Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ሁለተኛው ምዕራፍ የይዞታ ምዝገባ ተጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ በመሬት ዘርፍ የሰፈነውን የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የይዞታ ዳግም ምዝገባ ሁለተኛው ምዕራፍ ተጀመረ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ክልል በሆነው 54 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ የመንግሥት፣ የሕዝብና የግለሰቦች መሬትና ይዞታዎች በዘመናዊ መሬት ካዳስተር የማደራጀት ሥልጣን የተሰጠው፣ የከተማው የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ነው፡፡

ኤጀንሲው በቦሌና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች በሙከራ የጀመረውን የይዞታ ዳግም ምዝገባ በማስፋት፣ ባለፉት ስድስት ወራት 70 ሺሕ ይዞታዎችን ዳግም መመዝገቡን አስታውቋል፡፡

በዚህ ምዝገባ ሒደት ፈታኝ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ባለይዞታዎች በቂ ግንዛቤ ባለመያዛቸው ለማስመዝገብ ፈቃደኛ አለመሆን፣ በይዞታው ውስጥ የቀበሌ ቤት መገኘቱ፣ ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ ባለይዞታዎች በርካታ መሆን፣ የሰነድ አልባ ባለይዞታዎች መበራከት ተጠቃሽ ምክንያቶች ነበሩ ተብሏል፡፡ ከዚህ በዘለለ የይዞታ አስተዳደር ኤጀንሲ መረጃ አያያዝ ደካማ መሆንና ባንኮች ጥቅማቸውን በበቂ ሁኔታ ባለመረዳታቸው ተባባሪ አለመሆናቸው በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡

በተለይ በራሳቸው ይዞታ ውስጥ የቀበሌ ቤት በመኖሩ ይዞታቸውን ለመሸጥ፣ ለመለወጥና ለማደስ የተቸገሩ ባለይዞታዎች ለዓመታት ቅሬታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ ጊዜ ቢገልጹም ሰሚ አለማግኘታቸው ይነገራል፡፡

ባለፈው ዓርብ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ከመሬት ይዞታ ምዝግባና መረጃ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ፣ አስተያየት የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይህንን ችግር አጉልተውታል፡፡

‹‹ግቢው በስሜ ነው፡፡ መሀል ላይ የተወረሰብኝ አንድ የቀበሌ ቤት በመኖሩ ብቻ፣ ይዞታዬን መሸጥም መለወጥም ባለመቻሌ መጠቀም አልቻልኩም፡፡ ይህንን ሁኔታ ከባለአደራው አስተዳደር ጀምሮ አቤት ብልም ሰሚ አላገኘሁም፡፡ አሁን ዕድሜዬ እየሄደ ነው፤›› በማለት የችግሩን አስከፊነት በውይይት መድረኩ የታደሙ አንድ አዛውንት ተናግረዋል፡፡

የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ወዳጆ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በምዝገባ ሒደት የይዞታ መብት ያልተፈጠረላቸው ባለይዞታዎች ችግር ስለጠማቸው ውሳኔ አላገኙም ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው እስካሁን ካካሄደው የመጀመሪያው ምዕራፍ በመቀጠል፣ በሁለተኛው በጥልቀት ምዝገባ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለዚህ ሥራው ነዋሪዎችን በታዛቢነትና በቅሬታ ፈቺነት በማቀፍ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ስለቀጣዩ ሥራ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ይህ ምዝገባ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ከወረዳ በታች ባለው መዋቅር 450 ቀጣናና 2,224 ሠፈሮች ይኖሯታል ተብሏል፡፡ በቀጣዩ ምዝገባ ኤጀንሲው ትኩረት ሊያደርግበት ስለሚገባ ጉዳይ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ይህ አስተያየት መነሻ ያደረገው ሰሞኑን በተካሄደ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ ላይ በተከሰተ አንድ ጉዳይ ነው፡፡

በምሳሌነት የተነሳው አንዲት ዕጣ የደረሳቸው ወይዘሮ ቤታቸውን እንዳያገኙ ከተደረገ በኋላ ሌላ ግለሰብ ቤቱን በስሙ አዙሮ ይኖር ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ ማጣራት ተደርጎበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መታወቁ ተገልጿል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤቶች አስተዳደር ስለ ጉዳዩ የሚያውቀው እንደሌለ መናገሩን ይህን አስተያየት የሰጡ ግለሰብ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት በመጀመሪያ የመሬት ካርታ የሚሰጠው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ነው፡፡ ቢሮው የሰጠውን መረጃ እንዳለ ተቀብሎ ምዝገባ ማካሄድ ሕገወጥን ሕጋዊ ማድረግ ሊሆን ስለሚችል፣ ትክክለኛውን ባለይዞታ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ለመንግሥት አሳስበዋል፡፡

የመሬት ዳግም ምዝገባ በዋናነት ለተመዝጋቢው የንብረት ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ለይዞታ ግብይት፣ ለባንኮችና ለመሳሰሉት ተቋማት ሁነኛ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ከዚህ ቀደም ለመልካም አስተዳደርና ለሙስና ክፍተት የፈጠሩ ጉዳዮች መዝጋት የሚሉት ከጥቅሞቹ መካከል መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች