Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የካፒታል ገበያ ላይ ያተኮረ ዓውደ ጥናት ሊካሄድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፋይናንስ ተቋማት ባለሙያዎች የሚሳተፉበትና በካፒታል ወይም በስቶክ ገበያ አሠራር ላይ ያተኮረ ዓውደ ጥናትና ሥልጠና፣ ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ ከሆነው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በሚሠራው ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አስተባባሪነት መካሄድ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

      ዓውደ ጥናቱ ሥልጠናንም በማካተት ከነሐሴ 7 እስከ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አቤቱ መላኩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተዘጋጀው ዓውደ ጥናትና ሥልጠና ላይ ስለአክሲዮን ገበያ ገለጻ የሚያደርጉት ሚስተር ሰርጌይ አይቲያን (ዶ/ር) የተባሉና በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ምሁር መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ሚስተር ሰርጌይ በካሊፎንሪያ ኦክላድ ውስጥ በሚገኘው የሊንከን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተምና የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች ዳይሬክተርም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በዩኒቨርሲቲው በሚገኘው የዘርፈ ብዙ ትምህርት መስኮች የምርምር ማዕከል ኃላፊ ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ሚስተር ሰርጌይ፣ ‹‹Stock Market: Investment and Options›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ስለመጻፋቸውም ስለዓውደ ጥናቱ ከተሠራጨው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

አቶ አቤቱ እንደገለጹት ከሆነ፣ ዓውደ ጥናቱን ማዘጋጀት ያስፈለገው በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ እየተደረገ ካለው ለውጥ ጋር ተያይዞ የአክሲዮን ገበያ ምሥረታ አስፈላጊነት እየታመነበት በመምጣቱ ነው፡፡ በአፍሪካ ከሁሉም አገሮች በፊት ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ብትጀምርም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ዓይነቱ ገበያ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ፣ አገሪቱም ከሁሉ ኋላ ሆና መገኘቷ እንደሚያስቆጭ የሚገልጹት አቶ አቤቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ገበያ ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች በመታየታቸው፣ ቅድመ ዝግጅቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድም በካፒታል ገበያ ላይ ያተኮረ ዓውደ ጥናትና ሥልጠና በማካሄድ ሊመሠረት ስለሚችለው የካፒታል ገበያ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲቻል ለማገዝ ሲባል ዓውደ ጥናቱ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በመጀመርያው ቀን የዓውደ ጥናቱና የሥልጠናው መርሐ ግብር መሠረት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካፒታል ገበያ የሚገኝበት ደረጃን የሚያሳይ ይዘት ያለው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ይኽም የአክሲዮን ደላላ ድርጅቶች የአሠራር ሁኔታን የሚያሳይ ይሆናል፡፡ በሁለተኛው ቀን የአክሲዮን ግብይት፣ የጥሬ ገንዘብ የሒሳብ መዝገብ ሥርዓት በአክሲዮን ገበያ ውስጥ የሚስተናድበትን አሠራር የሚቃኝ መርሐ ግብር ተሰናድቷል፡፡

የካፒታል ገበያ ዓይነቶችና ባህሪያቸውን የተመለከቱ የሥልጠና ዓይነቶችም በዓውደ ጥናቱ መካተታቸው ታውቋል፡፡ የገንዘብ ዝውውር፣ የስቶክ ገበያ ማኔጅመንት፣ ቴክኒካል ትንተናን የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችም ይዳሰሳሉ ተብሏል፡፡ በዓውደ ጥናቱ ለኢንቨስትመንት ባንክ ባለሙያዎች፣ ለብድር ኃላፊዎች፣ ለአማካሪዎች፣ ለካፒታል ድርሻና ኢንቨስትመንት ተንታኞችና ለፋይናንስ አስተዳደር ተማሪዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንት አቤቱ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በአገሪቱ እየታየ ካለው ለውጥ ጋር ተያይዞ ግዙፎቹን የአገሪቱ ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑ፣ የስቶክ ገበያ በኢትዮጵያ የግድ መጀመር አለበት የሚለው ግፊት እየተበራከተ መጥቷል፡፡ የእነዚህ ኩባንያዎችን አክሲዮኖች በስቶክ ገበያ መሸጥ የሚያስችል አሠራር በመሆኑ፣ በስቶክ ገበያ ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ተከታታይ መድረኮች ሊጎለብቱ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች