Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጂቡቲ ወደብ በመጨናነቁ አጣዳፊ ዕቃዎች በሱዳንና በርበራ ወደቦች እንዲገቡ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ገቢ ዕቃዎች ማስተናገድ ከጂቡቲ ወደብ አቅም በላይ በመሆኑ፣ መንግሥት አጣዳፊ ዕቃዎች በሱዳንና በበርበራ ወደቦች እንዲገቡ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረት 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ወደ ሱዳን ወደብ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካይነት የመጣ 25 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የዕርዳታ እህል ደግሞ በበርበራ ወደብ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ገቢ ዕቃዎች በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ በመድረሳቸው የጂቡቲ ወደብ ተጨናንቋል፡፡

‹‹የጂቡቲ ወደብ መጨናነቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ የሱዳንና የበርበራ ወደቦችን ለመጠቀም ተወስኗል፤›› በማለት አቶ ካሳሁን ወቅታዊውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

የጂቡቲ ወደብ ሊጨናነቅ የቻለው ባለፉት 50 ዓመታት አጋጥሞ የማያውቅ ድርቅ በመከሰቱ ሲሆን፣ መንግሥት ይህንን አደጋ ለመቋቋም የገዛው 16 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ጂቡቲ ወደብ በመድረሱ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለተያዘው የምርት ዘመን የሚያስፈልገው 812 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ፣ በሁለት ምዕራፍ ግዢ ተፈጽሞ በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ መድረሱ ለመጨናነቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

አጋጥሞ በነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ፣ መንግሥት ከራሱ የገንዘብ ምንጮች 2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለግሉ ዘርፍ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዚህ የውጭ ምንዛሪ በመጠቀም የግሉ ዘርፍ ያስገባቸው የግንባታና ሌሎች ዕቃዎችም ጂቡቲ ወደብ ደርሰዋል፡፡ መንግሥት በተለይ ለስንዴና ለማዳበሪያ ትኩረት በመስጠት በአገሪቱ የሚገኙ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሙሉ እነዚህን ዕቃዎች እንዲያነሱ ተወስኗል፡፡

‹‹በቀን አሥር ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ እያነሳን ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ወደቡ በከባድ ተሽከርካሪዎችና ወረፋ በሚጠብቁ መርከቦች ተጨናንቋል፡፡ የተፈተንበትና ብዙ ልምድ ያገኘንበት ወቅት ነው፤›› በማለት አቶ ካሳሁን ወቅታዊውን የጂቡቲ ወደብ ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚሉት የጂቡቲ መንግሥት ለወደቡ መጨናነቅ ኢትዮጵያ በፕሮግራም ባለመመራቷ የመጣ ችግር መሆኑን፣ ይህ ደግሞ ወደቡ በሌሎች ዘንድ ያለውን ገጽታ የማያበላሽ ነው በማለት ቅሬታውን ገልጿል፡፡

ይህንን ቅሬታ በተመለከተ አቶ ካሳሁን ሲመልሱ፣ ይህ ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያ በገጠማት የድርቅ ችግር አዳዲስና ትልልቅ ገዢዎች በመፈጸማቸው ነው፡፡

‹‹1.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ (16 ሚሊዮን ኩንታል) አዲስ ግዢ ተፈጽሟል፡፡ የጂቡቲ መንግሥትም ወቅታዊውን ሁኔታ ሊረዳ ይገባል፤›› በማለት አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ መጨናነቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ልትከፍል አትገደድም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ካሳሁን ሲመልሱ፣ ውኃ ላይ ሆነው ተራቸውን ለሚጠባበቁ መርከቦች ኢትዮጵያ ኪራይ አትከፍልም፡፡ እያደረግን ያለነው የማይነሳ ምርት መርከብ ላይ እንዲቆይ ማድረግ ነው፡፡ የወደብ ኪራይ የሚጀምረው ዕቃ ከመርከብ መራገፍ ሲጀምር ነው ብለዋል፡፡

‹‹ይህንን ወቅታዊ ችግር ለመቅረፍ በአሁኑ ወቅት የተሰማሩትን አሥር ሺሕ ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ በሙከራ ሥራ ላይ ሆኖ እስከ አዳማ በማጓጓዝ ላይ ባለው ባቡር በመጠቀም 24 ሰዓታት እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው መረጃ ሦስት መርከቦች አንድ ጊዜ ሲያራግፉ 15 መርከቦች ወረፋ ይጠብቃሉ፡፡ ዕቃ ማራገፍ ሳይቻል አንድ ወር የቆየ መርከብ አለ በማለት አቶ ካሳሁን የክስተቱን ፈታኝነት ገልጸው፣ ከሌሎች አገሮች ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለማምጣት ቢታሰብም፣ በጂቡቲ ወደብ የፓርኪንግ ቦታ እንኳ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች