩረው የሚሠሩት ፎርኬዎች ኳስ የሚጫወቱትን ሮቦቶች ለመሥራት ዕውቀት ባያንሳቸውም መሠረታዊ መሣሪያዎችን አጥተው ብዙ ተቸግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህሩ ወጣት ዩሐንስ ታዬ የቡድኑ መሪ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የፎርኬ አባላት መሥራት የሚፈልጓቸውን ሮቦቶች ለመሥራት የሚሆኑ ወሳኝ ዕቃዎችን አገር ውስጥ ስለማይሠሩ በቀላሉ አያገኙም፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በአጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር ገበያ ላይም የሚገኙ አይደሉም፡፡
ስለዚህም ለሮቦቶቹ የሚያስፈልጉ አካሎችን ከውጭ ማስመጣት ነበረባቸው፡፡ ኳሱን ለይተው እንዲያዩ የሚያስችላቸውን ከአናታቸው ላይ የተገጠመውን ካሜራም እንዲሁ ከውጭ ያስመጡት ነው፡፡ አሻንጉሊቱ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስና ኳሱን ወደ መረቡ እንዲጠልዝ የማድረጉን ከባዱን ሥራ የመሥራት አቅም ቢኖራቸውም ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ከመሥራት ያለው የአቅርቦት ችግር ማነቆ ሆኖባው መቆየቱን ዮሐንስ ሲናገር በቁጭት ነው፡፡
ስሜትን ከሰው ፊት አንብቦ ድባቡን መቀየር የሚችል ሙዚቃ አማርጦ የሚጋብዝ ሶፍትዌርና ሌሎችም ዓይነት አዳዲስ ፈጠራዎች በገፍ በቀረቡበት በዚህ መድረክ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዚህ ዓመት በሐርድዌርና ኤሌክትሮኒክ ዲዛይን ባዘጋጀው የፈጠራ ውድድር ላይ ሁለተኛ የወጡት በርኖስ ዲዛይኖችም ተገኝተዋል፡፡ በርኖስ ዲዛይን ሁለተኛ የወጣበት ፈጠራ ሬዲዮ በላፕቶፕና በሌሎች ሬዲዮ ማስደመጥ በማይችሉ ኤሌክትሮኖክሶች ላይ ተገጥሞ ሬዲዮ ማስደመጥ የሚችል መሣሪያ ነው፡፡ ይህ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ላይ የሚገጠመው መሣሪያ ‹‹ቃና ዩኤስቢ›› እንዳሉት ከፈጣሪዎቹ አንዱ የሆነው ሚኪያስ ከበደ ይናገራል፡፡
ይህ የፈጠራ ሥራ እንደ ፍላሽ ዲስክ በላፕቶፕ፣ ዴስክቶፕ የመሳሰሉት ላይ የሚገጠም ሲሆን፣ የሳምንቱን የሬዲዮ ፕሮግራሞች ዝርዝር አካቶ የሚይዝ ነው፡፡ እንዳያመልጥዎ የሚፈልጉትን ፕሮግራምም ቀድቶ ማቆየት ይችላል፡፡ ሬዲዮ የማያስተላፉ ስልኮችን ጉድለት ይሞላል የሚለው ሚኪያስ፣ በዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ተጠቃሚው ጋ እንደሚደርስ ይናገራል፡፡ በርኖስ ተወዳድሮ ካሸነፈበት ቃና ዩኤስቢ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራዎችን ሠርቷል፣ እየሠራም ይገኛል፡፡
ካሉት የፈጠራ ሥራዎች መካከልም በእጅ መዳፍ ልክ የተሠራው ደጋ የተባለው ፈጣን ማቀዝቀዣ ነው፡፡ ይህ ማቀዝቀዣ በሄዱበት ሁሉ ይዘውት መንቀሳቀስ የሚችሉት ዓይነት ሲሆን፣ በረሃማ ቦታዎችን አቋርጠው እየተጓዙ ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት የሚያስችልዎ ግኝት ነው፡፡ ቀዝቃዛ ቢራ ቢያምሮ፣ ቀዛቃዛ እርጎ ቢያሰኝዎ ሌላም ቢፈልጉ የኤሌክትሪክ መኖር አለመኖር ሳያስጨንቆት ባሉበት ሆነው ቀዝቀዝ ማለት ያስችላል፡፡ የሚያስፈልግ ነገር ቢኖር ከላፕቶፕ፣ ዴስክቶፕ፣ ወይም ከሌላ የኃይል ምንጭ ጋር የሚያገናኙት ዩኤስቢ ኬብል ብቻ ነው፡፡ የሚያስፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለማግኘት የግድ ከባልቦላ ጋር የተያያዘ ሶኬት ሳያስፈልግ በዝቅተኛ ኃይል በፍጥነት የሚያቀዘቅዘውን ደጋ ፍሪጅ የሠሩት ስምንቱ የበርኖስ ዲዛይን አባላት ናቸው፡፡
‹‹ከዚህ በፊት ከዩኤስኤአይዲ ጋር በመተባበር ለገጠር ሰዎች ወተት የሚያቀዘቅዙበት ፍሪጅ ዲዛይን አድርገን ነበር፤›› የሚለው ሚኪያስ፣ በገጠርና ከተማ ያሉ ችግሮችን መፍታ የሚችሉ ፈጠራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ተናግሯል፡፡ የታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ትክክለኛ ታሪክ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ሌጀንድ የተባለ ታትሞ የተዘጋጀና በዌብሳይት የተዘጋጀ ኢንፎግራፊክስም አንዱ የበርኖስ ፈጠራ ነው፡፡
በርኖሶች ሌሎችም የማኅበረሰቡ ፈተናዎች የሚሏቸውን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ የሚሆኑ ፈጠራዎችን ይሠራሉ፡፡ እንደ እነሱ ያሉ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችም እንዲሁ ቢተገበሩ ኢትዮጵያን ከችግር የማውጣት አቅም ያላቸውን ፈጠራዎች እየሠሩ እነሆ ማለታቸው አልቀረም፡፡ ችግሩ ግን በአገር ልጅ ዕውቀት እምነት መጣልና ሥራቸውን ማጎልበት ሲያልፍ ኢንቨስት አድርጎ ተግባራዊነታቸውን ማረጋገጡ ላይ ነው፡፡ ከነበረው አንፃር ሲታይ አንዳንድ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም ትኩረት የሚሻ ዘርፍ ነው፡፡