በአዲስ አበባ ከተማ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስፋትና ጥልቀት ሲታይ የነዋሪዎች ቅሬታ ወደፊትም ተባብሶ እንደሚቀጥል ያመላክታል፡፡ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች፣ በወረዳዎች፣ እንዲሁም በማዕከል ጭምር ነዋሪዎች በመልካም አስተዳደር ዕጦት ለከፍተኛ ምሬትና እንግልት እየተዳረጉ ነው፡፡ የችግሩን ደረጃ ለማየት የመሀል ከተማና የማስፋፊያ ቦታዎች በሰፊው ይዞ የሚገኘውን የካ ክፍለ ከተማን ማሳያ አድርገነዋል፡፡ አቶ ፈቃደ ተረፈ የየካ ክፍለ ከተማ የሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽሕፈት ቤት የቅሬታና አቤቱታ አወሳሰን ክትትል ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በተለያዩ የመልካም አስተዳደር፣ የቅሬታ መሠረት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውድነህ ዘነበ አቶ ፈቃደን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ቅሬታ ሰሚ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ያለ መዋቅር ነው፣ ከሌሎች ክፍላተ ከተሞች የካ ክፍለ ከተማ የሚለየው ምንድነው?
አቶ ፈቃደ፡- እንደ አዲስ አበባ የሚነሱ ቅሬታዎች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ አብዛኛው ቅሬታ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ እንደ የካ ደግሞ ስንመጣ የካ የማስፋፊያ ቦታ ያለው ክፍለ ከተማ ነው፡፡ ከመሬት ጋር ተያይዞ፣ ከሰነድ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ለአብነት ከካርታ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ፣ ከስም ዝውውር ጋር ተያይዞ፣ ሰነድ አልባን ካርታ ከመስጠት ጋር (ሬጉራላይዝድ ከማድረግ)፣ የሚነሱ በጣም በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች መንግሥት ባስቀመጠው መመርያ መሠረት እየተፈቱ ናቸው ቢባልም አብዛኛው ቅሬታዎች የሚመጡት ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ አንደኛ የሰዎችን መብት አክብሮ ከመንቀሳቀስ፣ ከአገልጋይነት መንፈስ መዳከም ጋር የመጡትን ጥያቄዎች በቀጥታ ከመፍታት ይልቅ የማወሳሰብ ነገር ይታያል፡፡ ቦሌ፣ አቃቂና ከየካ ጋር ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ በእነዚህ ክፍለ ከተሞች ከማስፋፊያ ቦታ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች በቁጥርም ወጣ ብለው ይታያሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ አሥር ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ስድስቱ ማስፋፊያዎች ናቸው?
አቶ ፈቃደ፡- ማስፋፊያዎች ናቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ መሬቶች ስለተያዙ አሁን መንግሥት እያስተናገደ ያለው የ88ቱን እየጨረስን ነው፡፡ የ97ቱን እያስተናገድን ነው፡፡ ከ97 በኋላ ደግሞ በጣም በርካታ ግንባታዎች ተገንብተዋል፡፡ በዚያ መካከል ላይ የሚፈርሱ ቦታዎች አሉ፡፡ ነዋሪዎች በ2003 ዓ.ም. አይፈርስም በ97 በአየር ካርታ የታየ ቦታ ነበርና በሕገወጥ አፍርስ ብለውኛል፣ ባይፈርስብኝ ኖሮ አሁን መንግሥት ባወጣው መመርያ እጠቀም ነበር፡፡ የሚሉ ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ ስትመለከት ላይን ማፕላይ አለ፡፡ ቦታው ላይ ስትሄድ ግን ፈርሷል፡፡ አሁን ይኼንን ግንባታ ቢኖር ኖሮ ይኼ ሰው ይጠቀም ነበር ወይ ስትል አዎ ይስተናገድ ነበር፡፡ አሁን ግን ባለመኖሩ አይስተናገድም፡፡ በዚህ በዚህ መንገድ የቅሬታ ምንጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ቤቱ ሲፈርስ የነበሩ አመራሮች ደግሞ አሁን ላይ የሉም፡፡ መረጃም የለም ስለዚህ ግለሰቡ አሁን ልስተናገድ ይገባል በማለት ቅሬታ ያቀርባል፡፡
ሪፖርተር፡- መሬት ላይ እንግዲህ በአብዛኛው የሚቀርብላቸው የመሬት ቅሬታዎች በተመለከተ መለኪያዎቹ ምንድናቸው፣ ሪፈር ምታደርጉት ላይን ማፖች፣ የጂአይኤስ መረጃዎች ከመጀመርያ ጀምሮ አሉ?
አቶ ፈቃደ፡- መንግሥት ቅድም ያልከውን ጥያቄ ለማስተናገድ 95 በመቶዎቹን ለማስተናገድ ችለናል፡፡ ከስህተት በፀዳ መንገድ 95 በመቶ ማስተናገድ ይቻላል፡፡ መመርያው ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን በ88 ላይን ማፕ የሚታወቀው 88ቱ አይኤስ የመሳሰሉ አሉ፡፡ ቤቱ የማይታይ ከሆነ መንግሥት እንደ መብራት፣ ውኃ ከ88 በፊት ካስገባህ ትስተናገዳለህ፡፡ መብራትና ውኃ ግብርን የከፈልክበት ካለ እንደ አንድ ሰነድ ሆኖ ትስተናገዳለህ፡፡ ምክንያቱም በጂአይኤስ ላይ በፎቶግራፉ ሊነሱ የማይችሉ ቤቶች ይኖራሉ፤ ለምሳሌ ዛፍ ካለ ቤቱ ላይነሳ ይችላል ተብሎ ቢገመት በተለያዩ መንገዶች በ88 የጂአይኤስ አይታይም ቢባል መንግሥት ያስቀመጠው አማራጭ ምንድነው? አንደኛ ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ከ88 በጂአይኤስ ባይታይም በስፋት ላይ አረጋግጠህ ትመጣለህ፡፡ እነዛም ባይታዩም ቅድም ስልክ፣ መብራት፣ ውኃ ከ88 በፊት ካስገባህ ትስተናገዳለህ ማለት ነው፡፡ ከዚያ አያመልጥም፡፡ ካርታ ላለመስጠት እነዚህ ማስረጃዎች አምልጦ የሚወጣ ያለ አይመስለኝም፡፡ በተመሳሳይ 97ትም ላይን ማፕላይ ባይታይ፣ መንግሥት ያስቀመጠው ከ97 በመቶ ከገባለትና በአካባቢው አስተዳዳሪ በወረዳው ተረጋግጦ ከመጣ ይስተናገዳል፡፡ ስለዚህ ቅድም ያልኩህ 95 በመቶ እነዚህን የሚያሟሉ ናቸው፡፡ የማያሟሉ የምትላቸው በጣም ውስን ጉዳዮች ናቸው፡፡ የዚህ ዓይነት እስካሁን ድረስ አላጋጠመንም ቅድም እንዳልኩህ መብራት፣ ውኃ ስልክ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ የግብር ወረቀት እንደ ከ88 በፊት የገበሩ አሉ፤ ግን መብራትና ውኃ ይስተናገዳል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን የሊዝ አዋጅ የወጣው 2004 ዓ.ም. ኅዳር ላይ ነው፡፡ እስከዚህ ወቅት ሰነድ አልባ ግንባታ የገነቡ ሰዎች መስተናገድ አለብን ይላሉ፡፡ በተለይ ከ2003 በፊት የገነቡ ሰዎች መስተናገድ አለብን ይላሉ፡፡ በዚህ ወቅት ገንብተው ሕገወጥ ተብለው የፈረሱ አሉ፡፡ 97 አካባቢ ባላደረው አስተዳደር እያለ ብዙ አፍርሷል፡፡ አሁን ሕጋዊ የተደረጉት እነሱን ጨምሮ ነውና የእነሱስ ባይፈርስ ተጠቃሚ አይሆኑም?
አቶ ፈቃደ፡- በደንብ ይመጣል፡፡ ብዙ ቁጥር ያለ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የደረሰ አለ፡፡ ወረዳ 10 ወደ 50 ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ላይን ማፕ ላይ የሚታዩ 23 ቤቶች አሉ፡፡ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ እኛ በቦታው ላይ የሌለን ቤት እንደገና የማሠራት ሥልጣኑ የለንም፡፡ አሁን ባለው ላይ ነው ሥልጣን ያለን፡፡ ስለዚህ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ለክፍለ ከተማ የተላከና እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የደረሰ ጉዳይ አለ፡፡ እንደ ተገልጋይ ስትመለከተው ተበድለዋል፡፡ ላይን ማፕ ላይ የሉም ተብሎ ዝም ሊባል አይገባም፡፡ ማፕ ላይ ያሉ እየተስተናገደ ነው፡፡ በአስተዳደር ችግር የፈረሰባቸው ለምሳሌ ጉቦ ተጠይቀን ስላልሰጠን ነው ብለው የሚያነሱት ነገር አለ፡፡ የሰጡ በወቅቱ ድነዋል፡፡ ያልሰጡ ደግሞ እኛ ፈርሶብናል የሚሉ አሉ፡፡ እውነትነቱን ደግሞ የምታየው ተመሳሳይ የሆኑ ያልፈረሱ ቤቶች አሉ፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ሥልጣን ያለው አካል ይኼን ነገር አይቶ ቢወስንላቸው ደስተኞች ነን፡፡
ሪፖርተር፡- እስከ 97 ሚያዝያ ድረስ መመርያው አስቁመዋል፡፡ ግን ከዚህ በኋላም የገነቡ ሰዎች ልንካተት ይገባል የሚል ጥያቄዎች ያነሳሉ?
አቶ ፈቃደ፡- አሉ ይመጣሉ፡፡ አሁን የ2003ን ላይን ማፕ ይዘው የሚመጡ አሉ፡፡ ግን መመርያው እሱን እያካትትም፡፡ አሁን በቀጣይ ምን ይሆናል የሚለውን መንግሥት ነው የሚወስነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሊካተት ይችላል የሚሉ ሐሳቦች ይነሱ ነበር?
አቶ ፈቃደ፡- አሁን የተሠሩ ቤቶች በጣም በርካቶች ናቸው፡፡ መንግሥት ሕጋወጥ የሚለው አግባብ ያለው አካል ሳይፈቀድላቸው የተሠሩ ቤቶች ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይኼ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው፡፡ እነሱን መንግሥት ሕጋዊ ያረጋቸዋል? ልማቱን የማይፃረሩ ከሆነ ማስተር ፕላኑን የማያበላሹ ከሆነ ሕጋዊ ያደርጋቸዋል፡፡ ምናልባት ተስፋ ሊኖር ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- የፕሮፖርሽናል ካርታ ያላቸው ሰዎች ያሉ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ እየተስተናገዱ አይደለም፡፡ ቤት ለማደስ፣ ለመሸጥ ለመለወጥ ይቸገራሉ፡፡ ይህ ችግር ያለባቸው ወደ እናንተ ይመጣሉ? ሲመጡስ ምንድነው የሚደረግላቸው?
አቶ ፈቃደ፡- አሁን እንደውም የሆነ ሰርኩላር ወጥቷል፡፡ ከቀበሌና ከመንግሥት ቤቶች ጋር የተያያዙ ቤቶች ካርታ እንዳይወጣላቸው ተደርጓል፡፡ አንድ ሰሞን ተጀምሮ ነበር፡፡ የቀበሌ ቤቶችም ካርታ ይወጣላቸዋል ተብሎ ፕሮሰስ ተጀምሮ በሆነ ምክንያት ቆሟል፡፡ ምናልባት እሱን እስከሚጨርሱ ድረስ ይሁን ወይ ከእሱ ጋር የተደበላለቀ ይሁን አላውቅም፡፡ ግን አሁን ከዚህ ቤቶች ጋር የተደበላለቁ የግል ቤቶች እንዳይሰጣቸው የሚል ሰርኩላር ወጥቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ለግሎቹም ተሰጥቷቸዋል?
አቶ ፈቃደ፡- ይኸውልህ ፕሮፖርሽን የወጣላቸው አሉ፡፡ እነሱ በግንባታ ላይ ይቸገራሉ፡፡ አንዳንድ የተወረሱ ቤቶች የጋራ ማዕድ ቤትና የጋራ መፀዳጃ ቤት መገንባት በተመለከተ አንዱ አካል ሁለቱም ሊፈቅድ ይገባል፡፡ ይኼኛውም ተስማምተው ግንባታውን ሊያካሂድ ይገባል የሚል ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በፕሮፖርሽን ካርታ በፕላን ስምምነት ካላመጡ አይፈቀድላቸውም፡፡ ለቀበሌው ቤት ግን መፀዳጃ ቤት ትፈቅዳለህ፡፡ ለግሉ ግን ፕላን ስምምነት ካላመጡ አይፈቀድላቸውም ትላለህ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ለቀበሌ ፈቅዶ የግል ቤቶችን ፕሮሰስ ውስጥ ታካትተዋለህ፡፡ ምናልባት እሱ መታየት አለበት የሚል ነገር አለ፡፡ ነገር ግን በመልካም አስተዳደር ወረዳዎች ችግሮቹን ይፈታሉ ትክክልም ነው፡፡ አሁን አንዳንድ በኑሮ ደሃ የሆኑ አሉ፡፡ ካርታ ያላቸው ግን ፕሮፖርሽን ካርታ ነው፡፡ የወሰዱት አሁን እነሱን የፕላን ስምምነት ፕሮሰስ አለው፡፡ ከወረዳዎች ጋር እየተነጋገርን ቢያንስ ዘላቂ መፍትሔ ግለሰቦቹ እስኪያበጁ ድረስ ጊዜያዊ መፍትሔ የሚሰጡ ወረዳዎች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ረቂቅ ሊዝ አዋጅ ችግሩን ለመጨረሻ ጊዜ ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ፕሮፖርሽናል ካርታ 50 + 1 የቀበሌውን ቤት መጠቅለል እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ ግንባታዎችንም ሊያደርጉ ይችላል፡፡ የሚመጣላችሁም ምትመልሱት ነገር አለ?
አቶ ፈቃደ፡- ሰው እየመጣ ነበር፣ በእርግጥ ልማት ያፋጥናል፡፡ አሁን ለምሳሌ አንድ ትንሽ የቀበሌ ቤት ያለበት ሰፋ ያለ የግል ይዞታ ይዞ የተቀመጠ አለ፡፡ መንግሥት ዓይቶ እነዚህን ቤቶች ባለይዞታው ጠቅልሎ በሊዝ ወስዶ መንግሥትም ደግሞ ለዚያ ለቀበሌው ተነሺ ተለዋጭ የሚሰጥበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ እኛ ግን ባልወጣ መመርያ ልናስተናግዳቸው አንችልም፡፡ ስለዚህ እሱን መጠበቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ መኖርያ ቤቶች ስንመጣ የቀበሌ ቤቶችና የኪራይ ቤቶች ቁጥራቸው ይታወቃል?
አቶ ፈቃደ፡- ምናልባት ቤቶች አስተዳደር ሊያውቀው ይችላል፡፡ ምክንያቱም መዝግቦ ስለሚይዘው ማለት ነው፡፡ የቤቶች አስተዳደር ምን ያህል የቀበሌ ቤት አለ የኪራይ ቤት አለ የሚለውን ያውቁታል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ትንሽ ግራ የሆነብኝ የቀበሌም ቤት ያልሆኑ የኪራይ ቤቶችም ያልሆኑ ግን የመንግሥት ቤቶች የሆኑ ወረዳ 6 ውስጥ የታዩ ይመስለኛል፡፡ አንድ ችግር ትንሽ ገኖ ስለወጣ ምን ዓይነት የአስተዳደር አዝማሚያዎች ነው ያሉት? የኪራይ ቤቶች የሚተዳደሩበት ሌላ መንገድ አለ?
አቶ ፈቃደ፡- ባልሳሳት እንደ ክፍለ ከተማ ወደ 4,000 ቤቶች ባለቤት የሌላቸው ቤቶች አሉ፡፡ ማለት ቤቶች አሉና እነሱ ተለቅመው ለመንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት ለከተማው አስተዳደር ተላልፈው የተሰጡ ቤቶች አሉ፡፡ ሰዎቹ ለኪራይ ቤትም አይከፍሉም ማን እንደሠራቸውም አይታወቁም፤ የግልም የቀበሌም አይደሉም፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ቤቶች ተለቅመው ለመንግሥት እንደተሰጡ አውቃለሁ፡፡ አንዱ ማሳያ ከባላደራ አስተዳደሩ ተከራየሁ የሚሉት አቶ ዘለዓለም ገብረ እግዚአብሔር የሚባሉ አቤቱታ አቅራቢ መጥተው ነበር፡፡ እውነት ነው ውል አላቸው፡፡ ነገር ግን ከውሉ በኋላ ደግሞ ግለሰቡ ሕጋዊ ደረሰኝ ይሰጠኝ ብለው ባመለከቱበት ጊዜ ሕጋዊ ደረሰኝ አልሰጥም አለ ወረዳው፡፡ እንግዲያውስ ካልሰጣችሁኝ ደግሞ አልከፍልም ብለው አቆሙ፡፡ ፍርድ ቤት ተገባ፣ ፍርድ ቤት ከተገባ በኋላ ፍርድ ቤቱ ያከራያቸው አካል ሕጋዊ አይደለም አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ውሳኔ ሰጥቷል?
አቶ ፈቃደ፡- ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጠበት፣ ከዚህ በመነሳት ደግሞ ግለሰቡ ወረዳ አስተዳደሩን አዋውሉኝ ብለው መጡ፣ ወረዳ አስተዳደሩ ደግሞ ነገ ዛሬ እያለ አቆያቸው፡፡ ይኼን ምክንያት በማድረግ እኛ ዘንድ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ ስለዚህ እኛም ጠየቅን፣ የወረዳ አስተዳደሩ ሲመልስ የካ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጉዳዩን ይዞታል አለ፡፡ ቅድም ካልኩህ ቤቶች ጋር ተደምረው ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን ምላሽ እየተጠባበቅን እያለን ባለንበት ሰዓት ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር፣ ግለሰቡ ኪራይ አልከፍልም ብለዋል፡፡ ኪራይ ሳይከፍሉ ነው የተቀመጡት በሚል ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ተደረገ፡፡ ይኼ ደግሞ ምክንያቱም ግለሰቡ ውል ተዋውሎ ኪራይ ሲከፍል የነበረና ሕጋዊ ደረሰኝ ሰጡኝ ብሎ ባቀረበበት ጊዜ ደረሰኝ አልሰጥህም ተብሎ በተነሳ ክርክር ፍርድ ቤት ቀርቦ እነዚህ ሁሉ ፕሮሰስ እያለ ሰውየው ሕገወጥ አይደለም፡፡ ሕገወጥ ሊባል አይገባም፣ ወደ ሕጋዊ አካልም ቀርቧል ወይ አዋውሉኝ በአስቸኳይ እናይልሃለን ተብሎ ነበር፡፡ በሕገወጥ መንገድም አይደለም ቤቱን የያዘው በሚል መድረክ ፈጥረን ከክፍለ ከተማ የሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር አወያይተናቸዋል፡፡ ስለዚህ የክፍለ ከተማው ካቢኔ ሊያይላቸው ይገባል ብለን አስተላልፈናል፡፡
ሪፖርተር፡- በእርስዎ ፊርማ የወጣ ደብዳቤ ነበርና ጥያቄውስ ምላሽ አገኘ ወይስ አላገኝም?
አቶ ፈቃደ፡- የሚገርምህ ወደ 69 የሚሆኑ አቤቱታዎች ከክፍለ ከተማ ምላሽ ባለማግኘታቸው ተንጠልጥለው ቀርተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል ጊዜ?
አቶ ፈቃደ፡- በትንሹ ከሁለት ወር በላይ ምላሽ አላገኘም፡፡ ይኼን ደብዳቤ ምላሽ ባለመስጠት እንዲጠየቁ ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ከሰናቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህም ቤቶች የሚያስተዳድረው ቦርድ ነው፡፡ ቦርዱም የሚጠቀምባቸው ሪሲቶች እኔ እንደ ተመለከተኳቸው ሕጋዊ አይደሉም፡፡ ይኼ ችግር ሲነሳ ደግሞ ቦርድ ፈርሷል የሚል ነገር ተነሳ እሱ ላይ ያለው ነገር ምንድነው?
አቶ ፈቃደ፡- እሱም አስገራሚ ነገር ነው፡፡ አንደኛ በወቅቱ ሲጠቀምበት የነበረው ሴሪ ቁጥር የሌለው ደግሞ በገቢዎች ባለሥልጣን ታትሞ የወጣ ደረሰኝ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ቦርዱ ቤት እስከ ማከራየት እየደረሰ፣ እንዴት ነው ሕጋዊ አይደለም የምትለው? ማን ነበር ይኼንን አካል የሚመራው ወረዳው ተጠያቂ መሆን አለበት ብለናል፡፡
ሪፖርተር፡- የወረዳው ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ነው የሚመራው የሚል ነገር አለ?
አቶ ፈቃደ፡- ልክ ነው አንዳንድ ጊዜ የንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊም ይመራል፡፡ አንዳንዴ ምክትል ይሆናል፡፡ ከዚያም ሊወርድ ይችላል፡፡ ግን አሁን ይኼ ቦርድ ሕጋዊ አልነበረም ማለት የሕዝብ ሀብት በማን ሲተዳደር ነበር? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አቶ ዘለዓለም ይኼን ጥያቄ ካነሳ በኋላ ነው ቦርዱ የፈረሰው፡፡ ሕጋዊ ብለህ ወደ ማፍረስ የሄድከው በምን ሥሌት ነው፡፡ ይኼ ትንሽ አወዛጋቢ ነው፡፡ ምናልባት ወረዳው ይጠየቃል፤ ምክንያቱም ወረዳው ስለሚያስተዳድረው፡፡
ሪፖርተር፡- ከቤት ኪራይ ቦርድ የሚሰበሰብ ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ለሚሰጠው ሪሲት ደግሞ ሴሪ ቁጥር የለውምና በሕግ ፊት ተቀባይነት የሌለው ሪሲት እንደመሆኑ ራሱ ገንዘቡ በትክክለኛው ዓላማ ውሏል? እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ሊያስነሳ አይችልም፡፡
አቶ ፈቃደ፡- እሱን ነው እኔ የምልህ፡፡ ይኼ ቦርድ አይታወቅም ከተባለ እንዴት ነበር ሲያስተዳድር የነበረው? በጣም በርካታ ብር ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ ዘለዓለም ወደ 24,000 ብር ነው በወር ሲከፍል የነበረው፡፡ ከዚያም በላይ ቤቶች ይከራያሉ፣ በምን ደረጃ ነው ገንዘብ የሚገባው ማነው የሚያስገባው ባንክ ይገባል ወይ መንግሥት ያውቀዋል? አያውቅም? ስለዚህ ቅድም እንዳልኩህ ወረዳ አስተዳደሩ ተጠያቂ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ ቤቶች አሁን መተዳደር ያለባቸው እንዴት ነው?
አቶ ፈቃደ፡- አዎ የቤቶቹ ስታንዳርድ በአዋጅ 20/67 ከ100 ብር በላይ የሆኑ ቤቶችን የኪራይ ቤቶች ሲያስተዳድረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን በዚያ ኪራይ ቤቶች ተወርሰው ነበር? ወይስ አይደለም? የሚለው ነገር ማስረጃ ይጠይቃል፡፡ አሁን ከቤቶቹ ጥራትና ትልቅነት ተነስቶ ስትመለከተው የሆነ ነገር የሚያመላክት ነገር አለ፡፡ እንዴት በወረዳ ደረጃ ቀረ የሚል የሆነ ጥያቄ ያጭርብሃል፤ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ከመረጃ መደበላለቅ፣ ከመረጃ ማጥፋት ኪራይ ቤት እሱን ለቆ በወረዳ ደረጃ እየተዳደረ ነው የሚለው አይታወቅም፡፡ ይኼም አንድ ጥያቄ ነው፡፡ በራሱ ምናልባት ባለቤቱ ማነው የሚለው ጥያቄ አዋጅ ቁጥር 47/67 እነዚህ ቅፅ ዜሮ ዜሮ ላይ ተወርሰዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች የማን ናቸው? የሚለውን ነገር ፋይል ማኅደር ማገላበጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ዝም ብለህ ስትመለከተው ግን ቤቱ ባለቤት አልባ የሆነ ነገር ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ካናንተ ዘንድ በርካታ የመኖሪያ ቤትም የመሬትም ችግሮች ይመጣሉ፡፡ እናንተ ትመረምሩና መፈታት ያለበት ጉዳይ ወደ ሥራ አስፈጻሚ ነው ልትልኩ የምትችሉት፡፡ ሥራ አስፈጻሚው እናንተ የምትልኩትን በደንብ ጊዜ ሰጥቶ በመመልከት በኩል ያለው ደረጃ እንዴት ነው?
አቶ ፈቃደ፡- የኛ ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ይሰጣል፣ ቅሬታዎችን ያያል፣ ይመረምራል፡፡ ከመመርያ ጋር ያገናዝባል፡፡ ከዚያ በኋላ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ውሳኔ በሚሰጠው ላይ ቅድም እንዳልኩህ በመመርያ ቁጥር ደንብ ቁጥር 78/2008 ጽሕፈት ቤቱ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የሚቀርቡለትን ውሳኔዎችና ቅሬታዎች ይመረምራል፡፡ ከተገቢው ሕግ ጋር ያያል፣ ከዚያም በኋላ ይወስናል፡፡ ውሳኔውንም ደግሞ ያስፈጽማል፡፡ ስለዚህ ይኼንን ሲያደርግ የሚገጥመው ችግር አለ፡፡ ምርመራችንን የሚያደናቅፉ ምላሽ የማይሰጡ አካላት አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ምርመራ ይቆማል፡፡ ምላሽ ካልሰጡህ በመጨረሻ ውሳኔውን ለመስጠት ትቸገራለህ፡፡ አሁን ያለው ችግር ምንድነው? ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቀረቡላቸው ለምሳሌ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው? አካላት እንዲጠየቁ አላደረጉም፣ ባለማድረጋቸው ደግሞ እኛ ውሳኔ ልንሰጥ አልቻልንም፡፡ 60 ምናምን አካባቢ ምላሽ ያላገኙ ጉዳዮች አሉ፡፡ 21 አመራሮች መጠየቅ አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የኅብረተሰቡ ስሜት ምንድነው? ሰዎች ሲጉላሉ ብዙ ቦታ ደክመው ችግራቸው ሳይፈታ ሲቀር ወደ እናንተ ይመጣሉ፡፡ እናንተም ደግሞ የልብ ልብ ትሰጧቸዋላችሁ፡፡ በደንብ ዓይታችሁ እንደሚፈታ እርግጠኛ ሆናችሁ ምላሽ ከሰጣችሁ በኋላ እንደገና ወደ እዚያ ሄዶ ሲቀረቀር ምንድነው የሚፈጥረው ስሜት?
አቶ ፈቃደ፡- ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ በመንግሥት ላይም ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ከባድ ነው፡፡ አሁን የምታያቸው ከዚህ በፊት የተከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ባለመፍታታችን የተከሰቱ ነውጦች፣ ውጤታቸው ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ ጽሕፈት ቤት ተስፋ አድርጎ መጥቶ ምንም ዓይነት ነገር ሳያገኝ ሲቀር አንደኛ በጽሕፈት ቤቱ ላይ፣ በመንግሥት ላይ፣ በአስተዳደሩ ላይ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ይኼ ደግሞ ውሎ አድሮ የትም መድረክ ላይ ብዬዋለሁ፣ ፈንጂ ነው የሚሆነው፡፡ እውነቴን ነው የሕዝብ ነውጥ ያስነሳል፡፡ የሕዝብ አመፅ ያስነሳል፡፡ በመንግሥት ላይ ያለ እምነት ይቀንሳል፣ የምታያቸው ነገሮች የተከሰቱት ከዚያ ነው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም መድረክ እስከ ከተማ ድረስ ጉዳዩን አንስቼዋለሁ፡፡