Wednesday, February 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱሪዝም ዘርፍ ምላሽ የሚሰጥባቸው የቱሪዝም ጥያቄዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለበርካታ ዓመታት አገሪቱን በቱሪዝም ዓርማነት ወክሎ ለዓለም ሲያስተዋውቅ የቆየው 13 ወር ፀጋ የተሰኘው የአገሪቱ የቱሪዝም መለያ በአዲስ ተቀይሯል፡፡ መንግሥት ለረጅም ጊዜ ያገለገለውን መለያ መቀየሩ የማይቀር መሆኑን መግለጽ ከጀመረ ቢቆይም፣ አዲስ የቀየረውንና ሥራ ላይ ያዋለውን ‹‹Land of origins›› ወይም ‹‹የመገኛዎች ምድር›› የተባለውን አዲሱ የአገሪቱ መለያ ይፋ በማድረግ ማስተዋወቁ ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡

አሁን የቀየረውና ሥራ ላይ ያዋለው ዓርማ ወይም መለያ ከቀድሞው የተሻለበትን፣ የላቀበትንና የሚበልጥበትን አመክንዮ በአደባባይ ማሳወቅና ማስረዳት ቢጠበቅበትም በውጭ አገር ከሚደረግ ማስተዋወቅ በቀር ዓርማውን በሚመለከት የሚደረጉ ውይይቶች እምብዛም አለመሆናቸው እየታየ ነው፡፡ ነገር ነገርን ስላነሳው እንጂ ዋናው ጉዳይ አገሪቱ በቱሪዝም መስክ እያካሄደች ስላለችው እንቅስቃሴ መመልከት ነው፡፡

በአገሪቱ ሰፊ የቱሪስት መዳረሻና መስህብ ቦታዎች የሚገኙ በመሆኑ ከቱሪዝም መስክ ሊገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ መንግሥት በቅርቡ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ካሳየበት ኩነት መካከል ብሔራዊ የቱሪዝም ምክር ቤት ማቋቋሙ ይጠቀሳል፡፡ ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሚመራ ሲሆን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራን፣ በዘርፉ የሚመለከታቸው ሚኒስቴሮች፣ የሆቴል ባለሀብቶችና ባለሙያዎች ወዘተ. ተካተውበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆነ የአትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የተሰኘ መሥሪያ ቤትም ተቋቁሟል፡፡ የአገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች ማስፋፋትና ማስተዋወቅ ለቱሪዝም ድርጅት ከተሰጡ አደራዎች መካከል አንኳር ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ አዳዲስ ሆቴሎች በአገር ውስጥ ባለብቶች እየተገነቡ የውጭ ብራንዶችም እየመጡ መሆኑ ለቱሪዝም መስኩ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ መሠረት፣ በአዲስ አበባ በተለይ ከጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የሆቴል ግንባታ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በየወሩ በአማካይ ሁለት ሆቴል መከፈት የተጀመረበት ወቅት ላይ መደረሱን የማኅበሩ ሊቀመንበርና የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ብሥራት ገልጸዋል፡፡  ከስምንት ዓመት በፊት አዲስ አበባ የነበሯት ባለኮከብ ሆቴሎች 60 ብቻ እንደነበሩም አቶ ቢንያም ያስታውሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት 130 ባለኮከብ ሆቴሎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆን፣ በአምስት ዓመት ውስጥ ተጨማሪ 100 ሆቴሎች ምድቡን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል ያሉት አቶ ቢንያም፣ የባለኮከብ ሆቴሎች መበራከት ከዚህ ቀደም አገሪቱ ታጣ የነበረውን ትልልቅ ስብሰባዎች የማስተናገድ ዕድል እየተስፋፋ በመምጣት በአንድ ጊዜ ከአምስት ሺሕ በላይ ታዳሚዎች የሚስተናገዱበት ጉባዔን ማሰናዳት ጀምራለች፡፡

የትልልቅ ስብሰባዎች መምጣት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን መበራከት ብቻም ሳይሆን የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታዎችም እኩል በእኩል አስፈላጊ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድም ተስማሚ በመሆኗ ለትልልቅ ጉባዔዎች ተመራጭ መሆኗን አቶ ቢንያምም ሆኑ፣ የሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ምክትል ሰብሳቢና የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን ያምኑበታል፡፡ የሆቴሎች መበራከት ለስብሰባ የሚመጡ ታዳሚዎች ጥያቄ መመለሱና ምቾታቸውን ማስጠበቁ እየተሻሻለ መምጣቱ አያጠያይቅ ይሆናል፡፡

ነገር ግን የኮንፈረስ ቱሪዝም ታዳሚዎችን ያህል በዓላት ላይ ለመገኘት፣ ቅርስ ለመጎብኘት፣ ታሪክ ለማጥናት አለያም መልከዓ ምድሩ ማርኳቸው የሚመጡ፣ ከዚህም ሲልቅ የዱር እንስሳት ለማደን የሚጎበኙንን በሚመለከት ምን እየተሠራ እንዳለ ማወቅ ከባድ ነው፡፡ ቢሠራም በተግባር የሚታየው ነገር አጥጋቢ አይደለም፡፡ አገሪቱን ለመጎብኘት ከሚመጡ መካከል ሪፖርተር በጣት ከሚቆጠሩት የቃረማቸው ትዝብቶች የአገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች አሠራር ጥያቄ ውስጥ የሚከት ይሆናል፡፡

በቅርቡ እንዲሁ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት አስበው ከመጡ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአሥር ቀናት በላይ በሰሜንና ደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ቆይታ አድርጎ ተመልሷል፡፡ ይህ ሰው ምንም እንኳ በሚዲያ ቀርቦ እንዲህ ነው ማለቱን ባይወደም መስተካከል አለበት ያለውን ነገር ሁሉ ከመናገር አልተቆጠበም፡፡ አገሪቱ ለየትኛውም ጎብኝ የሚስማማ መዳረሻ እንዳላት መገንዘቡን ይገልጻል፡፡ ሐይቆች፣ ታሪካዊ፣ ቅርሳዊ፣ መንፈሳዊ እንዲሁም ባህላዊ መዳረሻዎቿ ለመጎብኘት ብቁ እንደሚያደርጓት አይጠራጠርም፡፡

ይሁንና አገልግሎት አሰጣጥና አገልግሎት መስጫዎች ችግር አለባቸው ሲል ፈርጠም ብሎ ይሞግታል፡፡ እንደ እርሱ ለስብሰባ ሳይሆን አገር ለማየት ብለው የሚመጡ፣ ከስብሰባ ታዳሚዎች ይልቅ እንደ እሱ የአገሪቱን ወዲህና ወዲያ ጫፍ እያዩ በቀናት ላይ ቀናትን እያጋመሱ የሚጎበኙት ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ሲጠቁም የታዘባቸውን ችግሮች በመጥቀስ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ትልልቅ የሚባሉ ሆቴሎችን ጨምሮ እስከ ክልሎች ሳይቀር ሥር የሰደደ የአካባቢና የግል ንጽህና ጉድለቶች በሰፊው ይታያሉ፡፡ የመታጠቢያ፣ የመጸዳጃ፣ የምግብ ማብሰያና የመኝታ ቤቶች ውስጥ የሚታየው የንጽህና ጉድለት ቶሎ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ መሠረታዊ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶች መጠበቅ እንዳለባቸውም ይመክራል፡፡ እንዲህ ባሉት ጉዳዮች ላይ ለቱሪስት ብቻም ሳይሆን በዋናነት ለአገሬው ሰው ሲባል የጤና አጠባበቅን እንዳያዛቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጎብኝው ፈረንሳዊ ትዝብቱን ይቀጥላል፡፡

በአገሪቱ ከከተማ እስከ አገር አቋራጭ ባለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ የሚሰጠው አገልግሎት ለአገሬውም ለጎብኝም የተስማማ መሆን እንዳለበት ሲተነትንም፣ ቱሪስቶች ገንዘብ ይዘው እንደሚመጡ በማሰብ ብቻ ውድ የትራንስፖርት መስመሮችን እንዲጠቀሙ መጠበቅም ሞኝነት እንደሚሆን ይገልጻል፡፡ እግርጥ እንደደረጃውና እንደቱሪስቱ በጀት አኳያ ለሚከፍለው ገንዘብ ተመጣጣኝ  ደረጃ ያላቸው አገልግሎቶችን ማቅረብ ተገቢ ቢሆንም፣ መሠረታዊ የጥራትም የጤናም ደረጃዎች መጓደል እንደማይገባቸው፣ በየትኛውም እርከን የሚገኝ የመንግሥት አካል እንዲህ ላሉት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት መከታተል እንደሚገባው ሲያስታውቅ፣ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ራሳቸው አገሪቱ አሁን ላይ በጎብኚዎች ያላት ተፈላጊነትን በመመልከት በጓሯቸው በኩል አጠያፊ ለሆኑት ነገሮች ትኩረት በመስጠት እንዲያስተካክሉ አሳስቧል፡፡

እውነትም በጎብኝና በአገሬው መካከል የኑሮ ደረጃ መገለጫ እስኪመስሉ ድረስ በአዲስ አበባም ሆነ በየክልሎች ሬስቶራንቶች፣ አነስተኛ ምግብ ቤቶች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ መናኸሪዎች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ግሮሠሪዎች ወዘተ. ውስጥ ከንጽህና አኳያ የሚታየውን ጉድለት ጉዳዬ የሚለው ያጣ መስሏል፡፡ እጅ የሚያስቆረጥም ምግብ ከተበላ በኋላ ለመጸዳዳት ዞር ሲባል አፍንጫ የሚሰነፍጡ፣ የሚተናነቁ፣ ከፊት ለፊት በተንቆጠቆጠ መብራትና ጌጣጌጥ ተውበው ከጓሮ በክፉ ሽታ፣ በአስቀያሚ ገጽታና በተዝረከረከ ንጽህና የሚቀበሉ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡

ከዚህ ሲብስም ለተስተናጋጅ ግድ የማይላቸው፣ ሻይ ቡና ለማለት የገባው ታዳሚ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ዞር ብለው የማይመለከቱ፣ ሊወጣ ሲነሳ እግር ጠብቀው ‹‹ምን ነበር›› የሚሉ አስተናጋጆችም ከትዝብት አላመለጡም፡፡ በተለይ በመንግሥት የሚተዳደሩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ጎልቶ የሚታይ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ጎልቶ ይታያል፡፡

እንዲህ ባለ አኳኋን የውጭ ጎብኚዎችን መሳብ ለኢትዮጵያ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቅሱ ጎብኚዎች፣ በሌላ አንፃር  ግን አገሪቱ ያላት ሰላምና ደኅንነት ለመጎብኘት ዕጩ እንዲያደርጋት የሚገልጹም አሉ፡፡ በዚያም ላይ ለቱሪስት ዓይንም ዕዝንም የሚገቡ፣ የሚያማልሉ፣ ከኢትዮጵያውያን በላይ ራሳቸው ምዕራባውያኑ ለጎብኚዎቻቸው የሚያስተዋውቋቸው ቅርሶችና ባህሎች በአገሪቱ መንሰራፋታቸውም አገሪቱን ለቱሪስት መዳረሻነት ብቁ ያደርጓታል፡፡

በአፋር ክልል የሚገኘው የእሳተ ገሞራ ቅንብብ ውስጥ የሚገማሸረው የኤርታሌ የእሳት ባህር፣ በደቡብ የኮንሶ እርከን ከነተፈጥሮውና ከኮንሶች ውብ ባህል፣ የ16 ብሔር ብሔረሰቦች ማደሪያ ደቡብ ኦሞ፣ የላሊባላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል ግንብ፣ የአክሱም ሐውልቶች ወዘተ. በዓለም ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ቅርሶች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ እነዚህን ቅርሶች የታቀፈች አገር፣ በሰላምና ፀጥታዋ የምትኮራዋ ኢትዮጵያ ግን የዱር እንስሳትን ብቻ በማስጎብኘት በዓመት ቢሊዮን ዶላሮችን ከቱሪዝም ከሚያጋብሱ አገሮች አንፃር  ሲሦውን ማግኘት ያልቻለች ሆና ትገኛለች፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት የአውሮፓ የቱሪዝምና የንግድ ምክር ቤት ኢትዮጵያ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ አገር መሆኗን ለዓለም አብስሮ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ግርምት የሚያጭሩ ዘገባዎችን አስነብበዋል፡፡ የቴሌቪዥን ዜናዎችን አዥጎድጉደዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በተለይ ደይሊሜይል በድረ ገጹ ያስነበበው ጽሑፍ ልብ ያማልላል፡፡

‹‹ብራማዋን ስፔንን እርሷት፣ ማራኪዋን ታይላንድንና የፍቅር ማደሪያዋን ፈረንሳይን ተዋቸው፤›› በማለት ያቀረበው ዘገባ ቀልብ ስቧል፡፡ አገሪቱ ያሏት በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችም ለምክር ቤቱ የዳኝነት አካል ትልቅ ሚዛን ደፍተው ኢትዮጵያ በዓለም መጎብኘት የሚገባት አገር በመሆን ቁንጮ ቦታውን ተቆናጣ ነበር፡፡ በርካታ ግለሰብ ጎብኚዎች አገሪቱ እንድትጎበኝ ብቁ ከሚያደርጓት መካከል የሕዝቦቿ ቀናነት ወይም እንግዳ ተቀባይነትም ሚዛን ከሚደፉ መካከል ይመደባል፡፡ ይህም ሆኖ በየመንገዱ ሳንቲም አምጡ የሚሉ፣ የውጭ ሰው ባዩ ቁጥር ዋጋ የሚቆልሉ፣ በአገሬውና በውጭ ሰው መካከል በግልጽ የሚታይ የዋጋ ልዩነት በየሙዚየሙ መኖሩ መሻሻል ከሚገባቸው መካከል በጎብኚዎቻችን የሚቀጠቀሱ ናቸው፡፡

 

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች