አቶ ኃይለየሱስ መዝገቡ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቼክ ስታንዳርዳይዜሽን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ
የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን ሁነኛ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ እየገቡ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ የክፍያ ሥርዓቱን ያፈጥናሉ የተባሉ አገልግሎቶችም ሥራ ይገባሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡ እንደ የካርድ ባንኪንግ፣ የሞባይል ባንኪንግና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የዛሬ ሦስት ወር ገደማም ቁልፍ ከሚባሉ የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓቶች መካከል አንዱ የሆነው የቼክ ክፍያ ሥርዓት አገልግሎት ጀምሯል፡፡ የቀድሞውን ቼክ ይተካል የተባለውና በዘመናዊ መንገድ የታተመውን ቼክ ባንኮች እንዲጠቀሙበት ተሠራጭቷል፡፡ ይህን አገልግሎት ለመጀመር ብዙ እንደተደከመም ተገልጿል፡፡ አዲሱን ቼክና ከዚሁ ጋር ተያይዞ መተግበር ያለበትን አሠራር ወደ ሥራ ለማስገባት፣ ብሔራዊ ባንክና ሁሉም ባንኮች በአባልነት የያዘው የባንኮች ማኅበር በመተባበር ሠርተዋል፡፡ ከ508 ሺሕ ዶላር በላይ ወጪ የወጣበት አዲሱ ቼክ ጠቀሜታው በተለያየ መንገድ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ዓለም በደረሰበት ደረጃ የተሰናዳ መሆኑና በቀላሉ በአታላዮች ሊዘጋጅ የማይችል እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ታኅሳስ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲሱ ቼክ ሥራ ላይ መዋሉ ይፋ ሲደረግ፣ አዲሱና አሮጌው ቼክ መሳ ለመሳ ሆነው ለስድስት ወራት እንደሚሠራባቸው ተገልጿል፡፡ ከዚያ በኋላ አዲሱ ቼክ የቀድሞውን ቼክ እየተካ ይሄዳል፡፡ የስድስት ወራት ጊዜ የተሰጠውም ያለምክንያት አልነበረም፡፡ አሮጌው ቼክ መሸጋገሪያ ጊዜው ያልቃል በሚልና አዲሱን ቼክ ደንበኞች እየወሰዱ አጠቃቀሙን እየተለማመዱ እንደሚሄዱ ጭምር ታሳቢ ተደርጐ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሽግግር የተሰጠው የጊዜ ገደብ ግማሽ ያህሉ ቢጠናቀቅም፣ የባንክ ደንበኞች አዲሱን ቼክ እንደታሰበው እየተጠቀሙበት አለመሆኑ ግን ብዥታን ፈጥሯል፡፡ እስካሁን ከቼክ ተጠቃሚዎች ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት እንኳን እየተጠቀሙበት አለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የአዲሱ ቼክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እንደታሰበው አለመሆኑ ደግሞ ዘመናዊውን የክፍያ ሥርዓት ለመተግበር እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ደንበኞች አዲሱን ቼክ ያለመጠቀማቸው ለምን? የሚለውን ጥያቄና በአጠቃላይ ለቼክ ስታንዳርዳይዜሽንና አሠራር ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ስለሚጠበቀው ሌላ አዲስ አሠራር፣ እንዲሁም ስለፕሮጀክቱ አጀማመርና አጠቃላይ ይዘት፣ ዳዊት ታዬ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በባንኮች ጥምረት የተፈጠረውን በብሔራዊ ባንክ የቼክ ስታንዳርዳይዜሽን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለየሱስ መዝገቡን አነጋግሯል፡፡ አቶ ኃይለየሱስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ወስደዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሒልኮ በኮምፒውተር ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ ከ15 ዓመታት በላይ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ሠርተዋል፡፡ ፕሮግራመርም ናቸው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በብሔራዊ ባንክ በአይቲ ዲፓርትመንት በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማምጣት በተዋቀሩ የተለያዩ ፕሮጀክት ውስጥ አገልግለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን አዲስ ቼክ በማሳተም አዲስ አሠራር ለመተግበር የተቋቋመው ፕሮጀክት፣ በባንኮችና በብሔራዊ ባንክ ጥምረት ተፈጥሯል፡፡ የሁለቱ አካላት ኃላፊነት ምን ነበር?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማምጣት ባንኮችም ሆኑ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይኼው ታስቦ በጋራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን በማዘመን ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት የተለየ ነው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት የሚከታተለው ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ካለቀ በኋላም በኃላፊነት የሚሠራውም ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ አለቀ ብለን አንተወውም፣ ቀጣይ ሥራዎች አሉት፡፡ አያቆምም፡፡ የየትኛውም አገር ልምድ እንደሚያሳየው በብሔራዊ የቼክ ስታንዳርዳይዜሽን ኮሚቴ የሚባል አለ፡፡ ይህ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ተረክቦ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ የቼክ ስታንዳርዳይዜሽን ፕሮጀክት ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማስረፅ ታስቦ የተተገበረ ነው፡፡ እስቲ ስለፕሮጀክቱ አጀማመር፣ ጉዞና አሁን የደረሰበትን ደረጃ ይንገሩኝ? ዓላማውስ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማዎች ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው ዓላማ ቼኮችን ወጥ ማድረግ ነው፡፡ በሥራ ላይ የነበሩት የባንኮች ቼኮች በቅርፅም በይዘትም የተለያዩ ነበሩ፡፡ ስለዚህ አሁን የተደረገው በመጠንም ሆነ በይዘታቸው አንድ ዓይነት ቼኮች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ተመሳሳይ ናቸው ሲባል ግን የባንኩ ዓርማና መለያ ቀለሞች የተለያዩ ቢሆንም ቅርፅ፣ ይዘታቸውና መጠናቸው አንድ ዓይነት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ሥራ አልቋል፡፡ ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ አሁን ባለው አሠራር ቼኮቹን ከባንክ ባንክ እየተቀያየሩ ነው የሚሠሩት፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ከሁሉም ንግድ ባንኮች ቼኮች ሲሰበስብ ይውላል፡፡ የሰበሰበውን ቼክ በየባንኮቹ በመለየት በመልክ በመልክ በማድረግ ዛሬ የሰበሰባቸውን ቼኮች በማግሥቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ ይልካቸዋል፡፡ ሌሎችም ባንኮች እንዲሁ በተመሳሳይ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያ እያንዳንዳቸው ባንኮች ቼኮቹን ይቀይራሉ፡፡ ሁሉም ባንኮች እንዲህ ባለው መንገድ ቼኮቻቸውን ይቀያየራሉ፡፡ የተቀያየሩት ቼክ ባንኮቹ እጅ ከገባ በኋላ ቼኩ ትክክል ነው አይደለም ብለው ይለያሉ፡፡ ሊከፈለው የሚገባው ከሆነ ቼኩ እዚያው ይቀራል፡፡ ወይም መመለስ ካለበት ደግሞ ይመለሳል፡፡ የተመለሰው ቼክ ተስተካክሎ ከመጣ ደግሞ እንደገና መጥተው ይቀያየራሉ፡፡ በዚህ አሠራር ቼኩ ብሔራዊ ባንክ ከደረሰ በኋላ በ48 ሰዓት ውስጥ ይጣራል፡፡ ባንኮቹ ብሔራዊ ባንክ ካላቸው አካውንት ተቀናንሶ ክፍያው ይፈጸማል፡፡ ይህንን ዓይነቱን አሠራር ለማስቀረት ባንኮች ቼኮቻቸውን በምሥል እንዲቀያየሩ የሚያደርገው ሁለተኛው ዓላማ፣ ቀጣዩ የዚህ ፕሮጀክት ሥራ ይሆናል፡፡ ይህ አሠራር ባንኮች ቼኮቹን ስካን እያደረጉ በምሥል ብቻ እንዲቀያየሩ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ አሠራር አንዱ ባንክ ወደ ሌላኛው ባንክ ወረቀቱን ወይም ቼኩን ይዞ ስካን አድርጐ ይልክለታል፡፡ አላላኩም በሰዓት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ቼኩ እንደመጣለት በየተራ ሊላክ ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ልምዱ ግን በባች መላክ ነው፡፡ ቼኩ ስካን ተደርጐ የተላከለት ባንክ ቼኩን ያይና ቼኩ ትክክል ነው አይደለም ብሎ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ መልስ የሚሰጥበት ጊዜም 24 ሰዓት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ውስጥ ምላሽ ካልሰጠ ቼኩን ተቀብሎታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ያለው ሲስተምም ይህንን መረጃ ይዞ፣ በብሔራዊ ባንክ ከሚገኘው የባንኮች አካውንት ሊከፈለው ወደሚገባው ባንክ አካውንት ይቀንስና ያሳልፋል፡፡ ባንኮቹም ወዲያውኑ ለደንበኛው ይከፍላሉ፡፡ ይህንን አሠራር ግን ገና አልጀመርንም፡፡
ይህንን አሠራር ለማስጀመር መመርያ ስለሚያስፈልግ መመርያው ተዘጋጅቶ ፀድቆ ተቀምጧል፡፡ ይህ የአገልግሎት ቼክ ትራንኬሽን ይባላል፡፡ ቼክ ትራንኬሽን ማለት ቼኮችን ከባንክ ወደ ባንክ ሄዶ መቀያየሩን ማስቆም ማለት ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመጀመር ባንኮች ስካን የሚያደርጉበት ስካነር ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያላቸው ስካነር ግን አንተ ቢሮ ካለው ስካነር የተለየ አይደለም፡፡ ምሥሉን ይቀርፃል ይልካል፡፡ አሁን የምንፈልገው ግን ይህንን ቼክ በተወሰነ መልኩ ማረጋገጥ የሚችል ስካነር ነው፡፡ ስካነሩ ቼኩን ሲያይ የቼኩን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ በዓይን የማይታዩ የቼኩ መለያ ባህሪያትን በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ አንድ የደኅንነት መገለጫ ነው፡፡ ዓለም የሚጠቀምበት አሠራር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን አገልግሎት የሚያውቅ ስካነር ነው የሚፈለገው፡፡ ይህ ካልሆነ ቼኩን ሊተፋው ችሏል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የቼኩ ምሥል የተላከለት ተቀባይ ባንክም እሱም የተላከለትን ቼክ የሚለይበት መሣሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ቴክኖሎጂና ሲስተም የሚቀበል መሣሪያ ባንኮቹ ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን አገልግሎት ለመጀመር ግን ባንኮች ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ወደዚህ አሠራር ለመግባት እየተዘጋጁ ነው፡፡ አሁን አስተምረናቸዋል፡፡ ከውጭ ባለሙያዎች በማስመጣት ማሽኑ እንዴት እንደሚሠራበት አሳይተናቸዋል፡፡ አሁን አንድ ሰባት የሚሆኑ ባንኮች ሲስተሙን ገዝተዋል፡፡ ስካነሩ ነው የቀራቸው፡፡ እዚህ ላይ ስካነሩ ብቻውን ጥቅም የለውም፡፡ ስካነሩና አፕሊኬሽኑ ሊናበቡ ይገባል፡፡ ቼክ ትራንኬሽን የሚባል አፕሊኬሽን አለ፡፡ ሰባቱ ባንኮች አፕሊኬሽን አለን ብለው ለብሔራዊ ባንክ አስታውቀዋል፡፡ የሚቀረን ስካነር ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የስካነር ስፔሲፊኬሽን እያዘጋጀን ነው፡፡ በቼክ ትራንኬሽን አሠራር ቼኩ ስካን ሲደረግ እያንዳንዱ ባንክ ሊከተለው የሚገባ ሥርዓትም ተቀምጦለታል፡፡ ብሔራዊ ባንክም ይህንን የሚቆጣጠር ክፍል ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ቼክን በስካነር አማካይነት መለዋወጥ ሲጀመር እንደ አሁኑ ቼኮችን ወደ ብሔራዊ ባንክ ይዞ መምጣትና መቀያየር ይቆማል ማለት ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዎ ይቆማል፡፡ ይህ ሁለተኛ ዓላማችን ሲሆን ከተሳካልን ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የምናደርገው ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከቼክ ሥርዓት አንፃር የሌሎች አገሮች ልምድ እንዴት ይታያል? አሁን እየተሠራ ያለው ሥራስ ከሌሎች አገሮች አሠራር ጋር እንዴት ሊነፃፀር ይችላል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- እስካሁን የነበረው የእኛ የቼክ ማጣራት ሥርዓታችን ኋላቀር ነው፡፡ አንዳንዴ እውነት መናገር ጥሩ ነው፡፡ የእኛን ስታየው ደግሞ የቼክ ማጣራት አዲስ አበባ ላይ ተወጥሮ ያለ ነው፡፡ ከዚያ አላለፈም፡፡ አሁን ዘመናዊ አሠራር ነው ተብሎ ዓለም የሚጠቀምበት ቼክ ትራንኬሽን ገባ፡፡ ቼክ ትራንኬሽን እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ ነው እየታወቀ የመጣው፡፡ ቼኩ ተቀምጦ ምሥሉ ብቻ ሄዶ እንዲከፈል ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እኛ ዓለም ብዙ የደከመበትን ነገር አልፈን ወደ ቼክ ትራንኬሽን እየገባን ነው፡፡ ስለዚህ የቼክ ማጣራት ሥራችን አሁን ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ደርሷል ማለት ነው፡፡ አሁን ለአገልግሎት ያበቃነውም ቼክ ደረጃ ዓለም ዛሬ የሚጠቀምበት ነው፡፡ ይህ ደረጃ ድንበር ዘለል ንግዶች ቢጀመሩ ለምሳሌ የኬንያና የኢትዮጵያ ባንኮች በቼክ ገንዘብ መለዋወጥ ቢችሉ፣ ይህንን ሊያስተገብር የሚችል እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የአይኤስኦ ስታንዳርዶችን ይዞ እንዲዘጋጅ የተደረገ ቼክ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ዓለም የደረሰበትን የአሠራር ደረጃ ተከትለን እንድንሄድ ያስችላል፡፡ እዚህ ላይ ቅድም ያልጠቀስኩትና ሦስተኛው የእኛ ፕሮጀክት ዓላማ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የቼክ ማጣራት ሥራ፣ በመላ የአገሪቱ ክፍል አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል ነው፡፡ ለማጣራት እንደ ቀድሞ አዲስ አበባ መምጣትን ያስቀራል፡፡ እዚያው አጣርቶ ክፍያ መፈጸም የሚያስችል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከሦስት ወራት በፊት አዲሱ ቼክ ጥቅም ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን እየታየ ያለው ግን በአብዛኛው የባንክ ደንበኞች አዲሱን ቼክ እየተጠቀሙ አይደለም፡፡ ይህንንም ከየባንኮቹ ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል፡፡ ምንድነው ችግሩ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዲሱን ቼኩን ሥራ ላይ ካዋልን ሦስተኛ ወር ላይ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን አንተ እንደገለጽከው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የተወሰነ ነው፡፡ የአዲሱ ቼክ እንቅስቃሴና የተጠቃሚዎች ቁጥር እንደተጠበቀው አይደለም፡፡ መጀመሪያ ባንኮች አዲሱ ቼክ ዘገየብን ይሉ ነበር፡፡ ቶሎ እንዲመጣ አስጨንቀውን ነበር፡፡ በቶሎ ለማስመጣት ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያውን ዙር ለመረከብ ብዙ ጊዜ ነው የፈጀብን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከታህሳስ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ ቼክ ሥራ ላይ ሲውል ጠብቀናቸው የነበረው የባንክ ደንበኞች ያለችግር ይጠቀሙበታል፣ ይዥጐደጐዳል ብለን ነበር፡፡ ግን ይህ አልሆነም፡፡
ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው? እናንተስ ደንበኞች በአዲሱ ቼክ አለመጠቀማቸው ለምንድነው ብላችሁ ልታጣሩ አልሞከራችሁም?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ለማጣራት ሞክረናል፡፡ በእኛ በኩል ይኼ ነው በማለት የሰጠነው ግምት የለም፡፡ አንድ እውነት ግን አለ፡፡ ይህም ቼኮች የሚሰጡበት ሥርዓት አለ፡፡ ደንበኛው ቼኩ አልቆብኛል ብሎ ሲጠይቅ ይሰጠዋል፡፡ እዚህ ላይ የእኔ ግምትና ሥጋት አዲሱ ቼክ ሥራ ላይ ከዋለም በኋላ አንድ የባንክ ደንበኛ ቼክ ጨርሻለሁ ስጡኝ ብሎ ባንኩን ሲጠይቅ አሮጌውን ይሰጣሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህንን ማድረግ እንደሌለባቸው ግን ለባንኮች ደግመን ደጋግመን ነግረናል፡፡ ይህ አንድ ችግር ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አሮጌው ለተወሰነ ጊዜ ቢቀመጥ ላይጐዳ ይችላል፡፡ ምናልባት አዲስ ደንበኛ ከመጣ ለእሱ ይሆናቸዋል፡፡ ካልሆነ አዲሱን ነው መስጠት ያለባቸው፡፡ ሌላኛው ግምቴ ደግሞ ደንበኞች ወደ ባንኮች አልሄዱ ይሆናል የሚል ነው፡፡ አዲሱን ቼክ የተቀበለም ደንበኛ ቢሆን በአዲሱ መገልገል ሊፈራ ይችላል፡፡ ይህም ሌላ አንድ ምክንያት ተደርጐ ሊቆጠር ይችላል፡፡ አዲሱን ቼክ ሥራ ላይ ሲውል አጠቃቀሙን በተመለከተ ሥርዓት አስቀምጠናል፡፡ የቀኑ አጻጻፍ ከቀድሞው የተለየ ነው፡፡ ይህንን የቼክ አሠራር ሥርዓት እያበላሸም ቢሆን መማር አለበት፡፡ የአዲሱን ቼክ አጠቃቀም ባንኮች ራሳቸው ከሥርዓቱ ውጪ እያዘጋጁ ስለሆነ መማር ያስፈልጋል፡፡ የሰዎችም ፊርማ ሆነ ገንዘብ በሚጽፉበት ጊዜ ምንድነው የሚታየው ችግር? እኛስ ምን ዓይነት ማስተካከያ መውሰድ አለብን? የሚለውን ለማወቅ ነበር የስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ ያስቀመጥነው፡፡ አዲሱን ቼክ ኅብረተሰቡ አለመጠቀሙ በኋላ ነው ችግር የሚፈጥረው፡፡ በአዲሱ ቼክ አለመጠቀም በኋላ ላይ በሚፈጠረው ግድፈት ክፍያ ሊዘገይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አዲሱን ቼክ ተቀብሎ እያበላሸም ይማር ነው የምንለው፡፡
ሪፖርተር፡- የተሻለ የክፍያ ሥርዓት እንዲኖር ደግሞ አዲስ ቼክ እንዲሠራጭ ተደርጓል፡፡ እናንተ ለባንኮቹ ነግረናል፣ አስተምረናል ብትሉም የቼኩ ተጠቃሚ ቁጥር አንሷል፡፡ ኅብረተሰቡ በአዲሱ ቼክ እንዲጠቀም እናንተም አልቀሰቀሳችሁም፡፡ ስለዚህ ችግሩ የእናንተም ነው ማለት አይቻልም?
አቶ ኃይለየሱስ፡- በመጨረሻ ላይ የተገነዘብነው ይህንን ነው፡፡ በዕቅዳችን መሠረት አስበን የነበረው በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተጠቅመን ማስተዋወቅ ነው፡፡ ዋናው ግን ባንኮች ደንበኞቻቸውን እየሰበሰቡ ያስተምራሉ የሚል ነው፡፡ እኛ ፖስተር አዘጋጅተን ሰጥተናል፡፡ ባንኮቹ ግን ደንበኞቻቸውን አላስተማሩም፡፡
ሪፖርተር፡- አሮጌውን ቼክ በአዲስ ለመተካት ከተሰጠው የስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ ውስጥ ሦስቱ አልቋል፡፡ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የአዲሱ ቼክ ተጠቃሚዎች እጅግ አነስተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ፣ ከዚህም በኋላ በቀሪው ሦስት ወራት ውስጥ ለውጥ ከሌለ ምንድነው የምታደርጉት? የታቀደ ነገር አለ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ሐምሌ ገና ነው፡፡ ከሐምሌ በፊት ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎች አሉ፡፡ አንዱ ቅድም የጠቀስኩልህ የቼክ ስታንዳርዳይዜሽን ብሔራዊ ኮሚቴ በሚወስነው መሠረት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሥራት ነው፡፡ ኮሚቴው ከባንኮችና ከብሔራዊ ባንክ በተውጣጡ አባላት የሚቋቋም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አታሚዎች ራሳቸው በኮሚቴ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም የሚታተመው ቼክ ሲስተሙ ውስጥ ችግር እንዳይፈጥር እነሱም የኮሚቴው አባል እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ነገር ግን ድምፅ የላቸውም፡፡ ኮሚቴው የሚመራበት የራሱ የሆነ ቻርተር ይኖረዋል፡፡ ቻርተሩም ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ ኮሚቴ አሁን ሥራ ይጀምራል፡፡ ሥራ መጀመሩ ደግሞ አሁን እንዲሠራጭ የታደለው ቼክ ለምን ተጠቃሚው አነሰ ብሎ ያይና መፍትሔ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር የእኛ ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎች አገሮች የቼክ አሠራርን ለማዘመን ሲሠሩ ችግሩ ገጥሟቸዋል፡፡ ባለፈው ጊዜ ከዓለም ባንክ የመጡ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ይህንን ፕሮጀክታችንን ያውቁታል፡፡ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ስንነጋገር ሊገጥሟችሁ ይችላሉ ብለው ከጠቀሱልን አንዱ አሮጌውን ቼክ የመላቀቅ ችግር ነበር፡፡ ከመጡት ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ በህንድ አዲስ ቼክ ለማላመድ ጊዜ ሲወስድ እንደ መፍትሔ የተጠቀሙበትን ዘዴ ነግረውን ነበር፡፡ ይህም አዲሱን ቼክ ዜጐቻቸው እንዲጠቀሙ ለማድረግ አሮጌውን ቼክ ሲያመጡ አዲሱን ቼክ እንደ ማትጊያ በነፃ እንሰጣቸው ነበር ያሉት፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን አዲሱን ቼክ ሥራ ላይ ለማዋል ምንም ችግር አይገጥመንም የሚል ግምት ነበር፡፡ ምክንያቱም ደንበኞች በቀላሉ ወስደው ይጠቀሙበታል፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ደንበኞች አዲስ ነገር ለማየት ይጓጓሉና በቶሎ ወስደው ይጠቀሙበታል ብለን አስበን ነበር፡፡ ግን በታሰበው ደረጃ አልተጓዘም፡፡
ሪፖርተር፡- በባንኮች እጅ ያለው የቀድሞ ቼክ መጠን ይህንን ያህል ብዙ ነው ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ባለፈው ዓመት አንድ መረጃ ሰብስበን ነበር፡፡ በዚያ መረጃ መሠረት ከአንድ ባንክ በስተቀር ባንኮቹ በእጃቸው ያለው የቀድሞ ቼክ እስካሁን ሊቆይ የሚችል አይደለም፡፡ ግን እኔ ከየት እንደሚመጣ አላውቅም፡፡ አሁንም ግን አሮጌውን ቼክ የሚሰጡ ባንኮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እኔ እስከማውጠው ድረስ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት አሮጌው ቼክ መኖር የለበትም፡፡ አሮጌውን ቼክ ያትም ከነበረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጠይቄ እንደተረዳሁት የቼክ ኅትመት መቆሙን ነው፡፡ ስለዚህ ከየት እንደሚመጣም ግራ ያጋባል፡፡ ይኼ ችግር የየባንኮቹ ቅርንጫፎች ጭምር ነው፡፡ ቅርንጫፎቹ ቼኩን የሚሰጡ የመሆናቸውን ያህል እዚያ አካባቢ ምናልባት ሥራ የተሠራ አይመስለኝም፡፡ ባለፈው ጊዜ አንድ የማውቀው የአንድ ባንክ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አግኝቼ ስለአዲሱ ቼክ ስጠይቀው፣ ያው አስቀምጨዋለሁ እስከ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ድረስ ጊዜ ሰጥታችሁን የለም እንዴ አለኝ፡፡ ይህንን በማድረጉ ሁለት ሥጋት እንዳለበት ነገርኩት፡፡ አንደኛው ችግር ደንበኛው ቼኩን ወስዶ ያለመጠቀሙ ባንኩ ለቼኩ ኅትመት ያወጣውን ወጪ ያለማሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ቼኩ ታትሞ የመጣው በእያንዳንዱ ደንበኛ ስም በመሆኑ ከዚያ ደንብኛ ውጭ ቼኩን የሚጠቀምበት የለም፡፡ ስለዚህ የቅርንጫፉ ኃላፊ ደንበኛውን ጠርቶ በስሙ የታተመውን ቼክ መስጠት ሲችል ዝም ማለቱ ባንኩን ላላስፈላጊ ወጪ ይዳርገዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አዲሱን ቼክ ደንበኞቻችሁ እንዲጠቀሙበት አለማድረጋችሁ ዓላማውን እንዲበላሽ እያደረጋችሁ ነው፡፡ በኋላ እኮ ደንበኞቻችሁን ነው ችግር ውስጥ የምትከቱት ብዬ ነገርኩት፡፡ ስለዚህ በባንኮች ዘንድ ያለው የግንዛቤ ክፍተት ለአዲሱ ቼክ ሥርጭት ማነስ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ባንኮች በደንበኞቻቸው ስም ያሳተሙትን ቼክ ያለማሠራጨታቸው ራሳቸውንም እንደሚጐዳ ተገልጿል፡፡ ደንበኛው ላይ ግን ችግር የሚፈጥረው እንዴት ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ይህንን ያልኩበት ምክንያት ከሐምሌ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ተነስቶ ከዚህ በኋላ መጠቀም የሚቻለው በአዲሱ ቼክ ብቻ ነው ብሎ መመርያ ቢያወጣ፣ ደንበኞች የግድ አዲሱን ቼክ መጠቀም ይጀምራሉ፡፡ ያኔ አሁን በአዲሱ ቼክ መጠቀም ያልጀመረ ደንበኛ የሚጽፈው ቼክ የተሰረዘ ነው የተደለዘ ነው ተብሎ ከመጨቅጨቅ ያድናል፡፡ ምክንያቱም በአዲሱ ቼክ አጠቃቀም ከዚያ ቀደም ከነበረው የተለየ በመሆኑ ቼኩ አሁን ተሰጥቷቸው እንዲለማመዱበት ካልተደረገ፣ በሚፈጠር ጥቃቅን ነገር ደንበኛው ሊጉላላ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ ቼክ የግድ ሥራ ላይ መዋል አለበት ተብሏል፡፡ ስለአዲሱ ቼክ ግን ብዙ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አልተሠራም፡፡ በአዲሱ ቼክ መጠቀም ጠቃሚ መሆኑም ተነግሯል፡፡ እንደ አንድ ቼክ ተጠቃሚ በአዲሱና በቀድሞው ቼክ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ደንበኛው በአዲሱ መጠቀሙስ የሚያስገኝለት ጥቅም እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ ይህንን ቼክ ባንኩ አሳትሞ ያመጣል፡፡ ከዚያ ለቼክ ተጠቃሚ ደንበኞች ይሰጣል፡፡ የቼክ ደንበኛው ደግሞ ለክፍያ ለሌሎች ይሰጣል፡፡ አሁን ያለውን ቼክ አይቼ የዚህ ባንክ ነው ለማለት ምንም መለያ የለውም፡፡ አዲሱ ቼክ ‘ወተር ማርክ’ (የቼኩ የተለየ መለያ የዋልያ ምሥል) አለው፡፡ አሁን በተለምዶ እንደምናደርገው የ100 ብር ኖትን ወደ ብርሃን አድርገን ትክክል ነው አይደለም ብለን እንደምንለየው፣ የተማረም ይሁን ያልተማረ ሰው ይህንን ቼክ ብርሃን ላይ አይቶ ይህ ቼክ የኢትዮጵያ ባንኮች ቼክ ነው ይላል፡፡ መንግሥት ሥራ ላይ ያዋለው አዲሱ ቼክ ነው ብሎ ሊወስን የሚችልበት አቅም የፈጠረ ነው፡፡ ይህ በቀድሞው ቼክ ላይ አልነበረም፡፡ አዲሱ ቼክን ብርሃን ላይ አድርገህ ስታየው የሚሰጥህ መረጃ ደንበኞች በቼኩ ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ አንዳንዴ አንዳንዱ የቀድሞውን ቼክ ለመቀበል ይፈራ ነበር፡፡ ሥጋት ነበረው፡፡ አሁን ግን ‘ወተር ማርኩን’ ብቻ በማየት ይረዳል፡፡ ‘የወተር ማርኩ’ ምሥል ደግሞ የዋልያ ስለሆነ በቀላሉ የሚለይ ነው፡፡ በጽሑፉም “IBEX” የሚል ይታያል፡፡
ሪፖርተር፡- በሁለቱም ቼኮች የመጠቀሙ ወይም የሽግግሩ ጊዜ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ያልቃል፡፡ ከሐምሌ በኋላ በአዲሱ ቼክ መጠቀም አስገዳጅ ሊሆን ይችላል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዎ ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የስድስት ወራት የሽግግር ጊዜ የተሰጠ ቢሆንም፣ አሁንም አሮጌው ቼክም እየተሰጠ ከሆነ ችግር አይፈጥርም? ምክንያቱም አንድ ቼክ እስከ ስድስት ወራት ሊያገለግል ይችላል፡፡ ከሥር ከሥር የሚሰጥ አሮጌ ቼክ ካለ ይኼ የሽግግር ጊዜውን አያራዝምም?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ይኼ የብሔራዊ ባንክ ሥልጣን ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከሐምሌ ጀምሮ ይህንን ቼክ መጠቀም ግዴታ ነው የማለት ሥልጣን አለው፡፡ በሒደቱ ላይ የሚወሰኑ ነገሮች አሉ፡፡ የሚቋቋመው ኮሚቴም የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ ኮሚቴው በቀረችው ሦስት ወራት ውስጥ የሚያመጣው ለውጥ ይታያል፡፡ አሁን ታየ የተባለው ችግር በአንድ ወር ሊለወጥም ይችላል፡፡ ይህ ታይቶ በአዲሱ ቼክ መጠቀም ግዴታ እንዲሆን ሐምሌ ላይ ሊፀና ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ግን አሮጌ ቼኮች አይጣሉም፡፡ ተጽፈው በእጅ የሚገኙ የቀድሞ ቼኮችም ጉዳይ ምን ይሁኑ የሚለው በብሔራዊ ባንክ ይወሰናል፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ጐን ለጐን የሚሠሩበት ጊዜ ተወስኗል፡፡ የሚያስፈልገው ጊዜ ተገድቧል፡፡ አስገዳጅ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እዚህ ላይ ይኼ ጊዜ ለደንበኞች ጠቃሚ ነው የሚባለው ለመጨረሻ ተከፋዩም ሆነ ቼኩን ለሚጽፈው ሰው የመለማመጃ ጊዜ ይሆነዋል በሚል ነው፡፡ የአዲሱ ቼክ አጠቃቀም መለመድ አለበት፡፡ ለምሳሌ አዲሱ ቼክ ሲያዝ መታጠፍ የለበትም ተብሏል፡፡ ምናልባት የታጠፈው ቼክ ሊፈጥር የሚችለውን የእጥፋት ምልክት ማሽኑ ሲያነበው ያልሆነ መረጃ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ደንበኛው ሊጐዳ ይችላል፡፡ አለማጠፍ ይመከራል፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁን ከአዲሱ ቼክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የገጠመ ችግር የለም? ምን ተገነዘባችሁ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ማሽኑ ሲያነበው ሊፈጠር የሚችል ችግር ሊኖር እንደሚችል እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር አልታየም፡፡ እስካሁን የአዲሱ ቼክ ተጠቃሚዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ችግሮችን በደንብ ለመለየት አልተቻለም፡፡ ተጠቃሚዎቹ ሲበዙ ሊለዩ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ ቼክ ሁሉንም ወገን እንደሚጠቅምና በቀላሉ ሊጭበረበር አይችልም ብላችኋልና ያስረዱን?
አቶ ኃይለየሱስ፡- የዚህ ቼክ አንዱ ጠቀሜታው ከቀድሞ ቼክ በተሻለ ለደንበኛው መተማመን የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ደንበኛው ቼኩን በአግባቡ ይዞ ከመጣ በዕለቱ ወደ አካውንቱ ይገባለታል፡፡ ቼክ ለማጣራት ወር፣ ሁለት ሳምንት፣ ሦስት ሳምንት ፈጀብን የሚለውን ነገር ያስቀራል፡፡ ይህንን ያስወግዳል፡፡ አዲሱ ቼክ ለማጭበርበር የተመቸ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ ቼክ በቀላሉ ለማጭበርበር አይመችም ሲባል እንዴት?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አንዳንድ ቼኮችን ዘመናዊ በሚባል ፎቶ ኮፒ ብታነሳቸው ከትክክለኛው ቼክ የማትለይበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ቼኩ ላይ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ አሁን አዲሱን ቼክ ፎቶ ኮፒ ስታነሳው ቮይድ የሚል ጽሑፍ ይዞ ነው የሚወጣው፡፡ ስለዚህ ቮይድ እያለ ክፍያ የሚፈጽም የለም፡፡ ስለዚህ አንዱ መከላከያ ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱ ቼክ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ቼኮቹን ለሁለት ነው የከፈልናቸው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያዋልነው ሁለት ዓይነት ቼክ ነው፡፡ ትልቁ ቼክ ለቢዝነስ ሰዎች፣ ለነጋዴዎችና ለባለድርጅቶች የሚሰጥ ነው፡፡ አነስተኛው ቼክ ደግሞ በቁጠባ ሒሳብህ ቼክ ማንቀሳቀስ የሚያስችልህ ነው፡፡ ስለዚህ የቁጠባ ሒሳብ ያለው ሰው ቼክ ጽፎ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ሁሉም ሰው ቼክ መጠቀም ይችላል ማለት ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዎ፡፡
ሪፖርተር፡- በቁጠባ ሒሳብ ቼክ ማንቀሳቀስ ይቻላል ማለት ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዎ! ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ባንኩ ቼኩን ሊሰጥህ ሲወሰን አንተን በአግባቡ ማጥናት አለበት፡፡ ቼኩን በአግባቡ ይጠቀምበታል ወይ የሚለውን ማየት አለበት፡፡ መብት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ግን ስጧቸው ብሎ አያስገድድም፡፡ ግን አመቻችቶላቸዋል፡፡ ባንኮቹ እያጠኑ ለጥሩ ደንበኞቻቸው መስጠት ይችላሉ፡፡ በቼክ ለመገልገል የግድ ነጋዴ ብቻ መሆን የለበትም በሚል ነው አሠራሩ የተፈጠረው፡፡ በእነዚህ ሁለት ዓይነት ቼኮች በምትሠራበት ጊዜ ወይም የቼክ ተጠቃሚዎች እየበዙ ከሄዱ እንደ አገር የገንዘብ ዝውውር ይቀንስና ወደ ቼክ እየተሸጋገረ እንዲሄድ ያስችላል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ገንዘብ ባንክ ላይ እንዲቆይ ያስችላል፡፡ ከባንክ ወደ ባንክ የሚገባ ስለሆነ ገንዘብ በጆንያ ይዞ መሄድን ያስቀራል፡፡ ከዚህ ባሻገር የክፍያ ሥርዓትን በከፍተኛ ደረጃ ያቀላጥፋል፡፡ በቼክ መጠቀም ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ ገንዘቡ በቼክ ወይም በወረቀት መንቀሳቀሱ፣ ገንዘብ (የብር ኖት) ለማሳተም የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪም ይቀንሳል፡፡ ገንዘብ ሲያረጅ የሚቃጠለውም በወጪ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ላለው ነገር ይጠቅማል፡፡ ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ ደግሞ ለምሳሌ አዋሽ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት ሚሊዮን ብር የሚከፈለው ገንዘብ ይኖራል፡፡ አዋሽ ባንክ ደግሞ ለዳሸን ባንክ መክፈል የሚኖርበት ሦስት ሚሊዮን ብር ይኖራል፡፡ ከአዋሽ ባንክ ለዳሸን ለመክፈል የተሳሰረ ነው፡፡ ገንዘቡን ያቀናንሳል፣ የመተላለፉን ነገር ያስቀራል፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል መሠረተ ልማት አለ፡፡ ባንኮቹ ይህንን ሊጠቀሙ ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት ግን በጣም ዘግይታችኋል፡፡ ለምን?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የቼክ ስታንዳርዱን ከእኛ አገር አሠራር ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ነበረብን፡፡ በእኛ አገር ስታንዳርድ ማዘጋጀት ነበረብን፡፡ የንግድ ሕጉ አለ፡፡ ሌሎች የሚያግዱህ ነገሮችም አሉ፡፡ ብሔራዊ ክፍያ አዋጁንም አሉ፡፡ የብሔራዊ ክፍያ አዋጁንም እያየንና እያገናዘብን ከእሱ ጋር ለመሄድ ብዙ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ አንዱ ምክንያት ይኼ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር ደግሞ ዲዛይን ነው፡፡ የየአንዳንዱን ባንክ ዲዛይን ለማሠራት ስንገባ አንዱ ነጣ ያለ አረንጓዴ ይሁንልኝ ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ ፈዘዝ ያለ ቢጫ ይላል፡፡ ይህንን ለመስማማትና ለመተማመን ዓመት ፈጅቶብናል፡፡ ዲዛይን ለመጨረስ ቀለም ለመምረጥ የነበረው ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡ ከቀለሙ ባሻገር መካከል ላይ የዲዛይን ለውጦች መጡ፡፡ ‘ወተር ማርኩን’ መሀል ላይ ነው ያስገባነው፡፡ ይህ ሲሆን ‘ወተር ማርኩን’ ምን እናድርገው ሲባል ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ይወስን ወይስ ባንኮች ሲባል፣ ፕሮጀክቱ የጋራ ስለሆነ ባንኮቹ ይወስኑ አማራጭም ያቅርቡ ተባለ፡፡ ምን ዓይነት ‘ወተር ማርክ’ እንጠቀም ምረጡና ላኩ ብለን ለባንኮቹ አማራጭ እንዲያቀርቡ ጠየቅን፡፡ ከሁሉም ባንክ ‘ወተር ማርኩ’ ይኼ ይሁን ብለው የተለያየ ምሥል ላኩልን፡፡ 46 ዓይነት ምሥሎችን ሰበሰብን፡፡ ከዚህ ውስጥ የሚቀራረቡትን ጨምቀን ስድስት ተመርጠው በስድስቱ ላይ ባንኮች ድምፅ እንዲሰጡ ተደረገ፡፡ ውጤቱ ሲታይ አንደኛ የተመረጠው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምሥል ነበር፡፡ ሁለተኛ የዋልያ ምሥል ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን በአዲሱ ቼክ ላይ ያለው መለያ ምሥል (ወተር ማርክ) የዋልያ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ምሥል ተመርጦ ለምን ዋልያ ተደረገ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ሁለተኛ የነበረውን የዋልያ ምሥል ነው የመረጥነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ምሥልን ለመጠቀም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጽሕፈት ቤትን የግድቡን ምሥል በቼኩ ላይ ለመጠቀም ስንጠይቅ መጠቀም አይቻልም በማለቱ፣ በቀጥታ በሁለተኛ ደረጃ የተመረጠውን ዋልያን ተጠቀምን፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቶቹ ሥራዎችም ጊዜ ወስደዋል፡፡ ሌላው ጊዜ የፈጀብን ደግሞ የቼክ ኅትመት ከመደረጉ በፊት የሚታተምበት ወረቀት መመርመር አለበት፡፡ ወረቀቱ ስታንዳርድ ነው ወይም አይደለም የሚባለው ነገር መመርመር ነበረበት፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ምርመራውን ከኢትዮጵያ ውጪ ልኮ ማካሄዱ ግድ ስለነበር ይኼ ጊዜ ወሰደ፡፡ በአይኤስኦ መረጋገጥ ስለነበረበት ይህም ተደረገ፡፡ ሌላው በዋናነት ጊዜ የፈጀብን ነገር ከየባንኮቹ ማግኘት ያለብን የደንበኞች ዳታ መዘግየት ነው፡፡ በአዲሱ ቼክ አሠራር መሠረት የቼክ ተጠቃሚው ደንበኛ ኩባንያ ወይም ስም በቼኩ ላይ መታተም አለበት፡፡ የተላከውን ዳታ ለማስተካከል ብቻ ከስድስት ወራት በላይ ፈጅቷል፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግልጽ እንዲሆን የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ቼክ ላይ የቼክ ተጠቃሚው ኩባንያ ወይም ስም ከቼኩ ጋር አብሮ አይታተምም ነበር፡፡ ባንኮቹ በራሳቸው መንገድ የደንበኞቻቸውን ስም በማሳተም ወይም በሌላ መንገድ የደንበኛቸውን ስም ይጽፋሉ፡፡ በአዲሱ ቼክ ላይ ግን ባንኮች የደንበኞቻቸውን አካውንትና ስም ለማተሚያ ቤቱ ልከው ቼኩ ላይ ነው ታትሞ የሚመጣው ተብሏል፡፡ ይህ ለምን ሆነ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- የመጀመሪያው ዙር አዲሱ ቼክ እዚያው ታትሞ ነው የመጣው፡፡ የሚቀለውም ይኼ ነው፡፡ ለቀጣዩ ግን ሌላ አሠራር አለው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ አንድ ሰው የቼክ ተጠቃሚ የባንክ ደንበኛ ቢሆን ቼኩ ሲታተም ስሙ ታትሞ ነው የሚወጣው ማለት ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዎ፡፡ ቼክ ‘ፐርሰናላይዜሽን’ ይባላል፡፡
ሪፖርተር፡- ባንኩ በዚህኛው ደንበኛ ስም ይህንን ያህል የቼክ ጥራዝ፣ ለዚያኛው ደንበኛዬ ደግሞ ይህንን ያህል ቼኮች ይታተሙልኝ እያለ እንዲታተምለት ሊያዝ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አንድ የቼክ ተጠቃሚ ደንበኛ ምን ያህል ቼክ ሊጠቀም ይችላል ተብሎ ነው የሚታዘዘው? በግምት የሚሠራ ነው ማለት ነው? አሁን ባንኮች በደንበኞቻቸው ስም ያሳተሙዋቸው ቼኮች ታትመው መጥተዋል፡፡ የአዲሱ ቼክ ተጠቃሚ የሆነ ሰው ቢቀርብ ስሙ የታተመበት ቼክ የለምና እንዴት ሊጠቀም ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ትክክል ነህ፡፡ ሁለቱን ተግዳሮቶች አመጣህልኝ፡፡ አዲስ የሚከፍተውን እናቆየው፡፡ ግን ባንኩ አንተን ከባንኩ ጋር ባለህ ግንኙነት ያውቅሃል፡፡ በዚህ የሥራ ግንኙነታችሁ ባንኩ በሁለት ወር በሦስት ወር ምን ያህል ቼክ እንደምትጠቀም መገመት አለበት፡፡ ነገር ግን የቢዝነስ እንቅስቃሴህ ሲያድግ የምትጠቀመው ቼክ ሊጨምር ይችላል፡፡ ሲያንስ ደግሞ ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን ባንኮቹ በግምት ይዘው ይህንን ያህል ሊጠቀም ይችላል ብለው እንዲታተምላቸው አዘዋል፡፡ በዚህ ነው እንጂ የአንተ ጥያቄ አይጠበቅም፡፡ እንደዚያ እናድርግ ካልን ይህንን ነገር ማምጣት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ያንን ዳታ እናሰባስብ ካልን ደግሞ ተጨማሪ ወራት ልንፈጅ ነው ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ስለዚህ እያንዳንዱ ባንክ በራሱ ግምት ይኼ ደንበኛዬ ይህንን ያህል፣ ያኛው ደግሞ ይህንን ያህል ብሎ አቀረበ፡፡ በዚያ መሠረት ነው የታተመው፡፡
ሪፖርተር፡- ወዳልመለሱልኝ ጥያቄዬ ልመለስ፡፡ አዲሱ ቼክ በእያንዳንዱ ቼክ ተጠቃሚ ኩባንያ ታትሞ ከመጣ አዲስ ቼክ ተጠቃሚ ቢመጣስ? ዛሬ የቼክ ተጠቃሚ ለመሆን የሚመጣ ደንበኛ እንዴት ይስተናገዳል? በስሙ ታትሞ የገባ ቼክ ከሌለ ምንድነው የሚደረገው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ለአዲስ ቼክ ተጠቃሚ ደንበኞች ሌላ የታሰበ ነገር አለ፡፡ ይህም በቀጣይ እያሰብነው ያለው በአዲሱ የቼክ ስታንዳርድ የደንበኛው የቅርንጫፉና የአካውንቱ ቁጥር የሌለበት ቼክ ማሳተም ነው፡፡ ለምሳሌ ለደቡብ ግሎባል ባንክ ቼክ ሲታተም በአዲሱ ቼክ ዲዛይንና ቅርፅ ሆኖ የደንበኛው ስም የሌለበት፣ የቅርንጫፍና የቼክ ቁጥር የሌለበት፣ የባንኩ ስምና ሌሎች መረጃዎች የተካተቱበት ቼኮች ለብቻ ይታተማሉ ማለት ነው፡፡ አዲሱ ደንበኛ ሲመጣ የደንበኛውን ስምና ቀሪ መረጃዎችን በቼኩ ላይ ታትሞ ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ አዲሱ ቼክ ተጠቃሚ ደንበኛ ሲመጣ ቼክ መክፈት የሚችል መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ለዚሁ አገልግሎት በሚውለው በቼክ ማተሚያ ማሽን የሚፈልገውን ያህል ቼክ ታትሞ እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ባንኮች ለአዲስ ደንበኞቻቸው ለሚሰጡት አዲስ ቼክ ቀሪውን መረጃ በቼኩ ላይ የሚያትምላቸው የተለየ ማተሚያ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው?
አቶ ኃይለየሱስ፡- አዎ፡፡ ነገር ግን ይህንን ሥራ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ልሥራው እያለ ነው፡፡ ሌላው ዓለም ላይ እንዲህ ያለውን ሥራ ለሌላ ነው የምትሰጠው፡፡ ቼክ የማተም ሥራ የባንኮች መሆን የለበትም፡፡ የማተሚያ ቤቶች ነው፡፡ በአገራችን በቼክ ኅትመትና በተያያዥ ሥራዎች ብርሃንና ሰላም ይታወቃል፡፡ ሴኩሪቲውን ያውቀዋል፡፡ እኛ የማናውቃቸውን ብዙ ነገሮች ያውቃል፡፡
ሪፖርተር፡- እንደገለጹልኝ ለአዲስ ደንበኞች ይሰጣል የተባለው ባዶ ቼክ ግን ታትሞ መጥቷል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ገና ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዛሬ አዲስ ቼክ ተጠቃሚ ቢመጣ ምን ይሰጠዋል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ደንበኛው ዛሬ ቢመጣ አሮጌው ቼክ ነው የሚሰጠው፡፡ ግን ባዶውን ቼክ ለማሳተም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የኮሚቴው አንዱ ሥራው ይኼ ነው፡፡ ግን የደንበኞች ስም ያልታተመበት ቼክ ከውጭ ታትሞ መጥቶ ብርሃንና ሰላም እንደሚቀመጥ ነው የታሰበው፡፡ ይህንን ለማድረግ እየተነጋገርን ነው፡፡ እኛ የምናስበው የባንኮች መረጃ ኦንላይን ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጋር ይገናኛል፡፡ ለዚህ ኃላፊነት ለተመደበ ባለሙያ አዲስ ቼክ ፈላጊ መረጃውን ሞልቶ ለብርሃንና ሰላም ሲልክለት፣ ማተሚያ ቤቱ በሚገባው የአገልግሎት ውል መሠረት በ24 ወይም በ48 ሰዓት አትሞ ይልክለታል፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱን ቼክ ሙሉ ለሙሉ ለማስገባት አሁንም ቀጣይ ሥራዎች መኖራቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአዲሱ ቼክ መጠቀም አስፈላጊ ነው እየተባለ ለአዲስ ደንበኛ የሚሆን ቼክ ያለመዘጋጀቱ ግን ብዥታን አይፈጥርም?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ለአዲስ ደንብኛ የሚሰጥ አዲሱ ቼክ አሁን ስለሌለን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወጥ የሆነ አገልግሎት ይሰጥ እየተባለ አዲሱን ቼክ መጠቀም ግድ ነው እየተባለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለአዲስ ቼክ ተጠቃሚ ደንበኛ አሮጌው ቼክ የሚሰጥ ከሆነ አሠራሩን ጉራማይሌ አያደርገውም?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ትክክል ነው፡፡ ይህ በሽግግር ጊዜ ያልቃል ብሎ ብሔራዊ ባንክ አቅዷል፡፡ ስለዚህ ባዶው ቼክ ከታተመ ክፍተቱ ይደፈናል፡፡ ምንም ዓይነት ችግር አይኖርም፡፡
ሪፖርተር፡- ማተሚያ ቤቱ የአዲሱን ቼክ ቀሪ መረጃዎች ሊያትም ይችላል?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ሊያትም ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- አዲሱን ቼክ ሥራ ላይ ለማዋል ሁሉም ባንኮች በጋራ ቼኮቻቸውን አንድ ላይ አሳትመው ወስደዋል፡፡ ከዚህስ በኋላ ተጨማሪ ቼክ ቢፈልጉ እንዳሁኑ በጋራ ነው ወይስ በግል ነው የሚያሳትሙት?
አቶ ኃይለየሱስ፡- ከዚህ በኋላ በየግል ነው የሚያሳትሙት፡፡ ነገር ግን ለቼኩ ኅትመት የሚውለውን ወረቀት በጋራ ቢያስመርቱ ወጪ ይቀንስላቸዋል፡፡ ለማጓጓዣም ይረዳል፡፡ አሁን እንዳየነው ባንኮቹ በጋራ የመሥራት ስሜት እያሳዩ ነው፡፡ አሁን ብሔራዊ ባንክ እየታገለ ያለው ነገሩን መስመር ለማስያዝ ነው፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትም አዲስ መሣሪያ አዞ እያስገባ ነው፡፡ ሐምሌ ላይ ይደርሳል፡፡ ባንኮች ደግሞ እንዲያሳትሙ ግፊት እያደረግን ነው፡፡