በዲሪርሳ ኢላላ ዱጋሳ
ታሪክ የሰው ልጆች መስተጋብራዊ እንቅስቃሴዎች፣ የተፈጥሮ ክስተቶች፣ አሊያም የሁለቱ ድብልቅ ውጤት ሆኖ ዘመናት ከነጎዱ በኋላ ትውልዶች አልፈው ትውልዶች ተተክተው መጪዎች ካለፉት በጎና ክፉውን፣ ስኬትና ውድቀትን፣ ጥፋትና ልማትን፣ ቀናና ጠማማን፣ ወዘተ በየወቅታቸውና ባሉበት ዘመን፣ አተያይ፣ ሚዛንና ልኬት ገምግመው ብይን፣ አድናቆትና ውግዘት ሰጥተው ውድቅ አሊያም ቅቡል የሚያደርጉት ዘመናትን ተሻግሮ ተዘግቦ የሚታወስ፣ የሚገመገም የድርጊቶች የኩነቶችና የክስተቶች ውጤት ነው፡፡ ለታሪክነት የዘመናት ፍሰት የትውልዶች ቅይይር ቁልፍ መሥፈርት ሲሆን፣ አንድ ክንውን መቼ ታሪክ ይሆናል ለሚለው ጥያቄ ቁርጥ ያለ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ግን ይገዳል፡፡ የታሪክና የቋንቋ ልሂቃን ግን ዕውቀትና ሙያቸው ስለሆነ የሚሉት ይኖራቸዋል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ አገዛዝ ካከተመ ዘንድሮ 42ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡ የዚያ ዘመን ክንውኖች ሁሉም ከትውልዶችና ከዘመን ጋር እንደ ወራጅ ወንዝ አልፈው ከጠባሳቸው በስተቀር በድርጊት የምናያቸው፣ አሊያም በነባራዊ ሕይወታችን ላይ በተጨባጭ የምንገነዘባቸው አይደሉም፡፡ ዳሩ ግን ተመሳሳይ ኩነቶቻቸው ዛሬም ሆነ ነገ ሊከሰቱ ቢችሉም፣ በያን ጊዜው ዓይነት ወይም ውጤታቸው የያኔዎቹ ካርቦን ቅጂዎች ሆነው አይገኙም፡፡ የደርግ አገዛዝ ዘመንም በግዱ ከተወገደ ዛሬ 25ኛ ዓመቱን ሊላበስ ሁለት ወራት ብቻ ይቀሩታል፡፡ የዚያም ዘመን አገዛዝ አንዳንድ ክንውኖችና ውጤቶቻቸው በማንኛውም መልክ እንደያኔው ሆነው አይደገሙም፡፡ እንዲያም ስለሆነ ሁለቱም ከነግሳንግሳቸው ወደ ታሪክ መዘክርነት ተካተዋል፡፡ እነኚህ ሁለት ዘመነ መንግሥታት ታሪክ በመሆናቸው ላይ ከሚመለከታቸው ልሂቃን ጋር የማያስማማና የሚያነታርክ ጉዳይ አይኖርም፡፡ በቃ ታሪክ ናቸው በሕይወት ስለሌሉ፡፡
ይህ ማለት በታሪክ ውስጥ የታዩ ሁኔታዎችና ክስተቶች ዳግም ተመልሰው አይታዩም ማለት አይደለም፡፡ ከፊሎቹ በተለያዩ ቦታዎች፣ ወቅቶችና ሁኔታዎች ማዕቀፍ ውስጥ በተለያዩ ሰዎች/ኅብረተሰቦች ፈጻሚነትና ተዋናይነት በተለያዩ ምክንያቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ መጠኖች ይደገማሉ፡፡ ውጤቶቻቸውም በተሻለ መልክና በከፍተኛ መጠን የሚገለጽበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ከትዝብት፣ ከአስተውሎት፣ ከትምህርት፣ ከጥናትና ምርምር እከላ የተነሳ እነኚህ በታሪክ ውስጥ የታዩ በጎ ክንውኖች ዳብረውና ጎልብተው ኅብረተሰብን የበለጠ እንዲጠቅሙ ተደርገው፣ አጥፊና አፍራሽ ድርጊቶች ደግሞ እርማትና ማስተካከያ ተበጅቶላቸው ጎጂና አፍራሽ ጎናቸው ተወግዶ አሁን ደግሞ ለኅብረተሰቡ አልሚ እንዲሆኑ ተስለው ይስተናገዳሉ፡፡ እናም ታሪክ በዚህ አኳኋን ራሱን ይደግማል፡፡ ያለፈው ያበጀውን አሻሽሎ ደግሞም ያበላሸውን አበጅቶ ለበጎ ማዋል ማለት ነው፡፡ የሁሉም እርሾ ያለው በዚሁ በምንኖርባት ዓለም ውስጥ እንጂ ከሌላ ከየትም ተቀድቶ አይመጣምና ነው፡፡ እንዲህ የሚሆነው ግን ታሪክ ሲሆን ነው፡፡
በጥቅል አነጋገር ታሪክ ምን መባል እንደሚችል ከላይ የማስቀመጥ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ከዚያን ውጪ ዘመናትን ያልተሻገረ፣ የትውልድ መተካካትን ያላስተናገደና በአንድ የዘመንና የትውልድ ማዕቀፍ ውስጥ የታየ የኅብረተሰብ ክንዋኔ የተፈጥሮ ክስተትና ውጤቶቹ ነባራዊ፣ በዓይን የሚታዩ፣ በስሜት የሚለኩና ውጤቶቹ በሙሉም ሆነ ከሞላ ጎደል በአሁኑ ሕይወታችንና ኑሯችን ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ እስከሆኑ ድረስ ታሪክ ከሚለው ተርታ ሊሠለፉ አይችሉም፡፡ በአንድ የተወሰነ ዘመን እየተመላለሱ የተፈጸሙ፣ በዚያው በአንድ ትውልድ ወይም ሥርዓት ተዋናዮችና በዚያው ሥፍራ የተደረጉ ክስተቶችና ውጤቶቻቸው ቀጣይ ክንውኖችና “የሞኝ ለቅሶ….” ዓይነት እንጂ፣ በታሪክ ውስጥ እንደሚባለው “መደገም” ዓይነት አንድምታ የሚሰጣቸው አይሆንም፡፡ በተለይም የፖለቲካ ክስተቶችና ተመሳሳይ ክንውኖች ከሆኑ ስላቅ ዓይነት ዝባዝንኬ ድርጊቶች ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም እንደ ሰው ልጆች ተሞክሮንና ከዚያም ዕውቀትን ካካበቱ የኅብረተሰብ አካላትና የኅብረተሰብ መሪዎች በኛው ዘመን፣ በኛው ከያኒነትና ፈጻሚነት ትናንትናና ከትናንት በስቲያ፣ አምናና አቻምና ያሳለፍናቸውን ድርጊቶች ዛሬም የምንነከርባቸው ከሆነ፣ ፈጽመን ባሳለፍናቸው ስህተቶች ውስጥ አሁንም የምንዘፈዘፍባቸው ከሆነ፣ መማርም ማስተማርም ያልቻልን ብኩኖች ሆነናል ማለት ነው፡፡ ለዚያውም ሕግም ሕገ መንግሥትም እያለን፣ ማጣቀሻ የዓለምና የየአገሮች ተሞክሮዎችም ሞልተው ተርፈው እያሉን፡፡ ያደለው ግን ከታሪክ ይማራል እንኳንስ ከራሱ ድርጊቶች፡፡ በዚሁ በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን ከሁሉም በተለይም ከኦሮሞ ጎምቱ “ፖለቲከኞች” አንፃር የታዩትን የፖለቲካ ስላቆች ጥቂቶቹን አንስቶ ቁም ነገር አልባነታቸውን ማሳየት ይቻላል፡፡ በእርግጥም ግለሰቦችን ማለት ሳይሆን ድርጊቶቻቸውን እንጂ፡፡ የአብዛኞችን ፖለቲካዊ የጀርባ ታሪክ ማንሳትና አካፋን አካፋ ማለት በተቻለ ነበር ሕግ ባይከለክል፡፡
የእኛዎቹም ጎምቱ “ፖለቲከኞች” የፖለቲካ ስላቅ እናንሳ ከተባለ ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለን ማየትን ይሻል፡፡ የዛሬዎቹ የፖለቲካ መሪዎቻችንና የፖለቲካ ፕሮግራሞች ቀራጮች ዋነኞቹን የመንግሥት መሪዎችንም ጨምሮ (የድል አጥቢያ ጨቅላዎቹን ሳናካትት)፣ አብለጫዎቹ የዛሬው ዘመን የፖለቲካ ፍጡሮች ሳይሆኑ የ1960ዎቹ ዘመን የታሪካዊው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ትውልድና ውጤቶቹ መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ ያ ትውልድና እንቅስቃሴው ደግሞ ረጅም ጊዜ ካስቆጠረ የእርስ በርስ ፍትጊያና ትግል በኋላ፣ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ አፈታት ላይ ከአንድ ጠንካራና የማያወላውል አቋም ላይ ለመድረስ በቅቷል፡፡ በዚህ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የትግል ዘመን ፈር ቀዳጅ ሚና የተጫወተውን ዋለልኝ መኰንን ታሪክ ይዘክረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዘመኑ ዓይነተኛ የቅራኔዎች ምንጭና የትግል አቅጣጫ የብሔር ብሔረሰቦች የራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት መሆኑ ቅቡል ከመሆኑም በላይ፣ “ተራማጅና አድኃሪ፣ አብዮተኛና ፀረ አብዮተኛ” (በያኔው የትግል ጎራ አሠላለፍ) በዚሁ ጥያቄ ላይ በሚይዘው አቋም ይፈረጅ ነበር፡፡ ትግሉም ከዚሁ አኳያ ቀጥሎ ብዙዎችና ኢሕአዴግም መፈክሩን አንግበው ከፍተኛ የትውልድ መስዋዕትነት ከፍለው በለስ የቀናው ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ድል ነስቷል፡፡ በአጭሩ ሲታይ አሁን በመድረክ ላይ ሆነው የፖለቲካውን መዘውር ከዚህኛውም ሆነ ከዚያኛው ወገን የሚዘውሩት ደግሞ፣ ዛሬ እነሱ ራሳቸው የሚወዛገቡበትን የፖለቲካ አጀንዳ በዚሁ መልኩ ቀርፀው ኅብረተሰቡን አስጨብጠው በሥሩም አታግለውት ህያው እንዲሆን ያደረጉት እነኚሁ የእኛዎቹ ጎምቱ “ፖለቲከኞች” ራሳቸው ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በ1987 ዓ.ም. ሲታወጅ በአንቀጽ 39 ቁጥር 1 ላይ ያሠፈረው “ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማንኛውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው” ሲል፣ በቁጥር 3 ላይ “ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው…” ሲል የእኛዎቹ ጎምቱ “ፖለቲከኞች” ያኔ ያኔ በሕዝብ ስም፣ በአገር ስም፣ በነፃነት ስም መሀላና ግዝት ያደረጉበትን ዓላማ ተገበረ፡፡ እነሱ ዛሬም ጭምር በሕይወት ስላሉ፣ እነሱ በትግሉ ሒደት ውስጥ ስላልተሰውና እነርሱ የመንግሥት ሥልጣን ስላልያዙ፣ ወይም ስለያዙ የትናንቱ ዕውነት እንደ ሐሰት ባልተቆጠረ፡፡ ወይም በዘበት እንደተገኘ የሚወሰድ ሳይሆን ይህ ድል ሕዝብ ልጆቹንና ንብረቱን፣ ጉልበቱንና ጊዜውን፣ ሞራሉንና ሥነ ልቦናውን ታሪክ ባላየው መልኩ መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣው መሆኑ ተዘንግቶ አንፃራዊው ባልተቀነቀነ፡፡ የእኛዎቹ ጎምቱ “ፖለቲከኞች”ም ቢሆኑ የትግሉ አቀጣጣዮችና ተዋናዮች ከመሆናቸው አንፃር የዚህ ድል መገኘት ከጎናቸው በትግሉ ሜዳ ውስጥ ለተቀነጠሱት ብርቅዬ ወንድሞቻቸው የሕይወት ካሳ፣ ለሕዝባቸው በደልና ጭቆና ዕንባ ማበሻ፣ ለተባረከ ዓላማቸው እማኝና ሐውልት ሆኖ የሚቀርብ እንጂ እነርሱ በግል/በቡድን የድሉን ዳቦ ስለ ገመሱ/አልገመሱ የሚያወድሱት/የሚያወግዙት ባልሆነ ነበር፡፡ ክፉ ድርጊት ሆነና ግን በፖለቲካ አመለካከት ሰበብ ራሳቸው የፈጠሩትን አጥፊ፣ የገነቡትን አፍራሽ ሆነው ሲገኙ የታሪክ ስላቅና የፖለቲካ አክሮባት ተዋናዮች ሆኑ፡፡ በሕዝብ ማፌዝና በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ማለት ሆነ፡፡ የእኛዎቹ “ፖለቲከኞች” የፖለቲካ ስላቅና ፌዝ በእንደምን መልኩ እንደሚገለጽም በጥቂቱ ለማሳየት ይቻላል፡፡ የእኛዎቹ “ፖለቲከኞች” የፖለቲካ አመለካከት/ቅኝት ልዩነትን እንደ ፀጋ የሚመለከቱ ሆነው ለመገኘት አልታደሉም፡፡ ይልቁንም ከያኔው ከወርቃማው የለጋነት የትግል ዘመናቸው ጀምረው እንኳንስ የአመለካከት ልዩነትን በአግባቡና በሠለጠነ አኳኋን ማስተናገድ፣ በቃላት አጠቃቀም ሳይቀር በመለያየት (ወዛደር/ላብአደር የመሳሰሉትን ያስታውሷል) ጦር የመሞሻለቅንና አፈሙዝ የመደጋገንን የመሰለ ጎታታ ተሞክሮ ተግተው ያደጉ ነበሩ፡፡ ይህ መጥፎ አባዜ ስላልለቀቃቸውም ቀደም ሲያቀነቅኑለት ዘመናት የሸኙበትንና የመሰከሩለትን ከአንድ ውጪ በወጉ የሚያላውስ ጎዳና የለም ብለው የተገዘቱለትን እንደ ዘበት ጣል አድርገው ውኃ ቀጠነ እያሉ የትየለሌ አቀበታማና ጎርባጣ መንገዶች ገና ሊጠርጉ ሲውተረተሩ ይታያሉ፡፡
ካፒታሊዝም ዛሬውኑ ሞቶ ተገንዞ ሲቀበር ካላየን፣ የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት ወዲያውኑ ካልተተገበረ፣ ዴሞክራሲ አሁኑኑ በምድሪቱ ላይ ካልሰፈነ፣ ወዘተ ባዮች አብዛኞቹ ዛሬ ሸሚዝ ቀይረው የነፃ ገበያና የሊብራል ዴሞክራሲ ወዳጆችና ተሟጋቾች፣ የኢትዮጵያ አንድነት አሊያም የመልክዓ ምድራዊ አከላል ጠበቆች በመሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ይታያሉ፡፡ እንደተለመደው ከጎናቸው ሳይሆን ከኋላቸው ያሠለፏቸውን ሺሕዎች ለሁሉም ዓይነት አደጋ ያጋትራሉ፡፡ ነገም ሌላ የፖለቲካ ሸቀጥ ይዘው ከች ለማለት፡፡ ትናንት ሕዝቦች ባህላቸውና ቋንቋቸው መታፈኑ፣ ማንነታቸውን መነጠቃቸው፣ በቄዬአቸው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መከልከላቸው፣ በመልከኞች መገዛታቸው ነው፡፡ የሕዝባችን ጠላት ትምክህተኛው የገዥ ቡድን ነው ሲሉ ዘመናትን ሸኝተው፣ ደግሞም ጎራ ቀይረው የምን ክልል፣ የምን ብሔር ዘርና ጎሳ እንጂ፣ የምን ፊንፊኔ አዲስ አበባ እንጂ ብለው ሲያጓሩ ከነበሩ የትምክህት መዘምራን ጋር ሲያዜሙ ከርመው (ያለፉትን ሁለት ምርጫዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አሠላለፍ ያስታውሷል)፣ አሁንም ደግሞ ዘወር ብለው ሲምሉና ሲገዘቱ ዘመናትን አስቆጥረው በእነርሱ ሠፈር ገበያው አልደራ ስላለ ሽው ብለው ሕዝቦቻችን የሚሏቸው በራሳቸው ቋንቋ መዳኘትና መማር ሲጀምሩ ሕዝቡ ደነቆረ፣ ከፋም ለማም ሕዝቦች የራሳቸውን አስተዳዳሪዎች መምረጥ ሲችሉ ደግሞ የእንትን አሽከሮችን መረጡ እያሉ ሲወሻክቱ፣ ቀደም ዓይንህ ላፈር ካሉት ጠላት ጋር በዓላማ ተሳስረው የፖለቲካ ግንባር ሲመሠርቱና( ከኢድኃቅና ከግንቦት 7 ጋር የተመሠረተውን ግንባር ያስታውሷል) ማስተር ፕላንን በማሳበብ ለኦሮሚያ ክልል ራሳቸውን በጥብቅና ሲቀጥሩ መሰሪ ስላቃቸውን ታዘብን፡፡ ከመሰሪነትም የክፉ ጠላት ድርጊት፡፡ በዘመነው ወቅት ማስተር ፕላን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እያወቁ፣ ማስተር ፕላኑ በኦሮሚያ ምድር ቢተገበር ፋይዳው ግልጽ መሆኑ ሚስጥር ሳይሆን አዲስ አበባን ከኦሮሚያ ነጥሎ በአስመሳይ ተቆርቋሪነት ከተማዋን የኦሮሚያ እንዳልሆነች አድርጎ ለሌላ ወገን አሳልፎ መስጠትን የበለጠ ምን ጠላትነት ይኖራል? ይኼ እንግዲህ ከወዲያኛው ወገን ያለው ነው፡፡
ከወዲህኛው ወገን ያለውም በተለየ ጨዋታ ሜዳ ላይ የሚከወን ቢሆንም ከፖለቲካ ስላቅ የፀዳ አይደለም፡፡ ቁልፍ ቁልፎቹ የዛሬና የትናንት ፖለቲከኞች ሳይሆኑ የዚያ የወርቃማው የፖለቲካ ዘመንና ትውልድ ፈርጦች ነበሩ፡፡ የያኔው አቀንቃኞችና አቀናቃኞች፣ የያኔው ተራማጆችና አብዮተኞች፣ በቅርቡም አሥርታትን የፈጀ፣ የሺሕዎችን የሕይወት ቤዛነትን ያስከፈለ መራራና እልህ አስጨራሽ ትግል ጀምረውና አታግለው ድልን የጨበጡ፣ ዛሬም መንግሥት በመምራት ከአገር ባሻገር በዓለም ደረጃ ዕፁብ ድንቅ የተባሉ ስኬቶችንም ለማስመዝገብ የበቁ ናቸው፡፡ የፖለቲካ መግቢያ መውጫ ሽንቁር ጠንቅቆ የገባቸው ስለሆኑ የተጨቆነ የተገፋ ሕዝብ ምን ስሜት እንደሚሰማው፣ ያመረረ የተከፋ ሕዝብ ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ ለእነሱ መንገር ለቀባሪው ከማርዳት ይቆጠራል፡፡ እኚህኞቹ የእኛዎቹ ጎምቱ “ፖለቲከኞች” ያኔ አይሞከሬውን በቁርጠኝነት ለምን እንደጀመሩ፣ በዚያ በለጋ ዕድሜአቸው የሰው ልጅ ይሸከመው ዘንድ ከቶውን የማይታሰብ መከራ ለምንስ ለመሸከም እንደበቁ ይዘነጋሉ ብሎ ጭራሹን አይታሰብም፡፡ ያኔ ክቡር ዓላማ ያስጨበጣቸው ብሩኁ አዕምሯቸው በረሃ፣ ንዳድ፣ ረሃብና መስዋዕትነትን ያስመረጣቸው ንፁህ ኅሊናቸው በዕድሜ ብዛት አሊያም በተመቻቸ ኑሮ ተለውጧል ማለት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ከሆነ በወርቃማ ቀለም የጻፉትን ታሪክ፣ በሕይወት ቤዛነትና በደም ቀለም ያሳመሩትን ግብረ ሰብነታቸውን በጥላሸት ሲለቀለቁት ማየትን ያህል አሳፋሪ ክስተትም አይኖርም፡፡
የመንግሥት አበሳ መቼም ቢሆን የሚቀር አይሆንም፡፡ በረባው ባልረበው፣ በሆነው ባልሆነው፣ በሀቁ በሐሰቱ መታማቱ መቦጨቁና መወገዙ የማንኛውም መንግሥት ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ሕግ ማስከበር፣ ሥርዓት ማስጠበቅ፣ ብያኔ መስጠት፣ አጥፊን መቅጣት፣ ወዘተ ሁሉንም ዜጎች በእኩል አያሰደስትም አያረካም፡፡ ያንኑ ያህል በሰው ልጆች የተመሠረተ የዜጎቹን መብት በፍፁምነትና በምሉዕ በኩሌነት ጠብቆ መሪዎቹ ሁሉ የራሳቸው ያልሆነ ሰባራ ስንጥር የሕዝብ ሀብት ሳይነኩ፣ ዜጎችን ያላግባብ ሳያንገላቱና ሳይበድሉ አንዲት ሰዓት ብቻ ስንኳ ብትሆን ያስተዳደረ የትኛውም መንግሥት በዓለም ላይ አልታየም፡፡ ወደፊትም አይፈጠርም፡፡ መንግሥት የኃይል መሣሪያ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ከሕዝብ በተረከበው ውክልና፣ ሥልጣንና ሥርዓት የማስጠበቅ ኃላፊነት ኃይልን ተጠቅሞ ሕግ ማስከበር ግዳጁ ነው፡፡ የእኛዎቹ ጎምቱ “ፖለቲከኞች” ሁኔታ ግን ቢሆንም ያሰኛል፡፡
ቢሆንም ያን የሚያህል የሕዝብ የድጋፍ ማዕበል በሁለት አሥርታት ውስጥ ብቻ በብርሃን ፍጥነት እየመነመነ ከዓይናቸው ሥር ሲሸሽ፣ የዓላማቸው ዓምድ እንደ ዘበት እየተናደ ሲሄድና ፍርስራሽ ብቻ የመሆን ምልክት ሲያሳያቸው፣ እየሌሉ አለን አለን ማለት ስላቅ ከመሆን ውጪ ሌላ ምን ሊሆን? ቢሆንም የአፄውም ሆነ የጁንታው መንግሥታት ከእነሱ የላቀ ለአገር የሠሩትና እነሱ ደግሞ ከሁለቱም የከፋ በሕዝብ ላይ የሠሩት ግፍ ሳይኖር እንዴትስ ለምንስ? ቢባል አጭሩ መልስ የተፉትን መልሰው ስለዋጡ፣ ለስግብግብነት አጎብድደው የሕዝብ ተዓማኒነት ስለከዳቸው፣ አገርን አሳንሰውና ሕዝብን ንቀው ራሳቸውን አልቀው ስለተገኙ ይሆናል፡፡ በዛሬው አባባል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሙስና መንሰራፋት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋትና የሕግ የበላይነት አለመኖር የሚባለው ሽሙንሙን ፖለቲካዊ ዚቅ ፍርጥ ብሎ በተራ አባባል ቢተረጎም ይኼው ሲሆን፣ አሊያም በአገርኛው “እኔ ከሞትኩ…” ማለት ነው፡፡ በእነኚህ ክፉ ድርጊቶቻው ባለፉት ሥርዓቶች በሌሎች ላይ መርገም ሲጭኑ ዘመናትን በትግል ሜዳ አሳልፈው፣ መቶ ሺሕዎችን የመስዋዕት በግ አድርገው ከተፈለገው ቦታ ሲደርሱ ታሪክ ራሱን በከፍተኛ ደረጃ ሲደግም የእነሱ ድርጊት ደግሞ ስላቅ ሆነ፡፡ ቢያንስ ላለፈው ግማሽ አሥርት ሕዝቡ እየተደረገበት ያለውን ክፉ ድርጊት በየስብሰባና ኮንፈረንሱ ጉሮሮው እስኪነቃ ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እየነገራቸው፣ ለሕዝብ ብሶት ሥፍራ ስላልሰጡና ለራሳቸው ከፍተኛ ግምት ስላላበሱ ከሳሽነታቸው ወደ ተከሳሽነት ቦታ ተቀየረ፡፡
ከላይ ያለውን ሐሳብ በሐቅ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከጅምሩ በአገሪቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ባለ ሉዓላዊ መብት ያደረገው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ በጎ ፍላጎት ላይ የተመሠረተች ፌዴራላዊ የአስተዳደር መዋቅር እንደምትከተል አበሰረ፡፡ እዚያው በዚያው በዚሁ ሰነድ ላይ ለአብነት ያህል (አንቀጽ 3 ቁጥር 1”….ከታች ቀይ ሆኖ በመሀሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል“ እና 2 “በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ ….” አንቀጽ 4 “የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር”፣ ምዕራፍ 10 “የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች”) በመባል የተጀመረው መፋለስ ታየ፡፡ ይኼው ቀጥሎ ላለፉት ዓመታት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የስፖርት ቡድኖች የብሔራዊነት ስያሜአቸው ከመቀጠሉም በላይ በመንግሥት ሚዲያዎች ሳይቀር ሲጠሩበት ይስተዋላል፡፡ አልፎ ተርፎ ቱባ ቱባ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ያላንዳች ኃፍረት ስለ”ብሔራዊ እርቅና መግባባት” በየሚዲያዎች ድምፃቸውን ከሕገ መንግሥቱ ጣሪያ በላይ ከፍ አድርገው ሲደሰኩሩ እንሰማለን፡፡ አገሪቷ ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ፣ እነሱ ብሔራዊ ተቋማትና ስለብሔራዊ መግባባት እርቅ ስላቅ እንጂ ኢሕአዴግ መቼም ስምን የሚያህል ነገር በየዋህነት ያወጣል ማለት ራሱ የዋህነት ነው፡፡ ዛሬ ክልላችን ሊወሰድብን ነው እየተባለ “በጥርጣሬ” እና “በሕዝብ ጠላቶች“ የሚነሳሳው ረብሻ ምክንያት የለውም ማለትስ እንዴት ይቻላል? ብሔራዊ ሲባል የየትኛው ብሔር መሆኑ ነው? ለምን ብሔራዊ ተብሎ ተሰየመ? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ጥርጣሬም በሕዝብ ጠላቶችም መነሳሳት የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥያቄውን ማንሳት በሕግ አግባብ በዚህ ዙሪያ መታገል ሕገ መንግሥቱ ራሱ የሚፈቅደው መብት ነው፡፡ ጥርጣሬስ እንዳይፈጠር የተሠራ ምን አለ?
ከዚሁ ሰነድ አካባቢ ሳንወጣ ሕገ መንግሥቱ ለኦሮሚያ በ“አዲስ አበባ“ ላይ የሰጠውን ልዩ ጥቅምና ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ እየነደደ ያለውን እሳት ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ “የእኛ የእኛ ነው የእናንተም የእኛ ነው” ማለት ካልሆነ በስተቀር ”አዲስ አበባ” የኦሮሞ ሕዝብ (የኦሮሚያ ሕዝብ ማለት አይደለም) መሬት ነው፡፡ ስለዚህም ልዩ ጥቅም ይኖረዋል መባሉ ግድፈት ባይኖረውም ለኦሮሚያ ክልል ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ልዩ ጥቅም ሲባል ግን በሕግና በደንብ ወይም በመመርያ መዘርዘር ይኖርበታል (የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፍ ጥቅሞች ተብሎ) እንጂ፣ በድፍኑ መተው አግባብ አልነበረም፡፡ በ”አዲስ አበባ” ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ዘርፍ (ምክር ቤት) ውስጥ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩትን የኦሮሞ ተወላጆች ሳይሆኑ የኦሮሚያ ነዋሪ ኦሮሞዎች ቀጥተኛ ወኪሎች ስንት መቀመጫ በቋሚነት ይዘዋል? ”አዲስ አበባ” በየዓመቱ ከምታገኘው የተለያዩ ገቢዎች ምን ያህሉን ለኦሮሚያ ታስገባለች? የኦሮሞን ሕዝብ የባህል፣ የታሪክ፣ የቋንቋ አሻራ የሚያሳዩ ስንት ተቋማት በ”አዲስ አበባ” ውስጥ ይገኛሉ? የኦሮሞ ሕዝብ የዚህች ከተማዬ ክርስትና ስም አይስማማኝም የተፈጥሮ ስሟ ፊንፊኔ ነው ብሎ ያወጀው ተንቆ፣ በአንድ ዘመን ጣይቱ ያወጣችው ስም ክብር አግኝቶ መርጋቱ ምንን ያሳያል? አያሌ የልዩ ጥቅም ቀርቶ ሕጋዊ ጥያቄዎችን ሕዝቡም ክልሉም ሊያነሱ ይችላሉ መብታቸውም ነው፡፡ የክልልና የአገሪቱ መዲና፣ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ ሆና ተጠሪነቷ ለኦሮሚያ ክልል ቢሆን ምን ተዓምርነት አለው “የእኛ የእኛ ነው የእናንተም የእኛ ነው” ማለት ካልሆነ በስተቀር፡፡ ስላቁ ባልኖረና በፊንፊኔ ሰበብ ተቀጣጥሎ የማይጠፋው እሳት ሁላችንንም ባልፈጀን፡፡
መንግሥታችን የሚከተለው የልማታዊ ኢኮኖሚ አቅጣጫ በቅርቡ ደግሞ የተባለው የአረንጓዴ ልማታዊ ኢኮኖሚ አቅጣጫን በአብነትነት መውሰድ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ፈለግ በልማት ወደኋላ ለቀሩት አገሮች አማራጭ የሌለው ብቸኛ ጎዳና መሆኑ አያወላዳም፡፡ መንግሥትም ይህን ጎዳና ለመከተል ሲወስን አገር ውስጥ ካሉት የነፃ ገበያ አቀንቃኞችና የሊብራል ዴሞክራሲ ጠበቆች ነን ባይ ተቃዋሚዎችም ሆነ ከምዕራባውያን የደረሰበት ተፅዕኖና ጫና ቀላል አልነበረም፡፡ ይህ ጎዳና ሲመረጥ ወኔና ቁርጠኝነት ከአርቆ አስተዋይነትና ከቅንነት ጋር ተሰንቆ ነበር፡፡ ጅምሩ እሰየው በል የሚያስብል፣ በዕውነትም የልማት ተጨባጥ ፍንጮች የታዩበትና የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ መልካም ወጋገን የታየበት ነበር፡፡ ልማታዊ ኢኮኖሚ ምልዓታዊ የሕዝብ ኑሮ መሻሻልን የሚያስገኝ የልማት ጎዳና ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ሒደቶችን የሚያቅፍና አያሌ ለውጦችን በኅብረተሰብ መዋቅሮች፣ በሕዝብ አስተሳሰብና ሥነ ልቦና፣ በአገራዊ ተቋማትና እንዲሁም በአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሀብት መበላለጥን በማጥበብና ድህነትን በመቅረፍ ማሳለጥንም ያካትታል፡፡ በተለይም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን በማስፈን፣ በኢኮኖሚ ወደኋላ የቀሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታ በተመጣጣኙ በማሻሻል፣ መልካም አስተዳደርን (የሕዝብ ተሳትፎን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ዴሞክራሲያዊ ሒደትን፣ ሰብዓዊ መብትን፣ ወዘተ) እስከ ጫፍ በመተግበር የመላ አገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት (Economic Growth) ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ልማትን (Economic Development) ማስገኘት ነው፡፡ የኢኮኖሚያዊ ልማት ሦስት እሴቶች ወይም ዓምዶች ልንል እንችላለን፡፡ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት፣ በራስ መተማመንን መላበስና ነፃነት መጎናጸፍ ናቸው፡፡ ከእነኚህ እሴቶች አንዲቷ ብቻ እንኳ ከተጓደለች ልማት የሚባል ነገር የለም ይላል ሳይንሱ፡፡
የዚህ አቅጣጫ ቅያሱም ጅምሩም በል አሰኝተውን ውሎ ሳያድር ግን የተገላቢጦሹን ተገንዝበን መቆዘም ያዝን፡፡ ልኬቱ የሚገለጸው እንደ አቅጣጫው ሁሉ ለራሱ በተበጀ ሚዛን መሆን ነበረበት፡፡ ቁመትና ወርድ በቁና፣ ዕድሜና ጊዜ በጋሻ እንደማይገለጹ ሁሉ የልማታዊ ኢኮኖሚ መለኪያ ሚዛኑ የተፃራሪው በሊብራል ዴሞክራቶች የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ ሆኖ አገሪቱ “ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት…’’ ማለት ተጀመረ፡፡ ጉድና ጅራት… ውኃን በቁና ለክቶ መጠኑን ማወቅ ሞኝ ያደርጋል፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ያንን ያህል የዋህ ነው ብሎ ማሰብ የሞኝ ሞኝ መሆን ነው፡፡ ሚስጥር አለው ቢባል ግን ብልጥነት ነው፡፡ ይህን ልኬት ካባ አድርጎ ቢለብስና በሕዝብም ፊት ቢቀርብ አንድም ከምዕራባውያን ገፊዎቹ ጋር በአንድ ቋንቋ በመነጋገር ዕርቅ ያወርዳል፣ በሌላም በኩል በዜጎች መካከል በእጅጉ እየሰፋ ያለውን የሀብታምና የደሃ የሀብት ልዩነት በሽታ ሸፋፍኖ የሚያልፍ ይመስለዋል፡፡ ይህ ልኬት ከቶውንም ሕዝቡ ያለበትን የኑሮ ደረጃ በተጨባጭ የሚያሳይ አይደለም፡፡ የአገሪቱን ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት በአገሪቱ ዜጎች ብዛት በማካፈል አማካይ ውጤት እንጂ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በቢሊዮኖች የሚዛቀውን የጥቂት ቱጃሮችን ገቢ ቤሳቤስቲን ከማያገኘው ዜጋ ጋር ደምሮ በማካፈል የሚገኝ ሥሌት ነው፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ ሁለት በመቶ የማይሞሉ ዜጎች፣ የአገሪቱን ጠቅላላ 98 በመቶ ገቢ በላይ መቆጣጠራቸውንና የሕዝቡ 98 በመቶ ደግሞ የአገሪቱን ገቢ ሁለት በመቶ በታች መያዙን ግልጽ አያደርግም፡፡ ይህ ማለት አያሌ ዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው አልተሟላም፡፡ በራስ መተማማን አልተላበሱም፡፡ ስለዚህም ነፃነት አልተጎናጸፉም ማለትን ያመላክታል፡፡ ዕድገቱ የጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች እንጂ የመላው ኅብረተሰብ አለመሆኑ አልተጻፈምም አልተነበበምም፡፡ ሳይታወቅ የተደረገ ሳይሆን ተብሎ የተደረሰ ስላቅ ነው፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል ይበጅ ነበር፡፡ በመርህ ደረጃ ያለውን ስላቅ ለመጥቀስ ያህል ነው፡፡
ሌላ አንኳር ስላቅ በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ያለው የጎምቱዎቻችን ስላቅ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚለው ሁለት አሥርት ተኩል በላይ የፈጀው ቅዳሴ ዘወትር የሚከነክን ጉዳይ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንደ ብሎኬት በአንድ ሌሊት ተደራርቦ ጧት በቁመናው ወጥቶ የማናየው በመሆኑ፣ ላይ ከጎምቱ ፖለቲከኞች አባባል ጋር አንዳችም ጥል የለንም፡፡ የቀደሙት ሥርዓቶች ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ አገሪቱን ሲመሩ እንዳልነበረና ሕዝቦቻችንም ዴሞክራሲያዊ ባህልን እንዳልገነቡም ሁሌ ከሚያፈሱት የዓዞ እንባ ጋርም የሚያጋጨን ሁኔታ የለም፡፡ የሚያነታርከን ጉዳይ እነኚህ ባዮች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባትን ኃላፊነት የመሸከም አቅም፣ ፍላጎትና ዓላማ አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ምላሹ አሉታዊ ነው፡፡ ጎምቱዎቻችን ከሁሉም በላይ አቅምና ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንድ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መለኪያው የሦስቱ የመንግሥት ተቋማት ወይም ዓምዶች (ሕግ አውጪ/አርቃቂ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አካላት) በየራሳቸው መቆም ራሳቸውን ችለው የመንቀሳቀስና አንዱ ሌላኛውን የመቆጣጠር አግባብ መኖር ነው፡፡ ይህ እውነታ ከሌለ የሕግ የበላይነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉት የዴሞክራሲ እሴቶች ስማቸውን እንኳ ማንሳት ለስላቅ እንጂ ለእርምት አይደለም፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ሁሉም የመንግሥት መዋቅር ኢሕአዴግ ሆኖ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” ዓይነት ነገር ነው፡፡ ለሥርዓቱ ጭራሽ መበስበስ ዓይነተኛው ሰበብ ይህ ሲሆን ውጤቱ የቁልቁል መወርወር ጉዞ ነው፡፡
ስለዚህም ነው ዛሬ የምንታመሰው፡፡ ጠያቂና ተጠያቂ የሌለበት ሥርዓት ከታችኛው ከትንሹ የመኃይማን ጥርቅም የቀበሌ ካቢኔ አንስቶ እስከ ላይኞቹ ቱባዎች ኅሊናቸውን ቀቅለው የበሉ ሹመኞች ድረስ ባሉት ነው የሕዝቦች መብት የሚደቆሰው፡፡ የአገርና የሕዝብ ንብረት የሚዘረፈውና የሚበዘበዘው፡፡ በዜግነትና በነዋሪነት መብቱ ማግኝት የሚገባው ትንሿ መታወቂያ ሺሕ ብር ድረስ የምትቸበቸበውና ሕገ መንግሥቱ ውጉዝ ከመአሪዮስ ያደረገው መሬት ደሃው ዜጋ ከላዩ ተፈንግሎ በጠራራ ፀሐይ ለኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶች በሚሊዮኖች የሚቸበቸበው፡፡ የኢሕአዴግ ሹመኞች ፎቅ በፎቅ ላይ የሚገነቡት፣ አስመጪና ላኪዎች የሆኑበት፣ የትላልቅ ንግድ ድርጅቶችና ሆቴሎች ባሌቤቶች ለመሆን የበቁትና ልጆቻቸውን በምዕራባውያን አገሮች ትምህርት ቤቶች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች ከፍለው የሚያስተምሩበት ሀብት ከሰማይ እንደ መና የወረደላቸው ሳይሆን፣ በግልጽ ቋንቋ በኢሕአዴግነታቸው የተከመሩበትን ሹመት በመገልገል የሰረቁት ሀብት ነው፡፡ ዳር ድንበሩ ከዚህ እዚያ ያልተባለለትና ሳይት ፕላን ያልተሠራለት አምስት ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት ለኢቨስትመንት ሰጥቼሃለሁ ብሎ የሚፈርም ሹመኛ፣ ከቶውንም በደግነቱ መንግሥተ ሰማያት ሊገባበት አይሆንም፡፡ ግንባር በሆነ ሥፍራ አሥራ ስድስት ሔክታር መሬት ለሪል ስቴት ኢቨስትመንት አስረክቦ ባለሀብቱ በየ200 እና በየ300 ካሬ ሸንሽኖ አንዳችም ብሎኬት ሳይጥልበት እያንዳንዱን ፕሎት በ300 ሺሕና በ400 ሺሕ ብር በመቸብቸብ ከቢሊዮን ብሮች በላይ ሲያጋብስ ተጨባጭ ጥቆማ ደርሶት ሕጋዊ ዕርምጃ ያልወሰደ ሹመኛን ከሌባ የሚለየው መሥፈርት የለም፡፡ የጉምሩክ ቀጣፊዎችን ጉዳይ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ምክር ቤት እንየው እያለ የሚነታረከው ስብስብ በአንደኛ ደረጃ ሕገ መንግሥቱን የከዳ ወገን እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡
ከቶውንም በሹመት ሽቅብ የሚወረወሩት እነዚህ ለመሆናቸው ከተደጋጋሚ የሕዝብ ዋይታና ተቃውሞ በላይ ተጨማሪ ማስረጃ ማቅረብ አያሻም፡፡ የኢሕአዴግ ሹመት ጦጣን ቢወረውሯት እህል ክምር ላይ አረፈች ዓይነት መሆኑ ሥውር አይደለም፡፡ ሁለት አሥርት ያህል የፈጀው የፀረ ሙስና ዚቅና የዓዞ እንባ ዘንድሮ ሕዝብ ምንነቱን በይፋ እየገለጠው ነው፡፡ ለሕዝብ ድምፅ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትና መናቅ፣ የኢትዮጵያ ማሪያ አንቶኔ መሆን ከቅሌትም ውርደት መሆኑን በጀግናው ኢሕአዴግ ላይ የታዘብነው በዘንድሮው ዓመት በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ የተፋውን ሲልስ በማየት ነው፡፡ ያወጃቸውን ሁለት አዋጆች መልሶ ሲሽር፡፡ ሲያፈገፍግ ሲሸሽ፡፡ ማወጅስ ለምን? መሻርስ ለምን? የጠንካራ መንግሥት ባህርይ አይደለም፡፡ ማስተር ፕላን ተሽሮ የዕውር ድንብር ሊሠራ! ኦሮሚያ የፊንፊኔ ቆሻሻና ዕዳሪ ማከማቻ ሆና አሁንም ልትቀጥል? ጉዳዩ ግዙፍ ሽንፈት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ ቅሌት ደግሞ በተቃዋሚዎቻቸው እጅ የገለማውን “አፋን ኦሮሞን ፌዴራላዊ ቋንቋ” የማድረግ ሹክሹክታ ደግሞ እየተናፈሰ ነው፡፡ ሌላ ስላቅና ውድቀታቸው! በመሠረቱ ቋንቋ መሣሪያ እንጂ ግብ አይደለም፡፡ በመሣሪያነት የኦሮሞን ሕዝብ ለማንቀሳቀስ ያኔ በጅምሩ የፖለቲካ አዋቂዎች በሚገባ ተገልግለውበት ሕዝቡን ዛሬ ካለበት ደረጃ ለመድረስ አብቅተውታል፡፡
እነዚህኞቹ በአንድ ወገን ሕዝቡን ለመሸንገል በሞተ ፈረስ እየጋለቡ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሌሎች ሕዝቦች ላይ የራሳችን የሚሉትን ቋንቋ ለመጫን እየዳዳቸው ነው፡፡ ሌላ የማያባራ እሳት ለመለኮስና ከተጠያቂነት በጭሱ ተሸፋፍኖ ለማምለጥ!! ይህችን ትንሿን የዴሞክራሲ ሀሁ ያልተረዱ ጉደኞች የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ምንም ያድርጉ ምንም ከሕዝቡ ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸውን ማሳያ ነው፡፡ ማስተር ፕላኑ ተሽሮም ሁከቱ አላባራም፡፡ ተቃውሞው ማስተር ፕላኑ ላለመሆኑ ጥርጥር አይኖርም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ድርጅቱ በሕዝብ መሳለቁን አልተወም፡፡ ንፁሁና ቆሻሻው ያልተለየበት የእከከኝ ልከክህ የግምገማ ጨዋታ ካልሆነ በስተቀር የኪራይ ሰብሳቢነት ኢኮኖሚን አጥፊነት፣ የሙስናን ጎጂነትና የመልካም አስተዳደር መጥፋትን ክፉነት መዝሙርና ቅዳሴ ከማሰማት ያለፈ ፋይዳ ያለው ሥራ አልሠራም ድርጅቱ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢው ማነው? እንዴትና ምን ያህል? ከእነማን ጋር ሰበሰበ? የተሰበሰበው የታል? ምንስ ዕርምጃ ተወሰደ? ሕዝቡ ለእነዚህና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቅልብጭ ያሉ መልሶች ይሻል እንጂ የድርጅቱን ስላቆችማ አስመልሶታል፡፡ ይኸው ነው መዳኛው እንጂ የእንትን መሀላ ደረት ያሰፋል እንዲሉ፣ ሰሞኑን በተለያዩ ከተሞች እንደተለመደው ተሰባስበው እንትን እንሆናለን ብሎ መማል ለሕዝቡ ቁብ አይመስለውም፡፡ በውስጣቸው መልካም አስተዳዳሪነት በአንድ ምሽት አያጥለቀልቃቸውም፡፡ ለአሥርታት የደፈቁትን ሕዝብ በሁለት ቀን ዲስኩር ነፃነት አያጎናጽፉትም፡፡ የሕዝብን ፍቅርና ክብር፣ የዓላማን ጽናትና ቅንነት ኢሕአዴግ ከመለስና ከዓለማየሁ ጋር በእፎይታ ገንዞ ቀብሯል፡፡
የኦሮሚያ ሹመኞች በእውነት የኢሕአዴግ ቁም ነገረኛ አባላት ከሆኑ፣ በዕውነት የሰናፍጭ ፍሬ ታህል ኦሮሞነት በውስጣቸው ካለች፣ በዕውነት የኦሮሞ ሕዝብ አደራ እንዳለባቸው ካመኑ ከላይኞቹ አፄና መሳፍንት ዓይነት አለቆቻቸው ጀምሮ እስከ ታችኞቹ የቀበሌ ነገሥታት ድረስ ያሉትን ዘራፊዎች እንደ ተለመደው በጓዳ ግምገማ ሳይሆን በሕዝብ ኮሚቴ በአደባባይ ያስፈትሹ፡፡ ያኔ የግልጽነትና የተጠያቂነት ስላቅ ቀርቶ የምር ሥራ ይሠራል፡፡ አለበለዚያ የኦሮሞን ሕዝብ ልብ መግዛት ዘበት ነው፡፡ እንደከዚህ በፊቱም የኦሮሞን ሕዝብ እንደማስፈራሪያም ተጠቅሞ በሥልጣን ላይ ተቆናጥጦ መቀጠልም ይቻል አይመስልም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ልቡን ያልሰጠው ኢሕአዴግ ደግሞ በኢሕአዴግነቱ መቀጠሉም ዘበት ነው፡፡ ኢሕአዴግም ቢሆን የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅምና ፋይዳ በጥንቃቄ ከጠበቀ የኦሮሞ ሕዝብ በኦሕዴድ አልቆረበ ወይም የኦሕዴድ ጂን አልለከፈው፡፡ ጨው ለራሱ ሲል ነው መጣፈጥ ያለበት፡፡ ተያይዞ ገደል ከመግባት ይበጃል፡፡ የአጉል ብልጣብልጥነትና ጀግንነት ጊዜ አልፏል፡፡ ላለፉት ሁለት አሥርታት ጆሮ ውስጥ ጠብ የማይል ዲስኩር ሲደሰኩሩ የነበሩት የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር መረራ ባለፈው ሰሞን ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ፣ ከዚህ ወዲያ ኦሕዴድ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ብቃት የለውም ያሉትን ቁም ነገር አድንቄ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የዘቢደር መንገድን ሲመርቁ “ድንችን ለማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ መንገዱ ያለው አስተዋጽኦ’’ ያሉትን ብታዘብም (ለአገሪቱ ማዕከላዊ ገበያ 30 በመቶ ቡና የሚያቀርበው የሊሙ ኮሳ ወረዳን መንገድ በዓይነ ኅሊናዬ እየቃኘሁ)፣ በሰሞኑ ንግግራቸው ደግሞ ሕዝቡ መንቃቱንና ካሁን ወዲያ ሊታለል እንደማይሞከር ባሳለፉት ምክር አሞገስኳቸው፡፡ ጀግና ጊዜ እንጂ ሌላ አይደለምና ዛሬ የነቃ ሕዝብ ጀግና ለመሆን መጣር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው እንዲያው ከንቱ ስላቅ ነው፡፡ የፖለቲካ ሶመርሶልት!!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡