Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገ ኢትዮጵያዊ መሪ

ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገ ኢትዮጵያዊ መሪ

ቀን:

በወልደ አማኑኤል ጉዲሶ

ብዙ ሰዎች ስለዓለም ሰላምና ብልፅግና፣ ስለሕዝቦች ነፃነት፣ አንድነትና ደኅንነት፣ ስለሰዎች አብሮነት፣ መቻቻልና መደጋገፍ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሊኖሩ ስለሚገቡ ፍቅርና ደስታ ብዙ ሲሰብኩ ሰምቻለሁ፡፡ ረዥም ጊዜ በፈጀ ፍሬ አልባ ንግግር አድማጭን፣ ተመልካችንና አንባቢን ሲያሰለቹም ተመልክቻለሁ፡፡ ትልልቅ አንደበቶች ያቆዩልንን አንዳንድ የጽሑፍ መረጃዎችንም በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ ሞክሬአለሁ፡፡

አንዳንድ አንደበተ ርቱዕ ግለሰቦች በንግግራቸው የሚያስተላልፉዋቸው ጣፋጭ መልዕክቶች የሰዎችን ህሊና እንደ መድኃኒት የሚፈውሱ ናቸው፡፡ የሚፈውሱ ብቻ ሳይሆኑ የዘወትር የህሊና ስንቅ ሆነው የሚያገለግሉና አብረው የሚዘልቁም ናቸው፡፡ እነዚህን በአዕምሯችን የተቀረፁ መልዕክቶችን እንርሳ እንኳን ብንል ፈጽሞ የማይረሱ፣ ደግሞም ሊረሱ የማይገቡ ቁም ነገሮች ስለሆኑ የትዝታ ሐውልቶችን በህሊናችን ተክለው ያልፋሉ፡፡ የመልዕክቶቹ ባለቤቶች ምድራዊ የሕይወት ዘመናቸውን አጠናቀው ‹ለወዲያኛው ዓለም ሲታጩም› ከእነ መልዕክቶቻቸው በቀጣዩ ትውልድ ዘንድ (የእነሱ ፍላጎት ባይሆንም) ሲወደሱና ሲከበሩ ይኖራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም መልዕክቶቻቸው ሰዎች ሲከፋቸው ብቻ ሳይሆን በጥላቻ፣ በደስታና በእርቅ ዘመን ሁሉ ሳይቀር ስማቸውን እየጠሩ ለጥንካሬ፣ ለይቅርታና ለሰላም የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ለዚህም አብነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን በጥቂቱ ብናነሳ አብርሃም ሊንከን፣ ማሪያ ቴሬዛ፣ ማኅተመ ጋንዲ፣ ኒልሰን ማንዴላ፣ . . . ወዘተ ማውሳት ይቻላል፡፡ የእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ስም በየዘመናቱ ከሌሎች ገዝፎ እየተነገረ ያለው ያለ ምንም ምክንያት አይደለም፡፡ በራሳቸው የራሳቸውን ሙገሳና ዕውቅና ፈልገውም ወይም ዝናችን ይነገርልን ብለው ለደጋፊዎቻቸው የቅስቀሳ ገፀ በረከት አዝንበው አይደለም፡፡ አንዱን ጠቅመው ሌላውን ለመጉዳት አስበውና አቅደው በመንቀሳቀሳቸውም አይደለም፡፡ እንደ ማንኛችንም ፍጡራን ሰው ሆነው ተወልደው፣ እንደ ማንኛችንም የሰብዓዊ ሰውነት ሰብዕና ተላብሰው፣ ነገር ግን በሰዎች መካከል ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጠላትነት ይልቅ ወዳጅነትን፣ ከቅርብ አሳቢነት ይልቅ ሩቅ አሳቢነትን፣ ከጠባብነት ይልቅ አብሮነትን፣ ከበቀል ይልቅ ይቅርታን፣ ከመጠራጠር ይልቅ መተማመንን ለወዳጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቻቸው ጭምር የሕይወት መስዋዕትነትን በሚያስከፍል ሁኔታ በቆራጥነት ማስተማር በመቻላቸው ነው፡፡ አስተምህሮዎቻቸው ለሰው ልጆች ዘላቂ ሕይወት ድንበር ዘለል መልዕክቶችና አስፈላጊ እንዲሆኑ ሳይታክቱ ስለሠሩ ነው፡፡

እነዚህም ተናጋሪዎች የአገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች፣ ምሁራን ወይም ሌሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ ከእነዚህም ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ማኅበራዊ አመጣጣቸው ሲታዩ በተፈጥሮ የተሰጣቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲታመን፣ ሌሎቹ ደግሞ ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች (ከአስተዳደግ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ፣ በግል ከሚያደርጉት አታካች ጥረት፣ . . . ወዘተ) ከሚያገኟቸው ውሎ አደር ክንዋኔዎች ወይም ከሚዳስሷቸው ክስተቶች ይህንኑ አቅምና ችሎታ እንዳገኙ ይታመናል፡፡

ይህንኑ ችሎታና አጋጣሚ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ዝናና ክብር ማግዘፊያ አድርገው ሲጠቀሙ ቀሪዎቹ ደግሞ ይህንኑ ‹‹ዝና›› ሌሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቀበሉና እንዲታዘዙላቸው፣ ወይም እነሱ የሚሉትን ብቻ አምነው ሲሰብኩ እንዲኖሩ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይህንን ለማድረግም የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይወጡት ዳገትና የማይወርዱት ቁልቁለት የለም፡፡ የሚገርመው ግን ይህ ክብርና ዝና ጊዜያዊ እንጂ ዘለዓለማዊ መሆኑን በአግባቡ ባለመረዳት እዚያው ‹‹ተሰቅለው›› የቀሩ ስለመኖራቸው፣ በርካታዎችን ስም እየጠቀሱ ዋቢ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በጥቂቱ ስለመልካም ስዎችና ስለመልካም ሥራዎቻቸው የዚህን ያህል ካወሳሁ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ፡፡

የአሜሪካ ዝነኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በዘመናቸው የሚከተለውን አባባል ተናግረው ነበር ይባላል፡፡ ‹‹የአንድ አገርና መንግሥት ባህል በሕዝቡ ልብና ሕይወት አብሮ ይዘልቃል፤›› እኚሁ ፕሬዚዳንት በመቀጠልም፣ ‹‹ስለሚኖርባት አገሩ ኩሩ የሆነ ዜጋ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ የሚኖርባት አገሩ የምትኮራበትን ሰው ማየት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው አሜሪካዊ ቢሆኑም ይኼው አባባላቸው ለእኛም ለኢትዮጵያውያን ጠንካራ መልዕክት አለው፡፡ አገራችን በእኛ እንድትኮራ፣ እኛም በአገራችን እንድንኮራ ማድረግ የሁላችንም የዘወትር ጥረት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ የሁላችንም የዜግነት ኃላፊነትም፣ ግዴታም ይመስለኛል፡፡ ነውም፡፡ ለዚህም አገራዊ ተልዕኮ ሁላችንም በሁሉ ሥፍራና ጊዜ ቁርጠኛ ሆነን መሥራት የሚጠበቅብን ይሆናል፡፡

በበኩሌ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበትን መሪ በእርግጠኝነት አግኝተናል ማለት እችላለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ያደመቀ ኢትዮጵያዊ መሪ ብቅ ብለውልናል፡፡ እኚህ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ለራሴ ስለዶ/ር ዓብይ አንዳንድ ነገር መጻፍ ስፈልግ የቱን ጽፌ የቱን መተው እንዳለብኝ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባኛል፡፡ የቱን አስቀድሜ የቱን ማስከተል እንዳለብኝም እንዲሁ፡፡ በየጊዜውና በየመድረኩ ከአንደበታቸው እንደ ጅረት ውኃ የሚፈልቁ ጣፋጭና አስተማሪ አገራዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ከተፈጥሮ የተገኙ? ወይስ በአጭር ጊዜ በራስ ጥረት? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ግን ኮርቼባቸዋለሁ፡፡ ኧረ ምን እኔ ብቻ! የሁላችንም ኩራት እንጂ፡፡

እያንዳንዱን መድረክ በሚመጥን ቋንቋ የሚናገሩት ቃላት፣ የሚያስተላልፉት መልዕክት አዕምሯችንን እየጠገነና እየፈወሰ፣ እያፋቀረንና እያቀራረበ ነው፡፡ ያለፉ ዓመታትን ቁርሾ ብቻ ሳይሆን የዘመናት አኗኗራችንን ፈትሸን ወደ ፊት እንዴት በአብሮነት መጓዝ እንዳለብን፣ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገር ዜጎች እያሳዩን ነው፡፡ በእርግጠኝነት አሳይተዋልም፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ተበጣጥሳና ተሸራርፋ ልትወቅድ ምንም ያህል ያልቀራትን ክቡርና ውድ አገራችንን ከገደል አፋፍ አድነው አንድ አድርገዋታል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዓለም ተቃዋሚዎችን ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ እንዲህ አገራዊ ሁኔታው ፈጣንና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ትኩሳት ባለበት ወቅት፣ ከአንደበታቸው በሚፈልቁ ህያው አባባሎች ብቻ ከሁሉም፣ በሁሉም አቅጣጫ እንዲህ ዓይነቱን ልባዊ ድጋፍ ማግኘት ዕድለኛ ናቸው ያሰኛል፡፡ ዕድለኞች ነን ከማለት ሌላ ምን ሊባል ነው! የሚጠቅመንና የሚሻለን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዕድሜ ይስጣቸው፣ ያዝልቅልን ማለት ነው፡፡

ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ማኅተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ ‹‹ከሁሉም ነገር የተሻለ ነው የሚባለው ለራስ ጥቅም ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል መስዋዕት መሆን ነው፤›› ይላሉ፡፡ እኚሁ አባት አክለውም፣ ‹‹ነገ ሟች መሆንህን አውቀህ ኑር፣ እስከ ወዲያኛው ነዋሪ መሆንህ አውቀህ ተማር፤›› ብለዋል፡፡ እኚህ መሪያችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ሙስናን አጥብቀው ይፀየፋሉ፣ ጠባብነትንና ዘረኝነትንም አምርረው ይታገላሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ደምቆና ተውቦ እንዲታይ ይፈልጋሉ፣ አገራዊና አኅጉራዊ የጋራ ተጠቃሚነት ጎልቶ እንዲወጣ ይመኛሉ፣ ኢትዮጵያዊነትን አስከብሮ የዘለቀውና ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ የመጣው ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ይፈልጋሉ፡፡ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ፣ በደሃውና በሀብታሙ፣ በነጩና በጥቁሩ፣ በወንዱና በሴቱ፣ በከተሜውና በገጠሬው ኢትዮጵያዊነት ደምቆ እንዲታይ ይፈልጋሉ፡፡ ታዲያ እኚህን መሪ በተግባር ያልደገፈ ሰብዕና ለመቼ ሊሆን ነው!! ነገን መጀመር የምንችለው እኮ ከዛሬ አንድ ብለን ነውና የየራሳችንን ድጋፍና አክብሮት እንስጣቸው፡፡ ከዚያም የጋራ ፍሬ እንለቅማለን፣ እንመገባለን፣ ለተከታዩ ትውልድ እንሰንቃለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታንና ምሕረትን ይዘምራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝብ የሚጠላውንና ሕዝብ የሚጎዳበትን ነገር እንዳንሠራ ይመክራሉ፡፡ ሁላችንንም ከአንድ እናት ማኅፀን የወጣን ሰብዓዊ ፍጡሮች አድርገው እያዩን ነው፡፡ የእርስ በርስ ጥላቻና ዘለፋ እንዲቆም እያስተማሩንና እያበቁን ነው፡፡ ጨርሶ ወደኋላ መመለስ እንደማንችል በማረጋገጥም ተከተሉኝ ብቻ ሳይሆን፣ አብረን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደፊት እንንቀሳቀስ እያሉ ነው ዶ/ር ዓብይ፡፡

የኃያሏ አገር አሜሪካ ተወዳጅ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በዘመናቸው እንዲህ ብለው ነበር ይባላል፡፡ ‹‹አሜሪካ በውጭው ዓለም ምክንያት ፈጽሞ አትጠፋም፡፡ አሜሪካ የምትጠፋው እኛ አሜሪካውያን እርስ በርስ በተደነቃቀፍንና ነፃነታችንን በራሳችን ባጣን ጊዜ ነው፤›› ነው ያሉት፡፡ ለአገራችንና ለሕዝቦቿ በፍቅርና በይቅርታ ኑሩ ብሎ ጥሪ ከማድረግ በላይ ምን ትልቅ ነገር አለ? የአንዲት ታላቅ አገር ሕዝቦች ስለሆንን እርስ በርስ ነባርና አዳዲስ ቅሬታዎች እያስታረቅን እንኑር ከማለት ሌላ ምን ታላቅ መልዕክት ይኖራል? ከተበታተነ ኢትዮጵያዊነት ኅብረ ብሔራዊነት ይሻላል ከማለት ሌላ ምን ትልቅ ነገር አለ? የታላቅነት ሚስጥርም አንድነት ነውና ወደዚህ ኢትዮጵያዊነት እንመለስ እያሉን ነው፡፡ እንደ ቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካ ወይም ሌሎች የዘረኝነት አቀንቃኞች እንደ ነበሩ አገሮች ወደዚህ ሠፈር መግባት አትችሉም ብለው ገደብ አላበጁም፡፡ ጥሪው ለሁሉም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በጋራና በተናጠል እያዳመቅን መኖርን እያደስን እንምጣ ነው የሚሉት፡፡

አንድ የነበርነውን ሕዝቦችና አንድ የነበረችውን አገራችንን የተለያየን ዜጎች የሚያደርገውን አካሄድ ሁሉ ከአሁን ወዲያ በጥብቅ ልናወግዝ ይገባናል፡፡ የኖርነው፣ ያደግነው፣ እስከ ዛሬ የዘለቅነው ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያገናኙን መልካም እሴቶች በመካከላችን ስለነበሩና አሁንም ስላሉን ነው፡፡ ወደፊትም አብረውን ይዘልቃሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች በጊዜያዊ ጥቅሞችና በሥልጣን ጥማት ሊደበዝዙ አይገባም፡፡ እነዚህን የጋራ ያልሆኑና ሊሆኑም የማይገቡ ፍላጎቶችን ልንፈቅድም አይገባንም፡፡ ለአንድታችንና ለአብሮነታችን ደንቃራ የሚሆኑ አስተሳሰቦች ሁሉ ወደኋላ የሚጎትቱን እንጂ ወደፊት የማያራምዱን ስላልሆኑ መክሰም አለባቸውና አንከተላቸው፡፡ የሚከተሉትን ሁሉ አግባብተንና አሳምነን እንመልሳቸው፡፡ ባረጀ ጨርቅ ላይ አዲስ ስፌት መስፋት የሚፈልጉትን ዘመኑ እንዳልሆነ እንንገራቸው፡፡ አዲስና አገራዊ ጠቀሜታ ያለውን አስተሳሰብ ይዘው የመጡትን ኢትዮጵያዊ መሪ በፍቅርና በአክብሮት እንቀበላቸው፡፡ መበለጥም ሆነ ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ መራመድ ችሎታ እንጂ ሽንፈት አይደለም፡፡ መሸነፍን የማይቀበል አንደበት ለማሸነፍም ዝግጁ አይደለም፡፡ አይሆንምም፡፡ ፖለቲከኛም አይደለም፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ቀደም ሲል ስለነበርንበት ታሪካዊ ሁኔታ መልካም ጅምሮችን ሲያደንቅ፣ ያለፉ ታሪኮች የዛሬ ሀብቶች ናቸውና ተገቢውን ቦታ ይሰጣል እንጂ አያጣጥልም፡፡ ብዙዎችን ያደንቃል፡፡ ያ ድንቅ እሴት የበለጠ ድንቅ የሚሆነው ግን ብዙ ስንሆን እንጂ ስንነጣጠል ያለመሆኑን አጥብቆ ያምናል፡፡ ከዛሬ 242 ዓመታት በፊት እንደተመሠረተች የሚነገርላት ኃያሏ አሜሪካ ኃያል ከሆነችባቸው ሚስጥሮች አንዱና ዋንኛው ስሟ ራሱ እንደሚያመለክተው፣ የተባበረች አሜሪካ በመሆንዋ እንጂ አንዳንዴም ወደ መፈራረስ የሚያዘነብሉ አጀንዳዎች ሳይኖሩባት ቀርተው አይደለም፡፡ በአንድነትና በአገር ጉዳይ ላይ ተደራዳሪ ስላልሆኑ ነው፡፡ ሀብታሙም፣ ደሃውም፣ መካከለኛ ገቢ ያለውም መብቱ እንዲከበርለት በወዎል ስትሪት አደባባይ ላይ ጎላ አድርጎ ይጮኻል፣ ይታገላል እንጂ፣ ገሩ እንድትጎዳና እንድትፈራርስ አይደራደርም፡፡ በመረጃ የተደገፈና በዕውቀት የተመራ ‹‹ተቃውሞ›› ያደርጋል እንጂ፣ በአሜሪካና በአሜሪካውያን ዙሪያ ቀልድ የለውም፡፡ አሜሪካውያን ጊዜያቸውንና ሃብታቸውን ለአገራቸው ዘላቂ ዕድገት ይጠቀማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዜጎች በመሆናቸውም ለአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች አገሮች ዜጎችም የተስፋ ምድር ሆነውላቸዋል፡፡ በየጊዜው እንደ ዶናልድ ትራምፕ (ፕሬዚዳንት) ያሉ አወዛጋቢ መሪዎች ቢመጡባቸውም፣ መናገር የሚገባቸውን ነገር ሁሉ መናገር በሚገባቸው አግባብ እየተናገሩ አርዓያ ሆነዋል፡፡ በአርዓያነታቸው ለእኛም ተርፈዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አባባል ‹‹እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች›› የአገርን ራዕይና ተስፋ የሚያጨናግፉ ተግባራትን አንፈጽም፡፡ ብንራብም ብንጠማም ኢትዮጵያዊነታችን ይሻላልና በኢትዮጵያዊነታችን እንዝለቅ፡፡ ውኃ በማቆርና በመሰብሰብ ፆም ያድሩ የነበሩ መሬቶችን እንዳለማን ሁሉ፣ ሰላምን በመነጋገርና በመመካከር እናልማ፡፡ የእርስ በርስ ግጭቶችን በወንድማማችነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያሰብንና እየተሳሰብን እናስወግድ፡፡ ለጊዜያዊ ሥልጣንና ጥቅም ብለን በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የማያባራ ቅራኔና ጥላቻ አናቆይ፡፡ መገዳደል፣ ማቁሰል፣ በጥላቻ ዓይን መተያየት ትርፍ የሌለው ቢዝነስ ነውና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናብቃ፡፡ በመደመር ችግራችንን በመፍታት የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእርግጥ መገንባት  እንችላለን፡፡ በሁሉም የአገራችን ክፍሎችና በተለያዩ ምክንያቶች በሌሎች የዓለም ክፍሎች ተበትነው የሚገኙ ዜጎቻችን ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር ይኑሩ፡፡ አናሳፍራቸው፡፡

እኛም እንደ ዜጋም፣ እንደ ሙያችንም፣ እንደ አካባቢያችንም በዶ/ር ዓብይ መሪነት በአገራችን የተለኮሰውን የለውጥ ማዕበል ሳይቀዘቅዝ የምንመራ ኃይሎች እንሁን፡፡ ከመጥፎ ድርጊትና ጊዜ ካለፈበት ዘረኝነት የራቅን ሕዝቦች እንሁን፡፡ ያኔ ኢትዮጵያዊነትን ይደምቃል፡፡ ከኢትዮጵያዊው መሪያችንና ከሕዝባችን ጋር አብረን መጓዝ እንችላለን፡፡ የሰላም አገርና ሰላማዊ ሕዝቦች መሆናችንን ለዘላቄታው ከፍ እያደረግን እንዘልቃለን፡፡

በመጨረሻም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኤርትራ ጉብኝት በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል የነበረው ወንድማማችነት ምን እንደሚመስልና እንዴት መቀጠል እንዳለበት ወደር በሌለው ሁኔታ ያመላከተ መሆኑን በገሃድ አሳይቷል፡፡ የአስመራ ከተማ  ዝብ በነቂስ ወጥቶ በደስታና በደስታ በታጀበ ዕንባ ሲቀበላቸው ስናይ፣ ለሃያ ዓመታት ተለያይተን የነበርነውን ያህል እያነባን እንድንከታተል አድርጎናል፡፡ አቀባበሉም ሆነ መስተንግዶው ፍቅር የተራቡ የሁለቱም አገር ሕዝቦች ከልብ ያስደሰተ ከመሆኑም በላይ መነጣጠሉ እንደማይጠቅም የማይረሳ ትዝታ ተክሎ ያለፈ ታሪክ ሆኖ አልፏል፡፡ በዚህ ወንድማዊና የሰላምን ጣፋጭነት አጣጥሞ ለሚያውቀው የኤርትራና ኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው ሁኔታ ራሱን ችሎ መጻፍ ያለበት ስለሆነ፣ ወደ ዋናው ርዕሰ ስመለስ አልጄዚራ ሰሞኑን በድረ ገጹ አስነብቦት በነበረው አስተያየቱ፣ ‹‹የኢትዮጵያው ዓብይ አህመድ ወደ ሌላው የአፍሪካ ጠንካራ መሪነት ይሸጋገር ይሆን?›› ማለቱ ትክክለኛ ትንበያ ይመስለኛል፡፡

እንደ አንድ የአገር መሪ ለራሳቸው ምንም ነገር ሳይጎድልባቸው ለሌሎች እንደ ሻማ መቅለጥ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸውና አብረን እንሁን፡፡ የዕውቀት ድህነት የለባቸውምና ኢትጵያዊነትን ካደመቁ መሪ ጋር እንቀላቀል፡፡ ሁሉም ዜጋ በፍቅር፣ በወንድማማችነትና በአብሮነት መኖር ከቻለ የአገሪቷ ሀብት የእናንተው ነው የሚሉን መሪ ናቸውና እንከተላቸው፡፡

‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ስለሰላም መነጋገር መጀመራቸው በአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙ ሁለቱ አገሮች፣ በአጠቃላይም ለመላው አፍሪካ የተስፋ ብርሃን ሊፈነጥቅ የሚችል አጋጣሚ ነው፤›› ብለዋል የዓለም ካቶሊካውያን ሊቀነ ጳጳስ ፍራንሲስ ሮም በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባደረጉት ንግግር፡፡ ስለሆነም እኚህን ኢትዮጵያዊነትን ያደመቁ መሪ እንከተላቸው፡፡ መልካሙን ለራሳችንም ሆነ ለአገራችን በመመኘት ለዛሬው በዚሁ ላብቃ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...