Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ የሚኖረው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ነው!

በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዳይኖር እያደረገ ያለው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ዋነኛው ምክንያት፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ ዋስትና የተሰጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ አለመከበር ነው፡፡ በአገሪቱ የሕጐች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት በመሠረታዊ መርሆዎቹ የሕዝብን ሉዓላዊነት፣ የሕገ መንግሥቱን የበላይነት፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን መከበር፣ የመንግሥትና የሃይማኖትን መለያየት፣ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነትን በማያወላዳ መንገድ አስፍሯል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩት የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የተወሰዱ በመሆናቸው አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ ለመፍጠር ጠቃሚ ናቸው፡፡  

ሕዝቡ የአገሪቱ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት መሆኑና ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚ እንደማይሆን በሚገባ ሠፍሯል፡፡ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ በመሆናቸው እንደሚከበሩ፣ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ በመሆናቸው አንዳቸው በሌላው ጣልቃ እንደማይገቡ፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ካጓደለ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ሲያጣ ከቦታው ለማንሳት እንደሚችል በግልጽ ደንግጓል፡፡ አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡

ይህ ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረና ተራማጅ ሊባል የሚችል ሕገ መንግሥት በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ክፍል ውስጥ፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ በርካታ አንቀጾችን ይዟል፡፡ የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶች መከበራቸውን፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ መከልከሉን፣ የተያዙ ሰዎች መብት እንደሚከበር፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት እንደሚከበር፣ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት እንደሚከበር፣ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ እንደማይሠራ፣ የክብርና የመልካም ስም መብት መከበሩን፣ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን፣ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት ዋስትና ማግኘቱን፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት መከበሩን፣ የአመለካከትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መከበሩን፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ በማንኛውም ሥፍራ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት ነፃነት፣ ወዘተ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ ትሩፋቶች ናቸው፡፡

በአገሪቱ በአሁኑ ጊዜ የሕዝብ ዋነኛ የምሬት መነሻ ምክንያት የሆኑት ብልሹ አስተዳደር፣ የፍትሕ መዛባትና ሙስና የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ ናቸው፡፡ ዜጎች አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች መሆን እንዳለባቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየተናገሩ ነው፡፡ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ቅንጣት ያህል ደንታ የሌላቸው ሹማምንትና ኔትወርኮቻቸው የበላይነቱን በያዙበት በዚህ ጊዜ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ያልተከበረለት ዜጋ እንዴት አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ይሆናል? ዜጎች በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ማሳያ የሆነው ዴሞክራሲ በወጉ ሳይከበርና የዜጎች መሠረታዊ መብቶች ተግባር ላይ ሳይውሉ በምን መተማመኛ ነው ዜጎች መንግሥትን የሚሞግቱት? ሌላው ቀርቶ ከሰሞኑ በዘመቻ በመወሰድ ላይ ባለው ዕርምጃ በታችኛው መዋቅር ውስጥ ካሉ አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ውጪ፣ የትኛው ቱባ ባለሥልጣን ተጠያቂ ሆኗል? ለይስሙላ ያህል ከኃላፊነት ተነሱ የተባሉ እጅግ በጣም ጥቂት ባለሥልጣናት እንኳ ሌላ ኃላፊነት ላይ ነው ሲቀመጡ የሚታዩት፡፡ ይህ ችግር በራሱ የሚናገረው አለው፡፡

ዜጐች በአገራቸው ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ሕገ መንግሥቱ ደንግጓል፡፡ የእኩልነት መብት ስላላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው በወረቀት ላይ የሕግ የበላይነት መከበሩን ነው፡፡ በተግባር ግን ዜጎች ተሳትፎ ለማድረግ አይደለም ጥያቄ ለማቅረብ እንኳ ሲሳቀቁ ነው የሚታየው፡፡ ዜጎች በነፃነት ተደራጅተው የፈለጉትን የፖለቲካ አመለካከት ማራመድና የሚፈልጉትን ፓርቲ መደገፍ፣ ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ፣ መሰብሰብና ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ፣ ወዘተ ዳገት ሆኖባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በጣም ከመጥበቡ የተነሳ አማራጭ ለማግኘት ችግር ተፈጥሯል፡፡ ሕዝብ በሚበድሉት አስተዳዳሪዎች ላይ ተቃውሞ ሲያቀርብ አዳማጭ የለውም፡፡ የታመቁ ብሶቶች ፈንድተው ሲወጡ ምላሹ አስከፊ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈሩት መሠረታዊ መብቶች ተግባራዊ የሚያደርጋቸው በመጥፋቱ፣ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የአገር ህልውናም እያሠጋ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ የሚፈጠረው?

ሕገ መንግሥቱ ተከብሮ በተግባር ሥራ ላይ መዋል የሚችለው የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት ሲኖርበት ብቻ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን ካልቻለና ባለሥልጣናትም ሆኑ ተመራጮች ኃላፊነታቸውን ሲያጓድሉ በሕግ ካልተጠየቁ፣ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ ሳይሆን የአገርን ህልውና የሚያናጋ አመፀኛ ኅብረተሰብ ይፈጠራል፡፡ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራትና ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪም በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑም እንዲሁ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት የሚገለጸው፣ በሕገ መንግሥቱ እንደሠፈረው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሚመርጣቸው ተወካዮቹና በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ የዴሞክራሲ አራቱ ቁልፍ ነጥቦች ማለትም ነፃና ትክክለኛ ምርጫ፣ የሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የሕግ የበላይነት የወቅቱ ጥያቄ ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ እነዚህን ተግባራዊ ማድረግ የመንግሥትም ሆነ የማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት ነው በማለት እያስታወቀ፣ ከዚህ በተፃራሪ የሚገኙ ደግሞ መጠየቅ አለባቸው፡፡ አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ የሚፈጠረው በዚህ መሠረት ብቻ ነው፡፡ ነፃና ኃላፊነት የሚሰማው ኅብረተሰብ ለዚህች አገር ያስፈልጋል፡፡

የሕዝብ ኃላፊነት አለብኝ የሚል ማንኛውም ወገን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ መታገል አለበት፡፡ ይህ ትግል ከአመፃ የራቀና ሕግን የተከተለ ሲሆን፣ ውጤቱም ከሚገመተው በላይ አመርቂ ይሆናል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ እስካሁን የተደረገው ጉዞ ያስገኘው ውጤት የሕዝብን መከፋትና ለተቃውሞ መነሳት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለበርካታ ዓመታት ሕዝብ ከእኔ ጋር ነው ቢልም፣ አሁን በተጨባጭ እየታየ ያለው ዕውነታ ይህንን አያሳይም፡፡ ከአሁን በኋላ ይህንን የተሳሳተ ዕይታ በመቀየር ዕውነታውን ማጣጣምና መስተካከል ነው ያለበት፡፡ ራስን እያታለሉ መኖር ለውድቀት መንስዔ ከመሆኑም በላይ ለአገር ህልውናም ጠንቅ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ማብራሪያ ችግሮችን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ፣ ወደ ራስ መመልከት ይበጃል ያሉት ትክክል ነው፡፡ ‹‹ሕዝቡ በአፉ ብቻ ሳይሆን በእጁ ጭምር ዞር በሉ ብሎናል፤›› ያሉት አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህ መንፈስ ሕገ መንግሥቱን በማስከበር ሰላማዊ፣ ሕጋዊ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ንቁ ኅብረተሰብ መፍጠር ይሻላል፡፡ አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ኅብረተሰብ መፍጠር የሚቻለው ደግሞ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበር ብቻ ነው!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...