- ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
- ደህና ነኝ፡፡
- መግለጫውን ሰሙት?
- የትኛውን መግለጫ?
- እኛን የሚመለከተውን መግለጫ ነዋ፡፡
- ኢትዮ ኤርትራ ላይ የተሰጠውን መግለጫ ነው?
- እሱ እኛን አይመለከትም እኮ፡፡
- ባለፈው ኤርትራ ሄደን ኢንቨስት እናደርጋለን ስላልከኝ ነዋ፡፡
- እሱን የሚመለከት ሳይሆን እኛን በዋናነት የሚመለከት መግለጫ ወጥቷል፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የብሩ ጉዳይ ነዋ፡፡
- የምን ብር?
- በካዝና ያስቀመጥነው ብር ጉዳይ ነዋ፡፡
- ስማ ላባችንን አንጠፍጥፈን ያመጣነው ገንዘብ አይደል እንዴ?
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ጥረን ግረን ባፈራነው ገንዘብ እኮ ልንሸማቀቅ አይገባም፡፡
- መንግሥት እኮ ይኼ አይገባውም፡፡
- እንዴ በአገራችሁ አትሥሩ እየተባለ ነው?
- መንግሥትማ ሕዝቡ ሠርቶና ለፍቶ እንዲያድግ ነው የሚፈልገው፡፡
- ታዲያ እኛ የሕዝቡ አንድ አካል አይደለንም እንዴ?
- እሱማ ነን፡፡
- ታዲያ የራሳችንን ብር ባንክ አስቀመጥነው ካዝናችን ውስጥ አስቀመጥነው መንግሥት ምን አገባው?
- ክቡር ሚኒስትር እኛም ካዝና ውስጥ ያስቀመጥነው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ መቼም?
- እኛ እኮ ባንኩን ስለማናምነው ነው ቤታችን በካዝና የምናስቀምጠው፡፡
- ምክንያታችንማ እሱ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድን ነው ታዲያ ምክንያታችን?
- ባንክ ያለንን የገንዘብ መጠን እንዳያውቅብን ነዋ፡፡
- እሱስ ቢሆን እንደ ሳዑዲ ባለሀብቶች ሀብታችንን የመደበቅ መብት የለንም እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ሀብቱም እኮ ቢሆን የእኛ አይደለም፡፡
- ታዲያ የማነው?
- ያው ግማሹ የስኳር፣ ግማሹ የባቡር ነው፡፡
- እና አትደልሉ ልንባል ነው?
- መደለልማ እንችላለን፡፡ እኛ ግን ሕገወጥ ድለላ ነው ያደረግነው፡፡
- ለማንኛውም እኔ በዚህ አልስማማም፡፡
- እኔ እኮ መግለጫው አስፈርቶኝ ነው፡፡
- መግለጫው ምንድነው የሚለው?
- ቤታችሁ ያለውን ገንዘብ አውጥታችሁ ባንክ አስቀምጡ እየተባልን ነው፡፡
- ባናስቀምጥስ ምን ሊያደርጉን ነው?
- ኦፕሬሽን እንጀምራለን ብለዋል፡፡
- የምን ኦፕሬሽን ነው?
- ያው እንግዲህ የቤት ለቤት አሰሳ ሊጀምሩ ይሆናላ፡፡
- ካሰሳው በኋላ ምን ሊያደርጉ?
- ካገኙማ ይወርሱናል፣ በዚያ ላይ ሌላ መዘዝ ሊኖረው ይችላል፡፡
- ታዲያ አንተ ምን አሳሰበህ?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ከመንግሥት ኦፕሬሽን በፊት ብሩን ባንክ እንዲያስገቡት ነዋ?
- እኔማ ሰሞኑን ይኼንኑ መግለጫ ሰምቼ ብሩን ወደ ሌላ ቦታ ለማሸሽ አስቤ ነበር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ብቻ በመንግሥት ኦፕሬሽን ጉድ እንዳይሆኑ፡፡
- ከመንግሥት ኦፕሬሽ በፊት በሌላ ኦፕሬሽን ጉድ ተሠርቻለሁ፡፡
- በምን ኦፕሬሽን?
- በአይጥ ኦፕሬሽን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ምሳ ሊበሉ ቤት ሄደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ሰዓቱ ረፍዷል እኮ ቢሮ አትገባም እንዴ?
- ባክሽ ዛሬ ቢሮ መግባት አልፈልግም፡፡
- ምን ሆንክ ደግሞ?
- ራሴን አሞኛል፡፡
- ምን ሆነህ?
- ሰሞኑን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብቻለሁ፡፡
- ማታም እኮ ምንም እንቅልፍ አልተኛህም ነበር፣ ያው ሥራ ይኖርሃል ብዬ ነው፡፡
- ምን ሥራ ይኖራል ብለሽ ነው? ብቻ ምንም ሰላም እየተሰማኝ አይደለም፡፡
- የተፈጠረ ነገር አለ እንዴ?
- የሰማሁት ነገር እየረበሸኝ ነው፡፡
- ልትታሰር ነው እንዴ?
- ኧረ ከኃላፊነቴ ሊያስነሱኝ ሳያስቡ አልቀረም፡፡
- እንዴት አወቅክ?
- መሥሪያ ቤት ሌላ ሰው አምጥተውብኛል፡፡
- በላይህ ላይ?
- አዲስ ሚኒስትር ዴኤታ ተሹሞብኝ ነው፡፡
- ምን ችግር አለው ታዲያ?
- ሰውየውን ቀልቤ አልወደደወም፣ አስፈርቶኛል፡፡
- ዝም ብሎ ሰው አስፈራኝ ብሎ ነገር አለ እንዴ?
- ለነገሩማ ስለሰውየውም እያጣራሁ ነው፡፡
- ታዲያ ምን አገኘህ?
- ሰውየው ሁለት ዶክትሬት ዲግሪ ነው ያለው፡፡
- አንተስ ቢሆን አንድ የዶክትሬት ዲግሪ አለህ አይደል እንዴ?
- የእኔ ታዲያ በግዥ ነዋ፡፡
- የሰውየውስ ትክክለኛ መሆኑን አጣርተሃል?
- እንዲያውም ሁለቱንም በወርቅ ሜዳሊያ ነው የጨረሰው፡፡
- ምን ትቀልዳለህ? ሌላስ?
- ስሚ ዩኤን በይው ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያልሠራበት ቦታ የለም፡፡
- አንተስ ቢሆን ስንትና ስንት የውጭ ድርጅቶችን እያማከርክ አይደል እንዴ ያለኸው?
- እኔ እኮ የውጭ ድርጅቶቹን የማማክረው በማስፈራራት ነው እንጂ እንደ እሱ በችሎታ አይደለም፡፡
- እሱ ግን የውጭ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠራ ከሆነ ለምን እናንተ ጋ መምጣት ፈለገ?
- የሚገርምሽ እኮ ደመወዙን በስንትና ስንት ቀንሶ ነው ለመሥራት የመጣው፡፡
- በጣም ነው የሚገርመው፡፡
- ይኼ ደግሞ ሰውየው ምንም ለገንዘብ ደንታ እንደሌለው ነው የሚያሳው፡፡
- አንተም ቢሆን እኮ ለገንዘብ ምንም ደንታ የለህም፡፡
- ስሚ የሙሰኞች ቀንደኛው መሆኔን ረሳሽው እንዴ?
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ሌላው የሚገርምሽ ደግሞ ሠራተኛው ሁሉ ወዶታል፡፡
- አንተንስ አባታችን ነው አይደል እንዴ የሚሉህ?
- ሰው እኮ ወረተኛ ነው ስልሽ፡፡
- እና በአንዴ ጠሉህ?
- አንቅረው ነው የተፉኝ፡፡
- የሰው ነገር እኮ ይገርማል፡፡
- አሁን ምን እንደማደርግ ጨንቆኛል፡፡
- ፖለቲካውን ጥርስህን የነቀልክበት አይደል እንዴ ምን አስጨነቀህ?
- ሊተኩኝ ይችላሉ ስልሽ? ቀለል አድርገሽማ እንዳታይው?
- ስማ በዚያ በሁለቱም በኩል በተሳለው ሰይፍ ቆራርጠህ ለምን አትጥለውም?
- በምን በተሳለው?
- በሐሜትና በአሉባልታ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት እየተገመገሙ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ያቀረቡት ሪፖርት በጣም ደካማ ነው፡፡
- እንዴት?
- አሁን ካለው ለውጥ ጋር ሊቀጥሉ ይችላሉ ብዬ አላምንም፡፡
- ምን እያላችሁ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር አስፈጽማለሁ ካሏቸው ሥራዎች ውስጥ አሥር በመቶውን እንኳን ማስፈጸም አልቻሉም እኮ?
- እንደምታውቁት የሠራተኞቹ አቅም በጣም አነስተኛ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ባደረግነው ማጣራት እርስዎ ራስዎ በቀን ውስጥ ከሁለት ሰዓት በላይ ሥራ ላይ አይገኙም፡፡
- ያው ለተለያዩ ስብሰባዎች ስለምወጣ እኮ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ስብሰባ እኮ ከሥራ ሰዓት ውጪ ቅዳሜና እሑድ ይደረግ ተብሏል፡፡
- ወሬ ሌላ ተግባር ሌላ አሉ፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- እናንተስ አወራችሁ እንጂ መቼ ተገበራችሁት?
- ክቡር ሚኒስትር የታቀዱ ፕሮጀክቶች እኮ በጊዜያቸው እየተተገበሩ አይደለም፡፡
- ታዲያ እኔ ምን ላድርግ?
- ክቡር ሚኒስትር የሁሉ ነገር ችግር እኮ ወደ እርስዎ ነው የሚያመራው፡፡
- አልገባኝም?
- መሥሪያ ቤቱን በአግባቡ መምራት ስላልቻሉ ነዋ ፕሮጀክቶቹ እየተጓተቱ ያሉት?
- በእኔ ምክንያት አይደለም እኮ ፕሮጀክቶቹ የተጓተቱት?
- ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ ስንፍና ነው ፕሮጀክቶቹ የተጓተቱት፡፡
- ሰነፍ ነህ እያላችሁን ነው?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ግን ይኼን አልቀበልም፡፡
- ለምን?
- ሠራተኞቹ እኮ ናቸው ሰነፎቹ፡፡
- ሠራተኞቹ ሰነፍ የሆኑት ሲቀጠሩ በችሎታ ሳይሆን በወንዝና በጅረት መሥፈርት ስለተቀጠሩ ነዋ፡፡
- ታዲያ ሠራተኞቹ ሲቀጠሩ እኔ አልቀጥር፣ ራሱን የቻለ ቅጥር ኮሚቴ አለ አይደል እንዴ?
- ቢሆንም ሥራውን ስለማይቆጣጠሩት መሥሪያ ቤቱ እርስዎን ነው የሚመስለው፡፡
- አሁን ይኼን ሁሉ ውርጅብኝ የምታወርዱብኝ ለምንድነው?
- እርስዎ በቅርቡ መነሳትዎ አይቀርም፡፡
- እ . . .
- ያው እርስዎን የሚተካ ሰው እስክናገኝ ድረስ ለጊዜው ይቀጥላሉ፡፡
- እና አንስታችሁ አውላላ ሜዳ ላይ ልትጥሉኝ?
- ለእርስዎ ምቹ ቦታ ይዘጋጅልዎታል፡፡
- ምን ልታደርጉኝ?
- አምባሳደር!
[ክቡር ሚኒስትር ከአማካሪያቸው ጋር ሆነው ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል ላይ ስለሚጠሩ ሰዎች እያወሩ ነው]
- አንተ ባለፈው የተነጋገርነው ነገር ረስተኸዋል መሰለኝ?
- የትኛውን ነገር ክቡር ሚኒስትር?
- በአገራችን ላይ የመጣውን ለውጥ በማስመልከት የሠራተኞችን ሞራል ለማነሳሳት ዓመታዊ የሠራተኞች ቀን በዓል ይኑረን አላልኩህም እንዴ?
- እሱማ ብለውኛል፡፡
- ታዲያ በበዓሉ ላይ የምንጠራው የእንግዶች ስም ዝርዝር የታለ?
- የራሳችንን ሠራተኞች አይደል እንዴ የምንጠራው?
- እኔ የምልህ የቪአይፒ ሊስቱን ነው፡፡
- እሱንማ ይኼው እንኩ፡፡
- እነማን ናቸው እነዚህ ሰዎች?
- አያውቋቸውም ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ የመጀመርያው ማን ነው?
- እኚህማ ኢትዮጵያዊ ውስጥ አሉ የተባሉ ሳይንቲስት ናቸው፡፡
- የምን ሳይንቲስት?
- በዕፀዋት ምርምር የታወቁ ሳይንቲስት ናቸው፡፡
- ከእሱ ቀጥሎ ያለውስ ሰውዬ?
- እሱ ደግሞ የታወቀ የሕክምና ባለሙያ ነው፡፡
- በዓሉ እኮ የሠራተኞች የደም ልገሳ ቀን አይደለም፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼኛውስ ማን ነው?
- እሱ ደግሞ ታዋቂ የባንክ ባለሙያ ነው፡፡
- ስማ የሠራተኞች ብድርና ቁጠባ ተቋም ለማቋቋም አስበን አይደለም እኮ በዓሉን ያዘጋጀነው?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ ይኼኛውስ ማን ነው?
- በአገራችን አሉ የተባሉ አርክቴክት ናቸው፡፡
- ሰውዬ ሕንፃችንን እናድስ ብዬሃለሁ እንዴ?
- አሁን ግን ግራ አጋቡኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ እኮ ጥራልኝ ያልኩህ ቪአይፒ ሰዎችን ነው?
- ከዚህ የበለጠ ቪአይፒ ከየት ይምጣ ታዲያ?
- የቪአይፒ ትርጉሙን አታውቅም እንዴ?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አገሪቷ ውስጥ ያሉት የቪአይፒ ሰዎች ማን እንደሆኑ ታውቃለህ?
- እነማን ናቸው?
- ሙዚቀኞች፣ የድራማና የፊልም ተዋናዮች፣ ተወዛዋዦችና ተመሳሳይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
- እ . . .
- እነዚህን ሰዎች እኮ ሕዝቡ በሙሉ ያውቃቸዋል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ የጥበብ ሰዎች ቪአይፒ አይደሉም እያልኩ ሳይሆን፣ እነሱ ብቻ ግን ቪአይፒዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡
- ስማ የመንግሥት ትልልቅ ፕሮግራሞች ላይ እኮ ቪአይፒ ተብለው የሚጠሩት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡
- እርስዎ የሚፈልጉት ቪአይፒ ገብቶኛል ግን የቪአይፒ ትርጉሙ ይለወጣል፡፡
- ትርጉሙ ምን ሊሆን?
- Very Incompetent Person!