Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር ፍቅርና የንግግር ተውህቦ ሲገመዱ 

 ፍቅርና የንግግር ተውህቦ ሲገመዱ 

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም መኮንን 

‹‹ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ አይቀናም፣ አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልንም አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለአመፃ ደስ አይለውም፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይፀናል፤›› መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕራፍ ፲፫ ከቁጥር ፬ ፯::

ዶ/ር ዓብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ እነሆ የአራተኛ ወራቸው መባቻ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተከታታይ 100 ቀናት በላይ በደስታና በተስፋ አሳለፈ፡፡ መጪው ጊዜም ብሩህ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በሐምሌ ልደታ ድንቅ ታሪክ አዩ፡፡ ከሃያ ዓመታት በኋላ ለኤርትራ ሕዝብ ‹‹ፍቅርን፣ ይቅርታንና መደመር››ን ይዘውለት የሄዱትን ዶ/ር ዓብይን የአስመራ ከተማ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በእቅፍ አበባና በዘንባባ ተቀበለ፡፡

በዓሉ ግርማ ሰሜናዊ ኮከብ ብሎ ያንቆለጳጰሳት አስመሪና በሐሴት፣ በፍንጠዛ፣ በፈንዲሻና በማኅሌት ተፍነከነከች፡፡ ‹‹ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር››ም ለሁለቱ ሕዝቦች ላለፈውም ሆነ ለመጪው ጸያሔ ፍኖት ሆኑ፡፡ 

በኮስታራ ገጽታ የሚታወቁት ቁመተ ሎጋው ኢሳያስ ሲስቁ፣ ሲፈግጉ፣ ሲፍለቀለቁና በዶ/ር ዓብይ ንግግር ወዲያው፣ ወዲያው ሲያጨበጭቡ ታዩ፡፡ በ‹‹ፍቅርና ስለፍቅር›› ተሸነፉ፣ ተማረኩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ በላይ ፈነጠዘ፡፡ ታሪከኛዋ ሐምሌ ልደታ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝቦች በደስታ አሰከረች፡፡ ቅዱሳን መላዕክት በሁለቱ አገሮች ሰማያት ላይ አሸበሸቡ፡፡ 

ዶ/ር ዓብይ በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን ልብ ውስጥ ለመግባት ከረዷቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ ያላቸው የንግግር ተውህቦ አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የዘረኝነት ጠንቅ አዕምሮ ውስጥ ሥር ሰዶ ስለሚደረጅ በቀላሉ አይነቀልም፣ ወይም አይገረሰስም፡፡ ዶ/ር ዓብይ ይህን መርዝ ለመንቀል በአዕምሯችን ውስጥ መልካም ፍሬ ያለው ዘር እየዘሩ ነው፡፡ ‹‹ስለፍቅርና በፍቅር፣ ስለይቅርታና በይቅርታ›› እንኖር ዘንድ ከንግግር ተውህቦ ጋር በልባችን ላይ የማይጠወልግ የፍቅር ችግኝ ተክለዋል፡፡ ይህ ችግኝ በአረም ታንቆ እንዳይጠፋ መንከባከብ ይኖርብናል፡፡

የሁለቱ አገሮች ከመቶ ሺሕ ሕዝብ በላይ ያለቀበትና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የቆሰሉበትን፣ በቁጥር ሊገመት የሚከብድ ንብረትና ሀብት የወደመበትን፣ ቤተሰቦች የተለያዩበትን፣ ወንድማማች ሕዝቦች የተላለቁበትን ጦርነት አካሂደዋል፡፡ ወደ ቀድሞው ግንኙነታቸው እንዲመለሱ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ብዙ ደክሟል፡፡ ያልተደረገ ጥረት አልነበረም፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ ፍቅር ግን አሸነፈ፡፡ ከፍቅር ስለሚወለደው ትህትና አንድ ብሒል እጠቅስ ዘንድ ይፈቀድልኝ፡፡

ሁለት መንገደኛ ውሾች ከተለያዩ አቅጣጫ በአንድ ጠባብ መተላለፊያ ቦታ ይገናኛሉ፡፡ ትንሽ እንኳን ቢገፋፉ ተንሸራተው ወደ ገደል የሚገቡበት አደገኛ ሥፍራ ነው፡፡ ይኼን በመረዳት አንደኛው ውሻ ለጥ ብሎ ተኝቶ ሌላው በላዩ ላይ ተራምዶ እንዲያልፍ አደረገው፡፡ ከእዚያም እሱም ተነስቶ በሰላም መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሐምሌ አንድና ሁለት ቀናት በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አዕምሮ ላይ የፈሰሰው ሐሴትና የፍቅር ዝናብ የትህትና ውጤት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ 

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ያቀረበችውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የተደረገው ጥረት ተዓምር ፈጥሯል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል አዲስ የወዳጅነት ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎችም ለሁለቱም አገሮች የሚጠቅሙ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ 

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንደተናገሩት፣ ‹‹ዛሬ በአስመራ ሕዝቡ ወጥቶ ያሳየው ትዕይንት ሌላ ተጨማሪ ንግግር አያስፈልገውም። የ‹እንኳን ደህና መጣችሁ› መልዕክት ብቻ አይደለም፡፡ ከልቡ የቆየውን እምቅ ፍላጎት ነው በይፋ የገለጸው። በዚህ አጋጣሚ ሁለቱንም ሕዝቦች እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። የዚህች አገር እውነተኛ ስሜት ምን እንደሚመስል ዓይታችሁታል። ዶ/ር ዓብይ የወሰደው ምርጫ ቀላል ምርጫ አይደለም። ለ25 ዓመታት ያጠፋነው ጊዜ፣ ያከሰርነው ዕድል በምንም መለኪያ መስፈር የሚቻል አይደለም። አሁን ግን አልከሰርንም። ከእዚህ በኋላ ባለው ጉዟችን ከዶ/ር ዓብይ ጋር አብረን ነን። የሚገጥመንን ፈተናም ሆነ መልካም ዕድል አብረን እንወጣዋለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ዶ/ር ዓብይም በበኩላቸው የሚከተለውን በልብ ውስጥ የሚጻፍ ንግግር አድርገዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ትግርኛ የለ! አማርኛ የለ! ቋንቋው ጠፍቶብኛል። ደስታዬን ግን ፊቴ ላይ እዩት። . . . ክቡር ኢሳያስ (ወዲ አፎም)፣ ለኤርትራ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ! አለን። ብዙ ሕዝብ ካለቀ በኋላም ቢሆንም፣ አሁን የጀመርነው ጉዞ አልረፈደም። እናንተ ኤርትራዊያን የሰላም ሐዋርያት የሆናችሁ ሰላም ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም. . . ሰላም አይደለም ለሰው፣ ለሰማይ አዕዋፍ እንኳን አስፈላጊ ነው።
አሁን ሁላችሁም ኢትዮጵያዊ ናችሁ። የኤርትራ ጳጳሳትና ሸሆች የኢትዮጵያም ናችሁ። ለልጆቻችሁ ሰላምና ፍቅር መፀለይ አለባችሁ። . . . ለልጆቻችን እኛ ያሰርነውን ገመድ፣ ያጠርነውን አጥር . . . ፣ እንዲፈርሱ እናድርግ።

‹‹የኤርትራ ሕዝብ ሆይ! የሠለጠንክና ሥራ ወዳድ ነህ። ግን ሰላም ከሌለ ፍሬያማ አትሆንም፡፡ ለእናንተ ሰላም ይገባችኋል። ስለውጊያ መስማት ይበቃናል። እኛ ሰላም ከሆንን ምሥራቅ አፍሪካም ሰላም ትሆናለች፡፡ በሌላ አገር ያሉ የሁለታችንንም ዜጎች እንደ ዕቃ ሳይሆን በክብር እንቀበላቸዋለን። በውቅያኖስ ሳይሆን በክብር እንልካቸዋለን፡፡ በፍጥነት በመሥራት የሁለቱን አገሮች ሕዝብ እንክሳለን፤›› ብለዋል። 

በንግግር ተውቦ የታደለ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፡፡ አፉ እንዳመጣለት ተናግሮ በኋላ አይቆጭም፡፡ በእብሪት የተሞላ ሰው የማዳመጥ ችሎታውን እያጣ የሚሄድ ሲሆን፣ ዝንባሌውም መናገር ብቻ ይሆናል፡፡ የራሱ ድምፅ መልሶ ጆሮው ላይ እስኪጮህበት ድረስ ስለራሱ ውዳሴ ከንቱ ያበዛል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ወደ ኋላ ተመልሶ የራሱን ሚዛን ለመረዳት በጣም ይቸገራል፡፡ ንግግራቸው በጨው የታሸ፣ አርቆ አስተዋዮች በደረሱበት ቦታ ሁሉ ክብር ያገኛሉ፡፡ አገርንም ያስከብራሉ፡፡ 

በኢትዮጵያና በኤርትራ ሰማያት የፍቅር ዝናብ እንዲዘንብ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በሐሴት እንዲፈነጥዙ፣ አዛውንትና ባልቴቶች ከቁዘማ እንዲወጡ፣ ካህናት ለታላቁ አምላካቸው እግዚአብሔር ማኅሌት እንዲያደርሱ ያደረጋቸው የዶ/ር ዓብይ ‹‹ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር›› ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁላችንም በጉጉት እንደተከታተልነው ዶ/ር ዓብይ ከአውሮፕላናቸው ከወረዱ ጊዜ ጀምሮ የፕሬዚዳንት ኢሳያስና የዶ/ር ዓብይ ሁኔታ ተጠፋፍተው የተገናኙ አባትና ልጅ ይመስሉ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚሳሳለትን የጠፋ ልጅ እንዳገኘ አባት ተፍነክንከዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይም ለሚወደው አባት ክብር እንደሚሰጥ አስተዋይ ልጅ ሆነዋል፡፡ እንደ መንፈስ አርነትና እንደ ፍቅር ጥልቀት፡፡ 

ከወጣትነት እስከ አዛውንትነት ዘመናቸው በጦርነትና በትግል ያሳለፉት ኢሳያስ ሰማያት ሳይቀር ያሸበሸቡባቸውን ሁለቱን ቀናት ሳያዩ እንኳን አልሞቱ እላለሁ፡፡ የኤርትራ ሕዝብም ዶ/ር ዓብይን የተቀበለው የጠፋ ልጁንና ወንድሙን እንዳገኘ ሰው በታላቅ ሆታና ዕልልታ ነው፡፡ በኤርትራ ታሪክ ይህን የመሰለ የሞቀ አቀባበል ለየትኛውም የአገር መሪ ተደርጎ አይታወቅም። ‹‹ደስታ ቀሊል›› ለሁለቱ አገሮች ሰላም ማጣት አንደበት ስለተጫወተው አፍራሽ ሚና ማንሳቱ የተገባ ነው፡፡ ‹ከደመና የሚከፈል መብረቅ ምድርን እንደሚያርሳት፣ ከክፉ አንደበት የምትወጣ ቃልም ልብን ታቆስላለችና ተጠንቀቅ› የሚል አባባል አለ፡፡ ቃላት ከአስተሳሰብ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ስለሆኑ ሐሳብ ቃላትን ያመነጫሉ፣ ቃላት የሐሳብ መዘውሮች ናቸው፡፡ ነገር በአንደበት ተገልጾ ንግግር ከመሆኑ በፊት የሚከማቸው በአዕምሮ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በአካባቢያችን ሰላም እንዲሠፍንና የምንናገረው ነገር ቀና እንዲሆን የምናልመውን መምረጥ ነው፡፡ በዚህ በኩል ዶ/ር ዓብይ ታድለዋል፡፡

አምርተን ነጣቂ፣ ተናግረን ሸውከኛ እንዳይኖርብንና ኑሮና ተስፋችን በሙሉ በ‹እርሱ ያውቃል› ብቻ እንዳይወሰን፣ ውስጣችንም ሆነ ደጃችን ፅልመት እንዳይሆን፣ በግፈራ ሳይሆን በምናብ በመኖር ሐሴት እንድናደርግና በየልቦናችን ያጠረሸው የነገር እርሾ ጠርቶ የሕይወት ጎህ እንዲታየን ለሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ‹ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር› ያስፈልጉናል፡፡ 

መጣጥፌን ናይሮቢ ከተማ የሚኖር መአሾ የተባለ ኤርትራዊ በቢቢሲ የአማርኛ ድረ ገጽ ላይ በተናገረው ድንቅ አባባል ላጠቃልል፡፡

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጉርብትና ዘለዓለም እንደሚቀጥሉ ጠቁሞ፣ ‹‹በኤርትራ አንድ አባባል አለን፡፡ የምትተኛ ከሆነ ጎረቤትህም መተኛት አለበት፡፡ ለሁለቱም አገሮች ሰላምን እመኛለሁ፤›› ብሏል፡፡ የመአሾ ምኞት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ምኞት ነው፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ኤርትራን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል  አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...