Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአንቂ ፊልሞች

አንቂ ፊልሞች

ቀን:

‹‹ሥራ የላትም›› የተሰኘው የሦስት ደቂቃ ፊልም በአንድ ደስተኛ ቤተሰብ ላይ ያተኩራል፡፡ የሚዋደዱ ባልና ሚስት እንዲሁም ልጆቻቸውን ያስቃኛል፡፡ እናቲቱ ማለዳ ተነስታ ቁርስ ሠርታ፣ ለልጆች ምሳ ከታ፣ ቤተሰቡን ሸኝታ ወደተቀረው የቤት ውስጥ ሥራ ትሸጋገራች፡፡ ቤት ማፅዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ ምግብ ማብሰል፣ ሕፃን ልጅ መንከባከብና ሌሎችም በርካታ ሥራዎች ይጠብቋታል፡፡ ፊልሙ ከቤተሰቧ ቀድማ ከእንቅልፏ ነቅታ ከሁሉም መጨረሻ የምትተኛውን እንስት ሕይወት ያሳያል፡፡ በፊልሙ መጨረሻ እሷና ባለቤቷ ወደ ቤታቸው እንግዶች ይጋብዛሉ፡፡ እንግዶቹም ባለቤትህ ሥራዋ ምንድነው? ብለው አባወራውን ይጠይቃሉ፡፡ እሱም ባለቤቱን በስስት ዓይን እየተመለከተ፣ ‹‹ሥራ የላትም፤ የቤት እመቤት ናት፤›› ይላል፡፡ ፊልሙ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አኗኗር ያንፀባርቃል፡፡ በቤት ውስጥ ሥራ የተጠመደች ሴት ከቤት ውጪ ባለ ሥራ ባለመሥራቷ ‹‹ሥራ የላትም›› በሚል ትገለጻለች፡፡

በተመሳሳይ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ባሉ ወንድና ሴት ልጆች መካከል ያለውን የሥራ ክፍፍል አለመመጣጠን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡ ጫናው በሕይወታቸው ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የሚያሳየው የሦስት ደቂቃ ፊልም ደግሞ ‹‹ዓለም›› ነው፡፡ ፊልሙ እናቷን የማገዝና ታናሽ እህቷን የመንከባከብ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ስለወደቀባት ታዳጊ ያወሳል፡፡ በዕድሜ የሚቀራረብ   ወንድሟ አንዳች የሥራ ኃላፊነት የለበትም፡፡ ታዳጊዋ ነፃ የትምህርት ዕድል የሚያስገኝ ፊልም በቴሌቪዥን ለመመልከት በጉጉት ስትጠባበቅ ታናሽ እህቷ ታለቅሳለች፡፡ እናቷ እህቷን እንድታባብል ያዟትና አባብላ ለማስተኛት ወደ መኝታ ክፍል ትገባለች፡፡ ወንድሟ ከጓደኞቹ ጋር ኳስ ለመጫወት ከቤት ሊወጣ ሲል በአጋጣሚ ፊልሙን ይመለከታል፡፡ ታዳጊዋ እህቷን አስተኝታ ወደ ሳሎን ስትመለስ ፊልሙ አልቋል፡፡ ወንድምየው ፊልሙን ተመርኩዞ የተዘጋጀ ፈተና አልፎ የትምህርት ዕድሉን ያገኛል፡፡ ቤተሰቡ ይደሰታል፡፡ ታዳጊዋ ግን ቅሬታዋን እንኳን ሳታሰማ በሐዘን ትዋጣለች፡፡  

ማኅበረሰቡ ባለማስተዋልም ይሁን ሆነ ብሎ በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ወደ አካላዊ ጥቃት የሚሄድበት ጊዜም አለ፡፡ ‹‹እሪታ›› የተሰኘው የሦስት ደቂቃ ፊልም ከትምህርት ቤት ስትመለስ በሁለት ወንዶች ተደፍራ ሕይወቷ ስለሚመሰቃቀልባት ታዳጊ ይተርካል፡፡ ጎበዝ ተማሪ የነበረችውና ብሩህ ተስፋ የነበራት ታዳጊዋ ከተደፈረች በኋላ ተስፋ ትቆርጣለች፡፡ ራሷን ለማጥፋት ስትሞክር ልትሰቀልበት የነበረው ገመድ የታሰረበት እንጨት ይወድቅና ሕይወቷ ይተርፋል፡፡ መደፈሯ የጣለባት ጥቁር አሻራ ግን እስከ ወዲያኛው በሕይወቷ ላይ እንደሚያንዣብብ ፊልሙ ያሳያል፡፡

ሦስቱ ፊልሞች የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የዘንድሮውን የሴቶች ወር (ማርች) በማስመልከት ባዘጋጀው ውድድር ከተሳተፉት 190 ፊልሞች መካከል ናቸው፡፡ የሐኒባል አበራ ‹‹ሥራ የላትም›› አንደኛ ወጥቶ 80,000 ብር፣ የያኒት ብርሃኑ ‹‹ዓለም›› በሁለተኛነት 40,000 ብር፣ እንዲሁም የፍሬዘር ፍሥሐና የካቢናድ ሰግጥ ‹‹እሪታ›› በሦስተኛነት 20,000 ብር ተሸልመዋል፡፡ ውድድሩ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች የሚሳዩ ፊልሞች የተሳተፉበት ሲሆን፣ አሸናፊዎቹን ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ኤምባሲ ያሳወቁት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ሐስለሽ ነበሩ፡፡

ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በፊልም ማቅረብ ለችግሮቹ መፍትሔ ለማግኘት ሁነኛ መንገድ እንደሆነ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ የውድድሩ አሸናፊዎችም ሐሳቡን ይጋራሉ፡፡ በሴቶች ላይ ያተኮሩት ፊልሞቻቸው አሁን እየታዩ ያሉት በዩቲዩብ ብቻ ቢሆንም በቀጣይ ተደራሽነታቸው ሲሰፋ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ እምነታቸው ነው፡፡ ሐኒባል፣ ‹‹ሲኒማ ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ የሴቶችን ጉዳይ ሰዎች ከሚያውቁት መንገድ በተለየ በማቅረብ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤›› ይላል፡፡

አጫጭር ፊልሞች ያላቸውን አቅም በመጠቀም፣ ሴቶች ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ መተረክ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ በፊልሙ ያለችው ሴት ቤተሰብ ደስተኛና የሚተሳሰብ ቢሆንም፣ የሷን አስተዋጽኦ በማሳነስ ‹‹ሥራ የላትም›› ይሏታል፡፡ በማኅበረሰቡ የዘወትር ኑሮ ያሉና ልብ የማይባሉ ተፅዕኖች በፊልም ቢንፀባረቁ ብዙዎች የየራሳቸውን ሕይወት እንደሚፈትሹ ያምናል፡፡

ያኒትም ተመሳሳይ ሐሳብ አላት፡፡ በማኅበረሰቡ የተለመዱና በሴቶች ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ እንኳን ብዙዎች የማይገነዘቧቸው ተግባሮች በፊልም መታየት እንዳለባቸው ትገልጻለች፡፡ ‹‹በገጠርም ይሁን በከተማ ያሉ ሴቶች ፊልሙ ላይ እንዳለችው ሴት ጫና አለባቸው፡፡ ቤተሰብ ሴት ልጁን ለመጉዳት ብሎ ባይሆንም ተፅዕኖ ያደርግባቸዋል፡፡ ይኼ በሕይወታቸው ላይ የሚኖረውን ጉዳት ብዙዎች አያስተውሉትም፤›› ትላለች፡፡ ፊልሟ በተለያዩ መድረኮች ታይቶ የለውጥ አንድ ዕርምጃ እንዲሆንም ትመኛለች፡፡

ፍሬዘር እንደሚናገረው፣ የሴቶች ጥቃት አሁንም እልባት ስላልተገኘለት በተለያየ መንገድ ስለችግሩ መወራት አለበት፡፡ ከአጭር ፊልሞች ባሻገር በፊቸር ፊልሞች በከፍተኛ በጀትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ቢሠራ መልካም ነው ይላል፡፡ ፊልሙ ላይ እንዳለችው ታዳጊ ሁሉ ብዙ ሴቶች መደፈርን የመሰሉ አካላዊ ጥቃቶች ሲደርሱባቸው ጩኸታቸውን የሚሰማ አካል ውስን ነው፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪው ኪነ ጥበብ ደግሞ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብሎ ያምናል፡፡

ሦስቱም ወጣቶች ከዚህ ቀደም የተሳተፉባቸው ፊልሞች ቢኖሩም ጀማሪ የሚባሉ ናቸው፡፡ በውጤታቸው እንደተደሰቱና በውድድሩ ልምድ እንዳካበቱ ይገልጻሉ፡፡ ከባለሙያዎች ጋር እንደተዋወቁና ስለ ሥራቸው ጥሩነት ማረጋገጫ እንዳገኙም ይናገራሉ፡፡ ሐሳባቸውን የምትጋራው ከውድድሩ የፊልም ባለሙያ ዳኞች አንዷ አዜብ ወርቁ ናት፡፡ እሷ፣ ቴዎድሮስ ተሾመና ዘለዓለም ወልደማርያም ፊልሞቹን ዳኝተዋል፡፡

አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች አማተር ስለሆኑ ውድድሩ ለሙያቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ትናገራለች፡፡ ፊልሞቹ የሴቶች ጥቃት ሲባል አካላዊ ብቻ አለመሆኑን ማሳየታቸው ጥሩ እንደሆነም ትገልጻለች፡፡ ‹‹ስለአምባገነን ባል ወይም የአካል ጥቃት ብቻ ሳይሆን ሴቶችን ወደኋላ ስለሚያስቀሩ ማኅበረሰባዊ ልማዶችም መወራት አለበት፤›› ትላለች፡፡

የአጭር ፊልም ሕግጋትን ጨምሮ የፊልሞቹ ታሪክ፣ የምስልና ድምፅ ጥራት፣ ትወናና ሌሎችም መሠረታዊ ነገሮች ከግምት ገብተዋል፡፡ ለፊልሞቹ በተሰጣቸው አጭር ጊዜ ከንግግር ይልቅ በምስል መግለጻቸውና ያነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማንፀባረቃቸውም መሥፈርቶች ነበሩ፡፡ አዜብ እንደምትለው፣ 190 ወጣት ባለሙያዎች መወዳደራቸው ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለአጭር ፊልም ትኩረት ባይሰጥም፣ ውድድሩ ግን አበረታች ነው ትላለች፡፡

 ኢትዮጵያዊት አሜሪካዊቷ ፕሮፌሰር ሉሲ ገብረእግዚአብሔር ዓምና በሰጡት ወርክሾፕ ከተካፈሉ ባለሙያዎች አንዷ በነበረችው አዜብ አገላለጽ፣ አጭር ፊልም በትንሽ በጀት ተሠርቶ ብዙ ትምህርት ይገኝበታል፡፡ ፊቸር ፊልም ሲሠራም የሚጠቅሙ ተሞክሮች ለማግኘትም ይረዳል፡፡ መልዕክትን በአጭሩ ለማስተላለፍና በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ለመድረስም ምቹ እንደሆነ በመግለጽም የአጫጭር ፊልሞች መብዛት ለአገሪቱ ፊልም ዕድገትም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታስረዳለች፡፡

የዓምናው ሥልጠና በሴቶች ጥቃት ላይ  ያተኮረ የፊልም ጽሑፍን ያማከለ ነበር፡፡ በወርክሾፑ ማጠናቀቂያ በተካሄደው የፊልም ጽሑፍ ውድድር አዜብ ‹‹ብትሆንስ›› በተሰኘ ጽሑፏ አሸንፋ በተሸለመችው 25,000 ብር ያሸነፈችበትን ጽሑፍ ወደ አምስት ደቂቃ ፊልም ለውጣለች፡፡ ወርክሾፑ ‹‹ቴሊንግ ኸር ስቶሪ›› (የሷን ታሪክ መንገር) የተሰኘ ሲሆን፣ የዘንድሮው ውድድር የወርክሾፑ ቀጣይና ‹‹ኸር ስቶሪ›› (የሷ ታሪክ) የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው፡፡ ያሸነፉት ፊልሞች በቀጣይ በየክልሉ፣ በትምህርት ቤቶችና ሌሎችም ሥፍራዎች ይታያሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...