Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መምራት ብቻ ሳይሆን መከተልም ጥበብ ነው!

ከቦሌ ወደ ሜክሲኮ እየተመምን ነው፡፡ ወያላው ሒሳብ መሰብስብ ሲጀምር ፍጥነቱ ያማረረው አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹ምነው ይኼን ያህል ገና መቀመጫውን ሳንነካ አክለፈለፍከን እኮ?›› እያለ ቀስ ብለን እንከፍላለን የሚል ዓይነት አስተያየት ሰጠ፡፡ ይኼን ጊዜ፣ ‹‹ላይቀርልን ዕዳ . . ›› ያለችው አንዲት ወጣት ሒሳቧን ለመክፈል ቦርሳዋን መበርበር ጀመረች፡፡ ‹‹ያው ዞሮ ዞሮ መክፈላችን አይቀርምና አሁኑኑ እንካ ውሰድልኝ፡፡ ዕዳ ነው የሰለቸኝ . . . ›› በማለት ሒሳቧን ከፈለች፡፡  

ወያላው፣ ‹‹ሒሳብዎትን በአስቸኳይ መክፈል የሥልጣኔ  መገለጫ ነው፤›› ሲለን፣ መቼስ የሰው ቢሮ መጥተን ምንም ክፉ መናገር አንችልም የወያላውን ምክር ለማድመጥ ተገደድን፡፡ አንድ ስለምንም ነገር ግድ የማይሰጠው የሚመስል ወጣት፣ ጆሮው ላይ ትልቅ የጆሮ ማዳመጫ ገጥሞ በራሱ ዓለም ውስጥ ሰጥሞ ይታያል፡፡

‹‹ይህን ወጣት ለተመለከተው ገጣሚው ‹ለአንዲት የገጠር ሴት› በማለት የጻፈው ግጥም ግልባጭ ይመስላል፤›› ያለን ጋቢና የተቀመጠ ነው፡፡ ነገሩን ሲቀጥልም፣ ‹‹ይኼኔ እኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማን እንደሚባሉ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ ተደመሩ የሰማም አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ አነሳሁት እንጂ ኢርፎኑን ሰክቶ ዓለሙን ረስቶ ከሚኖር ጎልማሳ ጋር ምን እንነጋገር ይሆን? እሱ አገር ቢገለበጥ አሊያም ቢለማ አይሰማ . . . ›› እያለ አንዳንዱ ወጣት ተዘፍቆ ስለገባበት ነገር አብራራ፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ ‹‹በዚህ ሰዓት ስለአገሩ የማያውቅ ወጣት ይኖራል ብዬ ጠርጥሬም አላውቅም ነበር፣ ምን ያደርጋል አንዳንዱ እኮ የለም . . . ›› እያለ ብቻውን ተገረመ፡፡

አንድ ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በሳል መሪ ነው ያገኘችው እንጂ ገና ሕዝቡ ዘንድ ብዙ ርብርቦሽ የሚጠይቅ ነገር አለ፤›› እያለ ሐሳቡን ሊያደርሰን ጥረት አደረገ፡፡  ሌላው ተቀበለውና፣ ‹‹መምራት ብቻ ሳይሆን መከተልም ጥበብ ይጠይቃል፤›› ሲለን አብዛኛዎቹ የታክሲው ተሳፋሪዎች አንገታቸውን ነቀነቁ፡፡ ጎልማሳው እንደገና፣ ‹‹ጥሩ መሪዎች ባለፈው ዘመናቸው ጥሩ ተከታዮች ነበሩ፤›› የሚል አስተያየት አከለበት፡፡ ከመሀል መቀመጫ አንዷ፣ ‹‹ዛሬ በማስተዋል መከተል ካልቻልክ፣ መቼም መሪ መሆን አትችልም፤›› ብላ ነገረችን፡፡

አንዱ ከወደ መሀል አካባቢ፣ ‹‹የተጋበዙ ዘፋኞች ሁሉ ባለመዝፈናቸው በጣም አዝኛለሁ፤›› ሲል ወያላው ተቀብሎት፣ ‹‹እኔ ራሴ ተጋባዥ አትሌቶች ሁሉ መድረኩ ላይ ትንሽ ሮጥ ሮጥ ቢሉ እያልኩ ነበር፤›› ሲለን ፈገግ አልንለት፡፡

ሾፌሩ ለመጀመርያ ጊዜ አስተያየቱን ሲሰጥ፣ ‹‹እኔን የገረመኝ ሩሲያ ያዘጋጀቸውን የዓለም ዋንጫ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን መውሰዳቸው ነው፤›› ሲለን፣ ወያላው ከአፉ ቀልቦ፣ ‹‹ለዚህ እኮ ነው የፈረንሣይ መሪ አገራቸው የጋበዟቸው፤›› እያለ ለመኮመክ ሞከረ፡፡ ሌላ የአገሩ ጉዳይ የሚቆረቁረው የሚመስል ወጣት፣ ‹‹እንዲህ ባሉ ታላላቅ ጉባዔዎች ላይ ለመጋበዝ አትሌት ወይም አዝማሪ መሆን ይጠይቃል ማለት ነው፤›› የሚል ጥያቄ አነሳ፡፡

ወያላው ሌላ ቀልድ ይዞ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹ልክ ፕሌኑ ሲነሳ . . . ›› እያለ ትኩረታችንን ሰበሰበ፡፡ እኛም ፕሬዚዳንቱን ምን ነክቷቸው ይሆን ብለን ወያላውን ማዳመጣችን ቀጠልን፡፡ ወያላውም፣ ‹‹የግመሉ አንገት ብቅ ብሎ አየሁት . . . ›› ብሎን ብቻውን ክትክት ብሎ ሳቀ፡፡ አንዱ ደግሞ፣ ‹‹እኛ የኤርትራን ሕዝብ እንወዳለን፣ ዳሩ ግን የኤርትራ ፕሬዚዳንትን እንደ ሰላም አምባሳደር መቁጠራችን አግባብ አይደለም፤›› ብሎ ነገር ቆሰቆሰ፡፡ ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡

የመጀመርያው ጎልማሳ፣ ‹‹እግዜሩ ጥሩ መሪ ሲሰጠን ጥሩ ተከታይ መሆን ሊያቅተን አይገባም፤›› የሚል ሐሳብ አስታጠቀን፡፡ ከጎልማሳው ሰውዬ ጋር ጉዳይ ያላት የምትመስለው ወጣት አሁንም ከጎልማሳው ቀጥላ መናገር ጀመረች፣ ‹‹እኔ አሁንስ የሰለቸኝ ወረተኛና ዘረኛ ነው፤›› ስትለን ሌላ ጉንጩን በጫት የወጠረ ደግሞ፣ ‹‹ሕዝቤን ከምክንያት ይልቅ ንፋስ ነው የሚያንጋልላት፤›› የሚል የመረቀነ ሰው አስተያየት ሰጠ፡፡ ወያላው እንደለመደው ጥልቅ ብሎ፣ ‹‹ሕዝቤ ከፍ አድርጎ ሲያውለበልብልህ ተጠንቀቅ በዚያው ሊለቅህ ይችላል፡፡ ባጨበጨበልህ እጁ ይፈጠፍጥሃል፤›› አለ፡፡

ይኼን ጊዜ ሾፌሩ፣ ‹‹እንዲያው አያድርግበትና ጠቅላዩ አንድ ነገር ቢሳሳት፣ ነገር ተበላሸ ማለት ነው፤›› ሲለን ሌላ ተቀብሎት፣ ‹‹የሰውዬውን ሰውነት ዘንግቶ ከመላዕክት ተርታ የዶለው ሁሉ አይምረውም፤›› እያለ ሥጋቱን ገለጠ፡፡ ይኼኔ፣ ‹‹ያን ሁሉ የሰማውን የምሕረት ትምህርት የት አሽቀንጥሮት ነው የማይምርህ?›› የሚል ጥያቄ ለሁላችንም ያቀረበልን ለግላጋ ወጣት ነበር፡፡

ጎልማሳው ፈገግ እያለ፣ ‹‹እንዲያው የሚያስተውል ሰው ጠፍቶ ነው እንጂ በእዚህ ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ለልጅ ልጅ የሚበቃ የፍቅርና የይቅርታ ዶፍ ነበር ያወረዱብን፤›› አለንና ቆዘመ፡፡ ወያላው አሁንም ዘው ብሎ፣ ‹‹ፍቅርና ይቅርታ የማያርሰው ሰው አለ እንዴ? ይኼን ሰውዬ እንግዲህ ዓብይ የሚባል የፍቅርና የይቅርታ ባህር ውስጥ ዘፍቀነው ካልረጠበ፣ በእርግጠኝነት ፍቅርንና ይቅርታን የሚከለክል ዣንጥላ ልቡ ላይ አድርጓል፤›› የሚል ማብራሪያ ሰጠን፡፡

‹‹ይቅርታ ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ምሕረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ጠላቶቻችንን መውደዳችንንም እንቀጥላለን . . . ›› እያለ የተናገረው መጀመርያ ስለኤርትራ ፕሬዚዳንት ሲያማርር የነበረው ሰው ነው፡፡ ወያላው፣ ‹‹ይሰውረነ!›› ሲለን፡፡ ከምን ይሆን ብለን አዳመጥነው፡፡ ሾፌሩ ሲያብራራ፣ ‹‹ከፅንፈኛ ሰው፤›› ሲል ወያላው፣ ‹‹ይሰውረነ!›› በማለት ተቀበለው፡፡ አሁንም ሾፌሩ፣ ‹‹ከዘረኛና ጠባብ አመለካከት ካለው ሰው፤›› ሲል አሁንም ወያላው ተቀብሎት፣ ‹‹ይሰውረነ!›› እያለ ተቀበለው፡፡ ከመሀል አንድ ሰው፣ ‹‹በታሪካዊ ቀን ተገኝቶ ታሪክ አስተማሪ ልሁን ከሚል ሰው፤›› ሲል ይኼን ጊዜ ወያላው ብቻ አይደለም አብዛኛው የታክሲ ተሳፋሪዎች፣ ‹‹ይሰውረነ!›› እያሉ ተቀበሉት፡፡

እኛም ወደ መዳረሻችን ሜክሲኮ ደርሰን ነበር፡፡ ሜክሲኮ ስንወርድ ከሌባው ከአጭበርባሪው ‹‹ይሰውረነ!›› እያልን በየአቅጣጫው ልንበታተን መንገዳችንን ስንይዝ፣ በመሀሉ ጣልቃ እየገባ ሐሳቡን ጣል ያደርግ የነበረው ሰውዬ፣ ‹‹ይሰውረነ ማለት ጥሩ ፀሎት ነው፡፡ ግን አሁን ዋናው መልካም ነገር ጥሩ መሪ ሲገኝ ለመመራት ወይም ለመከተል ጥበበኛ መሆን ነው የሚያዋጣው . . . ›› ሲለን አንገታችንን በይሁንታ ነቅንቀን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት