Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ያላቸውን ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ይፈልጋሉ››

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ በ600 ሚሊዮን ዶላር በመገንባት ኢንቨስትመንቱን አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የሲሚንቶ ከረጢት ፋብሪካም ለመገንባት አቅዷል፡፡ በድንጋይ ከሰልና በፖታሽ ማዕድን ፍለጋ የመሰማራት ሐሳብ አለው፡፡ ቃለየሱስ በቀለ የዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ ኢትዮጵያ የሽያጭና ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢንቨስትመንት በመጠኑ ቢነግሩን?

አቶ መስፍን፡- ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ ኢትዮጵያ በ600 የአሜሪካን ዶላር ወጪ ወጥቶበት ግንባታው ተጠናቆ፣ የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነው እ.ኤ.አ. ጁን 4 ቀን 2015 ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ ባለቤትና የቦርድ ሊቀመንበር አሊኮ ዳንጎቴ በተገኙበት ነበር የተመረቀው፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡ ይኼም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ያደርገዋል፡፡ ሁልጊዜም እንደምንለው ይህ ፋብሪካ እጅግ ዘመናዊ ነው፡፡ አውቶማቲክ የመጫኛ ማሽኖች ያሉት፣ በሮቦቶች የታገዘ ላቦራቶሪ ባለቤት ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊ የመጫኛ ማሽኖች ያሉት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው እንደሚታየው መኪኖች ለመጫን ተጨናንቆ ወረፋ የመጠበቅ ነገር የለም፡፡ በቀን እስከ 8,500 ቶን ሲሚንቶ ከፋብሪካችን ተጭኖ ይወጣል፡፡ በተለይ እኛ ምርት በጀመርንበት በሰኔና ሐምሌ 2007 ዓ.ም. በአገሪቱ የሲሚንቶ ምርት እጥረት ተከስቶ ስለነበር በብዛት እያመርትን ወደ ገበያ በማስገባት ገበያውን ማረጋጋት ችለናል፡፡ በኩንታል 450 ብር የነበረውን ዋጋ በእኛ መሸጫ ዋጋ ወደ 200 ብር ማውረድ ችለናል፡፡ ወደ ገበያ የገባነው ከጁን 5 ጀምሮ ሲሆን፣ ገበያ ውስጥ ምርታችን በጥራት፣ በዋጋና በአሠራራችን ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ አዲስ ፋብሪካ በመሆኑ ገበያ ውስጥ ለመግባት ትልቅ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም፣ ጥሩ የግብይት መርሐ ግብር ነድፈን በአቅርቦት፣ በምርት ጥራትና በዋጋ ላይ ወሳኝ ሥራዎች በመሥራታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገበያውን ተቆጣጥረነዋል፡፡

የስድስት ወር እንቅስቃሴያችንን ስንገመግም ዳንጎቴ ሲሚንቶ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ መያዙን ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ገበያው ላይ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 450 ብር በሚሸጥበት ወቅት እኛ ግን 207 ብር ዋጋ ይዘን ነው ወደ ገበያ የገባነው፡፡ ለአከፋፋዮቻችን ቅናሽ አድርገናል፡፡ የእኛ መሸጫ ዋጋ ፒፒሲ ሲሚንቶ 199 ብር፣ ኦፒሲ ሲሚንቶ 270 ብር ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞች ከፍተኛ የገበያ ድርሻ አለን፡፡ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ሐዋሳና ሌሎች የክልል ከተሞች ላይ ኅብረተሰቡ ተቀብሎን የእኛ ምርት በስፋት እየተሸጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሽያጭ ወኪሎች ነው ምርታችሁን የምታዳርሱት?

አቶ መስፍን፡- የጅምላ አከፋፋዮች አሉን፡፡ እነርሱም በየክልሉ የማከፋፈያ ሱቆች አሏቸው፡፡ በእነርሱ አማካይነት ኅብረተሰቡ ያለምንም ችግር ምርቶቻችንን ያገኛል፡፡ እርግጥ መጠነኛ የሎጂስቲክ እጥረት ገጥሞናል፡፡ ችግሩን ለመፍታት እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- 600 የሽያጭ ትራንስፖርት መኪኖች ከቻይና አስመጥታችኋል?

አቶ መስፍን፡- ለጊዜው 443 የጭነት ተሽከርካሪዎች ገብተው ሥራ ጀምረዋል፡፡ ቀሪዎቹ በቀጣይ ወደ አገር ገብተው ሥራ ይጀምራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ያሉት የጭነት ተሽከርካሪዎች በቂ አልሆኑም ማለት ነው?

አቶ መስፍን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ያሉት ተሽከርካሪዎች አልበቁንም፡፡ የዳንጎቴ ትልቁ ዓላማ የአገር ውስጥ ገበያን ከማርካት ባሻገር የውጪ ገበያ ላይ መሰማራት ይፈልጋል፡፡ በዚህም ትርጉም ያለው ሥራ ሠርተን ካለፈው የካቲት ወይም ከፌብሯሪ ወር ጀምሮ ወደ ሰሜን ኬንያ ኤክስፖርት ማድረግ ጀምረናል፡፡ እስካሁን 2200 ቶን ሲሚንቶ ኤክስፖርት አድርገን 240,000 ዶላር ገቢ አስገብተናል፡፡ በአጭር ጊዜ ይህን ያህል የውጭ ምንዛሪ አስገኝተናል፡፡ ዕቅዳችን ይህን በቅርቡ በሦስት እጥፍ ማሳደግ ነው፡፡ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት ወደ ኤክስፖርት እንድንገባ ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኤክስፖርት ላይ የሚነሳ አንድ ችግር አለ፡፡ ሲሚንቶ በመኪና ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ አጓጉዞ ትርፋማ መሆን አይቻልም ይባላል፡፡

አቶ መስፍን፡- የሲሚንቶ ምርት በልክ በመሆኑ ረዥም ርቀት ተጓጉዞ ውጤታማ መሆን አይቻልም የሚለው በአጠቃላይ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የእኛን አገር የቆዳ ስፋት ስትመለከት ሰፊ አገር ነው ያለን፡፡ ባህር ዳር ከእኛ ፋብሪካ 640 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው፡፡ ጎንደር 800 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ነው የምንደርሰው፡፡ ምርታችንን ጋምቤላ አድርሰናል፡፡ ስለዚህ ሰሜን ኬንያ ስንገባ ከእነዚህ አካባቢዎች ባልበለጠ ርቀት ተጉዘን ነው፡፡ በዚህ ውጤታማ ሆነናል፡፡ የእኛ ኩባንያ ወጪ ቅነሳ ላይ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ኢነርጂ አጠቃቀም ላይም ጠንቃቆች ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ መኪኖች እየጠየቅን ያለነው ኤክስፖርትን በበለጠ ለማስፋት ስላቀድን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከኬንያ ባሻገር ወደየትኞቹ አገሮች ኤክስፖርት ለማድረግ ታስባላችሁ?

አቶ መስፍን፡- ከኬንያ በተጨማሪ ሶማሊያን እናስባለን፡፡ ደቡብ ሱዳንንም እያሰብን ነው፡፡ በቅርቡ እኔና የኢትዮጵያ ዳንጎቴ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ደቡብ ሱዳን ተጉዘን ከትራንስፖርት ባለሥልጣናት ጥሪ ተደርጎልን መሠረታዊ ነገሮች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰን ነው የመጣነው፡፡ የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ ከሆነና የመንገዱ ሁኔታ ከተስተካከለ ደቡብ ሱዳን ሰፊ ገበያ እንዳለ አይተናል፡፡ ጂቡቲንም አይተናል፡፡ ጂቡቲ ውስን ገበያ ነው ያለው፡፡ በተወሰነ መልኩ ክሊንከር መላክ እንደሚቻል አጥንተናል፡፡ ሶማሌላንድና ሶማሊያ ሰፊ ገበያ አለ፡፡ ይህን ለማድረግ የሎጂስቲክ አቅማችንን ማሳደግ ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- የዳንጎቴ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ካሉት የዳንጎቴ ፋብሪካዎች በሽያጭ ብልጫ ማሳየቱን ሰምተናል፡፡

አቶ መስፍን፡- ትክክለኛ መረጃ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል፡፡ ለዚሁም የድርጅቱ ባለቤት ለሽያጭ ክፍሉ 40,000 ዶላር በሽልማት መልክ አበርከክተዋል፡፡ በ14 የአፍሪካ አገሮች ካሉት ፋብሪካዎች ከናይጄሪያ በቀር ከሌሎቹ ፋብሪካዎች በሽያጭ የተሻለ አፈጻጸም በማሳየታችን ተሸልመናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በወር ምን ያህል ቶን እያመረታችሁ ነው?

አቶ መስፍን፡- የዕቅዳችንን 100 በመቶ አሳክተናል ማለት ባንችልም ጥሩ አፈጻጸም ላይ ነን፡፡ በዚህ ወር 175,000 ቶን ሲሚንቶ አምርተን እንሸጣለን፡፡ እስካሁን ባለን አፈጻጸም 175,000 ቶን ሽያጭ እናሳካለን ብለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በበጀት ዓመቱ ምን ያህል ለመሸጥ አቅዳችኋል?

አቶ መስፍን፡- በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን በጀት ዓመት 2015 አንድ ሚሊዮን ቶን አምርተን ለገበያ አቅርበናል፡፡ ይህ እንዲህ በግማሽ ዓመት ውስጥ ነው ምክንያቱም ምርት የጀመርነው በሰኔ ወር ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡ ከሰኔ እስከ ታኅሳስ ባለው ስድስት ወር አንድ ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ሸጠናል፡፡ በዘንድሮ ዓመት ዕቅዳችን 2.3 ሚሊዮን ቶን አምርተን መሸጥ ነው፡፡ አጠቃላይ የማምረት አቅማችን 2.5 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ማስፋፊያ ፕሮጀክታችሁ ቢነግሩን፡፡

አቶ መስፍን፡- ዕቅዳችን አሁን ያለውን ፋብሪካ በእጥፍ ማሳደግ ነው፡፡ አሁን ያለን የማምረት አቅም 2.5 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ አዲስ የምንገነባው ፋብሪካ ተጨማሪ 2.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት የማምረት አቅማችንን በእጥፍ ጨምሮ በዓመት አምስት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ይኖረናል፡፡ በቴክኖሎጂና በዘመናዊነት አዲስ የሚገነባው ፋብሪካ አሁን ካለው ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱ ወጪ ምን ያህል ነው?

አቶ መስፍን፡- የማስፋፊያው ፕሮጀክት ጠቅላላ ወጪ 600 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታው መቼ ይጀመራል? ኮንትራክተሩስ ማነው?

አቶ መስፍን፡- የወረቀት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ተጨማሪ መሬት እንዲሰጠን ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥያቄ አቅርበን በጎ ምላሽ አግኝተናል፡፡ አሁን ያለን የመሬት ይዞታ 132 ሔክታር ነው፡፡ ተጨማሪ የሚያስፈልገን 18 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ የኦሮሚያ መንግሥት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አመራር ድረስ ለኩባንያችን ከፍተኛ ትብብር እያደረጉልን ይገኛሉ፡፡ ለምናቀርብላቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ይሰጡናል፡፡ የሁለተኛውን ፋብሪካ ግንባታ የሚያካሂደው የመጀመሪያውን ፋብሪካ የገነባው ሳይኖማ ኢንተርናሽናል የተባለው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታው መቼ ይጀመራል?

አቶ መስፍን፡- የዝግጅት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ግንባታው በያዝነው የአውሮፓውን ዓመት ይጀመራል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ፋብሪካው ተገንብቶ ይጠናቀቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለሙያዎች የሲሚንቶ ገበያው ተጨናንቋል እያሉ ነው፡፡ የማምረት አቅም ወይም አቅርቦት ከፍላጎት በላይ ልቆ ሄዷል እየተባለ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ተጨማሪ ፋብሪካ ለመገንባት እንዴት አቀዳችሁ?

አቶ መስፍን፡- ትክክለኛ ነጥብ ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ ጉባዔ ላይ ስለገበያ ችግር የተነሳው ሐሳብ ትክክል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የገበያ ዕድል አለ፡፡ በአገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ መመልከት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የሲሚንቶ ፍጆታ 62 ኪሎ ግራም ነው፡፡ የሰሃራ በታች ያለውን የነፍስ ወከፍ የሲሚንቶ ፍጆታ ስንመለከት 178 ኪሎ ግራም ነው፡፡ የዓለም የነፍስ ወከፍ የሲሚንቶ ፍጆታ 500 ኪሎ ግራም ነው፡፡ ከሰሃራ በታች ካለው ፍጆታ ጋር ስናወዳድረው ከፍተኛ ልዩነት ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት ዓይነት እያደገ ነው፡፡ ሁለተኛ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ ታቅዷል፡፡ እንደሚታወቀው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ሰንቋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በትክክል ተግባራዊ ከተደረጉ ከፍተኛ የሲሚንቶ ፍላጎት ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ የገበያ ችግር አያሳስብም፡፡ ለልማት ለኢኮኖሚ ዕድገት ሲሚንቶ መሠረታዊ ግብዓት ነው፡፡ ይህች አገር በሁለት አኃዝ እያደገች ስለምትገኝና ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚካሄድባት በመሆኑ ከፍተኛ የሲሚንቶ አቅርቦት ያስፈልጋታል፡፡ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ ነው፡፡ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አለ፡፡ የተለያዩ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦች እየተገነቡ ነው፡፡ የኃይል፣ የባቡር፣ የቴሌ መስመር ግንባታዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል የሚል እምነት አለን፡፡ የገበያ ሁኔታ አሳሳቢ አይሆንም፡፡ ኩባንያችንም የገበያውን ሁኔታ በሚገባ አጥንቶ ነው እየገባበት ያለው፡፡ እኛ የምናስበው የአገር ውስጥ ገበያን ብቻ አይደለም፡፡ የጎረቤት አገሮችን ገበያ እያጠናን ነው፡፡ የባቡር መስመር ዝርጋታ ተስፋፍቶ ከቀጠለ የባቡር ትራንስፖርት በመጠቀም ወደ ጎረቤት አገሮች በስፋት እንልካለን፡፡ ዳንጎቴ ደቡብ ሱዳን ሲሚንቶ ፋብሪካ የመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡ ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ከተዘረጋ ሌላ ፋብሪካ ከመገንባት ኢትዮጵያ ያመረትነውን ሲሚንቶ በባቡር ወደ ደቡብ ሱዳን እንልካለን፡፡ ስለዚህ እኛ የሚታየን ብሩኅ ተስፋ ነው፡፡ ጨለምተኞች አይደለንም፡፡ የምናመርተውን እንሸጣለን የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሲሚንቶ ከረጢት ማምረቻ ለመገንባት አቅዳችኋል፡፡ ስለሱ ቢገልጹልን፡፡

አቶ መስፍን፡- ቀደም ሲል የሲሚንቶ ከረጢት የምናስመጣው ከግብፅ ነበር፡፡ ሆኖም ፍላጎታችንን በምንፈልገው መጠን ሊያረካን አልቻለም፡፡ ስለዚህ ናይጄሪያ ከሚገኝ የዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ እህት ኩባንያ ከሆነው አግሮ ሳክስ ከሚባል የከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ መግዛት ጀምረናል፡፡ ይህ እስከመቼ ይቀጥላል የሚል ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበር ይህን ተመልክተው የኢትዮጵያው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የራሱ የከረጢት ማምረቻ ያስፈልገዋል ብለው ፋብሪካው እንዲገነባ መመርያ አስተላልፈዋል፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቱን የሚመሩ ባለሙያዎች ተልከው ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ የሲሚንቶ ከረጢት ማምረቻው በዓመት 120 ሚሊዮን ከረጢት የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ የሚገነባው ዘመናዊ ፋብሪካ ነው፡፡ አሁን ዳንጎቴ ሲሚንቶ አሽጎ ከሚሸጥበት ከረጢት እኩል ጥራት ያለው የፕላስቲክ ከረጢት የማምረት ብቃት ይኖረዋል፡፡ በዓመት ከሚመረተው 120 ሚሊዮን ከረጢት ውስጥ እኛ የምንጠቀመው 35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ይሆናል፡፡ የተቀረውን ከ60 እስከ 65 በመቶ ለሌሎች የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንሸጣለን፡፡ እስካሁን መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ብቻ ነው የራሱ ከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ ያለው፡፡ ሌሎቹ ከውጭ እያስገቡ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ስለዚህ እኛ እዚሁ እያመረትን ለገበያ ካቀረብን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንችላለን ማለት ነው፡፡ እንደውም የመጀመሪያው ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛ ምዕራፍ የመገንባት ዕቅድ አለ፡፡ የመጀመሪያው ፋብሪካ የሲሚንቶ ከረጢቶች የሚያመርት ሲሆን ሁለተኛው ፋብሪካ ግን ለስኳር፣ ለእህልና ለሌሎች ምርቶች ማሸጊያ የሚሆኑ የፕላስቲክ ከረጢቶች የሚያመርት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታው መቼ ይጀመራል?

አቶ መስፍን፡- ፍላጎታችን በቶሎ መጀመር ነው፡፡ ነገር ግን ከመሬት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፡፡ የፋብሪካው ግንባታ የሚያካሂደው አሁን የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ካለበት ፊት ለፊት ባለ ቦታ ላይ ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ አቅርበን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መልካም ምላሽ እየሰጠን ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታው ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?

አቶ መስፍን፡- መሬቱን ተረክበን ግንባታ ከጀመርን በስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ ግንባታውን የአገር ውስጥ ኮንትራክተር የሚያካሂደው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል በጀት ተመድቧል?

አቶ መስፍን፡- ለዚህ ፕሮጀክት 19 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዟል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳንጎቴ ሲሚንቶ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር ለአካባቢው ኅብረተሰብ ያደረገው ነገር አለ?

አቶ መስፍን፡- እንግዲህ አንድ ፋብሪካ ሲተከል የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆነው የአካባቢው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለ5000 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በቀጥታ በድርጅታችን ተቀጥረው የሚሠሩ 1,500 ሰዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ የአካባቢው ተወላጆች ናቸው፡፡ የሙገር፣ የእንጭኒና የሆለታ አካባቢ ተወላጆች ናቸው፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠው ለአካባቢው ተወላጆች ነው፡፡ ከሌላ አካባቢ የምናመጣው ከፍተኛ ባለሙያ ሲፈለግ ብቻ ነው፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ 200 የአካባቢው ተወላጆች በቅርቡ ሥራ ጀምረዋል፡፡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ስፖንዳ መክፈት፣ ማለያየትና ሸራ ማልበስ የመሳሰሉትን ሥራዎች ያከናውናሉ፡፡

በተለያዩ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች ላይ እየተሳተፍን ነው፡፡ በንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ እየሠራን ነው፡፡ ሌሎች ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ፕሮጀክት ቀርፀው እንዲያቀርቡልን ለወረዳው ኃላፊዎች ገልጸናል፡፡ በትምህርት ቤትና በጤና ጣቢያ ተቋማት ግንባታ ላይ የመሳተፍ ዕቅድ አለን፡፡ ይህ ባለሀብቱ ዳንጎቴ የሚደግፉት ሐሳብ ነው፡፡ የምትፈልጉትን ድጋፍ ሠርታችሁ አቅርቡልኝ ብለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የገጠማችሁ ችግር ምንድነው?

አቶ መስፍን፡- እንግዲህ ማንኛውም ሥራ የሚሠራ ሰው የተለያዩ ችግሮች ይገጥሙታል፡፡ በኤሌክትሪክ አቅርቦት በኩል የተጋነነ ችግር አልገጠመንም፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወጥ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ይፈልጋሉ፡፡ ኤሌክትሪክ መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን የኤሌክትሪክ ፍሰት መለዋወጥ (Fluctuation) የሲሚንቶ ማምረቻውን ያናጋዋል፡፡ ፋብሪካውን የምታስነሳበት ዋጋ በሚሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ማሽኑን ታቆመዋለህ፡፡ ስታስነሳ ለማስነሳት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል፡፡ የኤሌክትሪክ ፍሰት መለዋወጥ አለ፡፡ መቆራረጥም ብዙ ጊዜ ይገጥመናል፡፡ አንዳንዴም ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን ይቋረጣል፡፡ ይህ ከፍተኛ ችግር ይፈጥርብናል፡፡ ይሁን እንጂ ከበፊቱ ሁኔታዎች አሁን በመጠኑ እየተሻሻሉ ነው፡፡ በቀጣይ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ የበለጠ ይሻሻላል የሚል እምነት አለን፡፡ ኩባንያችን አንድ ችግር በሚገጥመው ወቅት የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ችግራችንን አዳምጠው ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት የሚያስመሰግን ነው፡፡ እስካሁን ከሁሉም ወገን ቀና ትብብር እየተደረገልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተፈጠረው የገበያ ፉክክር የሲሚንቶ ዋጋ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲተያይ አሁንም ቢሆን የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ዋጋ ውድ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኢነርጂ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የድንጋይ ከሰልና ፈርነስ ኦይል ነው የሚጠቀሙት፡፡ እነዚህ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል ወይም አማራጭ ኢነርጂ ለመጠቀም ኩባንያችሁ ምን ጥረት እያደረገ ነው?

አቶ መስፍን፡- እንደተባለው የአንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከፍተኛ ወጪ የኃይል ወጪ ነው፡፡ የኢነርጂ ወጪው ከ60 እስከ 65 በመቶ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ፈርነስ የሚጠቀም ፋብሪካ የለም፡፡ ቀደም ሲል ሙገር ነበር እሱም ወደ ድንጋይ ከሰል ቀይሮ እየተጠቀመ ነው፡፡ ፈርነስ ከመጠቀም የድንጋይ ከሰል መጠቀም የማምረቻን ዋጋ በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል፡፡ እኛ እስካሁን የምንጠቀመው ከደቡብ አፍሪካ የሚመጣ የድንጋይ ከሰል ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን አብዛኛዎቹ የአገር ውስጥ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ከደቡብ አፍሪካ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ነው፡፡ በቅርቡ በጅማ አካባቢ የሚመረተውን የድንጋይ ከሰል እያስመጣን ከውጭ ከሚመጣው ጋር አደባልቀን መጠቀም ጀምረናል፡፡ አሥር በመቶ የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል ከደቡብ አፍሪካው ጋር ቀላቅለን እየሞከርን ነው፡፡ ይኼ የመጀመሪያው ወጪ ቅነሳ ነው፡፡ የጅማው ድንጋይ ከሰል ካሎሪ ይዞታው ሲሚንቶ ለማምረት በቂ ሆኖ ከተገኘ ከውጭ ማስመጣት አቁመን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ እንጠቀማለን፡፡ ወይም ደግሞ በከፍተኛ መጠን አደባልቀን መጠቀም እንቀጥላለን፡፡ ይህን የሙከራውን ውጤት አይተን የምንወስነው ይሆናል፡፡

የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል አዋጪ ሆኖ ካገኘነው ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ ወስደን የድንጋይ ከሰል ፍለጋ ሥራ ውስጥ እንገባለን፡፡ ሌሎች አማራጭ የኃይል ምንጮችን እየተመለከትን ነው፡፡ ለምሳሌ ባዮማስ ወይም እንደ ቡና ገለባ ያሉ ምርቶችን መጠቀም ይቻላል፡፡ ይህ ግን ራሱን የቻለ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ፋብሪካችን ምርት ከጀመረ ገና ስምንት ወሩ ነው፡፡ እስካሁን የጀመርነው ሙከራ ግን የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል መጠቀምን ነው፡፡ በዚህም የማምረቻ ወጪያችንን ለመቀነስ የሚያስችለንን ሙከራ እያካሄድን ነው፡፡ የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል መጠቀም ከቻልን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋችንን አሁን ካለው በታች ማውረድ እንችላለን፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ጥናቱ ጊዜ የሚወስድ ይሆናል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች