አዳዲስ የግብርና ምርቶችን ለኢትዮጵያ ለማቅረብ ፍላጎት አላቸው
የጃፓኑ አይሱዙ ሞተርስ ኩባንያ በሽያጭ ወኪሉ በኩል ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የኩባንያው ተሽከርካሪዎች የሚገጣጠሙበት ፋብሪካ በኢትዮጵያ ሊተከል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
ኢቶቹ ኮርፖሬሽን የአይሱዙ ሞተርስ ኩባንያ የሽያጭ ዘርፍን የሚመራ አጋር ኩባንያ ሲሆን፣ ለበርካታ ዓመታትም በኢትዮጵያ የንግድ ወኪል ቅርንጫፉን በመክፈት የአይሱዙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ለገበያ ከሚያቀርቡ የአገር ውስጥ ወኪሎች ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የኢቶቹ ኮርፖሬሽን የአውቶሞቢል ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ከሳቴ ብርሃን መንግሥቴ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ የአይሱዙ መኪኖች የሚገጣጠሙበት ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፡፡
መገጣጠሚያ ፋብሪካው በአገር ወኪሎች አማይነት የሚገነባ ሲሆን፣ የፋብሪካው አምሳያ (ፕሮቶታይፕ) ዲዛይን ለአይሱዙ ወኪሎች ተልኮ ሥልጠናም ጭምር ስለመሰጠቱ ከአቶ ከሳቴ ብርሃን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የመገጣጠሚያው ሙሉ የዲዛይን ዝግጅት በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅም ተጠቅሷል፡፡ ይሁንና የሚተከለው ፋብሪካ አቅምና በዓመት ምን ያህል ይገጣጥማል የሚሉት ጉዳዮች ላይ ወደፊት ምላሽ እንደሚሰጥባቸው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዓመታዊ ሽያጩ ከ3,000 በላይ የሚገመተው የአይሱዙ ሞተርስ፣ ከዚህ ውስጥ በመደበኛው መንገድ ማለትም በኢቶቹ በኩል ሽያጫቸው የሚከናወነው ተሽከርካሪዎች ቁጥር 800 ገደማ ይገመታል ያሉት አቶ ከሳቴ ብርሃን፣ በየጊዜው ዕድገት የታየበት የአይሱዙ መኪኖች አቅርቦት በኢትዮጵያ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እንደገበያው ፍላጎት መጠን ማቅረብ እንዳልቻ የጠቀሱት ኃላፊው፣ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ አጋሩ ከነበረው ከጄነራል ሞተርስ ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ካኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያን ጨምሮ ሌላ ሦስተኛ ወኪል ኩባንያም የአይሱዙ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ለማከፋፈል ስምምነት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኤፍኤስአር እንዲሁም ኤንፒአር የተሰኙትን የአይሱዙ ሞዴል የጭነት መኪኖች ለኢትዮጵያ ገበያ እያቀረበ የሚገኘው ኩባንያ፣ ወደፊት ኤፍቪአር 23 እንዲሁም ኤፍቪአር 33 የተባሉ አዳዲስ ሞዴሎችን ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ እነዚህ የሥራ ተሽከርካሪዎች በተለይ የታሸገ ውኃ ለሚያመርቱና ለሌሎችም ተመራጭ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም የአይሱዙ ምርት የሆኑ አውቶቡሶችን ለኢትዮጵያ ገበያ ለማስተዋወቅ ፍላጎት ስለመኖሩም ተጠቅሷል፡፡
ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ የአይሱዙ ምርቶችን ሲያቀርብ የቆየው ኢቶቹ ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያም ሰሊጥና ቡና በመላክ እየተሳተፈ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በተያያዘ ዜና ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ውስጥ በተካሄደው የጃፓንና የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የንግድ ግንኙነት ፎረም፣ አይሱዙን ጨምሮ አምስት የጃፓን ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ግብርና ተጠቃሚ ያሏቸውን ምርቶች አስተዋውቀው ነበር፡፡ ቶፕኮን የሰኘው ኩባንያ ያቀረባቸው ቴክሎጂዎች በግብርናው መስክ ‹‹ፕሪሲሽን አግሪካልቸር›› እየተባሉ የሚታወቁና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ዕድገት የደረሰባቸውን ደረጃዎች ያካተቱ ውጤቶች ነበሩ፡፡
‹‹ክሮፕስፔክ›› የተሰኘው የኩባንያው ቴክኖሎጂ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀምን፣ የፀረ ተባይና የፀረ አረም አመጣጠንን፣ የውኃ ልኬትንና ሌሎችም ተጓዳኝ ግብዓቶችን በማመጣጠን ለሰብል ምርት እርሻ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በትራክተርና በሌሎችም የእርሻ መሣሪዎች ላይ ተገጥሞ የሚሠራ ነው፡፡ ማሩቤኒ የተሰኘው ሌላኛው የጃፓን ኩባንያም በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ቆይታ ያለውና በንግድ ዘርፍ በተለይ በቡና ላኪነት እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን፣ በጃፓን ከማዳበሪያ አምራችነት ጀምሮ በልዩ ልዩ የኬሚካልና የፕላስቲክ አምራችነት የገዘፈ ስም አለው፡፡ ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ግሪን ሐውስ የፕላስቲክ ሼድ እንደሚያመርትና ይኼንኑ ምርትም ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
ሌሎችም ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ያስተዋወቁበትንና ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር ሐሳብ የተለዋወጡበትን መድረክ ያዘጋጀው ጃፓን ኤክስተርናል ትሬድ ኦርጋኒዜሽን (ጄትሮ) የተሰኘው መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም በኢትዮጵያ ቢሮውን የከፈተው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጥያቄ ሲሆን፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ የአቶ ኃይለ ማርያምን ጥያቄ በመቀበል ተቋሙ ቅርንጫፉን በኢትዮጵያ እንዲከፍት መፍቀዳቸውን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የጄትሮ ኢትዮጵያ ኃላፊ ታካኦ ሴኪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው በኢትዮጵያና በጃፓን ኩባንያዎችና ኢንቨስተሮች መካከል የኢንቨስትመንትና የንግድ መረጃዎችን ያሠራጫል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያዙ ድጋፎችን በመስጠት ያግዛል፡፡ በዚህ ሒደት ቶሞኒየስ የተሰኘው የጃፓን ኩባንያ በቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የራሱን ፓርክ ለመሥራት ከ30 ሔክታር በላይ መሬት መጠየቁንና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ባለፈው ዓመት ስምምነት መፈረሙም ይታወሳል፡፡ ይህም ሆኖ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ስለመሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያትም ባለሀብቶቹ ስለኢትዮጵያ ያላቸው ግንዛቤና መረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል፡፡