Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ የተሰኘ ኢንስቲትዩት ሊቋቋም ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መፃኢ ዕድል ያላቸው የቴክኖሎጂ ዓይነቶችን በመለየትና በጋራ በማሰባሰብ፣ ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተብሎ በሚመሠረት ተቋም ሥር እንዲመሩ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መፃኢ ዕድል አላቸው ተብለው የተለዩት የቴክኖሎጂ ዓይነቶች ናኖ ቴክኖሎጂ፣ ባዮ ቴክኖሎጂ፣ ማቴሪያል ሳይንስ፣ ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂዎች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ የቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ዘርፎች በቀጣይ እንደ አገር ለመቆምና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ወሳኝና ከወዲሁ እንቅስቃሴ ሊጀመርባቸው የሚገቡ መሆናቸውን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሰነድ ይገልጻል፡፡

እያንዳንዳቸው የተለዩት ዘርፎች ራሳቸውን ችለው በኢንስቲትዩት ደረጃ እስኪወጡ ድረስ፣ በአንድ ተቋም ሥር አድርጐ ውስን ሀብትን አጣጥሞ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ሰነዱ ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም ውስን የሆኑትን ተመራማሪዎች በአንድና በጋራ በማሰባሰብ አንዱ ለሌላኛው እርሾና ድጋፍ በመሆን የሚጠቀሙበትን አደረጃጀት መፍጠር ማስፈለጉን በሰነዱ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተብሎ የሚጠራ ተቋም ለማደራጀት የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል በግለሰብ ምሁራን ፍላጐት የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማኅበር አደረጃጀቱን በመቀየር ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ኤሮስፔስ ኢንስቲትዩት ተብሎ እንዲዋቀር የሚያስችል ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማኅበር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተጠሪነቱ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዞሮ ማኅበርነቱን አጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሮስፔስ ሆኖ እንዲደራጅ የተፈለገውም የሬጉላተሪ፣ የምርምርና የልማት ዘርፍን አጣምሮ እንዲይዝ መሆኑን የሚኒስቴሩ ሰነድ ይገልጻል፡፡ ይህንኑ ዕውን ለማድረግም የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች