– በተከሰሱበት የደረቅ ቼክ ጉዳይ የ600 ሺሕ ብር ዋስ ተፈቀደላቸው
– በ500 ሺሕ ብሩ ዋስትና ላይ ክርክር አድርገው ለብይን ተቀጠሩ
ፍትሕ ሚኒስቴር ለአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ አባል አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ሰጥቶት የነበረውን ያለመከሰስ ዋስትና አነሳ፡፡
አቶ ኤርሚያስ በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ፈርማ ‹‹የወንጀል ምርመራ ማቋረጥን አስመልክቶ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 42 (1መ) እና የአስፈጻሚው አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 16 (5) በተደነገገው መሠረት፣ አቶ ኤርሚያስ ገንዘብ ሳይኖራቸው ቼክ አውጥተዋል በማለት የተጀመረባቸው ምርመራ ተጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ የተላከው የምርመራ መዝገብ ለጊዜው ተቋርጧል፤›› የሚል ደብዳቤ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጽፎላቸው ያለመከሰስ ዋስትና ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
አቶ ኤርሚያስ ከቤት ገዥዎች ጋር በተፈጠረ ውዝግብ ከጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ሆነው በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ፣ የፌዴራል ፖሊሲ ወንጀል መመርመር ዳይሬክቶሬት መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪው ላይ የሠራውንና የሚቀረውን ምርምራ ለፍርድ ቤት ሲያስረዳ አቶ ኤርሚያስ የሚያዙበት በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ለበርካታ ሰዎች ደረቅ ቼክ ጽፈው መስጠታቸውንና ወንጀል መሆኑን ሲያስረዳ ከርሟል፡፡ የመርማሪውን ክስ በመቃወም የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች አቶ ሞላ ዘገዬና አቶ መኮንን አራጋው፣ ‹‹ደረቅ ቼክን በሚመለከት አቶ ኤርሚያስ ከመንግሥት ያለመከሰስ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለክርክር መቅረብ የለበትም፡፡ መቅረብ አለበት ከተባለ የተሰጣቸው ያለመከሰስ ዋስትና መነሳት አለበት፤›› በማለት ሲከራከሩ መርማሪ ቡድኑም፣ ‹‹ስለተሰጠው ዋስትና ፌዴራል ፖሊስ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የደረሰው ደብዳቤም የለም፤›› በማለት ሲከራከር ከርሟል፡፡
ነገር ግን መንግሥት በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ፊርማ ተረጋግጦ ለአቶ ኤርሚያስ የተሰጣቸው ያለመከሰስ ዋስትና በራሳቸው በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ፊርማ፣ መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹ለፌዴራል ማዕከል መመርመርና ውሳኔ ማሰጠት ዳይሬክቶሬት›› በተላከ ደብዳቤ ‹‹በተጠርጣሪው ላይ ተቋርጦ የነበረው ምርመራም ሆነ የክስ ሒደት ካለ መቀጠል ያለበት መሆኑ የታመነበት ስለሆነ ጉዳዩ እንዲቀጥል አሳውቃለሁ፤›› በማለት ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱን እንዳስታወቁ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ለስድስት ሰዎች በድምሩ 4.9 ሚሊዮን ብር ቼክ የጻፉ ቢሆንም፣ በባንክ በቂ ስንቅ (ገንዘብ) ስለሌላቸው ‹‹ደረቅ ቼክ በማውጣት ወንጀል›› የተከሰሱ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በ600 ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ ዓርብ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ውሳኔ፣ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ በሚመለከት አቶ ኤርሚያስ ከፍተኛ ገንዝብ በደረቅ ቼክ ለስድስት ግለሰቦች መጻፋቸውን ገልጿል፡፡ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከቀላል እስራት እስከ አሥር ዓመታት በሚደርስ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ይቀጣሉ፡፡ በመሆኑም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67 (ሀ) መሠረት ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ በመግለጽ መከራከሩን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
የተጠርጣሪው አቶ ኤርሚያስ ጠበቆች አቶ ሞላ ዘገዬና አቶ መኮንን አራጋው በበኩላቸው ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ ዋስትና ተራ መብት ሳይሆን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የፈቀደው ግዙፍ መብት ነው፡፡ ይኼንን ግዙፍ መብት ሊያስቀር የሚችለው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 63 መሠረት የተጠቀሱ ጥፋቶችን ተላልፎ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ደንበኛቸው ክስ ተመሠረተባቸው እንጂ ድርጊቱን መፈጸም አለመፈጸማቸው የሚረጋገጠው ወደፊት በሚደረግ በማስረጃ ላይ በተመሠረተ ክርክር መሆኑን መግለጻቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ ከአገር ሊወጡና ላይመለሱ እንደሚችሉ የተናገረው ግምት እንጂ የተጨበጠ ነገር ባለመሆኑ፣ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል በመናገር መከራከራቸውንና የደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡
የሁለቱን ወገኖች ክርክር የሰማውና የክሱን አቀራረብ ከተገቢው ሕግ ጋር አገናዝቦና መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ ስለውሳኔው አስረድቷል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 (6) ማለትም የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ ዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ እንደሚችል መደንገጉን ፍርድ ቤቱ አስታውሷል፡፡ ዋስትና ሊከለክሉ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጣሪው የተከሰሰበት ጉዳይ ከ15 ዓመታት በላይ የሚያስቀጣ ሲሆን፣ ጉዳት የደረሰበት ሰው እንደሚሞት ከተገመተ በፀረ ሙስና ልዩ የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ክልከላ የተጣለባቸው ድንጋጌዎችና በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 67 (ሀ እና ለ) መሠረት መሆኑን በምሳሌነት ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡
በአቶ ኤርሚያስ ክስ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ድርጊት ያለው ከፍተኛ ገንዝብ 4.9 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ ሪል ስቴት ከመሆኑ አንፃር ገንዘቡ ከፍተኛ ሊባል እንደማይችል ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ ራሳቸውን ከፍትሕ አደባባይ ሊያጠፉ እንደሚችሉ ከመግለጽ ባለፈ፣ ዓቃቤ ሕግ በተጨባጭ ያሳየው ነገር እንደሌለና አሳማኝ አለመሆኑንም ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡ በተከሰሱበት ለስድስት ሰዎች ደረቅ ቼክ መቁረጥ ወንጀል፣ በስድስቱም ጥፋተኛ ቢባሉ በማለት ዓቃቤ ሕግ ያነሳው የግምት ክርክር ገና ክርክሩ ባልተጀመረበትና ምንም ነገር ባልታየበት ሁኔታ በመሆኑ አሳማኝ አለመሆኑንም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡
የተጠርጣሪው ጠበቆች አቶ ሞላና አቶ መኮንን ያቀረቡትን የዋስትና ጉዳይ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ መመርመሩን ገልጿል፡፡ ጠበቆቹ ዋስትና ተራ የመብት ጥያቄ ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ ግዙፍ መብት መሆኑንና በሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 59304 አስገዳጅ ውሳኔ እንደተሰጠበት ያነሱት መከራከሪያ ሐሳብ ተቀባይነት ማግኝቱንም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ደረቅ ቼክን በሚመለከት አቶ ኤርሚያስ የተጀመረባቸው ክስም ሆነ የምርመራ ሒደት መንግሥት እንዲቋረጥ ማዘዙን ጠበቆቹ ያነሱት የመከራከሪያ ነጥብ መሆኑን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ በዚህ ጉዳይ ዓቃቤ ሕግ አለማስተባበሉን አስታውቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ አቶ ኤርሚያስ ያለመከሰስ መብታቸው ከመጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተነሳ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ ያያዘ ቢሆንም፣ እንዳልተቀበለው ገልጿል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ የተጠርጣሪው ግዙፍ የዋስትና መብት እንዲነፈግ ያቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት እንዳላገኘ ገልጾ፣ አቶ ኤርሚያስ የ600 ሺሕ ብር ዋስትና ሲያሲዙ ከእስር እንዲፈቱና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መመርመር ዳይሬክቶሬት የወንጀል ምርመራ ቡድን አቶ ኤርሚያስ በሥር ፍርድ ቤት የተፈቀደላቸውን የ500 ሺሕ ብር ዋስትና በመቃወም ይግባኝ ባለበት ጉዳይ ክርክር ተደርጓል፡፡
መርማሪ ቡድኑ የሥር ፍርድ ቤት ምርመራውን ሳይጨርስ ዋስትና መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቶ፣ ቀሪ ምርመራውን እስከሚያስጠነቅቅ የተፈቀደው ዋስትና እንዲታገድለት ጠይቋል፡፡
የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች በበኩላቸው ከበቂ በላይ 70 ቀናት እንደተፈቀደለትና የሥር ፍርድ ቤት አቅጣጫ በመስጠት የመጨረሻ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶለት ለስምንተኛ ጊዜ ሲጠይቅ እንደከለከለው አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን እንዲመለከትም ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ በሥር ፍርድ ቤት የተፈቀደው የ500 ሺሕ ብር ዋስትና ትክክል መሆን አለመሆኑን መርምሮ ብይን ለመስጠት፣ ለመጋቢት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡