Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዳማ ንግድ ምክር ቤት ምርጫና ነባሩን ቦርድ ያቆየው ውጤት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ውጭ ከሚገኙ የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ከፍተኛ የአባላት ቁጥር እንዳለው የተገለጸው የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባካሄደው ምርጫ የቀድሞው አመራሮች በድጋሚ ተመረጡ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ካካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ጐን ለጐን በተደረገው ምርጫ፣ እስካሁን በኃላፊነት ላይ የቆዩትን የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና አምስት የቀድሞ የቦርድ አባላት በድጋሚ መርጧል፡፡ በተጓደሉት አባላት ምትክ ደግሞ አዲስ የቦርድ አባላት እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው የተካሄደው ከየዘርፉ በተወከሉ 250 የምክር ቤት አባላት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ140 በላይ ተወካዮች በመገኘታቸው የዕለቱ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሊከናወን ችሏል፡፡

የምርጫ ሒደቱም ለዚሁ ምርጫ ተብሎ በተዋቀረ የምርጫ አመቻች ኮሚቴ ታጭተው ለጠቅላላ ጉባዔ የቀረቡ መሆናቸው ተገልጾ የተካሄደ ነበር፡፡ የምርጫ አመቻች ኮሚቴው ከአንድ ወር በፊት ተዋቅሮ ለመወዳደር ፈቃደኛ የሆኑ ተወዳዳሪዎችን እንዲያፈላልግና ለውድድር ዕጩ እንዲያደርግ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ በወሰነው መሠረት ወደ ሥራ የገባ ነው ተብሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ለፕሬዚዳንትነት ሦስት፣ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ሦስት፣ ለቦርድ አባላት ደግሞ 27 ዕጩዎችን ይዞ መቅረቡን የአመቻች ኮሚቴው አባላት ለጠቅላላ ጉባዔው አሳውቀዋል፡፡

በሁሉም የኃላፊነት ቦታዎች የቀረቡትን ዕጩዎች በማስታወቅ ወደ ምርጫው እንዲገባ የቀረበው ሐሳብ ከመፈጸሙ በፊት ግን፣ ከአንዳንድ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት እስካሁን ያገለገለው አመራር መልካም ስለሠራ ራሱ ይቀጥል፤ ባይሆን በተጓደሉ አባላት ምትክ አዲስ የቦርድ አባላትን እንምረጥ የሚል ሐሰብ ቀርቦ ነበር፡፡

ሆኖም ይህንን ሐሳብ የሚቃወሙ አንድ የጠቅላላው ጉባዔ ተካፋይ ‹‹ይህ መሆን አይችልም፡፡ በጅምላ ይመረጡ ማለት አይቻልም፤›› በማለት የሰነዘሩት አስተያየት ጠቅላላ ጉባዔው በሁለቱ ሐሳቦች ላይ ሰፊ አስተያየት እንዲሰጥበት አድርጓል፡፡ በሥራ ላይ የቆዩትን የቦርድ አባላት እንዳለ እናሳልፋቸው የሚለውን ሐሳብ የተቃወሙት አባል፣ ሁሉን እኩል ሠርተዋል ስለማይባልና በጅምላ ማሳለፉ የምርጫ ሒደትን የሚጣረስ በመሆኑ፣ ድምፅ በመስጠት ምርጫው መካሄድ ይኖርበታል በማለት ተከራክረዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅንም ስለሚጣረስ ምርጫው ድምፅ ተሰጥቶበት ይካሄድም ብለዋል፡፡  

ይህንኑ አስተያየት ተከትሎ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ፈይሳ አራርሳም ምርጫው ፍትሐዊ መሆን ስላለበት፣ በጥቅሉ ይለፉ የሚለውን ሐሳብ እሳቸውም እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹የጠቅላላ ጉባዔው አመቻች ኮሚቴው ካቀረባቸው ዕጩዎች ሌላ ተጨማሪ ተወዳዳሪዎችን በማከል ምርጫው ሊካሄድ ይችላል፤ እኛም ብንሆን በጥቅሉ ይለፉ የሚለው ተገቢ ስለማይሆን በድምፅ ምርጫው ይካሄድ፤›› በማለታቸው ቤቱ ድምፅ በመስጠት ምርጫ ይካሄድ ወደሚለው ሊጋድል ችሏል፡፡

በዕለቱ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ደረጀ መገርሳም፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምርጫ ሥርዓቱን ተከትሎ ማካሄዱ ሁሉንም ሊያስማማ ይችላል ብለው፣ በጥቅሉ ይመረጡ የሚለው ሐሳብ ቀርቶ በዕጩዎቹ ላይ ድምፅ እንዲሰጥ የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡

በዚሁ ሐሳብ መሠረት በአመቻች ኮሚቴው የቀረቡት ዕጩዎችን በማስተዋወቅ እጅ በማውጣት በተደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት፣ ከአንድ የቦርድ የቀድሞ አባል በስተቀር በአቶ ፈይሳ አራርሳ የሚመራው የቀድሞ ቦርድ በሙሉ በድጋሚ እንዲመረጥና በተጓደሉት ቦርድ አባላት ደግሞ አዲስ ተመራጮች ተካተዋል፡፡

በዚህ ምርጫ በፕሬዚዳንትነት ከተመረጡት አቶ ፈይሳ አራርሳና በምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ድምፅ ካገኙት አቶ መገርሳ ረጋሳ ሌላ አቶ ከበደ ጨቋላ፣ አቶ ገነነ ክፍሌ፣ አቶ አበበ በንቲ፣ አቶ ጌታሁን ኢታና፣ አቶ ጌታሁን መኮንን፣ አቶ ዘውዴ ዲባባ፣ ወ/ሮ እልፍነሽ ሰለሞን፣ ወይዘሮ ተሚማ ሁሴንና አቶ ሲሳይ በዳዳ በቦርድ አባልነት ተመርጠዋል፡፡ በዚሁ መሠረት አዲሱ አሠራር ቃለመሃላ ፈጽሟል፡፡

ከምርጫው ቀደም ብሎ በፕሬዚዳንቱ የቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ሥራዎች በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ ሪፖርቱ በጠቅላላ ጉባዔው ያለምንም ተቃውሞ ፀድቋል፡፡ ዓመታዊ ሪፖርቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁለት ሺሕ የነበረው የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር 1025 መድረሱን ጠቅሷል፡፡

የምርጫው ውጤት በዚህ ውጤት ቢጠናቀቅም የምርጫ አካሄዱ ችግር ነበረበት የሚሉ አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡ በድጋሚ ከተመረጡ የቦርድ አባላት ጭምር የምርጫው አካሄድ ላይ ቅሬታ እንደነበራቸው ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡ የተወሰኑ ወገኖች ለመመረጥ የቡድን ሥራ ሠርተዋል፤ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከተገኙት ተሳታፊዎች ውስጥ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ያልሆኑ ነበሩበትና የመሳሰሉት አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ እነዚህ አስተያየቶች ግን በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያልተነሱ ነበሩ፡፡ ለፕሬዚዳንትነት በተደረገው ውድድር ላይ በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ አንዱ በዕለቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አልነበሩም፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ከታጩ ለምን ቀሩ የሚለው ጥያቄ ተነስቶ ሲተችበትም ነበር፡፡ ግለሰቡ ለዚህ ውድድር ፍቃደኛ ናቸው ቢባልም እርሳቸው ግን መረጃ አልነበራቸውም የሚሉም ወገኖች አሉ፡፡ ይህ በመሆኑ የምርጫ ውጤቱ ወደ አንድ ወገን እንዲያጋድል ማድረጉንም ቢጠቁሙም፣ አመቻች ኮሚቴው ግን  ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ የነበሩት ግለሰብ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ መግለጻቸውን ገልጿል፡፡

በምርጫው ሒደት ላይ የተነሳው ሌላው አስተያየት ደግሞ የአመቻች ኮሚቴው ወደ ሥራ እንዲገባ ውሳኔ የተሰጠው ከአንድ ወር በፊት ቢሆንም፣ ኮሚቴው ግን ወደ ሥራ የገባው ምርጫው ከመካሄዱ ሦስት ቀናት በፊት መሆኑም አግባብ አይደለም የሚለው ነው፡፡ አቶ ፈይሳ ግን አመቻች ኮሚቴው ሥራውን የጀመረው እንደተባለው ሳይሆን ቀድሞ ነው ይላሉ፡፡ ተወዳዳሪዎች የቀረቡትም ፍቃደኝነታቸው ተጠይቆ ነው ብለዋል፡፡

በሥራ ላይ የቆየው ቦርድ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ ጠንካራ የሚባል መሆኑንና ብዙ ሥራዎችን የሠራ መሆኑን የጠቅላላ ጉባዔው ሪፖርት ይገልጻል፡፡ የቀረበው ሪፖርትና የኦዲት ሪፖርት በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ቢሆንም፣ የምርጫ ሒደቱ ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው ተብሏል፡፡

እኒህ አስተያየት ሰጪ እንደጠቆሙት ከየትኛውም ቦርድ በተለይ በተግባር የታየ ሥራ የሠራና ዘመናዊ አሠራሮችንም ያጠናከረ ሆኖ ሳለ፣ በምርጫው ሒደት ላይ ግን ክፍተት ታይቶበታል ይላሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ምርጫው በካርድ መሆን ሲገባ እጅ በማውጣት እንዲፈጸም ማድረጉ ትልቅ ግድፈት ነው ብለዋል፡፡ የተወሰኑ አባላትን ለማስመረጥ የተሠራ ሥራ ነበረም ይላሉ፡፡

ጐን ለጐን የቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት ግን ንግድ ምክር ቤቱ ወደ ተሻለ ጐዳና ያመላከተ ነው ይላል፡፡ ተጨማሪ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎችን ማካሄዱ የንግድ ኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ ከከተማው አስተዳደር ጋርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያከናወናቸው ተግባራት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተወድሶለታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አብዛኛዎቹ የንግድ ምክር ቤቶች ሁሉ በአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ አብዛኛው ተመራጮች በድጋሚ የተመረጡ ናቸው፡፡

ሁሉም በተከታታይና በተለያዩ የምርጫ ዘመኖች ከሁለትና ከሁለት ጊዜ በላይ የተመረጡ በመሆናቸው፣ አዳዲስ ተመራጮች ወደ አመራር መምጣት ያልቻሉበት ነው የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ አቶ ፈይሳ እንደገለጹትም አዳዲስ አመራሮች እንዲመጡ ፍላጐታቸው በመሆኑና ንግድ ምክር ቤቱን ሊመሩ የሚችሉ ተወዳዳሪዎች እንዲገቡ ጥረት መደረጉን ተናግረው ወደፊትም ይህ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

በምርጫው ዕለትም የምርጫ አመቻች ኮሚቴው በዕጩነት ካቀረባቸው ሌላ ተጨማሪ ዕጩዎች እንዲካተቱ የፈለግነውም ለዚህ ነበር ብለዋል፡፡ አቶ ፈይሳ የንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የተመረጡት ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ በአንድ የምርጫ ዘመን ደግሞ በቦርድ አባልነት አገልግለዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች