አበረታች ቅመሞች ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ጀምሮ ጥንታዊ በሆነው የፈረስ ስፖርት ውድድር ላይ ተወዳዳሪዎች ይጠቀሙበት እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ776 ዓመት ላይ በይፋ በተጀመረው በጥንታዊው ኦሊምፒክም ቢሆን ስፖርተኞች በውድድር ወቅት የበለጠ አቅምና ጉልበት ይኖራቸው ዘንድ በውል የማይታወቁ የተለያዩ አነቃቂ ባህላዊ ቅመሞችንና ንጥረ ነገሮችን ይጠቀሙ እንደነበረ ይወሳል፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ደግሞ በባህላዊው መንገድ የተጀመረው ይኼው አደገኛ ወረርሽኝና ጥፋት በፍጥነት በመስፋፋት በየአገሩ በመዘውተር ብቅ ብቅ ማለት መጀመሩ፣ ይህም በጊዜውና በወቅቱ በሳይንሳዊ ዘዴና ጥናት በፍፁም ይደገፍና ይታገዝ ስላልነበረ ቁጥጥርና ክትትሉም በዚያው መጠን ደካማ በመሆኑ በስፖርተኞች ሕይወት ላይ ሳይቀር የራሱን ተፅዕኖ ሲያደርስ መቆየቱ መረጋገጡ ተረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የዚሁ ወረርሽኝ ሰለባ መሆኑ ከታወቀም ሰነባብቷል፡፡ የወረርሽኙን ስፋትና መጠን ግምት ያስገባ የሚመስለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ መጋቢት 24 እና 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ የስፖርት መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ መነሻ ጥናታዊ ጽሑፎች እንዲቀርቡ በማድረግ እንዲወያዩበት አድርጓል፡፡ በርካታ በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአትሌቲክሱ በኃያልነታቸው የሚታወቁ አገሮች በአደገኛ ቀጣና ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ መኖሩ ነው የተረጋገጠው፡፡
በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ሕክምና ኃላፊ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን አማካይነት በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በአሁኑ ወቅት አትሌቲክሱን ጨምሮ ለበርካታ ስፖርትና ስፖርተኞች ቀጣይ ሕይወት ላይ እንቅፋት መሆኑ እየተነገረለት የሚገኘው የአበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ምርመራ አጀማመርን የተመለከተ ይገኝበታል፡፡ በዚሁ መሠረት የመጀመርያው ፀረ አበረታች እንክብሎች በሰው ላይ በሳይንሳዊ ዘዴ እ.ኤ.አ. በ1968 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ በዚያን ወቅት በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ የአዕምሮ አነቃቂዎችንና (CNS Stimulants) ሰውነትን የሚያደነዝዙ (Norcotics) ለይቶ ለማግኘት መቻሉን፣ ይህ ፀረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች እንቅስቃሴ በሳይንቲስቶች (የስፖርት) ከአራት ዓመት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ1972 በሙኒክ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ከ2,000 በላይ የስፖርተኞች ናሙና በቤተ ሙከራ መፈተሽ መቻሉን ባቀረቡት ጥናት አሳይተዋል፡፡
የአበረታች ቅመሞቹን ዓይነትና የሚሰጡትን አገልግሎት አስመልክቶ ዶ/ር አያሌው፣ በተፈጥሮና በዘመናዊ ሥልጠና ያገኙትን ሁለንተናዊ አቅም በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ውጤታማ የሚያደርጉ ቅመሞችና መድኃኒቶች መሆናቸው፣ በአትሌቶች አካላት ላይ የሚመጣው ለውጥ ከፍተኛ መሆን፣ በመተንፈሻ አካሎች ላይ የማይታመን ለውጥ ማምጣትና ከፍተኛ ድካምና የሕመም ስሜቶችን መቀነስ መቻላቸውና ሌሎችንም አካተው የያዙ መሆናቸውን በጥናቱ ቀርቧል፡፡
የአበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች አወሳሰድን አስመልክቶ ጥናት አቅራቢው፣ አትሌቶቹ ከፍተኛ ገንዝብ ለማግኘት፣ ልዩ ዝናንና ክብርን እንዲሁም ሁልጊዜ ‹‹እኔ ብቻ›› ለማለት፣ ስግብግብነት ሲበረታ፣ ድርጊቱን ለመፈጸም የሚገፋፉዋቸው ደግሞ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና የማናጀር ተወካዮች ስለመሆናቸው ጭምር በጥናቱ አመላክተዋል፡፡
አበረታች ቅመሞቹና መድኃኒቶቹ ከተወሰዱ በኋላም የሚያስከትሏቸው ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶችም በርካታ መሆናቸው በጥናቱ ቀርቧል፡፡ እነዚህ ቅመሞች በተለይም በሥልጠናም ሆነ ውድድር ጊዜ ሊወሰዱ እንደማይገባ፣ ከተወሰዱ ግን ትላልቅ ውስጣዊ አካሎችን ለጉዳት እንደሚዳርጉ፣ ዕድገትን ያለ ወቅቱና ጊዜው ማቋረጥ፣ የወንድነትን ዘር መቀነስና ሴቶች የወንድነትን ባህሪያት እንዲወስዱ (እንዲይዙ) ማድረግ፣ ለደም ግፊትና ለኮሌስትሮል ሕመሞች መጋለጥ፣ ሌላውና እጅግ አሳሳቢው ደግሞ ለሱሰኝነት መጋለጥ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ አቶ መንግሥቱ አበበ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ሰኔ 30 ቀን 1999 ዓ.ም. በልዩ ስብሰባ በአዋጅ ቁጥር 554/1999 በመንግሥታቱ የፀደቀውን የፀረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ኮንቬንሽን አፅድቃለች፡፡ በዚሁ መሠረትም አበረታች ቅመሞቹንና መድኃኒቶቹን ተጠቅሞ መገኘት በአገሪቱ የወንጀለኛ፣ የፍትሐ ብሔርና የአስተዳደራዊ ሕግ መሠረት ቅጣት እንደሚተላለፍበት አስረድተዋል፡፡ እንደ ሕግ ባለሙያው፣ ቅጣቱ ከተጠቃሚው በተጨማሪ አበረታች ቅመሞቹንና መድኃኒቶቹን ያመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ የሸጠ፣ ያከፋፈለ፣ በባለሙያነት ያዘዘ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ በድርጊቱ ተሳታፊ ሆኖ የተገኘ ሁሉ ተፈጻሚ ይደረግበታል፡፡
ሌላውና በዋናነት የተነገረው ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የፀረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ኤጀንሲ (ዋዳ) እንድታሟላ የተጠየቀችውን ለማሟላት የአምስት ወር ጊዜ ገደብ እንደተሰጣት፣ ይህም አገሪቱ ከአራት ወራት በኋላ በሚከናወነው በሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ያለ አንዳች ችግር መካፈል እንደምትችል ማረጋገጫ ማግኘቷን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ የተናገሩት ተጠቃሽ ነው፡፡