– የወጡትን ሕጐች ለመተግበር በጋራ አለመሥራት ችግር ሆኗል
በአገሪቱ የማስታወቂያ ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ባለድርሻ አካላትና ይህንን ለመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት በቅንጅት አለመሥራት፣ ሸማቾች በሐሰተኛና በአሳሳች ማስታወቂያዎች የሚደርስባቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቋቋም አለመቻላቸው ተገለጸ፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም በቅንጅት እንዲሠሩ ጥያቄ ቀረበ፡፡
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሐሙስ መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ከማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ግንዛቤ ለማስጨበጥ ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ፣ ሸማቾችን ከሐሰተኛና ከአሳሳች ማስታወቂያዎች ለመከላከል የወጡትን ሕጐች ተግባራዊ ለማድረግ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በቅንጅት አለመሥራት ለሕጐቹ ተግባራዊነት ተግዳሮት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የአገሪቱን የማስታወቂያ ሥርዓት በበላይነት ለመምራት ኃላፊነት በተሰጠው የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ተፈጻሚ የሚሆን የማስታወቂያ ሕግ በ2004 ዓ.ም. ወጥቷል፡፡ እንዲሁም ሐሰተኛና አሳሳች ማስታወቂያዎች በሸማቹና በንግድ ውድድሩ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመከላከል፣ በ2006 ዓ.ም. የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አዋጅ ቁጥር 823/2006 ድንጋጌ ቢወጣም፣ ተቋማቱ በቅንጅትና በጋራ ባለመሥራታቸው ለሕጉ ተፈጻሚነት ተግዳሮቶች እንደሆኑ በዕለቱ የቀረበው ጥናት ጠቁሟል፡፡
በማስታወቂያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ መንግሥታዊና የንግድ ተቋማት የማስታወቂያ ሥራን ከአምራቹና ከነጋዴው ፍላጐትና ጥቅም አኳያ ብቻ መመልከት፣ ችግሩን ለመግታት አንደኛው እንቅፋት እንደሆነ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
የማስታወቂያ ዘርፍ ተዋናዮች የሚሠሩትን ማስታወቂያዎች ውበትና ማራኪነት ትኩረት ከመስጠት ውጪ፣ በሸማቾች ላይ የሚደርሰውን ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከግምት ውስጥ ሲያስገቡ አይስተዋልም ሲሉ የባለሥልጣኑ የግንዛቤ ማስጨበጥና የሕግ ተፈጻሚነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አበራ በመክፈቻ ንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ በሕገወጥ መንገድ ለመክበር የሚያስቡ ነጋዴዎችና አምራቾች ሸማቹን ስለሚገዛው ምርትና አገልግሎት ያለውን የጥራት፣ የመጠን፣ የዋጋና ለሚሰጠው ዋስትና ያለውን የግንዛቤ እጥረት ከፍተኛ ትርፍ ለማካበት እየተጠቀሙበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሳሳችና ሐሰተኛ ማስታወቂያዎች በተለይ በሕክምና፣ በምግብ፣ በትምህርትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተጠቃሚ ሸማቾችን ለጉዳት እየዳረጉዋቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በዕለቱ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ሐሰተኛና አሳሳች ማስታወቂያዎች የሚገለጹበት የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ ቃላትን ያላግባብ መጠቀምና የልኬት መሣሪያዎችን ማዛባት፣ ያልተሰጠ ዕውቅናን ወይም ማረጋገጫን በአሻሚና በአሳሳች ወይም ባልተገባ መንገድ ማቅረብ፣ ሌሎችን ማንኳሰስ፣ መፍትሔ የማይሆን ዋስትና መስጠት፣ ወዘተ ከተዘረዘሩት ውስጥ ይገኙበታል፡፡
ነፃ የትምህርት ዕድል ተብሎ የምዝገባ፣ የአስተዳደርና የትምህርት መገልገያዎች ክፍያ ማስከፈል በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚታይ ችግር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም ‘ታላቅ ቅናሽ’፣ ‘የማጣሪያ ሽያጭ’ የሚሉና በተግባር ግን እውነተኛ ያልሆኑ የተለመዱ ሐሰተኛና አሳሳች ማስታወቂያዎች በብዛት እየተስተዋሉ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ የአንድን ምርት ዋጋ ተጨማሪ እሴት ታክስና የአገልግሎት ክፍያን ሳይደምሩ ማስተዋወቅ፣ ‘ነፃ ስጦታ’ እንደሚሰጥ ገልጾ ማስከፈል፣ ‘አስመስሎ በተሠራ ምርት እንዳይታለሉ’ የሚሉ አሳሳችና ሐሰተኛ ማስታወቂያዎች እየተለመዱ መምጣታቸው አሳሳቢ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የማስታወቂያ ወኪሎች፣ የማስታወቂያ አሠሪዎችና ይህንን የሚያሰራጩ አካላት በሚሠሩዋቸውና በሚያቀርቧቸው የማስታወቂያ ውጤቶች ትክክለኛና የወጡትን ሕጐች የማይፃረሩ መሆኑን ትኩረት ሰጥተው ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
በዓውደ ጥናቱ ላይ በተደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ተወካይ አቶ ይስማ ጅሩ፣ አምራቾች ከማስታወቂያ አንፃር የአመለካከት ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ‘አምራቾች፣ ዳጎስ ያለ ትርፍን እንጂ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያመጡትን ጫና አለማየት ዋነኛው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የማስታወቂያዎች በባለሙያዎች አለመሠራት ሌላው የችግሩ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የሕግ ክፍተት የለም፡፡ የሕግ ማዕቀፍ አለ፡፡ በጥራትና በደረጃ ብቻ ተወዳዳሪ ለመሆን መጣር ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም አመለካከት መገንባት አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ አጽንኦት የሰጡት አቶ ይስማው አያይዘውም፣ ‹‹ኅብረተሰቡ ከፈጣሪ ቀጥሎ የሚያምነው ሚዲያን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኅብረተሰቡ እሴት ነው፡፡ ስለዚህም የሚዲያ ተቋማት ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ እነዚህን እሴቶች ማስጠበቅ መቻል አለባቸው፤›› ብለው ደረጃዎች ኤጀንሲ የተለያዩ አስገዳጅ ደረጃዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አስገዳጅ ደረጃዎችና ምልክት በምርቶች ላይ መኖራቸውን አረጋግጦ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው፣ እንዲሁም በተለይ የሚዲያ ተቋማት ይህንን ምልክት የመጠቀም ፈቃድ መሰጠቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የማስታወቂያ ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ እሱባለው ሻውል በበኩላቸው፣ ሚዲያዎች አስገዳጅ ደረጃ የሚያስፈልጋቸው ምርቶች ምልክት ከሌላቸው እንዳይተዋወቁ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
እንዲሁም የሕፃናትን አስተዳደግ፣ የሴቶችንና የወጣቶችን መልካም ሥነ ምግባር በመፃረር የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ክልክል መሆናቸውንና ትውልድን፣ አስተሳሰብን፣ ፆታን፣ ባህልና ታሪክን በአሉታዊ መንገድ የሚቃረኑ ማስታወቂያዎች አግባብ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ማስታወቂያዎች የሚሠሩት በሙያው ፕሮፌሽናል ያልሆኑና ተገቢ ትምህርትና ሥልጠና ባልወሰዱ ግለሰቦች መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንንም ክፍተት ለማጥበብ የትምህርት ተቋማት በዘርፉ ሥልጠና የሚሰጡበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ አቶ እሱባለው ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በሞኒተሪንግና በጥቆማ የሚያገኛቸው ሕጉን ያልተከተሉ ማስታወቂያዎች ላይ ምርመራ እንደሚያደርግና ውጤቱንም ተከታትሎ መልስ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ማንኛውም አካል ጥቆማውን ለባለሥልጣኑ ማቅረብ እንደሚችል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ከተሳታፊዎች የተሰነዘረውን በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚሰቀሉ የቢራና የመጠጥ ማስታወቂያዎችን አግባብ አለመሆን አስተያየት በተመለከተ፣ ጉዳዩ ከመሥሪያ ቤታቸው ሥልጣን ውጪ መሆኑንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውጭ ማስታወቂያዎችን የሚመለከት ሞዴል ደንብ ተዘጋጅቶ ከሦስት ዓመት በፊት እንደተሰጠ አቶ እሱባለው ገልጸዋል፡፡
በባለሥልጣኑ የገበያ መረጃ ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜ፣ አሳሳችና ሐሰተኛ ማስታወቂያዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ሐሰተኛና አሳሳች ማስታወቂያዎች በሸማቹ፣ በንግድ ውድድሩና በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለመግታት በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም በሁሉም ወገኖች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት ከመሥራት በተጨማሪ፣ አስተማሪ የሆነ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት መስጠትና በተጓዳኝም ሕጉን ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡