Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርገና ምንም ያልተነካው የኢኮኖሚ ጉዳይ

ገና ምንም ያልተነካው የኢኮኖሚ ጉዳይ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዓህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ፣ በአገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድጋፍ እንደተቸራቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በመሳፍንት የተበታተነችውን ኢትዮጵያ አንድ አድርገው እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያልተዳፈነ ፍቅር ተጎናፅፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሁለት መቶ ዓመታት የማይዳፈን ፍቅር ከኢትዮጵያውያን ሊያገኙ እንደሚችሉ፣ በአዲስ አበባ በተደረገላቸው የድጋፍ ሠልፍ ላይ አንዲት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊት ይዛ የወጣችውን መፈክር ብቻ ዓይቶ ማወቅ ይቻላል፡፡ የያዘችው መፈክር ‹አገሬን ስላከበርክ አከበርኩህ› የሚል ነበር፡፡ በየትኛውም ዘመን የነበሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው እንዲህ ናቸው፡፡

በዚህ ዘመን የሕዝብን ሙሉ ፍቅርና ክብር ለማግኘት ፍቅሩም ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን አንድነትን ከመፍጠሩ ባሻገር የሚቀረው ነገር አለው፡፡ ለዚህ ዘመን ከፖለቲካዊ አንድነት ባሻገር የሰዎች ኢኮኖሚያዊ ሕይወትም በመንግሥት ፖሊሲ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ በዓይን ስለሚታዩት የከተማ ፎቆች ብቻ ሳይሆን በዓይን ስለማይታዩት ስለሚራቡ፣ ስለሚጠሙ፣ ስለሚታረዙና መጠለያ ስላጡ ብዙ ሚሊዮን ሕዝቦች ሕይወትም ግድ እንደሚላቸው አልጠራጠርም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝባዊ አንድነት ፖለቲካው የሰጡትን ትኩረት ያህል ለኑሮ ደረጃ መሻሻል እንዲሰጡ በፖለቲካው እንደተሳካላቸው፣ በኢኮኖሚውም እንዲሳካላቸው ሁላችንም በሙያችን ልናግዛቸው ይገባል፡፡ ስለሚታየው ብቻ ሳይሆን ስለማይታየውም እንንገራቸው፡፡

እሳቸው ከመጡ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የሚያሳድጉ፣ የመንግሥት ተቋማትን በግልና በመንግሥት ሽርክና እስከ መሥራት የደረሱ አንዳንድ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ስለወሰዱ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ኦፊሴላዊ ዋጋና የጥቁር ገበያ ዋጋ እየተቀራረቡ መጥተዋል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር የፈጠሩዋቸው ትብብሮችና ዕይታን በቀጣና ደረጃ የማስፋት ሥራዎች ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡ ይሁንና የሸቀጦቻችን ዋጋዎችና የብራችን ምንዛሪ መጣኝ ከጎረቤቶቻችን ጋር በምናደርጋቸው የንግድ ግንኙነቶች ተጠቃሚም ተጎጂም ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡ ለአብነት አንዳንድ ምሳሌዎችን ወስደን እንመልከት፡፡

የሠራተኛው ዝቅተኛ ደመወዝና ለምግብ እንኳን የማይበቃ የኑሮ ሁኔታ፣ እንዲሁም የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበት እንደ ቀጠሉ ናቸው፡፡ አጠቃላይ የዋጋ ንረት አመልካች በሁለት አኃዝ ላይ እንደተንጠለጠለ ከራረመ፡፡ በሦስት ወራት ውስጥ የኢኮኖሚ ለውጥ መታየት አለበት በሚል ጀብደኝነት ሳይሆን፣ ወደ ፊት ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣል ከሚል እሳቤ አንዳንድ ነጥቦችን አነሳለሁ፡፡

ዓምና በፋሲካ ከነበረበት 150 ብር አሻቅቦ ከ170 እስከ 180 ብር ገብቶ አስደንግጦን የነበረው የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ፣ ዘንድሮ ከፋሲካ በኋላም 300 ብር በመድረሱ ለሥራ መስክ ከወጣሁበት በደቡብ ክልል የዳውሮ ዞን ዋና ከተማ ተርጫ ርካሽ ነው በሚል አንዱን ኪሎ በ200 ብር ሒሳብ ገዝቼ መጣሁ፡፡ ቅቤውን ለማንጠር አስፈላጊ ከሆኑት ቅመማ ቅመሞች ኮረሪማ ለመግዛት ከባለቤቴ ጋር ለቤታችን ቅርብ ወደ ሆነው አስኮ ገበያ ጎራ ብለን ነበር፡፡ የአንድ ኪሎ ኮረሪማ ዋጋ 360 ብር ሆኖ ስለጠበቀን ከመገረምም አልፎ አስደንግጦናል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደማደርገው ወዲያው ወደ አዕምሮዬ የመጣው ጉዳይ ይኼንን ዋጋ ዝቅተኛ የወር ገቢ ከሚያገኘው ከሠራተኛው የወር ደመወዝ ገቢ ጋር ማነፃፀር ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስነበበው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች የሚያገኙት የተጣራ የወር ደመወዝ ገቢ 600 ብር ሁለት ኪሎ ኮረሪማ ሊገዛም እንደማይችል አሰላሁ፡፡ ሰሞኑን የዝዋይ የአበባ እርሻ ልማት ሠራተኞች በሚከፈላቸው 800 ብር ያልተጣራ ደመወዝ ገቢ ቅር ተሰኝተው፣ ከአስቀጣሪያቸው ጋር አተካራ ውስጥ መግባታቸውንም ከኮረሪማው ዋጋ ጋር አነፃፀርኩ፡፡ ለሐዋሳው ግጭት የኢንዱስትሪ ፓርኩ ደመወዝም እንደ አንድ ምክንያት መነሳቱን በሽውታ ባገኘሁት መረጃ መሠረት፣ ኢኮኖሚያዊው የኑሮ ሁኔታ ጉዳይ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ዓብይ ችግር እንደሚሆን የሚያመለክት እንደሆነም ተገነዘብኩ፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለሥልጣናት፣ ‹‹ርካሽ ጉልበት አለን፣ ኑና መዋዕለ ንዋይ አፍስሱ፤›› ከተባሉት የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጋር እንዴት እንደ ምንስማማም አሰብኩ፡፡ ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ርካሽ ጉልበትና ርካሽ የኃይል ምንጭ ፍለጋ ከባንግላዴሽና ከስሪላንካ ነቅለው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡት፣ ከእዚህም ፋብሪካዎቻቸውን ነቅለው ቢሄዱ ሊገጥመን የሚችለውን ችግር ገመትኩ፡፡

ወደ ሥራ በፍጥነት ገብተው የሥራ አጡ ቁጥር እንዲቀንስ የሚፈለጉት ወጣቶች ለቤት ኪራይ በማትበቃ የወር ደመወዝ፣ የወላጆቻቸውን ቤት ለቀው ሥራ ተቀጥረው ርቀው ለመሄድ እንደማይፈልጉ የታመነ ነው፡፡ ሥራው እነሱን ፍለጋ ቤታቸው ድረስ ይምጣላቸው ማለትም የማይቻል ጉዳይ ነው፡፡ ሥራ ፈላጊው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ሥራ ካልተቀጠረና እናት አባቱ ቤት ተቀምጦ የሚሠራ ሥራ የሚጠብቅ ከሆነ፣ ምን ያህል ወጣት ሥራ ሊያገኝ እንደሚችል ማሰብ ግራ አጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ወጣቱ ለምን አገሩን ጥሎ እንደሚሰደድም በአገሩ ውስጥ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራት ዕድል አለመፈጠር እንደ በቂ ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡

ከቤት ኪራይ ተርፎ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለምግብና ለልብስ ወጪ በቂ ገቢ ለማግኘት፣ ቢያንስ ሦስትና አራት ሺሕ ብር የወር ደመወዝ ገቢ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ የሠራተኞች መብት ተሟጋች የሆነው የዓለም የሥራ ድርጅት በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ከድህነት ወለል በታች ለሠራተኞች እንዳይከፍሏቸው ቢከራከርም፣ ስለኢትዮጵያው ስድስት መቶ ብር ወይም ሃያ ዶላር ገደማ የአንድ መቶ ስልሳ ሰዓታት ወይም የአንድ ወር ደመወዝ ክፍያ በቀን ከአንድ ዶላር በታች መሆን ጉዳይ ድምፁን አሰምቶ አያውቅም፡፡

ዝርዝር የሥራ ቅጥርና ደመወዝ አወሳሰንና እንዲሁም ዝርዝር የሸቀጦች ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት የገበያ ኢኮኖሚ ጉዳይ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ጥናት መስኩም የግል ኢኮኖሚ (Microeconomics) ጉዳይ ቢሆንም፣ ዝርዝሩ ለጥቅሉ ጥቅሉም ለዝርዝሩ አስተዋጽኦ ስለሚያደርጉ የፖሊሲ ጉዳይ ከሆነው የብሔራዊ ኢኮኖሚ (Macroeconomics) ጉዳይ ነጣጥሎ መመልከቱ በቂ አይደለም፡፡

ስለሆነም ከላይ የተመለከትናቸውን የሥራ ቅጥርና የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋዎች ሁኔታ የመሳሰሉት ውዝግቦች የሚከሰቱት በሁለት ተወራራሽ ምክንያቶች እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ የዝርዝር ሸቀጦች አወሳሰን የገበያ ኢኮኖሚ ጉዳይ ሲሆን፣ ሁለተኛው የጥቅል አገራዊ ምርት መጠን ጥቅል የሥራ ቅጥር ሁኔታና የጥቅል ዋጋ አመልካች የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ የብሔራ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን ችግር ማስወገድ የሚችለው ጥሬ ገንዘብ የሚያሠራጨውና የንግድ ባንኮች ጥሬ ገንዘቡን ከሚገባው በላይ፣ አርብተው የዋጋ ንረት እንዳይፈጥሩ የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ነበር፡፡

በብዙ አገሮችም ብሔራዊ ባንክ ይኼንን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ይደረጋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች እንዲያውም ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች በጋራ ያቋቋሙት ድርጅት ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ይህን ኃላፊነቱን ከመወጣት ይልቅ፣ በፖለቲካው ጉያ ውስጥ ተደብቆ የቆየው ብሔራዊ ባንክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም በቂ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡  

የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛንን አዛብቶ አገሪቱን ያለ ውጭ ምንዛሪ ያስቀረው ብሔራዊ ባንክ፣ ሞርጌጅ ባንክ በሚል የመጠሪያ ስም በበርካታ አገሮች ልዩ ትኩረት የተሰጠውንና በደርግ ጊዜም ብዙ የመንግሥት ሠራተኞችን የቤት ባለቤት ያደረገውን የቤቶችና ኮንስትራክሽን ባንክን ያለ በቂ ምክንያት ከንግድ ባንክ ጋር የቀላቀለውን ብሔራዊ ባንክ፣ በዝቅተኛ የቁጠባ ወለድ መጣኝ ቆጣቢው ደሃ ሕዝብ እንዲበዘበዝ ያደረገውን ብሔራዊ ባንክ፣ የልማት ባንኩን አንድ አራተኛ ሀብት የተበላሸ ብድር ዝም ብሎ የተመለከተን ብሔራዊ ባንክ፣ በዋጋ ንረት ሕዝቡ ሲንገበገብ ብሮችን ወይም ምንዛሪዎችን ወደ ገበያው ውስጥ ሲረጭና ንግድ ባንኮች የተረጨውን ምንዛሪ ከልክ በላይ በብድር ሲያረቡ ዝም ብሎ የተመለከተን ብሔራዊ ባንክ፣ የብር ሸቀጦችን የመግዛት አቅም ተዳክሞ በውጭ ምንዛሪ ተመን ዋጋው እንዲረክስ ያደረገውን ብሔራዊ ባንክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀላሉ ነው የተመለከቱት፡፡

ብዙ የአፍሪካ አገሮች በሰነዶች የገንዘብ ገበያ መርህ ሲመሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች የሰነዶች ገንዘብ ገበያ ቢቋቋም ካፒታልን አሰባስቦ ለአገሪቱ ዕድገት ይጠቅማል ብለው ቢጠይቁም፣ የጥቂቶች ፖለቲካ አጀንዳን ለማሳካት ብሎ ኢትዮጵያ በባንክ ብድር የገንዘብ ገበያ መርህ ብቻ እንድትመራ ያደረገ ብሔራዊ ባንክ፣ በአማርኛ ሪፖርቶቻቸው ጥሬ ገንዘብን (Money) እና ገንዘብን (Finance) በጥሬነት ደረጃ ለያይተው የማይናገሩ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ (Monetary Policy) አውጪ ባለሥልጣናት እንዲበራከ ያደረገውን ብሔራዊ ባንክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀላሉ ነው የተመለከቱት፡፡ 

አዳዲስ ተሿዋሚዎች የተመደቡለት ቢሆንም፣ ተሿዋሚዎቹ ምን ያህል ያሻሽሉታል የሚለው ጉዳይ አልታየም፡፡ ኢኮኖሚክስ እንደ ሐኪሙ፣ እንደ መሐንዲሱ፣ እንደ አካውንታንቱ በተሾሙበትና በተመደቡበት ቦታ አገልግሎት በመስጠት ሕዝብን የሚጠቅሙበት ሙያ ሳይሆን፣ ዓሳ አጥምዶ ከማብላት ዓሳ ማጥመድን ማስተማር እንደሚባለው በመጽሐፍ የሚያውቁትን ለሕዝብ በማሳወቅ ለሕዝብ የበለጠ መጥቀም የሚቻልበት ሙያ እንደሆነ፣ እኔንም በሙያው ለመጻፍ ያነሳሳኝ ይህ እምነቴ እንደሆነ ከእዚህ በፊት በጻፍኳቸው ጽሑፎች በተደጋጋሚ ገልጫለሁ፡፡ በተለይም ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን በተሰኘው ሁለተኛው መጽሐፌ እንደ መግቢያ ሐሳብ ተጠቅሜአለሁ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ውስብስብ ኢኮኖሚ ላላቸው አገሮች የብሔራዊ ባንክ ገዥነትን ለሚያክል የሕዝብኑሮ ደረጃን ወሳኝ ቦታ ከፍተኛ ሹመት ግን፣ ቢያንስ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲ በገንዘብ ኢኮኖሚ መመረቅንና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለበርካታ ዓመታት መሥራት  እንደ ቅድመ ሁኔታ እንዲታይ አስተያየት ስሰጥም ቆይቼአለሁ፡፡

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ በፕላን ኮሚሽን ውስጥ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን በማቀድ የተወሰኑ ዓመታት ልምድ ቢኖራቸውም፣ ኮሚሽኑ ቁሳዊ ምርቶችን እንጂ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦትን ያቅድ ስላልነበረ በትምህርት ዝግጅታቸውም የኢንቫይሮመንት ኢኮኖሚስት እንጂ፣ የገንዘብ ኢኮኖሚስት ስላልሆኑ ምን ያህል ሊያሻሽሉት እንደሚችሉ ጥርጣሬ አለኝ፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚጽፉ አንድ ኢኮኖሚስት በአንድ ወቅት ‹‹ሰሜድ ኢን ተፈራ ደግፌ›› በማለት የባንክ ሥርዓቱ በንጉሡ ዘመን የነበሩት የብሔራዊ ባንክ ገዥ እንደፈጠሩት ያልተቀየረ እንደሆነ ገልጸውታል፡፡ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ስለአገሪቱ ኢኮኖሚ ውይይት እንድናደርግ በኤፍኤም 97.1 ከእኔ ጋር የተጋበዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማክሮ ኢኮኖሚ መምህር፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያወዛገበው ብሔራዊ ባንኩ እንደሆነ ተናግረው ተመሳሳይ አቋም ይዘናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት እኔ በፖለቲካው ብመራም ባለሙያዎች ደግሞ በሙያቸው ይመሩኛል ሲሉ ሰምቼአቸዋለሁ፡፡ ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሙያዬ የምመክራቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚ ማሻሻል ከፈለጉ፣ በቅድሚያ ሊያስተካክሏቸው ከሚገቡ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ብሔራዊ ባንኩ የመጀመርያው እንደሆነ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለኢኮኖሚው ጉዳይ በቂ ትኩረት አልሰጡም የምልበት ሌላም ጉዳይ አለኝ፡፡ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ከቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱን ስከፍት በጊዜ ጥበት ምክንያት ለመስማት ያልቻልኩትን ምሁራን ስለኢኮኖሚው ኮንፈረንስ አድርገው ካበቁ በኋላ፣ የኮንፈረንሱ አዘጋጅ የሆነው የአቶ መለስ ዜናዊ አካዳሚ ፕሬዚዳንት የመዝጊያ ንግግር ሲያደርጉ ሰማሁ፡፡

የአካዳሚው ፕሬዚዳንት ተሳታፊዎቹ ሳያውቁት ልማታዊ መምህራንን እየመለመሉ እንደነበር፣ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አንድ ብቻ ልማታዊ ሰው እንደነበር እሳቸውም አቶ መለስ ዜናዊ እንደነበሩ ገለጹ፡፡

ሁለት ነገሮች ወደ አዕምሮዬ መጡ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የለውጥ ማዕበል ጋር የማይመጥን፣ ወጣቱና ምሁራን የሊበራሉንም ሆነ የልማታዊ መንግሥቱን ኢኮኖሚ ግራ ቀኙን ዓይተው እንዳይመዝኑ በግብር ከፋዩ ገንዘብ የርዕዮተ ዓለም አካዳሚ ከፍታ በአንድ የኢኮኖሚ መስመር ሰዎችን እያጠመቀች መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው በብቸኛው ልማታዊ ሰው በእሳቸው ራዕይ ነው የምንኖረው የሚለውን አስተሳሰብ አጠገባችን አስቀምጠን፣ የራሳችን የሆነ አዲስ አስተሳሰብ እንዴት ሊኖረንና ሊዋሀደን እንደሚችል ግራ የሚያጋባ መሆኑ ናቸው፡፡

‹በሰው ራዕይ ነው የምኖረው፣ የራሴ የሆነ ራዕይ የለኝም› የሚል ሰው ራሱን በራሱ የማወቅና የማሰብ ነፃነት የነፈገ ሰው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለተመራማሪ ኢትዮጵያውያን የሚመጥን አስተሳሰብ አይደለም፡፡

የቀድሞ አስተሳሰብ በሙሉ ስህተት ነው ባልልም፣ በአዲስ አስተሳሰብ ለመራመድ በሕዝብ ገንዘብ ተገዝቶ የሕዝብን ጭንቅላት ለመቆጣጠር የተሞከረ ስህተት የነበረን የቀድሞ አስተሳሰብ ከእነ ምልክቶቹ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ የግለሰቦችን ነፃነት ላለመጋፋት ግለሰቦች የራሳቸውን የርዕዮተ ዓለም ትምህርት ቤት ከፍተው መማር ለሚፈልግ ማስተማር ይችላሉ፡፡ በሕዝብ ገንዘብ ይህን ማድረግ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ 

እነዚህን ከላይ የገለጽኳቸውን ትኩረት የሚሹ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ለአብነት ገለጽኳቸው እንጂ፣ የማይጠቅመውን የአሮጌውን አስተሳሰብ ላለማስታወስ አስወግዶ በአዲስ ለመተካት የሚያስፈልጉ ሥር ነቀል ለውጦችን ለማምጣት በፖለቲካ፣ማኅበራዊናኢኮኖሚያዊ ሕይወታችን ውስጥ ተሸንቅረው ያሉና ወደኋላ ሊጎትቱን የሚችሉ አስተሳሰቦችና ድርጊቶችን ቢያንስ በግብር ከፋዩና በሕዝብ ገንዘብ ማራመድ እንደማይቻል ወስኖ፣ ከእነ ምልክቶቹ ማጥፋት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ፎቶግራፍም እኮ ብዙ ነገር ይናገራል፣ ያስታውሳል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...