‹‹የሕዝብና የመንግሥት መብት ጥቅም ካልነካ ተጣርቶ ይስተናገዳሉ›› የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
በደቡብ አፍሪካ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከፍተኛ ዕውቅና ማግኘታቸውን የሚናገሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን፣ በፍርድ ቤት ጨረታ ወጥቶ ተወዳድረው ያሸነፉትንና ሙሉ ክፍያ የፈጸሙበትን ይዞታ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አስተዳደር ላለፉት ሰባት ዓመታት ሊያስረክባቸው ባለመቻሉ መቸገራቸውን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ባለመብቶቹ አቶ ግርማ ብሩና አቶ እዮብ በላይ የሚባሉ ሲሆኑ፣ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እየሠሩ መሆኑን የሚናገሩት ባለሀብቶቹ፣ ሰኔ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣ ግልጽ ጨረታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አፓርታማ 66 በሚባለው አካባቢ ውስጥ የሚገኝ የመኖሪያና የዳቦ ቤት ይዞታ በ270 ሺሕ ብር በማሸነፍ ክፍያውን ወዲያው መፈጸማቸውን ይናገራሉ፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም መምርያ የገዙትን ይዞታ ነሐሴ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ያስረክባቸዋል፡፡
የፍርድ አፈጻጸም መምርያው ሲያስረክበቸው የወረዳው ተወካይ፣ የፖሊስ ተወካይና ሌሎች ታዛቢዎች መገኘታቸውን የተናገሩት ባለይዞታዎቹ ቦታው ሰነድ አልባ ቢሆንም፣ በ1988 ዓ.ም. ጂአይኤስ ውስጥ የሚታይ መሆኑንና በአግባቡ በሐራጅ በፍርድ ቤት ጨረታ የይዞታው ባለቤት መሆናቸው በተገለጸው አቶ ጌታቸው ፈረደና አቶ ስመኝ በቀለ ከተባሉ ግለሰቦች የተረከቡ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ባለይዞታዎቹ ቤቱን ከተረከቡ በኋላ ዋና መኖሪያቸውና የሥራ ቦታቸው ወደሆነው ደቡብ አፍሪካ ሲመለሱ ለሦስት ወራት አከራይተውት የሄዱ ቢሆንም፣ የክፍለ ከተማው ደንብ አስከባሪ ‹‹ሕገወጥ ይዞታና ሰነድ አልባ ነው›› በማለት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ዳቦ ቤታቸውንና መኖሪያ ቤቱን ማፍረሱን ተናግረዋል፡፡
የደንብ አስከባሪው ተግባር ያበሳጫቸው አቶ ግርማና አቶ እዮብ፣ በአገሪቱ ሕግ መሠረት በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን በፍርድ ቤት በተደረገ ሕጋዊ ጨረታ የገዙትንና በሕጋዊ መንገድ የተረከቡትን ይዞታ ሕገወጥ አስመስሎ ማፍረሱ በራሱ ሕገወጥ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ለወረዳ አንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት፣ ለክፍለ ከተማው ይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ጽሕፈት ቤትና ለሌሎችም ለሚመለከታቸው አካላት ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል፡፡ አንዱ ለሌላኛው ‹‹መረጃ መጠየቅን ይመለከታል፤›› በማለት ደብዳቤ ከመጻፍ ባለፈ ምንም የፈጸሙላቸው ነገር እንደሌለም ገልጸዋል፡፡
በክፍለ ከተማው ሥር የሚገኙ የመሬት ልማትና ሌሎች ቢሮዎች በደንብ አስከባሪው የፈረሰው የባለይዞታዎቹ የዳቦ ቤትና የመኖሪያ ቤት ወደነበረበት እንዲመለስ፣ ባለይዞታዎቹ በሕጋዊ መንገድ የገዙት መሆኑን በመግለጽ በሰጡት መረጃ መሠረት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከምክትል ከንቲባና ከመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው ባለይዞታዎቹ በአግባቡ እንዲስተናገዱና አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንዲደረግላቸው በወረቀት ላይ ያረፈ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ ወረዳውና ክፍለ ከተማው ሊያስፈጽሙላቸው እንዳልቻሉና ግራ እንደገባቸው ገልጸዋል፡፡
የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ያፀናው ቢሆንም እስካሁን ቦታውን ሊያስረክቧቸውና ሕጋዊ ካርታ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ የሚናገሩት ባለይዞታዎቹ፣ ከሚኖሩበት ደቡብ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ ወደ አገራቸው በመመለስ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየገቱባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በደቡብ አፍሪካ በማስተባበር ለህዳሴው ግድብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከመሆኑም በላይ፣ አገራቸው ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማግባባትና የኢትዮጵያን ለውጥ በመንገር እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴም የተወሰኑ የመንግሥት አካላት የሚያውቁ ቢሆንም፣ በእነሱ ላይ እየደረሰ ያለው የመልካም አስተዳደር በደል በሌሎቹም ላይ ደርሶ እንዳያስወቅሳቸው መፍራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳይሬክቶሬት ጄኔራልና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እየደረሰባቸው ያለውን በደል በማስረዳት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ባለይዞታዎቹ፣ በጥቂት ቢሮክራቶች ምክንያት የአገሪቱ ባለሥልጣናትና መንግሥት ስማቸው እየተነሳ ‹‹የፍትሕ ያለህ›› መባሉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ በሁለት ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠን ሕጋዊ መብት መንግሥት ተመልክቶ መብታቸውን እንዲያስረክብላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በይዞታቸው አካባቢ የሚገኝና በተለምዶ አፓርታማ 66 በሚል የሚጠራው የነዋሪዎች ማኅበር ‹‹ለግሪን ኤሪያ እንፈልገዋለን›› በማለት የፍርድ ቤትን ውሳኔ ለማሻር፣ ከአንዳንድ የወረዳና የክፍለ ከተማ ሕገወጦች ጋር የሚያደርገውን እንቅስቃሴም እንዲያቆም እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ባለይዞታዎቹ ያነሱትን ተቃውሞና ደረሰብን ያሉትን በደል በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት አስናቀ፣ ባለይዞታዎቹ ምንም ጥፋት የለባቸውም ብለዋል፡፡ ሁሉንም ነገር የፈጸሙት ሕጉን ተከትለው ነው፡፡ ችግሩን የፈጠረው ፍርድ ቤቱ መሆኑን ገልጸው፣ ካርታ የሌለውን ቦታ ‹‹በጂአይኤስ ውስጥ ይታያል›› በማለት ለጨረታ አቅርቦ መሸጡ ተገቢ አለመሆኑንና ለተነሳው ችግር ሁሉ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹ግሪን ኤሪያችን ነው›› በማለት ተቃውሞ ማንሳታቸውን የገለጹት አቶ ታምራት ጉዳዩ በሕግ የተያዘ መሆኑን ጠቁመው፣ የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም አለመንካቱ ተረጋግጦ ለባለይዞታዎቹ ሊተላለፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የባለይዞታዎቹ ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የሕግ ውሳኔው መከበር ስላለበት የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ይጠናቀቅና ካርታ ሠርተን እናስረክባለን፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው በቅርቡ የተሾሙ በመሆናቸው ጉዳዩን ገና እያዩት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡