እሑድ መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰማያዊ ፓርቲ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የተላለፈውን አምስት የፓርቲውን አባላት የማሰናበትና የማገድ ውሳኔ፣ ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ስብሰባ ያካሄደውና ውሳኔውን የመረመረው የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን በሥነ ምግባር ኮሚቴው የተላለፈውን ውሳኔ አገደ፡፡ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ ለሪፖርተር ዕገዳውን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከሚመለከተው አካል ከመገለጹ በፊት ውሳኔው በተለያየ መንገድ በመሰማቱ፣ በውሳኔ አሰጣጡ ሒደት ላይ አንዳንድ ችግሮች በመኖራቸው፣ እንዲሁም ከታገዱት አባላት መካከል ይግባኝ ያስገባ በመኖሩ ምክንያት ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን አግደነዋል፤›› ሲሉ አቶ አበበ የዕግዱን ምክንያት ገልጸዋል፡፡
የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከቻለባቸው ምክንያቶች በዋነኛነት ውሳኔው ከፓርቲው ሕገ ደንብ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ፣ ግልጽ ያልሆነ ነገር በማካተቱና አስፈላጊውን የሥነ ሥርዓት ሒደት ስላልተከተለ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ግልጽ ያልሆነ ነገር አለው የሚለውን በተመለከተ፣ ‹‹ተባረዋል የተባሉት አባላት ገንዘብ አጥፍተዋል ከሚል ክስ በስተቀር ተከሳሾቹ በስንት ብር ተጠያቂ እንደሆኑ በግልጽ የሚገልጽ ነገር የለም፡፡ በፓርቲው ደንብ መሠረት የፓርቲውን ሊቀመንበር በተመለከተ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጠው አካል ጠቅላላ ጉባዔው በመሆኑ ውሳኔው የመተዳደሪያ ደንቡን ጥሷል፡፡ እንዲሁም የውሳኔው ሒደት የሥነ ሥርዓት ጉድለት አለው ሲባል ደግሞ ተከሳሾች በሌሉበት ምስክሮች መሰማታቸው አግባብ ስለሌለው ነው፤›› በማለት አቶ አበራ አብራርተዋል፡፡
ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች ኮሚሽኑ በአመራሮቹ ላይ የተወሰደውን ዕርምጃ ማገዱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩን እየመረመርን ስለሆነ በራሳችን የማጣራት ሒደት ጉዳዩን አጣርተን የራሳችንን ውሳኔ በ15 ቀናት ውስጥ የምንሰጥ ሲሆን፣ እኛ የምንሰጠው ውሳኔም የመጨረሻው ይሆናል፤›› በማለት አክለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን አለው ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሰብሳቢው፣ ‹‹የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ውሳኔ የመጨረሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ይግባኝ ሲሉና ምናልባት መስመሩን የለቀቀና ሥነ ሥርዓት ያልተከተለ ነገር አለ ተብሎ ሲገመት፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ይኖረዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 8 ላይ ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ‹‹የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን በሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የተሰጡ ውሳኔዎችን ይግባኝ ይመረምራል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔም ይሰጣል፤›› በማለት አስቀምጧል፡፡
ይህ ሥልጣን በፓርቲው ደንብ መሠረት እንደተሰጣቸው የሚገልጹት ሰብሳቢው፣ ‹‹የእኛ ውሳኔ የሥነ ምግባር ኮሚቴውን አቅም አልባ እንዳደረገው የሚገለጹት ነገሮች መሠረተ ቢስ ናቸው፤›› በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡
‹‹ለሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ክብር አለን፡፡ አባላቱ ሥራቸውን በአግባቡ እንደሠሩም እናምናለን፡፡ ሥራቸውን በሚሠሩበት ወቅት ግን የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚያ ችግሮች ደግሞ በውሳኔው ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ብለን በማመናችን እንደገና ጉዳዩን ለማየት አግደነዋል እንጂ፣ እነርሱ ሥራቸውን በሚገባ ለመሥራት ጥረት አድርገዋል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
አምስት አባላት ያሉት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን በጠቅላላ ጉባዔው ይቋቋማል፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላላ ጉባዔው ሲሆን የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡፡ የፓርቲው ገንዘብና ንብረት በአግባቡ በሥራ ላይ መዋላቸውን መከታተልና መቆጣጠር፣ በፓርቲ ውስጥ የሚከሰቱ የአባላትም ሆነ የአመራር አካላት የሥነ ሥርዓት ጉዳዮችን የሚያይ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ማቋቋም፣ እንዲሁም ከአባላት የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ የአሠራር ጉድለቶች በወቅቱ እንዲታረሙና ችግሮቹም እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ የሚሉ፣ ወዘተ ናቸው፡፡