መንግሥት በድርቅ ለተጎዱ 10.2 ሚሊዮን ተረጂዎች የሚከፋፈል 499.5 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት ያወጣውን ጨረታ፣ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ የተባለ የውጭ ኩባንያ አሸነፈ፡፡ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ይህንን ስንዴ የሚያቀርበው በ2.2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህንን ጨረታ ለማሸነፍ 11 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቢወዳደሩም፣ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ዝቅተኛ የተባለ ዋጋ በማቅረብ ሁሉንም ጠቅልሎ መረከብ ችሏል፡፡
መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከፍቶ፣ መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. አሸናፊነቱ የተገለጸለት ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል፣ በሦስት ምድብ ተከፍሎ የወጣውን ጨረታ በማሸነፍ ከመንግሥት ግዥና ንብረት አገልግሎት ጋር ውል ገብቷል፡፡
ኩባንያው በሦስት ምድብ ተከፍሎ የወጣውን ጨረታ ለመጀመርያው ምድብ በአንድ ቶን 195.10 ዶላር፣ ለሁለተኛው ምድብ በአንድ ቶን 204.40 ዶላርና ለሦስተኛው ምድብ በአንድ ቶን 109.512 ዶላር አቅርቧል፡፡
በዚህ ጨረታ ከተወዳደሩት መካከል ሲኦኤም ዩኬ፣ ሚድ ገልፍ፣ አምሮፓ፣ ቦሊን ኮል ግሪን ይጠቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ በጨረታው ከተወዳደሩ አሥር ኩባንያዎች ጋር ሲነፃፀር ፕሮሚሲንግ ያቀረበው ዝቅተኛ በመሆኑ አሸናፊ ሊሆን መቻሉ ተገልጿል፡፡ ኩባንያው በድምሩ 499.5 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ 101.2 ሚሊዮን ዶላር (2.2 ቢሊዮን ብር) ይከፈለዋል፡፡
አሸናፊው ኩባንያው ለማቅረብ የተስማማውን ስንዴ በተለይም ከሩሲያ፣ ከቡልጋሪያ፣ ከዩክሬን፣ ከሩማንያ፣ ከሞልዶቪያና ከመሳሰሉ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ግዥ በመፈጸም በ180 ቀናት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ስምምነት ፈጽሟል፡፡
በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አማካይነት ከለጋሾችና ከኢትዮጵያ መንግሥት 680 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዟል፡፡ ነገር ግን እስከሚቀጥለው ዓመት ጥር ወር ድረስ ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡
መንግሥት በዚህ ዓመት 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ፈጽሟል፡፡ ከስንዴ በተጨማሪ ለነፍሰ ጡር እናቶችና ለሕፃናት አልሚ ምግቦች ከአገር ውስጥ ኩባንያዎችና ከውጭ አገሮች ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ በላይ መንግሥት በተለይ ለአርብቶ አደሮችና ለአርሶ አደሮች እንስሳት መኖ በማከፋፈል ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡